ለስምንት ዓመታት የተሰወረው ተፈላጊ

0
8

በቱርክ የመንግሥት ባለስጣን መስሎ በመቅረብ ሦስት ጊዜ ስርቆት መፈፀሙ በፍርድ ቤት ተረጋግጦ የተበየነበትን ግለሰብ የሦስት ዓመት ቅጣት ሳይፈፅም በመጥፋቱ ከ2018 የካቲት   ወር ጀምሮ በተገኘበት ቦታ እንዲያዝ የእስር ማዘዣ ከተቆረጠበት ከስምንት ዓመታት በኋላ ፆታውን የቀየረ በማስመሰል ሲንቀሳቀስ መያዙን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡

በየአካባቢው ቱግረል ባሻር የተሰኘውን ግለሰብ ፖሊስ ለዓመታት ሲፈልገው ቆይቷል፤ ነገር ግን ሳይያዝ ቆይቶ በቅርቡ በኢስታንቡል ካዲኮይ በተሰኘ ወረዳ በተካሄደ ልዩ  የፍለጋ አሰሳ እና ክትትል  ማንነቱ ሊለይ ችሏል፡፡ በአሰሳው የባሻር ጉዳይ ከሌሎቹ ተፈላጊዎች ለዓመታት የተሰወረበት እና የተገኘበት ሁኔታም የተለየ መሆኑን  ድረ ገጹ አስፍሯል፡፡

ተፈላጊው ቱግረል ባሻር የፊት ገፁን በመቀያየር እና የእህቱን መታወቂያ በመያዝ ፆታውን የቀየረ (ሴት) መስሎ ለስምንት  ዓመታት በአንድ ጣሪያ ስር መኖሩ ተረጋግጧል፡፡

ከስምንት ዓመታት በፊት በተገኘበት እንዲያዝ የተበተነውን የወንጀለኛውን ፎቶ ግራፍ በዘመናዊ መሣሪያ አሁን ሲያዝ ካለው ገፅታ ጋር ማመሳከር ችለዋል፡፡ በዚህም ባሻር በጥንቃቄ የፆታ ለውጥ ያደረገ ለመመስል መመኮሩ ተረጋግጧል፡፡ከፊሎች ፆታውን ቀይሯል የሚል አስተያየት ቢሰጡም እውነታው ግን በጥንቃቄ ራሱን ከእህቱ ጋር መማመሳሰሉ እንጂ አለመቀየሩ ነው በግልጽ የተመላከተው፡፡

በመጨረሻም ማንኛውም ወንጀለኛ ከህግ ማምለጥ እንደማይችል ያሰነበበው ድረ ገጹ ቱግረል ባሻር  በመጀመሪያ የተወሰነበትን የሦስት ዓመታት እስር በወንዶች ማረሚያ ቤት ፈፅሞ በዚያው አሁን ላይ በፈፀመው የማጭበርበር ወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን ነው በማጠቃለያነት የሰፈረው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here