የማምሻ ዕድሜ እና የትውልዱ ኃላፊነት

0
26

በጠዋቱ የማሕበራዊ አምድ መጣጥፌን ለማዘጋጀት ባሕር ዳር ከተማ በምትገኘው ወደ ሰላም አድርጊው ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን አቅንቼ ነበር፡፡ በዚያም ዐይኔ የቤተክርስቲያኑን አጥር ተደግፈው ጸሎት የሚያደርጉ ፀጉራቸው ሙሉ በሙሉ ወደ ነጭነት የተቀየረ አዛውንት ላይ አረፈ፡፡ እማሆይ ስፈልግ ባዬ ይባላሉ፤ ዕድሜያቸውን በውል ባያውቁትም አባታቸው በጣሊያን ወረራ ጊዜ መወለዳቸውን እንደነገሯቸው ያስታውሳሉ፡፡

እማሆይ ስፈልግ የሚኖሩበትን አካባቢ (ጭምባን )ከሁለት ዓመት በፊት ጥለው ነበር ባሕር ዳር የከተሙት፡፡ በአሁኑ ጊዜም ከልጅ ልጆቻቸው ጋር እየኖሩ ናቸው፡፡ አንደኛው የልጅ ልጃቸው ቤተክርስቲያን እንዳደረሳቸውም ነገሩኝ፤ “የልጅ ልጆቼ ባይደግፉኝ ኖሮ ለልመና እዳረግ ነበር!” በማለትም የእንባቸው ምስጢር ባይገባኝም ዱብ ዱብ አደረጉት፡፡

ሌላው በዛው ቤተክርስቲያን የሚረዳቸው ሰው ስለሌለ በልመና ተሰማርተው ያገኘኋቸው ደግሞ የ85 ዕድሜ አዛውንት አቶ አለኸኝ በለው ይባላሉ፡፡ ከፎገራ ወረዳ እንደ መጡ የነገሩኝ  አዛውንቱ ልጆቻቸውን በሞት ስላጡ የሚረዳቸው ሰው አልነበረም፡፡ ኑሯቸው ያሳሰባቸው ጎረቤቶቻቸው  “ከተማ ቢሄዱ ሰው ይረደዎታል” ሲሏቸው የእነሱን ምክር ሰምተው ወደ ባሕር ዳር መጡ፤ በየቤተክርስቲያኑ  እየተዟዟሩም የዕለት ጉርሳቸውን እየለመኑ ይኖራሉ፡፡

አዎ! የነዚህ ይሁለት ዓለም ሰዎች ታሪክ የብዙዎች ኢትዮጵያውያን አረጋዊያን ታሪክ ነው፡፡ አንዳንዶች በመጨረሻው ዘመናቸው ጧሪ ቀባሪ ሲያገኙ አንዳንዶች ደግሞ ለልመና አደባባይ ይወጣሉ፡፡ ይሁንና አሁን ላይ አረጋዊያን የምንላቸው በጉብዝና ጊዜያቸው ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ቤተሰብ ያስተዳደሩ፣ ማሕበረሰብን ይመሩ የነበሩ ናቸው፡፡ አሁንም በማምሻ ዕድሜ ላይ ኾነውም እድሉን ካገኙ የሚያበረክቱት ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡

የአረጋዊያን ሚና

ሁሉም አረጋውያን በረጅም የሕይወት ልምዳቸው እና በጥበባቸው ማኅበረሰቡን በበጎ መንገድ የመምራት ዐቅምና የላቀ የመሪነት ተሰጥኦ አላቸው፡፡ አዳዲስ የሥራ ፈጠራ ሐሳቦችን በማስፋፋት፣ ለሀገር ታሪክ እና ቅርሥ ጥበቃ በማድረግ፣ በሽምግልና እና በባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓት ሰላምን በማስፈን እንዲሁም ትውልድን በማስተሳሰር እና በማቀራረብ በኩል የማይተካ ሚና ይጫወታሉ፡፡

አረጋውያን በመልካም ምክራቸው የማሕበረሰብ አንድነት እንዲጠናከር የሚያደርጉ አማካሪዎች፣ የጥንታዊ የባሕል፣ ወግ እና ልማድ ማሕደር ጥበብ የተሞላበት ሀገር በቀል እውቀት አጋሪዎች እንዲሁም ቤተሰብን በመደገፍ ልጆችን በፍቅር የሚንከባክቡ የሕይወት መሠረቶች ናቸው፡፡ ታዲያ ይህንን የአረጋዊያንን አበርክቶ ለመዘከር በየዓመቱ የአረጋውያን ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ እና በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ይውላል፡፡

