ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊያዊና ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር የሺህ ዓመታት ዕድሜ ያለው ነው፤ ይሁን እንጂ የባሕር በር ማጣቷ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ብሔራዊ ደኅንነት፣ ሉዓላዊነትና በዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።
የታሪክ መዛግብት እንደሚያስገነዝቡት ከጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔና የባሕር ንግድ ታሪክ እስከ ዘመናዊው ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ ድረስ የባሕር በር ጉዳይ ከኢትዮጵያ ኅልውና እና የዕድገት ጉዞ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህ ወሳኝ የሕልውና ጉዳይ በተለያዩ ያልተገቡ ምክንያቶች ከሀገራችን እጅ ወጥቶ ቆይቷል፡፡
ኢትዮጵ እና የባሕር በር ባለቤትነቷ በታሪክ መነጽር
ጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ በዓለም ገናና እንዲኾን ያስቻለው የአዱሊስ ወደብ ባለቤት መኾኑ ነበር፡፡ ይሁን እንጅ በ15ኛው ክፍለ ዘመን በዐፄ ዘርዓያዕቆብ ዘመን የባሕር በሩን ደኅንነት ለመጠበቅ “ባህረ- ነጋሽ” የተባለ ልዩ የሥልጣን መዋቅርም ተዘርግቶ ነበር፡፡
በሌላ በኩል በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኦቶማን ቱርክ እና የጣሊያን መስፋፋት በኢትዮጵያ የባሕር ባለቤትነት ጉዳይ የታሪክ ጠባሳን ጥሎ አልፏል፡፡ ይህ የኦቶማን ቱርክ ወረራ ሀገራችን ምጽዋን እና አርኪቆን እንድታጣ አድርጓል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ደግሞ ጣሊያን የውጫሌን ውል መሥረት በማድረግ እና አሰብን በመግዛት ሀገራችንን የባሕር በር አሳጥታለች፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በ1983 ዓ.ም የደርግ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ ኢሕአዴግ ሀገሪቱን የማስተዳደር ስልጣን ያዘ፤ ይህን ተከትሎም በ1985 ዓ.ም ኤርትራ ሉዓላዊት ሀገር ኾነች፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ሙሉ በሙሉ እንድታጣ አድርጓታል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ጸጋ ያጣችው በፖለቲካ ሸፍጥ እና የሀገሪቱ ሰፊ ሕዝብ ባልወሰነበት ዴሞክራሲያዊ ባልኾነ መንገድ ነው።
የባሕር በር ማጣት እና ጫናዎቹ
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ባለመሆኗ በዓመት ከአራት ቢሊዮን ዶላር (ከ655 ቢሊዮን ብር ) በላይ ወጭ ታደርጋለች፡፡ የውጭ እና ገቢ ንግድ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት በጅቡቲ በኩል የሚያልፉ በመሆናቸው ሀገሪቱ ባለፉት 36 ዓመታት ውስጥ ብቻ ለጅቡቲ ወደብ ኪራይ እስከ 72 ቢሊዮን ዶላር አውጥታለች። ይህም ከ30 በላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያስገነባ ነው፡፡
በተለያዩ መስኮች የተካሄዱ የጥናት ውጤቶችን ይፋ የሚያደርገው ሪሰርች ጌት እንዳስነበበው የባሕር በር ማጣት በውጭ ንግድ ላይ የሚደረግን እንቅስቃሴ ውድ ያደርገዋል። እጅግ ከፍተኛ ለኾነ የውጭ ምንዛሪ ወጪም ያጋልጣል። የሉዓላዊነትና የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ሌላው ጫና ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ አንዳንዱ እንቅስቃሴ በሌሎች ሉዓላዊ ሀገራት እጅ ውስጥ በመኾኑ የሀገርን የጂኦፖለቲካ ድርድር አቅም ስለሚያዳክም ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ወደብ አልባነት የንግድ ተወዳዳሪነትን ይቀንሳል፤ ይህም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች የዋጋ ንረት እንዲገጥማቸው በማድረግ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሀገሪቱን ተወዳዳሪነት ይጎዳል። ሀገራችንም ታዲያ በፖለቲካ ሴራ እና ባልተገባ መንገድ የባሕር በር በማጣቷ ከላይ የተዘረዘሩትን ጫናዎች ተሸክማለች፡፡
