የበረሃው መርከብ

0
4

ልጆችዬ! በዓለማችን ላይ ካሉ እንስሳት ሁሉ እጅግ በጣም ታጋሽ፣ ብልህ እና አስደናቂ የተፈጥሮ ስጦታ የተሰጠው እንስሳ የትኛው እንደሆነ ታውቃላችሁ? እሱም ግመል ነው! ግመል የሚኖረው እጽዋት በሌሉበት፣ እጅግ በጣም በሚሞቅ እና በደረቅ አሸዋ በተሸፈነ በረሃ ውስጥ ነው። በዚህ አስቸጋሪ የበረሃ ሕይወት ውስጥ እንደ ልብ መጓዝ ስለሚችል ሰዎች “የበረሃው መርከብ” ብለው ይጠሩታል። እስቲ ይህ አስደናቂ እንስሳ በውስጡ የደበቃቸውን ምስጢሮች አንድ በአንድ እንያቸው፡፡

የጀርባው ምስጢራዊ ጉብታ

ብዙ ሰዎች ግመል በጀርባው ላይ ባለው ጉብታ ውስጥ ውሃ የሚያከማች ይመስላቸዋል። ነገር ግን እውነቱ ሌላ ነው! በዚያ ጉብታ ውስጥ የሚያከማቸው ልዩ ስብ ነው። በበረሃ ውስጥ ምግብ እና ውሃ በጠፋበት ጊዜ ይህ ጉብታ ውስጥ ያለው ስብ እየቀለጠ ለሰውነቱ ኃይል እና ጉልበት ይሰጠዋል። ግመል ለብዙ ቀናት ምግብ ሳይበላ ሲቆይ ጀርባው ላይ ያለው ጉብታ እየቀነሰ እና ወደ ጎን እየተንጠለጠለ ይሄዳል፤ እንደገና ምግብ ሲበላ ግን ቀጥ ብሎ ይሞላል።

ውኃን የመጠጣት አስገራሚ ችሎታ

ግመል ለአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ ያለ ምንም ውኃ መጓዝ ይችላል። ነገር ግን ውሃ በሚያገኝበት ጊዜ የሚያሳየው ፍጥነት እና አቅም በጣም ያስገርማል። በአንድ ጊዜ እስከ 130 ሊትር ውኃ (ይህ ማለት ወደ 13 የሚጠጉ ትላልቅ ባልዲዎች ማለት ነው!) በ10 ደቂቃ ውስጥ ብቻ መጠጣት ይችላል። የጠጣውን ውኃ ሁሉ በሰውነቱ ውስጥ በጥንቃቄ ስለሚይዘው በሞቃቱ ፀሐይ እንኳን ሰውነቱ በቀላሉ አይደርቅም።

ከአሸዋ አውሎ ነፋስ ራሱን የሚጠብቅበት ዘዴ

በበረሃ ውስጥ ኃይለኛ ንፋስ ሲነሳ አሸዋው በረር እያለ የሰውንም ሆነ የእንስሳትን ዓይን እና አፍንጫ ይደፍናል። ግመል ግን ለዚህ የተዘጋጀ የተፈጥሮ መከላከያ አለው። ዓይኖቹን ከአሸዋ የሚጠብቁ ረዣዥም  የዓይን ሽፋሽፍቶች አሉት። ንፋሱ ሲበረታ ደግሞ አሸዋ ወደ ውስጥ እንዳይገባበት አፍንጫውን ሙሉ በሙሉ መዝጋት ይችላል! እኛ አፍንጫችንን በእጃችን እንይዛለን እሱ ግን እጅ ሳያስፈልገው በራሱ ፍላጎት ይዘጋዋል።

የእሾህ አፍቃሪው እንስሳ

እኛ ሰዎች እሾህ ስንነካ ይወጋናል፣ ያመናል። ግመል ግን በበረሃ ውስጥ የሚበቅሉትን ሹል እሾሃማ እጽዋት ልክ እንደ ለስላሳ ቅጠል አድርጎ ያኝካቸዋል። አፉ እና ከንፈሮቹ በጣም ወፍራም፣ ጠንካራ እና ልክ እንደ ጎማ የመለጠጥ ባህሪ ስላላቸው እሾሁ በጭራሽ አይወጋውም፤ አይቆርጠውም።