የበዓሉ ታሪካዊ ዳራ

የአረጋውያን ቀን መከበር የጀመረው እ.አ.አ በ1991 ሲሆን ዓላማውም አረጋውያን ያበረከቱትን  አስተዋጽኦ ለመዘከር፤ ለአረጋውያን እውቅና ለመስጠት፤ ሁሉንም ዕድሜ አካታች ማሕበረሰብ ለማበረታታት፤ በሕይወታቸው ላይ ተጽዕኖ የሚያደርሱ ጉዳዮችን ለመፈተሽና መፍትሔ ለመስጠት፤ በትውልድ መካከል ያለውን አብሮነት ለማጎልበት እና በሕብረተሰቡ ዘንድ ሰፊ ግንዛቤ ለመፍጠር በመታሰቡ ነው፡፡

የዘንድሮው ዓለም ዓቀፍ የአረጋውያን ቀን  መሪ ቃልም፤ “እንክብካቤ እና ደኅንነት ለአረጋውያን መልካም ሕይወት!” የሚል ነው፡፡ አረጋውያን በዕድሜ መግፋት፣ በጤና መታወክ እና በኢኮኖሚያውይ ድጋፍ ማነስ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች በሰፊው ተጋላጭ ስለሚሆኑ በየደረጃው ትኩረት ሊሰጣቸው እና የተቀናጀ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አመላካች የኾነ መሪ ቃል ነው፡፡

የአረጋውያን ትርጉም

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትርጉም መሠረት አረጋውያን የሚባሉት ዕድሜያቸው 60 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ በሀገራችንም በአሁኑ ጊዜ ይኸው ትርጉም ተቀባይነት ያለው ሲሆን ከጡረታ መውጫ ዕድሜ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

ከሰሞኑ የአረጋውያን ቀን በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን(ሚኮ) ቅጥር ግቢ ሲከበርም እንደተገለጸው  በክልሉ የአረጋውያን ቁጥር በፍጥነት በማደግ ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከዘጠኝ ሰዎች አንዱ አረጋዊ ነው፤ በ2050 ደግሞ ከአምስት ሰዎች መካከል አንዱ አረጋዊ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ከተሜነት፣ የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት እና ዘመናዊ የሕይወት ዘይቤ ለአረጋዊያን ቁጥር መጨመር ምክንያት ኾነዋል፡፡

የአማራ ክልል የፕላን እና ልማት ቢሮ ከ2010 እስከ 2022 ባካሄደው የሕዝብ ብዛት ትንበያ መሠረትም በክልሉ የአረጋውያን ቁጥር አንድ ሚሊዮን 468ሺህ 543 (6 ነጥብ 14 በመቶ) ደርሷል፡፡ ቁጥሩም በየዓመቱ በ01 ነጥብ 31 በመቶ ያድጋል፡፡

የአማራ ክልል አረጋውያን ቁጥር በዕድሜ ሲታይ ከ60 እስከ 74 ዓመት 73 በመቶ፣ ከ75 እስከ 80 ዓመት 11 በመቶ እና 80 ዓመት በላይ የኾናቸው ደግሞ 16 በመቶ ደርሷል፡፡ 20 በመቶ የሚኾኑት በከተማ ሲገኙ በገጠር ደግሞ 80በመቶ ይኖራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የአረጋውያን ዋና ዋና ፈተናዎች

ምንም እንኳን አረጋውያን በሀገር ግንባታ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም ለበርካታ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች የተጋለጡ ናቸው፡፡

 

የሕዝብ ቁጥር እድገት፦ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና የጤና አገልግሎት እየተሻሻለ በመምጣቱ የሰዎች የሕይወት ዘመን (Life Expectancy) እየጨመረ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት የአረጋውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ክፍ ብሏል፡፡ ቁጥሩ መጨመሩ ደግሞ ፈተናዎች እንዲበራከቱ ምክንያት ኾኗል፡፡

 

የማኅበራዊ ዋስትና እጥረት፦ በመንግሥት ወይም በመደበኛ ድርጅቶች ውስጥ ሲሠሩ ከነበሩት ውጪ በግብርና እና መደበኛ ባልሆነ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ አረጋውያን በቂ የጡረታ ወይም የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን የላቸውም፡፡

የጤና አገልግሎት በቀላሉ ተደራሽ አለመሆን፡- ከዕድሜ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሥር የሰደዱ ሕመሞች (እንደ ደም ብዛት፣ ስኳር፣ የልብ ሕመም እና የመርሳት በሽታ/Dementia) ነፃ ወይም አነስተኛ ክፍያ ያለው ሕክምና እጥረት አለባቸው፡፡ “75በመቶ የሚሆኑት አረጋውያንም በትንሹ በአንድ ከባድ በሽታ ይጠቃሉ” የሚል ጥናትም ይፋ እንደተደረገ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

