የሙስናን አዙሪት እንስበር!

0
28

ሙስና በሀገር ምጣኔ ሀብት፣ በፍትሕ ሥርዓት እና በኅብረተሰብ የሥነ-ምግባር እሴት ላይ ከፍተኛ ጠባሳ የሚጥል ችግር ነው። ስለሆነም የሙስናን አዙሪት መስበር ግድ ይላል፡፡

የሙስናን አዙሪት ለመስበር ደግሞ መነሻ ምክንያቱን ማወቅ ያሻል፡፡ ሙስና የተወሳሰቡ ሁኔታዎች ድምር ውጤት ነው፡፡  የተቋማት የአሠራር ግልጽነት ማጣት፣ ደካማ የውስጥ ቁጥጥር እና ተጠያቂነት የሌለው ያልተገደበ ሥልጣን መኖር፣ ስግብግብነት    ሙስና እንዲፈለፈል ምቹ ሁኔታን ከሚፈጥሩ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው።

በሌላ መልኩ የሕግ የበላይነት መሸርሸር፣ ሙስና የሠሩ ሰዎች በሕግ አለመጠየቃቸው እና የቅጣት ርምጃዎች አድሏዊ መሆን፣ “እኔስ ምን እሆናለሁ?” የሚል የድፍረት ስሜት ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ በተለምዶ ሙስናን እንደ “ብልጠት”፣ ታማኝነትን ደግሞ እንደ “ሞኝነት”  መቁጠር እና  “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል”  የሚል የኖረ ገፊ ብሂል መኖር  እንዲሁም በዝምድና፣ በቡድን እንዲሁም በትውውቅ የመጠቃቀም ለሙስና መስፋፋት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ሙስና የሀገርን ምጣኔ ሀብት ከማቆርቆዝ ባሻገር የዜጎችን ተስፋ የሚያጨልም፣ እሴትን የሚሰብር ማነቆ ነው።  ሙስና የሕግን ሚዛን እያዛባ፣ የሕዝብ ሀብትን እያባከነ እና ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ እየሸረሸረ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የፀረ-ሙስና ንግግሮችን እንዲሁም ወቅታዊ ዘመቻዎችን መስማት አዲስ አይደለም፡፡ ትልቁ ክፍተት ሙስናን የአንድ ግለሰብ የግል ስግብግብነት ውጤት ብቻ አድርጎ በመቁጠር ጥቂቶችን ማሰር እና ወጥነት ላው መልኩ የመተግበር ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ችግር ከስሩ ነቅሎ ለመጣል ለሙስናን በር የሚከፍቱ የሥርዓት ክፍተቶች ላይ ለይቶ መሥራት ሲቻል ነው፡፡ ደካማ ቁጥጥር፣ የተንዛዛ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት፣ “ማን ይጠይቀኛል?” የሚለው ድፍረት ተቋማትን እንደ ሸረሪት ድር ጠላልፈዋቸዋል፡፡

ብዙዎች አፍሪካ የሙስና መናኸሪያ ብቻ እንደሆነች ቢያስቡም፣ ጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እና አሠራር በመዘርጋት ዓለም አቀፍ አርአያ መሆን የቻሉ የአፍሪካ ሀገራት አሉ፡፡ ሙስናን ከስሩ ነቅሎ ለመጣል እና ዳግም እንዳይከሰት ለመከላከል አርአያ የሆኑ ሀገራት አሉ፡፡  ጠንካራ የሕግ ተቋማት በመመሥረት፣ ጥብቅ የፀረ-ሙስና ሕግ እና የፋይናንስ ግልጽነትን በማስፈን በማድረግ ውጤታማ የሆኑ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት አሉ፡፡ የተረጋጋ ዴሞክራሲ፣ ገለልተኛ የዳኝነት አካል እና በሕዝብ አመኔታ የተገነባ የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት በመዘርጋት ሙስናን በከፍተኛ ደረጃ መከላከል የቻሉ ሀገራት በርካታ ናቸው።

