የድካም ፍሬ እንዳይባክን!

0
31

“የጎበዝ ማጭድ ታስታውቃለች፣

እንደ ሀዘንተኛ ፊቷን ፈጅታለች፣

እራሷን ታማ ሻሽ ጠምጥማለች።

አልቢኑ ስለት ሰውየው ደፋር፣

ይከምረዋል ነዶን እንዳፈር።” በማለት ከበጋው ወቅት ጀምሮ ማሳውን አርሶ፣ አለስልሶ፣ ዘርቶ እና  አርሞ ሰብሉን በጥሩ ሁኔታ ለአጨዳ ያደረሰ አርሶ አደር  ማጭዱ ሳይቀር እንዲህ በግጥም ይወደሳል፡፡

ወርቃማው የሰብል ስብሰባ ወቅት አየሩን በበረከት ድባብ ሞልቶታል። ፀሐያማው ሰማይ ከታታሪ አርሶ አደሮች ላብ ጋር ተስማምቶ ማሳዎች ዐይን በሚማርኩ ሕብረ ቀለማት ባላቸዉ የአበቡ አዝርዕት  ሸፍኗዋል፤ በበቆሎ፣ በኑግ፣ በጤፍ፣ በበርበሬ፣ በሰሊጥ…፡፡

በዚህ አስደሳች የልፋት ፍሬ ማጨጃ ወቅት በስልክ ተገናኝተን ባወጋናቸው ታታሪ አርሶ አደሮች ድምፅ ውስጥ የተስፋ እና የጥጋብ ዜማ ይስተጋባል። ተፈጥሮ ፊቷን አብርታ፣ አርሶ አደሩም ወገቡን አስሮ ማሳው ላይ ደፋ ቀና በሚልበት በዚህ ወቅት በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የጃዊ ወረዳ  አርሶ አደር ውዱ ብርሐን እና በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ነዋሪዉ አርሶ አደር ጋሻው ግዛው የዘንድሮ የእርሻ ውሎ ውጤታማ እና ለሌሎችም አርአያ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ውዱ ብርሐን በማሳቸው ላይ የተሸፈነው ሰብል ሲታይ ልብን በደስታ ይሞላል። አሁን ላይ በደቦ እና ቤተሰባቸውን አስተባብረው የደረሰውን ሰብል  አጭዶ እና ወቅቶ ምርቱን ወደ ጎተራ ለማስገባት በከፍተኛ ርብርብ ላይ ይገኛሉ።

“ያለፉት ሁለት ሳምንታት አየሩ ፀሐያማ በመሆኑ ለሰብል ስብሰባችን ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮልናል” የሚሉት አርሶ አደር ውዱ የዘንድሮው የሰብል ቁመና እጅግ ተስፋ ሰጪ መሆኑን በደስታ ይናገራሉ። በማሳቸው ላይ የተለያዩ የቅባት እና የጥራጥሬ ሰብሎችን በስፋት አልምተዋል፤ ሦስት ሄክታር ሰሊጥ፣ አንድ ሄክታር በቆሎ፣ አምስት ሄክታር አኩሪ አተር እንዲሁም በሌላ ማሳቸው ላይ ደግሞ ለውዝ ዘርተዋል። በአሁኑ ወቅት በቆሎ፣ ለውዝና ሰሊጥ እየሰበሰቡ ነው፡፡ ሰፋ ያለ መሬት የሸፈነው አኩሪ አተር ደግሞ በቅርብ ቀናት ውስጥ ደርሶ ወደ ማከማቻ እንደሚገባ እየተጠባበቁ ነው።

የአርሶ አደር ውዱ የስኬት ሚስጥር ግን ጉልበትን በብዛት መገልገላቸው ብቻ አይደለም ለዘመናዊ አሠራር ያላቸው ቅርበት እንጂ፤ መሬታቸውን በወቅቱ ለማረስ ትራክተርን፣ ምርታማነትን ለማሳደግ ደግሞ ሰውሠራሽ ማዳበሪያን በበቂ ሁኔታ ተጠቅመዋል።

“ከዚህ ቀደም በራሳችን ባህላዊ መንገድ ነበር ጎተራችንን የምንጠቀመው፤ አሁን ግን በመንግሥት የግብርና ባለሙያዎች በሚሰጡን ምክር መሰረት ዘመናዊ ጎተራ በመጠቀም ምርት እንዳይባክን እንጠነቀቃለን፤” በማለት የድህረ-ምርት አያያዛቸውን ገልፀዋል፡፡

ተለዋዋጭ የሆነው የአየር ንብረት ድንገተኛ ዝናብ ይዞ ቢመጣ እንኳን ምርታቸው እንዳይበላሽ  በአንድ ሳምንት ውስጥ የደረቀውን ሰብል በፍጥነት ወቅተው ወደ ጎተራ ለማስገባት የጊዜ ገደብ አስቀምጠው እየሠሩ ይገኛሉ። ከዚህ ትጋታቸውም በዋና የገቢ ምንጭነት ከያዙት የሰሊጥ ማሳቸው ብቻ እስከ 15 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ በልበ ሙሉነት ነግረውናል።

