መስከረም ለኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች የተስፋ እና የልምላሜ ወር ነው። ከደጋው እስከ ቆላው በተዘረጋው ማሳ ላይ ከበጋው ጀምሮ ሲያርስ፣ ሲያለሰልስ፤ አረምና ተባይ ሲከላከል የከረመ አርሶ አደር መስከረም ተገባዶ ጥቅምት ሲገባ ሰብሉን ለመሰብሰብ ቀሪ ጊዜያት ቢኖርም ልቡ በሀሴት ይሞላል፤ አረንጓዴ ካባ የመሰለው አዝመራው ለፍሬ ሲዘጋጅ ማየት ደግሞ እንኳን አርሶ አደሩን ሸማቹንም ያስደስታል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ አረንጓዴ ተስፋ በቀላሉ ወደ ጎተራ አይገባም፤ ተፈጥሮ ከምትለግሰው በረከት ጀርባ አዝመራውን ከአደገኛ ተባዮች እና በሽታዎች ለመታደግ በቀሪ ጊዜያት ሌት ተቀን የሚደረግ እልህ አስጨራሽ ትግል አለ።
በሰሜን ጎጃም ዞን በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የሰብል በሽታዎች ከፍተኛ ተመራማሪ እስመለዓለም ምህረቱ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት “በስንዴ ላይ የሚከሰተው የስንዴ ዋግ፣ በድንች ላይ የሚታየው የድንች ምች እንዲሁም በበቆሎ እና ማሽላ ላይ የሚከሰተው አገዳ ቆርቁር” ሰብሉን ክፉኛ ከሚጎዱት በሽታዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው። አርሶ አደሩም በየጊዜው የክትትል ሥራ ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል። ተባዮች እና የሰብል በሽታዎች በወቅቱ ቁጥጥር ካልተደረገባቸው የምርት መጠንን እስከ 40 በመቶ ይቀንሳል። አለፍ ሲልም ሙሉ በሙሉ ምርት ሊያሳጣ እንደሚችል ተመራማሪዉ ያስገነዝባሉ። የአንድ ሀገር የምግብ ዋስትና የሚረጋገጠው በዘር ወቅት በሚዘራው መጠን ብቻ ሳይሆን ሰብሉን ተንከባክቦ ለፍሬ እስኪበቃ ድረስ በሚደረገው ጥበቃ ጭምር ነው።
በምዕራብ ጎጃም ዞን የጃቢ ጠህናን እና በሰሜን ሸዋ ዞን ሲያደብርና ዋዩ ወረዳ የሚኖሩ አርሶ አደሮችም ሰብላቸው ፍሬ ማፍራት በጀመረበት በዚህ ወቅት (መስከረም አጋማሽ) ማሳቸውን ከአረም እና ከተባይ ነፃ ለማድረግ የሚያደርጉትን ክትትል እና ቁጥጥር አጠናክረው ቀጥለዋል። አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት በሰብል ላይ የሚታዩት የትል እና የፈንገስ ምልክቶች በወቅቱ ካልተገቱ ድካማቸውን ሁሉ መና እንደሚያስቀሩት ጠንቅቀው ያውቃሉ። የሰብል ጥበቃ የሚጀምረው ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ሳይሆን ከመከሰቱ በፊት በሚደረግ ቅድመ ጥንቃቄ መሆኑንም የአርሶ አደሮች ግንዛቤ ያሳያል።
በጃቢ ጠህናን ወረዳ ፍራጥ አዳንኸኝ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ሀሰን ይመር ለበኵር እንደገለጹት እርሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው አርሶ አደሮች በዋናነት የሚያመርቷቸው እንደ በቆሎ፣ በርበሬ፣ ጤፍ እና ዳጉሳ የመሳሰሉ ሰብሎች ናቸው። ከሦስት ሄክታር በላይ መሬታቸውን በተለያዩ ሰብሎች በዘር የሸፈኑት አርሶ አደር ሀሰን ከተፈጥሮ ችግሮች ጋር እየተጋፈጡ ሰብሎችን በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን በስልክ ነግረውናል።
የክረምቱ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመግባቱ እና አልፎ አልፎ በመዝነቡ ምክንያት የዝናብ እጥረት መከሰቱን የገለጹት አርሶ አደሩ ይህም በተለይ በበቆሎ ሰብል እድገት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል ፈጥሮ እንደነበር ነግረውናል። ከዚህ ቀደም በሰብሉ ላይ ተከስቶ የነበረው የተምች ወረርሽኝ ከከፍተኛ የፀሐይ ሙቀት ጋር ተዳምሮ የሰብሉን እድገት ተፈታትኖት እንደነበርም ጠቁመዋል። ይህን በተፈጥሮ ሳቢያ የመጣባቸውን ችግሮች ተቋቁሞ ቀድመው የዘሩት የበቆሎ ሰብል አሁን ላይ ለእሸት በቅቷል። ሌሎች ዘግይተው የዘሯቸው ሰብሎችም የዝናብ ስርጭቱ እስከ ጥቅምት የሚቆይ ከሆነ ያቀዱትን ምርት ለማግኘት ተስፋ አድርገዋል።