እንደ  ሩዋንዳ  ያሉ ሀገራት ከ1994ቱ የርስ በርስ እልቂት በኋላ ያመጡት ለውጥ  እጅግ አስደናቂ ነው።  ሙስናን በምንም ዓይነት ቦታ ልንሰጠው አይገባም የሚል መርህን በማስፈናቸው ባለሥልጣናት ሳይቀሩ በሙስና ሲጠረጠሩ ወዲያውኑ ይከሰሳሉ፤ ይታሰራሉ። ዲጂታል አስተዳደርን በመዘርጋት ከሞላ ጎደል አብዛኞቹ የመንግሥት አገልግሎቶች (የመሬት፣ የፈቃድ፣ የመታወቂያ ወዘተ.) በኦንላይን በመስጠት ቀልጣፋ እና ግልጽ አሠራርን ዘርግተው ሙስናን ታግለዋል፡፡

ከእነዚህ ሀገራት የምንማረው ገለልተኛ እና ጠንካራ የፀረ-ሙስና ተቋማትን በማቋቋም፣ የፖለቲካ አመራሩን ቁርጠኝነት በማሳደግ እንዲሁም የተቋማት ነጻነትን እና አሠራር በማዘመን ብሎም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በማጣመር ግልጽ እና ቀልጣፋ አሠራርን ከተጠያቂነት ጋር መዘርጋት ከተቻለ ሙስናን ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር አሳይተዋል። ይህ ሲሆን ሕዝቡ በመንግሥት እና በሕግ የበላይነት ላይ ያለው እምነት ይጨምራል፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ የመንግሥትን ሕጋዊ ቅቡልነት ያሳድገዋል፡፡

ሙስናን ከምንጩ ለማድረቅ ተቋማዊ ሥር-ነቀል ለውጥ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ የበርካታ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ሙስናን ለመግታት የሚቻለው ሳያሰልሱ ስለ ሙስና አደገኛነት ከማስተማር ባለፈ የሕግ ማዕቀፎችን በማጥበቅ እና የቢሮክራሲ ቀዳዳዎችን በመድፈን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የመጀመሪያው ርምጃ ሊሆን የሚገባው በብቃት ላይ የተመሠረተ አስተዳደርን (ሜሪቶክራሲን) ማረጋገጥ ነው፡፡ የሲቪል ሰርቪሱን ሹመት እና ቅጥር ከፖለቲካ ታማኝነት እንዲሁም ከዝምድና አላቅቆ በዕውቀት እና በሙያዊ ብቃት ብቻ መምራት ያስፈልጋል፡፡

ይሁን እንጂ፣ ከሙስና አዙሪት ለመውጣት ተቋማዊ ማሻሻያ ብቻውን መፍትሔ አይሆንም፡፡ ሙስናን እንደ “ብልጠት”፣ ሐቀኝነትን ደግሞ እንደ “ሞኝነት” የሚመለከተው የተዛባ አስተሳሰብ እንዲሁም አባባል ትግሉን ግማሽ መንገድ ያስቀረዋል፡፡ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚልን የኖረ ታማኝነትን የሚንድ ነውረኛ ብሂል በመተው ዜጎች ጉቦ ከመስጠት እና ከመቀበል ተቆጥበው በንቃት ድርጊቱን በጋራ ሊጋፈጡት እንዲሁም ሊያጋልጡት ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን የሙስናን አዙሪት መስበር ይቻላል፡፡

በጥቅሉ የሙስና ትግል ስኬት የሚለካው በተገቡ ቃላት ወይም በሚደረጉ ንግግሮች ብዛት ሳይሆን፤ በተዘጉ የሙስና ቀዳዳዎች፣ በተዘረጉ ግልጽ አሠራሮችና የሕዝብ አመኔታ ነው፡፡ የመንግሥት ቃል በተግባር ሚዛን ተመዝኖ ውጤታማ እንዲሆን፣ ትግሉ ከወቅታዊ ዘመቻ ወጥቶ ወደ ጸና ጸረ ሙስና ሥርዓት ግንባታ መሸጋገር አለበት፡፡ ጊዜው የንግግር ሳይሆን፣ ሙስናን ከሥሩ የሚነቅል ጠንካራ እና ገለልተኛ ተቋማዊ ሥርዓት ለመገንባት ሁሉም መረባረብ አለበት፡፡

 

በኲር የጥቅምት 2 ቀን 2019  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here