ሁለት ጊዜ ማሰብ

0
14

የሰው ልጅ ታሪክ አብዛኞቹ ውድቀቶች የሚመነጩት ከመጥፎ ዓላማ ሳይሆን ከደካማ አስተሳሰብ ነው። ብዙ ጊዜ ችግርን ለመቅረፍ የምንወስዳቸው ፈጣን እርምጃዎች የዛሬን ህመም ሲያስታግሱ የነገውን አደጋ በእጥፍ ያወሳስባሉ።

ፈጣን እፎይታንና ቀጥተኛ ውጤትን ብቻ የሚያየው የመጀመሪያ ደረጃ አስተሳሰብ ዓለምን በጠባብ መስኮት ሲመለከት ጠቢባን፣ ስትራቴጂስቶች እና ስኬታማ መሪዎች ግን የመዘዞቹን መዘዝ አስቀድመው የሚያሰሉበትን “የሁለተኛ ደረጃ አስተሳሰብ” ይጠቀማሉ።

ይህ አስተሳሰብ አንድን እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት የምንጠይቀው “ከዚህስ በኋላ ምን ይመጣል?” የሚለው የጥበብ ሁሉ መነሻ የሆነው የማይታጠፍ ጥያቄ ነው።

በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ሥር በነበረችው የቬትናም ከተማ ሃኖይ ውስጥ አስከፊ የአይጥ ወረርሽኝ ተከሰተ።

የከተማዋ አስተዳዳሪዎች አይጦችን ለማጥፋት አንድ ፈጣን መፍትሔ አቀዱ። ማንኛውም ዜጋ የአይጥ ጅራት ቆርጦ ላመጣ የገንዘብ ሽልማት እንዲሰጠው ወሰኑ።

ውሳኔው በመጀመሪያ እይታ እጅግ ብልህ ይመስል ነበር፤ ሰዎች ጅራቶችን በብዛት ማምጣት ጀመሩ። አስተዳደሩም በስኬቱ ተደሰተ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ጅራታቸው የተቆረጠ ነገር ግን በሕይወት ያሉ አይጦች በብዛት መታየት ጀመሩ። አስተዳዳሪዎቹ አይጦች ጅራታቸው ከተቆረጠ ይጠፋሉ የሚል ግምት ነበራቸው።

ሰዎች ሽልማቱን ለማግኘት ጅራታቸውን ብቻ ቆርጠው ይለቋቸው ነበር፤ የባሰውን ደግሞ ብዙ ዜጎች አይጦችን በየጓዳቸው በስፋት ማራባት ጀመሩ። ዋናው ትኩረታቸው አይጦችን ከማጥፋት ይልቅ ሽልማቱን ማግኘት  ላይ አደረጉ።

አስተዳደሩ እውነታውን ተረድቶ ሽልማቱን ሲያቆም አርቢዎቹ ፋይዳ የሌላቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ አይጦች ወደ ከተማው ለቀቋቸው፤ በመጨረሻም የሃኖይ አይጦች ቁጥር ከቀድሞው በብዙ እጥፍ ጨመረ።

ይህ ታሪካዊ ክስተት የሚያሳየን አንዱን መሠረታዊ እውነት ነው። አብዛኛው የሰው ልጅ ችግሮችን ለመፍታት ሲነሳ የድርጊቱን ፈጣንና ቀጥተኛ ውጤት ብቻ ይመለከታል፤ ይሄ “የአንደኛ ደረጃ አስተሳሰብ” ይባላል።

የመጀመሪያ ደረጃ አሳቢዎች ዓለምን በቀጥተኛ መስመር  ያያሉ፤ ድርጊት “ሀ” ወደ ውጤት “ለ” ያመራል ብለው ብቻ ያምናሉ። ነገር ግን እውነተኛው ዓለም የተወሳሰበ፣ እርስ በርሱ የተሳሰረ እና የሰንሰለት ምላሾች  ያሉበት ነው።

ጠቢባን፣ ድንቅ መሪዎች እና ስትራቴጂስቶች የሚጠቀሙት መሣሪያ ግን የሁለተኛ ደረጃ አስተሳሰብ  ነው።

ይህ አስተሳሰብ አንድን ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ከዚህስ በኋላ ምን ይመጣል?  የሚለውን የማይታጠፍ ጥያቄ ደጋግሞ ይጠይቃል።

ታዋቂው የዎል ስትሪት ባለሀብት ሃዋርድ ማርክስ “ዘ ሞስት ኢምፖርታንት ቲንግ” በተባለው ድንቅ መጽሐፋቸው ላይ እንዳስረዱት በአንደኛ እና በሁለተኛ ደረጃ አሳቢዎች መካከል ያለው ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል የሰፋ ነው።

የመጀመሪያ ደረጃ አሳቢ “ይህ ኩባንያ ጥሩ ምርት አለው፣ ገቢውም እያደገ ነው፤ ስለዚህ አክሲዮኑን ልግዛ” ይላል። ይሄ ቀላል እና ማንም ሊደርስበት የሚችል ድምዳሜ ነው።

