በሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ አላላ ቀበሌ መሬታቸውን ለበጋው (ለመስኖ) የዘር ወቅት እያዘጋጁ ከሚገኙ ትጉህ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ኑሬ ወርቁ አንዱ ናቸው። ያለፈው የመኸር ወቅት ለአቶ ኑሬ የተሻለ የሚባል ነበር። ሙሉ የእርሻ መሬታቸው በቀይ ሽንኩርት፣ በማሾ እና በማሽላ ተሸፍኖ ነበር፡፡ አንድ ሄክታር ማሳ ሽንኩርት፣ አንድ ነጥብ አምስት ሄክታር ማሾ እንዲሁም አንድ ሄክታር በአገዳ እህል አልምተዋል፡፡
ይህን ሁሉ የሆነው ደግሞ ዝናብን ሳይጠብቁ የመስኖ ውኃን ከከርሰ ምድር ተቆፍሮ ከወጣ ውኃ ጋር በማቀናጀት በሁለት የሞተር ፓምፖች በመታገዝ ሰብላቸውን በማልማት ላይ ናቸዉ። ዘንድሮም ከህዳር ወር ጀምሮ ማሳቸውን በስንዴ፣ ጤፍ፣ ጎመን እና ቲማቲም ለመሸፈን ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
አቶ ኑሬ ዘመናዊ ግብርናን ለመተግበር ቢሞክሩም የግብርና ግብዓት አቅርቦት በተለይም የነዳጅ ጉዳይ የዘወትር ራስ ምታት እንደሆነባቸው ጠቁመዋል፡፡ የአርሶ አደሩ ሌላው ትልቅ ስጋት የተሻለ ምርት የሚሰጥ ምርጥ ዘር ነው። እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ በ2013 ዓ.ም የመጣው “ሲዋን እና ቀቀባ” የተባሉ የስንዴ ምርጥ ዘሮችን በአንድ ሄክታር እስከ 41 ኩንታል ምርት ሰጥቷቸው ነበር። አሁን እየቀረበ ያለው ዘር ግን የምርት መጠኑን ከሄክታር ወደ 18 እና 20 ኩንታል አውርዶታል።
ችግሮች ቢኖሩም እንኳ አርሶ አደር ኑሬ ተስፋ ቆርጠው እጃቸውን አላጠፉም። “ኅብረተሰቡ መሬቱን አዘጋጅቷል። እኔም ሦስት ሄክታር ስንዴ እዘራለሁ ብዬ የእርሻ ሥራ እና ሌሎች ግብዓቶችን እያሟላሁ ነው” ብለዋል፡፡ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ እና ነዳጅ ግን በመንግሥት በኩል በወቅቱ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡
በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ወንዳጣ ቀበሌ የሚኖሩ አርሶ አደሮችም የመኸር ሰብላቸውን እየሰበሰቡ ወደ በጋ መስኖ ሥራ እየገቡ ነው። ከበኵር ጋዜጣ ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉት አርሶ አደር አላቸው ገላዬ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የበቆሎ ሰብላቸውን የመሰብሰብ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ። የጤፍ፣ የዳጉሳ እና ሌሎች ሰብሎችንም እየተንከባከቡ ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም በውኃ ሞተር ፖምኘ በመታገዝ ስንዴ፣ ሽንብራና ጓያ በመስኖ ለማልማት የእርሻ ሥራ ጀምረዋል።
ይሁን እንጂ አርሶ አደሮች በመስኖ ልማቱ ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው ጠቁመዋል። ዋነኛው ችግር የነዳጅ አቅርቦት እና የዋጋ ንረት ነው። ባለፈው ዓመት በነዳጅ እጥረት ምክንያት ከፊሉ ማሳቸው ጦም ማደሩን አስታውሰወዋል፡፡
ነዳጅን በሕገ-ወጥ ገበያ በውድ ዋጋ እንደገዙም ገልጸዋል። ይሁንና አርሶ አደሩ ምንም እንኳን የነዳጅ እጥረት ቢፈትናቸውም ተስፋ ሳይቆርጡ መሬታቸውን እያረሱ የዘንድሮውን የበጋ መስኖ ሥራቸውን በተጠናከረ ሁኔታ እያከናወኑ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን የኤፍራታና ግድም ወረዳ በተያዘው ዓመት የበጋ መስኖ ልማት ሥራ ጀምሯል። በተለይም በበጋው ወራት የተሻለ የስንዴ ምርት ለማግኘት ከወረዳ እስከ ቀበሌ ድረስ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
የወረዳው የመስኖ ልማት ቡድን አግሮኖሚ ባለሙያ አቶ አየለ ደስታ በስልክ እንደገለጹት ወረዳው በዚህ ዓመት በመስኖ ልማት ሰባት ሺህ 62 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዷል፡፡
ከዚህ ውስጥ አምስት ሺህ 957 ሄክታር ነባር እንዲሁም አንድ ሺህ 105 ሄክታር ደግሞ በአዲስ እንደሚለማ ጠቅሰዋል። ከዚህም ከ611 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ የሰብል ምርቶችን ለማግኘት ታቅዷል።
