አዲሱ ፍልሚያ እና ውጥረቱ

0
44

የነዳጅ ዘይት ሀብት ለዘመናት የዓለም አቀፍ ፖለቲካ፣ የጦርነቶች እና የጂኦፖለቲካዊ ሽኩቻዎች ዋነኛ ማዕከል  ሆኖ ዘልቋል፡፡ ሀገራት  የነዳጅ መስኮችን ለመቆጣጠር እና የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ ኾኖም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የዓለምን የኃይል ሚዛን የሚቀይር፣ የሀገራትን ብሔራዊ ደኅንነት የሚወስን እና መሪዎች ወደ ድርድር እንዲመጡ የሚያስገድድ አዲስ የተፈጥሮ ሀብት ብቅ ብሏል   ውኃ፡፡ አሁን ላይ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ እንዲሁም በደቡብ እስያ የሚስተዋሉት የፖለቲካ ውጥረቶች እንደሚያሳዩት የውኃ እጥረት ከአካባቢያዊ ወይም ከልማት ጉዳይነት አልፎ የደኅንነት፣ የሉአላዊነት እና የጂኦፖለቲካዊ የበላይነት ጉዳይ  ኾኗል፡፡

 

የችግሩ ገጽታ እና ዋና ዋና መንስኤዎች

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት በዓለም ላይ ከሁለት ቢሊዮን በላይ ሕዝብ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት የማግኘት እድል የለውም፡፡ ችግሩን ይበልጥ አደገኛ የሚያደርገው ደግሞ በዓለም ላይ ካሉ ዋና ዋና ወንዞች እና የውኃ አካላት መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከአንድ በላይ ሀገራትን አቋርጠው የሚያልፉ ድንበር ተሻጋሪ መሆናቸው ነው፡፡

በአሁኑ ዘመን ዓለማችን በበርካታ ምክንያቶች ሳቢያ ለውኃ እጥረት ተጋልጣለች፡፡ የሕዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ እድገት አንደኛው ምክንያት ሲሆን የከተሞች መስፋፋት፣ የኢንዱስትሪዎች እድገት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረግ የግብርና መስፋፋት የውኃ ፍጆታን በእጥፍ ጨምረውታል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥ እና የከፋ ድርቅ ነው፡፡ የሙቀት መጠን መጨመር፣ የዝናብ ስርጭት መዛባት እና ተደጋጋሚ ድርቅ  ምንጮችን እያደረቁ ይገኛሉ፡፡ ይህም ቀደም ሲል የነበረውን የውኃ ፍሰት በመቀየር ሀገራትን ወደ አልታሰበ ግጭት እየከተታቸው ነው፡፡

የቴክኖሎጂ ክፍተት እና የውኃ ብክነት ሦስተኛው ለውኃ እጥረት አጋላጭ ምክንያት ነው፡፡ በብዙ የውኃ አጠቃቀም ባለሙያዎች እንደተነገርው በየሀገራት የሚስተዋለው ነባር እና ውኃ አባካኝ የግብርና መስኖ ዘዴ  እንዲሁም በረሃ ላይ ከፍተኛ ውኃ የሚጨርሱ ሰብሎችን ማልማት የውኃ እጥረቱን ይበልጥ አባብሶታል፡፡

 

አራተኛው ምክንያት ደግሞ ሀገራት የውኃ ሀብታቸውን እንደ ብሔራዊ ሕልውና ጉዳይ በመቁጥር በብቸኝነት ወይም በበላይነት ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ጥረት ውጥረቱን ማባባሱ ነው፡፡

 

በውኃ ምክንያት ውጥረት ውስጥ የገቡ ቀጣናዎች

የዓባይ (ናይል) ተፋሰስ እና የዲፕሎማሲው አዲስ ምዕራፍ

በአፍሪካ ቀንድ ያለው የዓባይ ወንዝ ጉዳይ የዓለም  አቀፍ  የውኃ ፖለቲካ ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ዘመን እ.አ.አ በ1929 እና በ1959 የተፈረሙት ውሎች አብዛኛውን የውኃ ድርሻ ለታችኞቹ ሀገራት (ለግብጽ እና ሱዳን) በመስጠት የውኃው ዋና ምንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያን እና ሌሎችን የተፋሰሱን ሀገራት ያገለሉ ነበሩ፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ መገንባቷ በምሥራቅ አፍሪካ የነበረውን ታሪካዊ የበላይነት ሚዛን ቀይሮታል፡፡ ለኢትዮጵያ ግድቡ የልማት፣ የኃይል እና ከድህነት የመውጫ አቅም እንዲሁም የሉአላዊነት ምልክት ሲሆን ግብጽ ደግሞ የሕልውና አደጋ ደቅኖብኛል ትላለች፡፡