ከጃዊ ወረዳ ወጣ ብለን ወደ ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ስናቀና ደግሞ ሌላ የትጋት ተምሳሌት እናገኛለን- አርሶ አደር ጋሻው ግዛው፡፡ አርሶ አደሩ  በዘንድሮው የምርት ዘመን ከፍተኛ የገበያ ተፈላጊነት ባላቸው የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው  እየሠሩ ይገኛሉ።

“የዘንድሮው ዝናብ መጠነኛና ለእርሻ ሥራችን እጅግ ተስማሚ ነበር፤” በማለት ተፈጥሮ ያደረገችላቸውን ድጋፍ የሚያስታውሱት አቶ ጋሻው እስከ አራት ሄክታር በሚደርስ መሬት ላይ አኩሪ አተር፣ ሦስት ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ ሰሊጥ እንዲሁም በተወሰነ ማሳ ላይ ጤፍ በማልማት የሰብል ስብጥራቸውን አስፍተዋል።

መረጃውን እስካጋሩን ጥቅምት የመጀመሪያው ሳምንት ድረስ ሰሊጡ ለአጨዳ  ደርሶ ሌሊት እና ቀን እየተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ቀጣዩ የህዳር ወር አጋማሽ ደግሞ የአኩሪ አተር ስብሰባ በስፋት የሚጀመርበት ነው። አቶ ጋሻው እንደሚያስረዱት ትልቁ ፈተና ምርቱን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን በሰላም ወደ ጎተራ ማስገባት ነው። በተለይ እንደ ሰሊጥ ያሉ ጥንቃቄ የሚሹ ሰብሎች ልዩ እንክብካቤ ይሻሉ። ሰሊጥ ታጭዶ በሚከመርበት (ሂላ በሚደረግበት) ወቅት ምስጥ ገብቶ ምርቱን እንዳያበላሸው ልዩ ፀረ-ተባይ ኬሚካል ይረጫል። ይህ ጥንቃቄ የታጨደው ሰብል  ደርቆ እስኪወቃና ምርቱ በተሽከርካሪ ተጓጉዞ  ማከማቻ እስከሚገባ ይዘልቃል፡፡

የጃዊው ነዋሪ አርሶ አደር ውዱ ብርሐን እና የመተማው አርሶ አደር ጋሻው ግዛው እንደ ሚሉት ማሳ፣ የሥራ ትጋት፣ ዘመናዊ የግብዓት አጠቃቀም፣ የባለሙያ ምክር እና ጥንቃቄ የተሞላበት የድህረ-ምርት አያያዝ ሲጣመሩ እንዴት የሀገርን ኢኮኖሚ መደገፍ የሚችል ምርት ማግኘት እንደሚቻል የሚያሳዩ ህያው ምስክሮች ናቸው። በአካባቢያቸው ተስማሚው የአየር ንብረት ከአርሶ አደሩ ላብ ጋር ተዳምሮ አሁን ማሳዎቹ በረከትና ጥጋብ አብሳሪ ሆነዋል። እነዚህ በፀሐይ የነደዱ፣ በዝናብ የታጠቡ እጆች ዛሬም የሀገርን ኢኮኖሚ እንደተሸከሙ ናቸው። የዘንድሮው ምርታቸው ማሳያም የሀገር እድገት መሰረት የሚጀምረው ከእነዚህ ጀግና አርሶ አደሮች ማሳ መሆኑን በድጋሚ ያረጋገጠ ነው።

አርሶ አደሩ ሌሊት  እና ቀን ተግቶ፣ ፀሐይና ዝናብ ተፈራርቆበት ያመረተው እህል ሙሉ በሙሉ ጎተራ ይገባል ወይ? በሀገራችን የግብርና ዘርፍ ውስጥ በስፋት ከሚነሱ ፈተናዎች አንዱ የሆነው የምርት ብክነት ጉዳይ ከእርሻ ማሳ አንስቶ እስከ ማዕድ ድረስ ያለውን ሰንሰለት የሚፈታተን ትልቅ ችግር እንዴት መፍታት ይቻላል? ለሚሉት ጥያቄዎቻችን በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የድህረ-ምርት አያያዝ ባለሙያ አቶ ምትኩ መላኩ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውናል።

አቶ ምትኩ እንደገለጹት የምርት ብክነትን በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፍሉታል። የመጀመሪያው “የመጠን ብክነት” ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “የጥራት መጓደል ብክነት” ነው። ይህ ብክነት የሚጀምረው ገና ዘር መሬት ላይ ከሚወድቅበት የቅድመ-ምርት ጊዜ አንስቶ (በአረም፣ በነፍሳት፣ በበሽታ… ምክንያት) እስከ ድህረ-ምርት (ከመሰብሰብ፣ ማጓጓዝ፣ ማበጠር፣ ማከማቸት እስከ ማዕድ) ድረስ ባለው ረጅም ጉዞ ውስጥ ነው።