ባለሙያው እንዳብራሩት ከሚለማው ማሳ በአንደኛው እና በሁለተኛው ዙር አምስት ሺህ 719 ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል ብቻ ይሸፈናል። ከዚህም 217 ሺህ 322 ኩንታል የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ለአንድ የግብርና ሥራ ስኬት የግብዓት አቅርቦት ወሳኝ ነው። ወረዳው ይህንን በመረዳት ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያን ለማቅረብ እየሠራ ነው።
አቶ አየለ ለበኵር እንደገለጹት “ለስንዴ ልማት ከአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ 150 ኩንታል ተመድቦልን ተረክበናል፡፡ ቀሪውን ደግሞ አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም ከወሰደው ምርጥ ዘር እርስ በእርሱ እንዲለዋወጥ በማድረግ የዘር ፍላጎቱን ለመሸፈን እየሠራን ነው። ከዚህ በተጨማሪም ሲዋን እና ቀቀባ የተሰኙ የስንዴ ዝርያዎችም ጥቅም ላይ ይውላሉ” በማለት ችግሮችን ለመፍታት እያደረጉት ያለውን ጥረት አሳውቀዋል፡፡
ለስንዴ ልማቱ አምስት ሺህ 719 ኩንታል ዩሪያ እና አምስት ሺህ 719 ኩንታል ዳፕ የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ባለሙያው፤ ወደ መጋዝን እንዲገባና አርሶ አደሩ እንዲጠቀምበት እየተደረገ ይገኛል። የመስኖ አውታሮችን የማፅዳትና ዝግጁ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።
በወረዳው 36 ኪሎ ሜትር ዘመናዊ እና 97 ኪሎ ሜትር ባህላዊ ቦይ፣ 52 የእጅ ውኃ ጉድጓዶች እንዲሁም 602 የውኃ ሞተር ፓምፖች ለዘንድሮው የመስኖ ሥራ ዝግጁ ሆነዋል።
ባለፈው ዓመት አርሶ አደሩን ሲያማርር የነበረውን የነዳጅ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ዘንድሮ የተሻለ አሠራር ተዘርግቷል ብለዋል። “ከንግድ ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመነጋገር የመስኖ መሬት እና የውኃ ሞተር ፓምፕ ያለው ማንኛውም አርሶ አደር ምንም አይነት እንግልት ሳይደርስበት በሚፈልገው ሰዓት ደብዳቤ እየተጻፈለት ነዳጅ እንዲያገኝ አሠራር ዘርግተናል” በማለት አቶ አየለ መረጃን አጋርተዋል።
እስካሁን (እስከ ጥቅምት አጋማሽ) ባለው መረጃ 461 ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር ለመሸፈን ማሳው ታርሶ እና ተለስልሶ ለዘር ዝግጁ ሆኗል፡፡ ከዚህ ውስጥ 51 ሄክታር መሬት ላይ ዘር ተዘርቷል። በቀጣዮቹ ወራትም ወረዳው አቅዶት የተነሳውን ከ217 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለማሳካት አርሶ አደሩ እና የግብርና ባለሙያዎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ሥራቸውን ቀጥለዋል።
በተመሳሳይ የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የመስኖ ተቋማት አጠቃቀም፣ አስተዳደርና ጥገና ቡድን መሪ አቶ ብሩክ ካሳ የዞኑን የ2019 ዓ.ም የበጋ መስኖ ልማት ቅድመ ዝግጅት ለበኵር አጋርተዋል፡፡ ዞኑ በ2019 ዓ.ም 56 ሺህ 017 ሄክታር መሬት (38 ሸህ 867 ነባር እና 17 ሺህ 150 አዲስ) በመስኖ በማልማት አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዷል፡፡
ከዚህ ውስጥ ዋነኛ ትኩረት የሆነው የበጋ መስኖ ስንዴ 37 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማግኘት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡ እቅዱን ለማሳካትም ከ115 ሺህ ኩንታል በላይ የዳፕና ዩሪያ ማዳበሪያ እንዲሁም ከ67 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ቀርቧል፡፡
ከስምንት ሺህ 986 በላይ የሞተር ፓምፖች ጥቅም ላይ እንደሚዉሉ አመላክተዋል፡፡ በዚህም ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ያለማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኀብረተሰቡን በማስተባበር 381 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው (42 ኪ.ሜ ዘመናዊ እና 340 ኪ.ሜ ባህላዊ) የካናል (የቦይ) ጠረጋ ተከናውኗል፡፡