ከረጅም የዲፕሎማሲ ሽኩቻ በኋላም የላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በማጽደቅ ታሪካዊውን የ “ናይል ተፋሰስ ኮሚሽን”  መሠረት ጥለዋል፡፡ ይህም የቀደሙትን አግላይ ስምምነቶች በሕጋዊ መንገድ የመተካት ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

 

የመካከለኛው ምሥራቅ የወንዞች ውጥረት

በመካከለኛው ምሥራቅ የጤግሮስ እና የኤፍራጠስ ወንዞችን መነሻ ያደረገው የቱርክ፣ ሶሪያ እና ኢራቅ ውጥረት ሌላው በውኃ ምክንያት ዓለምን ሥጋት ውስጥ የከተታት ውጥረት ነው፡፡ ቱርክ በወንዞቹ ላይ የገነባቻቸው ግዙፍ ግድቦች ወደ ታችኞቹ ሀገራት የሚፈሰው የውኃ መጠን እንዲቀንስ በማድረጋቸው በሶሪያ እና በኢራቅ በኩል ከፍተኛ የግብርና፣ የኢኮኖሚ እና የአካባቢ ቀውስ መፈጠሩ ተገልጿል፡፡

 

የኢንዱስ ወንዝ የውኃ ስምምነት

የኢንዱስ ወንዝ የውኃ ስምምነት በሕንድ እና ፓኪስታን መካከል እ.አ.አ በ1960 የተፈረመ ታሪካዊ ስምምነት ነው፡፡ ይህ ውል በዓለም ላይ ካሉ ስኬታማ የድንበር ተሻጋሪ የውኃ አካላት ስምምነቶች አንዱ ተደርጎ ቢወሰድም በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው የቆየ የፖለቲካ ውጥረት እና በተደጋጋሚ በሚነሱ ግጭቶች ምክንያት አሁንም ድረስ ለከፍተኛ አደጋ እና ፈተናዎች ተጋርጧል።

 

የብራህማፑትራ ወንዝ

ቻይና በቲቤት አምባ ላይ በብራህማፑትራ ወንዝ ላይ የምትገነባቸው ግዙፍ ግድቦች በሕንድ እና ባንግላዴሽ ዘንድ ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ፈጥረዋል፡፡

 

የታላላቅ  ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሚና

የውኃ ፖለቲካ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ብቻ የሚደረግ ፍልሚያ አይደለም፡፡ ታላላቅ ሀገራት (እንደ አሜሪካ እና ቻይና ያሉ) እንዲሁም የባሕረ ሰላጤው ሀገራት እና የፋይናንስ ተቋማት (እንደ ዓለም ባንክ) የራሳቸውን ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎት ለማስጠበቅ በውኃ ዲፕሎማሲ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ የፋይናንስ ተቋማት በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ለሚገነቡ ፕሮጀክቶች ብድር እና ርዳታ የመከልከል ወይም የማገድ ርምጃዎችን በመውሰድ፤ ታላላቅ ሀገራት ደግሞ በድርድር ጠረጴዛዎች ላይ የፖለቲካ ጫና በማድረግ (ለምሳሌ በአሜሪካ አዘጋጅነት በሕዳሴው ግድብ ላይ ተካሂዶ የነበረው ድርድር) የኃይል ሚዛኑን ወደ አንድ ወገን ለማዘንበል ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡

 

ለመኾኑ  የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዓለም አቀፍ ሕጎች ምን ይላሉ?

በሀገራት መካከል የሚፈሱ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የውኃ አካላት አጠቃቀም እንዲሁም አስተዳደርን የሚመሩ ዓለም አቀፍ ሕጎች የተፋሰስ ሀገራትን ፍትሐዊ የመልማት መብት እና የጋራ ትብብር የሚያረጋግጡ ሕጋዊ አንቀጾች አሏቸው፡፡ እነዚህ ሕጎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.አ.አ በ1997 በጸደቀው የድንበር ተሻጋሪ የውኃ አካላት ኮንቬንሽን  ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡

በዚህ ኮንቬንሽን መሠረት አንቀጽ 5 እና 6 በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም ዙሪያ የሚያተኩሩ ሲሆን ማንኛውም ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ የሚያልፍበት ሀገር የወንዙን ውኃ በፍትሐዊ እና በምክንያታዊ መንገድ የመጠቀም እና የመልማት ሙሉ መብት አለው፡፡ ክፍፍሉም በውኃው መጠን ብቻ ሳይሆን በሀገራቱ የሕዝብ ቁጥር፣ በማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት፣ በመልክዓ-ምድራዊ አስተዋፅኦ እና በአማራጭ የውኃ ምንጮች መኖር ላይ ተመስርቶ ይወሰናል፡፡