በአሸዋ ላይ የማይሰምጡ እግሮች

በአሸዋ ላይ መሮጥ ወይም መራመድ በጣም አድካሚ ነው። የእኛ እግር ወደ አሸዋ ውስጥ ይሰምጣል። የግመል እግሮች ግን ከታች ሰፊ፣ ጠፍጣፋ እና እንደ ትራስ ለስላሳ ናቸው። ይህ ተፈጥሮው ትኩስ አሸዋው እንዳያቃጥለውና ወደ ውስጥ ሳይሰምጥ ልክ በምንጣፍ ላይ እንደሚራመድ በበረሃው ላይ በኩራት እንዲጓዝ ይረዳዋል።

ልጆችዬ! ግመሎች በጣም አስተዋይ፣ ታማኝ እና ሰላማዊ እንስሳት ናቸው። በበረሃ የሚኖሩ ሰዎችን ሸክም በመሸከም፣ ወተት እና የግመል ጸጉር በመስጠት ትልቅ ውለታ ይውላሉ ይላል ብሪታኒካ ኪድስ ላይ ያገኘነው መረጃ።

ተረት

የጦጣና የበቅሎ ፍርድ

አንድ ለምለም የኢትዮጵያ ገጠር ውስጥ እጅግ ታማኝ እና ታጋሽ የሆነች በቅሎ ሌት ተቀን ሳታጉረመርም የጌታዋን ከባድ ሸክም ትሸከም ነበር። በአቅራቢያው በሚገኝ ትልቅ የዋርካ ዛፍ ላይ የምትኖር ሥራ ፈትና ተንኮለኛ ጦጣ ግን በበቅሎዋ ታማኝነት በመቅናት “ለምን ለጌታሽ ትደክሚያለሽ? እንደ እኔ በነፃነት አትኖሪም” እያለች ታሾፍባት ነበር። በቅሎዋ ግን የጌታዋን ውለታ እንደምታከብር እና ታማኝነት መቼም ቢሆን ዋጋ እንዳለው በመግለጽ የጦጣዋን ክፉ ምክር ሳትቀበል ቀረች።

በበቅሎዋ እምቢተኝነት የተናደደችው ጦጣ ማታ ጌታው በተኛበት ጊዜ የበቅሎዋን ገመድ ፈትታ የጓሮ አትክልቱን በሙሉ አበላሸችው፤ ጌታው ሲነቃ አትክልቱ ጠፍቶ በቅሎዋም ተፈትታ ስላገኛት አጥፊዋ እሷ መስላው በዱላ ደበደባት። በቅሎዋ መበደሏ በጣም ቢያሳዝናትም እውነቱን ልታስረዳው አልቻለችም፤ ጦጣዋ ግን ከዛፍ ላይ ሆና በበቅሎዋ መከራ ትስቅ ነበር። ይሁን እና ተንኮለኛዋ ጦጣ በሌላ ምሽት አትክልት ስትሰርቅ ጌታው እጅ ከፍንጅ ያዛት።

ጌታው እውነተኛዋ አጥፊ ተንኮለኛው ጦጣ መሆኗን በተረዳ ጊዜ በቅሎዋን ይቅርታ ጠየቃት እና ከዚያ ቀን ጀምሮ በታላቅ ፍቅር ይንከባከባት ጀመር፤ ስግብግቧ እና ክፉዋ ጦጣ ግን ከአካባቢው ተባረረች። ይህ ተረት የሚያስተምረን ተንኮል እና ስራ ፈትነት መጨረሻቸው ውድቀት መሆኑን ሲሆን በትዕግስት እና በታማኝነት የሚሠራ በጎ ሥራ ግን ሁልጊዜም እንደሚያሸንፍ ነው።

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ተረቶች

ሞክሩ

  1. የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት ምን ምን ናቸው?
  2. ዙሮ ዙሮ ራቱ ጥፊ ምንድን ነው?
  3. በኢትዮጵያ ትልቁ ተፈጥሯዊ ሐይቅ ማን ነው?

መልስ

  1. አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ
  2. ወንፊት
  3. ጣና

ነገር በምሳሌ

  • ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል። — ለሌሎች የማያስብና ሰውን የማይረዳ ግለሰብ ችግር ላይ ሲወድቅ የሚረዳው አያገኝም።
  • አልማዝ በቆሻሻ ውስጥ ቢቀመጥም ውበቱ አይጠፋም። — እውነተኛ ጎበዝ ወይም ጥሩ ሰው ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ቦታ ቢሆን ማንነቱ አይቀየርም።
  • ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል። — ሳይዘጋጁ በችኮላ የተጀመረ ነገር መጨረሻው አያም።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here