የባሕር በር ባለቤትነት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
እንደ ሪሰርች ጌት መረጃ የባሕር በር ባለቤት መሆን የውጭ ንግድን ፈጣን፣ አስተማማኝ እና ዝቅተኛ ወጪ እንዲኖረው በማድረግ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እና የኤክስፖርት ንግድን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።
ኢትዮጵያ ያላት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ አቅም ከባሕር በር ጋር ቢጣመር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል፤ በቀይ ባሕር እና በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የሰላም፣ የጸጥታ እና የኢኮኖሚ ትብብር ማዕከል እንድትሆን ማስቻሉ ደግሞ አንደኛው አበርክቶ እንደሆነ የመረጃ ምንጩ ጠቁሟል።
ከዚህ በተጨማሪም የባሕር በርን እና የባሕር ትስስር አገልግሎቶችን (Maritime Services) በባለቤትነት ማስተዳደር በርካታ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የውጭ ምንዛሪ ክፍተትን ለመሙላት ወሳኝ ሚና አለው።
የእያንዳንዱን ዜጋ የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚያንኳኳውን የባሕር በር ጥያቄን መንግሥት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ይዟል፡፡ ይህ ሀገራዊ ጥያቄም የመንግሥት አንደኛው አጀንዳ ስለመኾነኑ ነው በቅርቡ በተካሄደው የፌደራል መንግሥት ምሥረታ ወቅት የተነገረው፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከባሕር በር ከ60 ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት የምትገኝ ብቸኛዋ ሀገር ናት፤ የባሕር በሯን ያጣችው ደግሞ በፖለቲካዊ እና የውጭ ጣልቃ ገብነት ምክንያቶች ነው፡፡ ይህም በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እና ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ከባድ ሸክም ጥሎባታል፡፡
የባሕር በር ማጣት በሀገር ግንባታ፣ በሉዓላዊነት እና በዜጎች ኑሮ ላይ ዘርፈ ብዙ ጫናን ያስከትላል፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በመንግሥት ምሥረታ ወቅት እንደተናገሩት የባሕር በር በትኩረት ከተያዙ ሀገራዊ አጀንዳዎች መካከል ዋናው መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒሥትሩ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ “የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምክንያታዊና ፍትሐዊ ጥያቄ ነው” በማለት አስገንዝበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒሥትሩ አክለውም፤ “አቅም በነበረን ወቅት የራሳችንን ጉዳይ ራሳችን ወስነናል፤ በተዳከምን ጊዜ ግን ሌሎች በእኛ ላይ ወስነውብናል፤ በተዘጋጀንባቸው ዘመናት ከቀይ ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ፣ ከሜዲተራኒያን እስከ አትላንቲክ ተጉዘናል፡፡ ባልተዘጋጀንበት ወቅት ደግሞ መውጫ መግቢያ በራችን ተዘግቶብናል” በማለት ነው የጉዳዩን አሳሳቢነት ያስገነዘቡት፡፡ ይህንን መብት ለማስከበር ጦርነት እንደማያስፈልግ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስሥር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ “ይህን ለማሳካት ጦርነትም ኾነ የኃይል አማራጭ አንፈልግም! ፍላጎታችንን ማሳካት የምንሻው በሰላማዊ አማራጭ ነው” ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