በዞኑ የ2018/19 የምርት ዘመን እንዴት ነው? ስንልም ለዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ጥበቃ ባለሙያ ለአቶ አለነ ባዝዘው በስልክ ጥያቄ አንስተን ነበር። ባለሙያው ለበኵር እንደገለጹት በምርት ዘመኑ ከ272 ሺህ 744 ሄክታር በላይ መሬት በመኸር ሰብሎች ተሸፍኗል። ይህንንም ሰፊ እርሻ ውጤታማ ለማድረግ 470 ሺህ 394 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ዳፕ እና ዩሪያ) እንዲሁም ከ204 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እና የአካባቢ ዘር ለአርሶ አደሩ ጥቅም ላይ ውሏል። ምርታማነትን ለማረጋገጥ ከሚሠሩ ዋና ዋና ተግባራት አንዱ የሰብል ጥበቃ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የዘንድሮው የመኸር ወቅት ገና ከጅምሩ አልጋ በአልጋ አልነበረም። በመሬት ዝግጅት ወቅት የነበረው ዝናብ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ከግንቦት አጋማሽ እስከ ሐምሌ ወር ድረስ የተከሰተው የዝናብ መቆራረጥ በአካባቢው አርሶ አደሮች ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኖ ነበር። በተለይም በወቅቱ ተዘርቶ የነበረው በቆሎ በዝናብ እጥረት ሳቢያ ተጎድቷል። ይሁን እንጂ አርሶ አደሩ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። በዝናብ እጥረት የተጎዳውን ወደ አራት ሺህ 577 ሄክታር የሚጠጋ የበቆሎ ማሳ መልሶ በማረስ በአጭር ጊዜ በሚደርሱ እንደ ጤፍ፣ ስንዴ እና ጥራጥሬ ባሉ ሰብሎች ተክቶታል።
አርሶ አደሩ ከዚህም ባሻገር በማሳ ላይ የአፈር እርጥበትን የመጠበቅ፣ ውኃ የማቆር እና የብክነት መከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም የዝናብ እጥረት አደጋ በብልሃት ማለፍ ተችሏል። እስካሁን ባለው ሂደት በዘር ከተሸፈነው ማሳ ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው (ከ262 ሺህ ሄክታር በላይ) ከአረም መጽዳቱን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በማሳዎች ላይ እንደ መጤ ተምች፣ መደበኛ ተምች እና አገዳ ቆርቁር የመሳሰሉ ሰብል አውዳሚ ተባዮች ተከስተው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በተደረገው ከፍተኛ ጥረት በዘጠኝ ሺህ 820 ሄክታር መሬት ላይ የታየውን ተባይ መቆጣጠር ተችሏል። ለዚህም ስኬት ዘመናዊ ኬሚካሎችን ብቻ ሳይሆን አርሶ አደሩ የከብት ሽንት እና የተለያዩ ባህላዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ከሦስት ሺህ 500 ሄክታር በላይ ማሳን ከተባይ ነጻ ማድረግ የቻለበት ተሞክሮ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ይላሉ ባለሙያው።
ባለሙያው አክለውም በዞኑ በየሳምንቱ የሚካሄደው የመስክ ክትትል፣ የድጋፍ እና የግብረ-መልስ አሰጣጥ ሥርዓት አርሶ አደሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ንቁ ሆኖ ሰብሉን እንዲንከባከብ አድርጎታል። በቀጣይ ጊዜያት የተባይ እና የበሽታ መከላከል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
በምርት ዘመኑ ምንም እንኳ የተፈጥሮ ፈተናዎች ቢያጋጥሙም በተከናወኑ የመፍትሔ ርምጃዎች አሁን ላይ ሰብሎች በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝም ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡ በምርት ዘመኑም 14 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት የተያዘው እቅድ ይሳካል የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው።
በተመሳሳይ በሰሜን ሸዋ ዞን ሲያደብርና ዋዩ ወረዳ የምትገኘው የሮሜ ቀበሌ ለም መሬት ዘንድሮም በአረንጓዴ ካባ ተውባለች። በአካባቢው አብዛኛው አርሶ አደር ስንዴ፣ ጤፍ፣ ባቄላ፣ ምስር እንዲሁም አልፎ አልፎ ገብስ እንደሚያመርት ከአርሶ አደሮች አንደበት መረዳት ችለናል። አርሶ አደር ነብዩ ቸሬ በሰፊው ማሳቸው ላይ የዘሩት ሰብል ተስፋ ሰጭ መሆኑን ጠቁመዋል።
አርሶ አደሩን የዝናቡ መዘግየት ቢያሰጋቸውም ተፈጥሮ ግን ፊቷን ሙሉ በሙሉ አልነሳቻቸውም። ዛሬ በማሳቸው ላይ ስንዴው፣ ምስሩ እና ባቄላው ለምልሞ ይታያል።