 

የከተሞች መስፋፋት እና የቤተሰብ ቅርፅ መለወጥ፦ የከተሞች መስፋፋት እና የኑሮ ውድነት ቤተሰቦች አረጋውያንን በቅርበት የመንከባከብ አቅማቸውን እየፈተነው ይገኛል፡፡

አረጋውያንን ለመደገፍ የሚደረጉ የመፍትሔ እንቅስቃሴዎች

ኢትዮጵያ የአረጋውያንን መብት እና ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችሉ ብሔራዊ የአረጋውያን ፖሊሲዎችን እና የድርጊት መርሃ ግብሮችን ቀርፃ በመተግበር ላይ ናት፡፡ እንዲሁም እንደ መቄዶንያ የአረጋውያን እና የሕመምተኞች መረዳጃ ማዕከል ያሉ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች መጠለያ፣ ምግብ እና ሕክምና በማቅረብ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

አረጋውያንን  የመንከባከብ፣ የመደገፍ እና መብቶቻቸውን የመጠበቅ ልምድ በዓለም ዙሪያ እንደየባህሉ እና እንደየኢኮኖሚው ይለያያል፡፡ በዓለም ሀገራት አረጋውያን የሚኖሩበትን የኑሮ ጥራት፣ ደኅንነት እና ማሕበራዊ ሁኔታዎችን በመመዘን የሚለካው ኢንተርናሽናል ግሎባል ኤጅ ዋች ኢንዴክስ (HelpAge International Global AgeWatch Index)  መሠረት ለአረጋውያን ምቹ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና የተሻለ የኑሮ ሁኔታን በመፍጠር ቀዳሚ የሆኑት ኖርዌይ፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ኔዘርላንድስ እና ጃፓን ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት ለአረጋውያን የተሻለ ዓለም የፈጠሩበት ስኬታማ ተሞክሯቸውን በቀጣይ ዕትም እናስነብባችኋለን፡፡

መረጃ

በኢትዮጵያ የአረጋውያንን መብት፣ ደኀንነት እና እንክብካቤ ለማረጋገጥ በተለያዩ ዋና ዋና ሕጎች ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎችና አንቀጾች የሚከተሉት ናቸው፦

  1. የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት
  • አንቀጽ 41 (5) — የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች፦ “መንግሥት አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችን… ለማቋቋምና ለመርዳት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዐቅም በፈቀደ ደረጃ እንክብካቤ የማድረግ ኃላፊነት አለበት” በማለት የመንግሥትን ግዴታን ያስቀምጣል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014 (አንቀጽ 18/1/ሐ)፦ የጡረታ መውጫ ዕድሜ 60 ዓመት መሆኑንና የአገልግሎት ጡረታ አበል የማግኘት መብትን ይደነግጋል።

የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1268/2014 (አንቀጽ 18/1)፦ ለግል ዘርፍ ሠራተኞችም በተመሳሳይ የጡረታ ዕድሜ 60 ዓመት መሆኑንና የማኅበራዊ ዋስትና መብታቸውን ያረጋግጣል።

  • አንቀጽ 198 — የቀለብ መስጠት ግዴታ፦ በቀጥታ ወላጆችና ተወላጆች (ልጆችና የልጅ ልጆች) እንዲሁም በወንድማማቾችና እህትማማቾች መካከል የቀለብ የመስጠት ግዴታ እንዳለ ይደነግጋል፡፡ ይህም አረጋውያን ወላጆች በልጆቻቸው የመደገፍ መብት እንዳላቸው ያረጋግጣል፡፡
  • አንቀጽ 84 (1) (ሠ) —የትኛውም ወንጀል በዕድሜ መግፋት ምክንያት ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ሰዎች (አረጋውያን) ላይ ሲፈጸም በፈጻሚው ላይ የሚጣለውን ቅጣት ያከብዳል፡፡
  • አንቀጽ 658 (ሀ)፦ ያለበቂ ምክንያት አረጋውያንን የመርዳትና ቀለብ የመስጠት ሕጋዊ ግዴታን አለመወጣት በወንጀል እንደሚያስጠይቅ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶች

  • የአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር የአረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮል፦ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በሐምሌ 2020 ያጸደቀችው ይህ አህጉራዊ ሰነድ አረጋውያን ከጥቃት እና ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመጠበቅ (አንቀጽ 8) እና በማንኛውም መጠለያ ውስጥ ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ እንክብካቤ የማግኘት (አንቀጽ 10) መብታቸውን ያረጋግጣል፡፡

 

( ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥቅምት 9  ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here