“በሀገራችን አሁን ባለው መረጃ መሰረት እስከ 30 በመቶ የሚደርስ የምርት ብክነት ያጋጥማል፤ ይህ ደግሞ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የድካም ፍሬ መና መቅረት ነው” በማለት አቶ ምትኩ የችግሩን ስፋት በአሃዝ አስደግፈው ገልፀዋል። ለዚህ ብክነት ዋና ምክንያቶች ናቸዉ ብለው የሚያነሷቸው ደግሞ አርሶ አደሩም ሆነ ነጋዴው ምርትን በአግባቡ እና በጥንቃቄ አለመያዙ እንዲሁም ኋላቀር የሆኑ የአሰባሰብ እና የማከማቻ ልምዶችን አለማዘመኑ ነው።

የምርት ብክነትን መቀነስ የሚቻለው በሁለት ቁልፍ ስልቶች መሆኑን ባለሙያው ያሰምሩበታል።

ግንዛቤ መፍጠር፦ ይህ አርሶ አደሩን ብቻ ሳይሆን ነጋዴዎችን፣ ቸርቻሪዎችን እና ዩኒየኖችን በሙሉ ማቀፍ ያለበት ሥራ ነው። ሁሉም አካል ምርትን ስለመያዝ ጥበብ በቂ እውቀት ሊኖረው ይገባል።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም፦ የመሰብሰቢያ፣ የመውቂያ፣ የማበጠሪያ፣ የማድረቂያ እና ዘመናዊ የማከማቻ ቴክኖሎጂዎችን (እንደ ዘመናዊ ጎተራ እና ፒክስ ባግ) በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ ነው።

ምርትን በሚገባ ለማከማቸት “ክሬብ” የተሰኙ እህልን አየር እንዲያገኝ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው።

በአማራ ክልል ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቴክኖሎጂ አጠቃቀም  አበረታች ለውጦች እየታዩ መሆኑን አቶ ምትኩ ይመሰክራሉ። አርሶ አደሩ ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ (በትራክተር ማረስ) ቴክኖሎጂን እየተላመደ ነው። በተለይም ስንዴን ለማጨድ እና ለመሰብሰብ የኮምባይነር ማሽኖች አጠቃቀም በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል። ከዚህም ባሻገር ለጤፍ፣ ገብስ፣ ሩዝና ማሽላ የሚሆኑ ልዩ ልዩ የመውቂያ ማሽኖች በስፋት ሥራ ላይ ውለዋል። ይህ እንቅስቃሴ በተለይ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ጎንደር እና ወልቃይት ጠገዴ ዞኖች ውስጥ እጅግ አበረታች ደረጃ ላይ ይገኛል።  ቢሆንም ግን ከአርሶ አደሩ ፍላጎት አንፃር የድህረ- ምርት ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በበቂ ሁኔታ ለማሳደግ ገና ብዙ ሥራ ይጠበቃል ነው ያሉት።

በዘንድሮው የመኸር ወቅት  በክልሉ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቀድመው የደረሱ እንደ ገብስ፣ ቦለቄ፣ ማሾ፣ ሰሊጥ እና ጤፍ የመሳሰሉ ሰብሎች በመሰብሰብ ላይ ይገኛሉ። እስካሁንም ከ250 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ያለው ምርት ተሰብስቧል።

ባለሙያዉ እንዳስገነዘቡት አርሶ አደሩ ሰብሉን በወቅቱ መሰብሰብ፣ ሲከምርም በደረቅ ቦታ ማስቀመጥ፣ በአግባቡ ማድረቅ፣ ማገላበጥ፣ በጥንቃቄ ማጓጓዝ እና መውቃት ይገባል፡፡

በተጨማሪም አርሶ አደሩ ሰብሉ በደረሰበት ቅጽበት ጊዜ ሳያጠፋ፣ ከፀሐይና ዝናብ እንዲሁም ከብክነት በጸዳ መልኩ በፍጥነት እንዲሰበስብ  አቶ ምትኩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

መረጃ

የምርት ብክነትን ለመቀነስ ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች፦
ከመጠን በላይ ሳይደርቅ በወቅቱ መሰብሰብ፤
ፀሐያማ እና ደረቅ አየር በሆነባቸው ቀናት ምርትን መሰብሰብ፤
የታጨደውን ሰብል በአግባቡ አናፍሶ እና አድርቆ መከመር፤
እንደ ኮምባይነር ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፤
ከአፈር ጋር እንዳይቀላቀል ዘመናዊ ጆንያዎችን መጠቀም፤
ምርቱን ለማጓጓዝ ተገቢውን ማሸጊያ መጠቀም፤
ከተባይ የሚከላከሉ ከብረት የተሠሩ የእህል ማከማቻ ጎተራዎችን መጠቀም ይገባል፡፡

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here