የምርት ማሳደግ ሚስጥሩ መሬት በማስፋት ብቻ ሳይሆን ምርጥ ዘርን በመጠቀም ጭምር መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ለዚህም ሲባል ቀቀባ እና ሲዋን የተሰኙ በሽታን የሚቋቋሙና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የስንዴ ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ እንደሚቀርብ ተናግረዋል ፡፡
አመራሩ በየሳምንቱ በዙም (Zoom) ከወረዳዎች ጋር እየተወያየ እለታዊ ሪፖርቶችን እየገመገመና የአርሶ አደሩን ችግር በማሳ ጠላይ እየፈታ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል፡፡ ከነዳጅ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የነዳጅ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችን የመለየት እና የሚያገኙበት መንገድ እየተመቻቹ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ኑሬ እና አቶ አላቸው ያሉ አርሶ አደሮች ከተፈጥሮ ጥገኝነት ተላቀው፣ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ሌሊት ከቀን እየሠሩ ያሉት ለራሳቸው ሕይወት መሻሻል ብቻ ሳይሆን ለሀገር የምግብ ዋስትና ጭምር ነው። በሰሜን ጎጃምና በኤፍራታና ግድም የታቀዱት ዕቅዶች እውን የሚሆኑት የወረቀት ላይ ቁጥሮች ወደ ተግባር ሲቀየሩ እና የአርሶ አደሩ መሰረታዊ ጥያቄዎች (ነዳጅ፣ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር) ያለምንም እንግልት በወቅቱ ሲቀርቡለት ብቻ ነው።
በአማራ ክልል በ2019 ዓ.ም 734 ሺህ 432 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ከ95 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል። የቢሮው የመስኖ ተቋማት አጠቃቀምና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ምኒሊክ ሙላት ለበኩር እንደገለጹት ዘንድሮ ከሚለማው መሬት ውስጥ 250 ሺህ ሄክታሩ በአዲስ የሚሸፈን ነው። በተለይም ለበጋ መስኖ ስንዴ ልዩ ትኩረት የተሰጠ ሲሆን 400 ሺህ ሄክታር በማልማት 16 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል።
ለዕቅዱ ስኬትም የተሻለ ምርት የሚሰጡትን እንደ ‘ቀቀባ’ እና ‘ሲዋን’ ያሉ ምርጥ ዘሮች እና አፈር ማዳበሪያን የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ ነው። ከዚህ ቀደም በነዳጅ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ይስተዋል የነበረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም አርሶ አደሩ በስፋት የሶላር ውኃ ማውጫ ፓምፖችን እንዲጠቀም እየተደረገ ይገኛል። ከነዳጅ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ከአጋር አካላት ጋር በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
አርሶ አደሩን በማነቃቃት እስካሁንም በተደረገው ርብርብ ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በበጋ ስንዴ መሸፈኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። በመጭው ጥቅምት 21 ቀን 2019 ዓ.ም በክልሉ የመስኖ ልማት የንቅናቄ መድረክ እንደሚካሄድ ነው ዳይሬክተሩ ያመላከቱት፡፡
መረጃ
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት በስፋት እየተሠራበት የሚገኝ ዘርፍ ነው።
ለዚህ ልማት ስኬታማነት የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነጥቦች፦
- ተስማሚ መሬት
- አስተማማኝ የውኃ አማራጭ
- ተስማሚ የዘር ምርጫ
- የማዳበሪያ አጠቃቀም
- የመስኖ ቴክኖሎጂ (ቁሳቁስ)
- የአረም፣ የተባይ እና የበሽታ ቁጥጥር
- ዕውቀትና የሰው ኀይል
- የኀይል አቅርቦት (ነዳጅ፣ የፀሐይ ኀይል) እና ሌሎች ግብዓቶች፡፡
የመረጃ ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ናቸው።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