በአሁኑ ወቅት ሰብሉ በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አርሶ አደሮችም ማሳቸውን ከአረም በማጽዳት እና በመንከባከብ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ። የምርት መሰብሰቢያው ወቅት ገና ቢሆንም የሰብሉ ወቅታዊ ቁመና ግን ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ከአቶ ነብዩ ጋር በስልክ በነበረን ቆይታ ድምጻቸው ደስታቸውን ያሳውቃል።
በዞኑ የሰብል ምርትን ጥራት እና መጠን ለማስጠበቅ ወቅቱን የጠበቀ አረም የማረም እና ተባይ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል። በምርት ዘመኑ 562 ሺህ 686 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 20 ሚሊዮን 839 ሺህ 188 ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል፡፡
በዞኑ በ2018/19 የምርት ዘመን 559 ሺህ 757 ሄክታር ማሳ የሸፈነ ሰብል ለማረም ታቅዶ በመጀመሪያው ዙር 544 ሺህ 102 ሄክታር ሰብል መታረሙን በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አበበ ጌታቸው ተናግረዋል።
በዞኑ በሰባት ወረዳዎች የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ የሰብል ጉዳት ለመከላከል የኬሚካል ርጭት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም በ85 ሄክታር መሬት ላይ 170 ሊትር ኬሚካል ጥቅም ላይ ውሏል፡፡
በዚሁ እንቅስቃሴ በሁለተኛው ዙር 382 ሺህ 945 ሄክታር የሸፈነ ሰብል ማረም የተቻለ ሲሆን፤ አርሶ አደሮች አረምን አስቀድመው ለመከላከል እና ከተከሰተም በኋላ በብቃት ለመቆጣጠር በባለሙያ የሚሰጡ ምክረ-ሀሳቦችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ከፍተኛ ተመራማሪው እስመለዓለም (ዶ/ር) ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገጹት ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ ዘዴዎች ሁሌም ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል። ብዙውን ጊዜ ተባይ ሲከሰት የመጀመሪያው ርምጃ ወደ ፀረ-ተባይ ኬሚካል መሮጥ እንደሆነ ይታሰባል። ሆኖም የግብርና ተመራማሪዎች ይህንን አካሄድ አጥብቀው ይሞግታሉ።
ባለሙያው “ኬሚካል የመጨረሻው አማራጭ ይሁን፤ ባህላዊና የተቀናጁ የቁጥጥር ዘዴዎች ይቅደሙ” ይላሉ። ተባዮችን ገና በዕንቁላል ወይም በእጭ ደረጃቸው እያሉ በእጅ ለቅሞ ማጥፋት እና በበሽታ የተያዙትን ነቅሎ ማስወገድ የችግሩን መስፋፋት በከፍተኛ ሁኔታ ይገታል።
ፀረ ተባይ እና አረም ኬሚካልን ከአቅም በላይ ሲሆን ብቻ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት የሚመክሩት ተመራማሪው፤ ይህም ሲሆን አርሶ አደሩ ኬሚካሉን ከሕጋዊ ነጋዴዎች ከመግዛት ጀምሮ የአጠቃቀም መመሪያውን መሰረት አድርጎ መርጨት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
እንደ ተመራማሪው ማብራሪያ ኬሚካል መጠቀም ግድ በሚሆንበት ጊዜ ያለአግባብ እና ከልክ በላይ የሚረጩ ኬሚካሎች ሰብሉን ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ስነ-ምህዳር፣ የንብ መንጋዎችን እንዲሁም የሰውን እና የእንስሳትን ጤና አደጋ ላይ ይጥላሉ። ኬሚካል መረጨት ያለበት ንቦች ወደ ቀፎአቸው በሚመለሱበት ሰዓት እና ትክክለኛውን የመድኃኒት መጠን በመጠበቅ መሆን አለበት። አርሶ አደሩ ጠዋት እና ማታ ማሳ ውስጥ በመዘዋወር የቅጠሎችን ጀርባ፣ የአገዳዎችን መገጣጠሚያ እና ስሮችን መፈተሽ የመጀመሪያ ሥራው ሊሆን እንደሚገባም ይመክራሉ።
መረጃ
የሰብል ምርታማነት ከፍ እና ዝቅ እንዲል የሚያደርጉ ምክንያቶች፡-
የአፈር ለምነት፦ አፈሩ በውስጡ የያዘው ማዕድን እና ንጥረ ነገር።
የአየር ንብረት፦ የዝናብ መጠን እና ስርጭት፣ የፀሐይ ብርሃን እና የሙቀት መጠን።
የዘር ጥራት፦ በሽታን መቋቋም የሚችሉ እና የተሻሻሉ ዝርያዎችን መጠቀም።
የግብርና ቴክኖሎጂ፦ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን፣ መስኖን እና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም።
የሰብል እንክብካቤ፦ አረምን፣ ተባይን እና በሽታን በወቅቱ መከላከል ናቸው።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የመስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