የሁለተኛ ደረጃ አሳቢ ግን ጥልቀት ወዳለው አድማስ ይሻገራል፤ “ኩባንያው ጥሩ መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን ይህንን ሁሉም ሰው ስለሚያውቀው የአክሲዮኑ ዋጋ ከመጠን በላይ ተሰቅሏል? ገበያው የሚጠብቀው እድገት ካልተሳካ ምን ይፈጠራል? ተፎካካሪዎች ለዚህ ምን ምላሽ ይሰጣሉ?” በማለት የመዘዞቹን መዘዝ ያሰላል።

ሥነ-ምህዳራዊው ምሁር ጋሬት ሃርዲን እንደሚያስተምሩት በተወሳሰበ ሥርዓት ውስጥ  አንድን ነገር ብቻ ለይቶ ማድረግ አይቻልም።

የትኛውም እርምጃ ያልታሰቡ፣ የተደበቁ እና ዘግይተው የሚፈነዱ የጎንዮሽ ውጤቶች አሉት። ለምሳሌ፦ በኢኮኖሚክስ ውስጥ የቤት ኪራይ ዋጋ ሲንር መንግሥታት የኪራይ ቁጥጥር ሕግ ያወጣሉ።

የአንደኛ ደረጃ አስተሳሰብ ውጤት ግልጽ ነው። ተከራዮች ወዲያውኑ ርካሽ ቤት ያገኛሉ። የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ አስተሳሰብ ግን እውነታውን ያጋልጣል። የቤት ባለቤቶች ቤቶቻቸውን መጠገን ያቆማሉ፣ አልሚዎች አዳዲስ ቤቶችን መገንባት ይተዋሉ። በሂደትም የቤቶች እጥረት በከፋ ሁኔታ ይባባሳል፣ በመጨረሻም ጥቁር ገበያ ይፈጠራል። ፈጣን እፎይታ የሰጠው መድኃኒት በረጅም ጊዜ በሽተኛውን ይገድለዋል።

ይህ ሕግ በዕለት ተዕለት የግል ሕይወታችንም ውስጥ በኃይል ይሠራል፤ የሕይወት አጠቃላይ ስኬት የሚወሰነው በዚህ አስተሳሰብ ልህቀት ነው።

ፈጣን እርካታ የሚሰጡን ነገሮች፣ ጣፋጭ ምግቦች፣ አልኮል፣ ስልክ ላይ ሰዓታትን ማባከን፣ ወይም አስቸጋሪ ውሳኔዎችን ማሸሽ የመጀመሪያ ደረጃ ጥቅማቸው እፎይታና ደስታ ነው።

የሁለተኛና የሦስተኛ ደረጃ መዘዛቸው ግን ውፍረት፣ የጤና መታወክ፣ የጊዜ ብክነት እና የሕይወት ውድቀት ነው። በተቃራኒው እንደ ጠንክሮ መሥራት፣ መጽሐፍ ማንበብ፣ ስፖርት መሥራት እና ቁጠባ ያሉ ልማዶች በመጀመሪያው ደረጃ አድካሚና አሰልቺ ናቸው፤ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ ፍሬያቸው ግን የላቀ ጤና፣ የገንዘብ ነፃነት እና ወደር የለሽ የአእምሮ ሰላም ነው።

የሁለተኛ ደረጃ አስተሳሰብን የሕይወታችን መርህ ለማድረግ ሦስት ወሳኝ የአስተሳሰብ መነጽሮችን መልበስ ያስፈልጋል።

የጊዜ አድማስን ማስፋት፦አንድን እርምጃ ስንወስድ «ይህ ውሳኔ በ10 ደቂቃ፣ በ10 ወር እና በ10 ዓመት ውስጥ ምን ዓይነት ለውጥ ያመጣል?» (10/10/10 ሕግ) ብሎ መጠየቅ።

የሌሎችን ምላሽ አስቀድሞ መገመት፦ውሳኔያችን በሌሎች ሰዎች፣ ተፎካካሪዎች ወይም ሥርዓቶች ላይ የሚያሳድረውን የስነ-ልቦና ተፅዕኖ እና እነሱ የሚወስዱትን የአጸፋ እርምጃ ማስላት።

የመፍትሔውን አደጋ መመርመር፦ያመጣነው መፍትሔ ራሱ ሌላ አዲስና የከፋ ችግር እንደማይወልድ በጥልቀት ማረጋገጥ።

በፍጥነት፣ በስሜታዊነት እና በቅጽበታዊ ጭብጨባ በሚነዳው የዘመናችን ዓለም ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ አስተሳሰብ ብርቅዬ ጥበብ ነው።

ጥልቀት የሌለው አስተሳሰብ ዛሬን አድምቆ ነገን ያጨልማል፤ የሁለተኛ ደረጃ አስተሳሰብ ግን የዛሬን ህመም ታግሶ የነገውን ብርሃን ያበራል።

በመሆኑም ከመንጋው ተለይቶ ስኬታማ፣ አርቆ አሳቢ እና ጥበበኛ መሪ ለመሆን “ከዚህስ በኋላ ምን ይመጣል?” የሚለውን ጥያቄ የሕይወት መርህ ማድረግ ከሁሉ የላቀው አስተማማኝ መውጫ መንገድ ነው።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here