“የውጭ ግንኙነታችን የኢትዮጵያን ተጽዕኖ በዓለም ላይ ሊያሳይ በሚችል መልኩ እንዲቃኝ ይደረጋል፤ ከሁሉም የዓለም ሀገራት ጋር ብሔራዊ ጥቅማችንን መሠረት አድርገን በትብብር የመሥራት መርሐችንን እንገፋበታለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒሥትሩ እንዳሉት የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያለ ባሕር በር እውን ሊኾን አይችልም፤ በመኾኑም በሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያ ወጥቶ መግቢያ በር እንዲኖራት መንግሥት ተግቶ ይሠራል። የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ ሙሉ በሙሉ የሚደገፍ ነው፤ ቢኾንም “መዘንጋት የሌለበት ትልቁ እውነት ኢትዮጵያ እየጠየቀች ያለው በታሪክ የእሷ የነበረውን መብት ነው!” ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም እ.አ.አ በ1982 የጸደቀው የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ስምምነት እንደሚያስገነዝበው ወደብ አልባ ሀገራት ወደ ባሕር የመድረስ መብት አላቸው። በዚህ ዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ወደብ አልባ ሀገራት ከባሕር ዳርቻ ሀገራት ጋር በሚያደርጉት ስምምነት የባሕር በርን የመጠቀም መብት አላቸው።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት እና በሰላማዊ መንገድ አስተማማኝ የባሕር በር እንዲኖራት የምታደርገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግዋል፡፡ ሀገሪቱ በዲፕሎማሲያዊ አግባብ የባሕር በር ለማግኘት ያደረገችው ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እና ይሁንታ ለማግኘት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት መጣሉንም አስረድተዋል።
ወደብ አልባነት በሉዓላዊነት እና በዜጎች ኑሮ ላይ የሚያመጣውን ዘርፈ ብዙ ጫና በተመለከተ በደብረ ብርሐን ዩኒቨርሲቲ የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ሐሳቡ ተስፋም ለአሚኮ ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡ እንደ አቶ ሐሳቡ ማብራሪያ የባሕር በር ጉዳይ የኢኮኖሚ ወይም የፖለቲካ ውይይት ርዕስ ብቻ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፤ ይልቁንም የሀገሪቱን ታሪካዊ መብት፣ የብሔራዊ ደኅንነት ምስጢር ጥበቃ እና የዘላቂ ኅልውና መረጋገጥን እውን የሚያደርግ የሉዓላዊነት መሠረት ነው፡፡ ወደብ አልባ መኾን በተለይም በወታደራዊ እና በቴክኖሎጂያዊ መረጃዎች ላይ የሚያመጣው አደጋ ከፍተኛ ነው፡፡ መምህሩ ይህንን ሲያብራሩ “በሌላ ሀገር ሳሎን የሚያልፍ ሰው የተሰወረ ምስጢር ሊኖረው አይችልም” በማለት ይገልጹታል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ የምታስገባቸው ስትራቴጂያዊ ቁሶች በጎረቤት ሀገራት የፍተሻ እና የምርመራ ማዕቀፍ ውስጥ ማለፋቸው የሀገሪቱን ስስ ብልት ለጠላቶች አሳልፎ የመስጠት አደጋ አለው፡፡ በተጨማሪም በጅቡቲ ውስጥ በርካታ ባላንጣ የውጭ ኀይሎች የጦር ሠፈራቸውን መሥርተዋል፤ በእነዚህ ኀይሎች መካከል ግጭት ቢፈጠር ቀድማ መውጫ በሯን የምታጣው ኢትዮጵያ ናት፡፡
በሌላ በኩል ዜጋው በየዕለቱ ለሚገጥመው የኑሮ ውድነት ዋናው ምክንያት ረጅሙ የሎጂስቲክስ መስመር እና ለጎረቤት ሀገራት የሚከፈለው ከፍተኛ የትራንዚት እና የጉምሩክ ክፍያ ነው፡፡ ነጋዴው ይህንን ወጪ በቀጥታ ወደ ሸማቹ ስለሚያስተላልፈው የወደብ አልባነት የመጀመሪያው ሰለባ ራሱ ዜጋው መኾኑን መምህሩ ያስገነዝባሉ፡፡
ዜጎች በልዩ ልዩ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልዩነት ቢኖራቸውም በሀገር ደኅንነት እና በዘላቂ ኅልውና ላይ ግን የልዩነት መስመር ሊሰመር አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዞ ታሪካዊ ስህተትን በሰላማዊ መንገድ የሚያርም፣ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጠናክር እና የጋራ ብልጽግናን የሚያመጣ ነው፡፡ በሁሉም መስፈርቶች የወደብ ባለቤት መሆን የሚያስገኘው ትርፍ በእያንዳንዱ ዜጋ ቤት የሚደርስ በመኾኑ በአንድነት መቆም ይገባዋል።
(ሰናይት በየነ)
በኲር የጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