ሀገራት በሚያካሂዷቸው ፕሮጀክቶች በሌሎች ሀገራት ላይ “ከፍተኛ ጉዳት”  እንዳያደርሱ ጥንቃቄ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው የተደነገገው ደግሞ በኮንቬንሽኑ አንቀጽ 7 ነው፡፡ ያልተጠበቀ ጉዳት ቢደርስ እንኳን ሀገራቱ ካሳ የመክፈል ወይም የመፍትሔ ርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለባቸው፡፡

አንቀጽ 9 እና 12 ደግሞ ሀገራት ስለ ውኃ ፍሰት እና መጠኑ መደበኛ መረጃ የመለዋወጥ እና ትልቅ ፕሮጀክት ከመጀመራቸው በፊት የማሳወቅ ግዴታ እንዳአለባቸው ያብራራል፡፡

በተጨማሪም በኮንቬንሽኑ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙ ወይም ሁሉንም ሀገራት ያላካተቱ  ስምምነቶች በዘመናዊ ዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው ተብራርቷል፡፡

 

የውኃ ዲፕሎማሲ እና መፍትሔዎች

ውኃ የግጭት መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ሁሉ በተቃራኒው ሀገራትን የሚያስተስር እና ሰላምን የሚያመጣ የትብብር ድልድይ የመሆን ዕድሉም ከፍተኛ ነው፡፡ የውኃ ሀብት ፍልሚያን ለማስቀረት እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚከተሉት መፍትሔዎች ወሳኝ ናቸው፦

የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትስስር፦ የውኃ ሀብትን ለኃይል ማመንጫነት የሚጠቀሙ ሀገራት (እንደ ኢትዮጵያ ያሉ) ኃይልን ለጎረቤቶቻቸው

በመጠነኛ ዋጋ በማቅረብ የቀጣናውን ኢኮኖሚ ማስተሳሰር ይችላሉ፡፡

የቴክኖሎጂ እና የዘመናዊ አሰራር ሽግግር፦ ታችኞቹ ሀገራት ውኃ አባካኝ የግብርና መስኖ ዘዴዎችን በመቀየር፣ የከተማ የቆሻሻ ውኃዎችን መልሶ በማጣራት እና የባሕር ውኃን ወደ ንጹህ ውኃ የመቀየር ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በወንዞች ላይ ያላቸውን ጥገኝነት መቀነስ አለባቸው፡፡

“ቨርቹዋል ውኃ”፡- ውኃ አጥርተው የሚያመርቷቸውን እና ከፍተኛ ውኃ የሚጨርሱ ሰብሎችን የውኃ ሀብት ከተትረፈረፋባቸው  ሀገራት በማስገባት የውኃ እጥረትን ማቃለል ይቻላል፡፡

ፍትሐዊ የትብብር ማዕቀፎች፦ የቀደሙ አግላይ ውሎችን በመተው የሁሉንም ተፋሰስ ሀገራት እኩልነት የሚያረጋግጡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መከተል እና ግልጽ የመረጃ ልውውጥ ማድረግ የጥርጣሬ እና የስጋት መንፈስን ይቀርፋል፡፡

በመሆኑም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የውኃ ጉዳይ የቴክኒክ ወይም የኃይድሮሎጂ ጉዳይ ብቻ መሆኑ አብቅቶ የሀገራት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ የብሔራዊ ደኅንነት እና የዲፕሎማሲ ዋና ማዕከል ኾኗል፡፡ በመጪዎቹ አስርት ዓመታት ዓለም የምትከተለው የውኃ ዲፕሎማሲ መስመርም በሁለት መንገዶች በኩል ሊያተኩር እንደሚችል ባለሙያዎች ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ አንደኛው በራስ ወዳድነት፣ በብቸኝነት፣ በበላይነት እና በቆዩ አግላይ ውሎች ላይ የተመሠረተ ግጭት የሚያስከትል መንገድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በፍትሐዊነት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ዘላቂ ትብብር ነው፡፡

ስለዚህ ሀገራት ሁለተኛውን መንገድ የመምረጥ ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም በአየር ንብረት ለውጥ ዘመን የሚከሰት የውኃ ቀውስ ለአንድ ሀገር ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ አካባቢው ውድቀትን የሚያመጣ በመሆኑ የውኃ ዲፕሎማሲን ማጠናከር የዓለም ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጫ ዋነኛ መሳሪያ ነው፡፡

 

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥቅምት 9  ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here