የአደራዉ ልጅ የብርሃን ጉዞ

0
15

በሕይወት መንገድ ላይ የሚያጋጥሙ ፈተናዎች እና የኑሮ ማዕበሎች የሰውን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሁልጊዜ አይወስኑም፤ በጽናት የማይጓዙ መንገድ ላይ ቢቀሩም ጠንካራ ሰዎችን ደግሞ ወደ ላቀ የከፍታ ማማ ያሸጋግራሉ። አንዳንዶች በችግር እና በድህነት ጫና ተስፋ ቆርጠው ሲቆሙ፣ ሌሎች ደግሞ ያጋጠማቸውን ፈተና እንደ መሰላል ተጠቅመው የሕልማቸውን ጫፍ ይረግጣሉ።

በትጋት መሥራት፣ ከውድቀት መነሳት እና የደግ ሰዎችን የቁርጥ ቀን እጅ ማግኘት ለታላቅ ስኬት መሠረት እንደሚሆን በተግባር ካሳዩን ተስፈኛ ወጣቶች መካከል የብሩክ ወለላው ታሪክ ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል። የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ተፈትኖ ከ600 ውስጥ 520 ነጥብ በማስመዝገብ አስደናቂ ስኬት የተቀዳጀው ይህ ወጣት፣ የሕይወት እና የትምህርት ጉዞው ፈተና የበዛበት እንጂ በጭራሽ አልጋ በአልጋ አልነበረም።

ብሩክ የትምህርት ገበታውን የጀመረው ገና በአምስት ዓመቱ በመዋዕለ ሕፃናት ነበር። በወቅቱ ከምትወደው እናቱ ጉያ ስር ይኖር የነበረ ሲሆን፣ እናቱም የኑሮን ሸክም ለማቅለል እና ለልጇ የተሻለ ነገን ለመፍጠር ስትል ከባሕር ዳር ከተማ ወደ ሰባታሚት ቀበሌ ተዛወረች። በዚያም በሆቴል ሥራ ተቀጥራ ከመሥራት አልፋ አነስተኛ የግሮሰሪ ንግድ በመጀመር ልጇን ለማሳደግ ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም።

ይሁን እንጂ የኑሮው ፈተና ከበድ ያለ በመሆኑ ንግዱ ሳይሳካ ቀረ። በመሆኑም ትሠራበት የነበረውን በመልቀቅ በባሕር ዳር ከተማ ጎርደማ ገብርኤል አካባቢ ትንሽ ቤት ተከራይታ መኖር ጀመሩ። ብሩክ በአካባቢው በሚገኝ ትምህርት ቤት ትምህርቱን መከታተል ጀመረ፤ ይሁን እንጂ ገና የሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ የለወጠ አሳዛኝ ክስተት አጋጠመው።

የወደፊት ተስፋው፣ አለኝታው እና የሕይወት መሠረቱ የነበረችው እናቱ በድንገት ታማ ሆስፒታል ከገባች በኋላ በማግስቱ ሕይወቷ አለፈ። በወቅቱ ገና ለጋ ሕፃን የነበረው ብሩክ እናቱን በሞት በማጣቱ የተፈጠረበትን የሥነ-ልቦና ስብራት እና የሕይወት ለውጥ ለመቋቋም እጅግ አዳጋች ሆኖበት ነበር። ይህ ከባድ ሐዘን በትምህርቱም ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አሳድሮበት እንደነበር በማስታወስ በመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ብዙም መማር እንዳልቻለ በትካዜ ይናገራል።

ብሩክ እያደገ ሲመጣ ለትምህርቱ ያለው ትኩረት እና ፍቅር ከፍ እያለ መጣ። በተለይም ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ ንባብን አጥብቆ ያዘ። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከስቶ ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ እንኳን እሱ ከትምህርት እና ከንባብ አልተለየም። በዚሁ ጥረቱ ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል አንደኛ በመውጣት ጉልህ መሻሻል ያሳየ ሲሆን፣ የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን የተሻለ ውጤት በማምጣት ወደ ኢቲዮ-ጃፓን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተቀላቀለ።

ዘጠነኛ ክፍል ውጤቱ አነስ ቢልም ዐሥረኛ ክፍል ግን ውጤቱን ወደ 90 በመቶ ከፍ በማድረግ በክፍሉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ። በመቀጠልም ዐሥራ አንደኛ ክፍል 94 በመቶ አማካይ በማምጣት ብቃቱን ያስመሰከረ ሲሆን፣ በ12ኛ ክፍል ሙሉ ትኩረቱን በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ላይ አድርጎ ከጓደኞቹ ጋር በቤተ መጻሕፍት በማጥናት 520 ነጥብ አስመዘገበ።

በአሁኑ ወቅት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዕድል ያገኘው ብሩክ፣ በቀጣይ የሕክምና ትምህርቱን አጠናቆ በልብ ሕክምና ስፔሻላይዝ የማድረግ ሕልም እንዳለው አጫውቶናል። ይህን የሙያ ዘርፍ ለመምረጥ ምክንያት የሆኑት ደግሞ በሀገራችን ከልብ ጋር የተያያዙ በሽታዎች እና የደም ግፊት መጨመር፣ እንዲሁም ከታካሚው ቁጥር አንጻር የሐኪሞች ማነስ ናቸው፤ በመሆኑም በሙያው ሕዝቡንና ሀገሩን ለማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት አድሮበታል።

ብሩክ ድህነትን በትምህርት ጥናት ያሸነፈ፣ የሞተች እናቱን የመጨረሻ አደራ በስኬት የተወጣ ድንቅ ወጣት ነው።

ይህ ሁሉ ስኬት ግን የብሩክ የግል ጥረት ብቻ አይደለም። እናቱ በሞት አፋፍ ላይ ሆና የቀረቻትን የመጨረሻ እስትንፋስ ሰብስባ “የልጄን ነገር አደራ… አደራው ለእናንተ ነው!” ስትል የተናገረቻትን ቃል ጠብቀው፣ ልጁን እንደ ዐይን ብሌናቸው በመንከባከብ ያሳደጉት የአሳዳጊዎቹ ውለታ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። የአደራ አሳዳጊ እናቱ ወ/ሮ አዳነች ሞላ ጥጥ በመፍተል እና ሸማ ተራ ወስደው በመሸጥ ለልጁ ቁርስና መሠረታዊ ፍላጎቶችን ያሟሉለት የነበረ ሲሆን፣ አሳዳጊ አባቱ አቶ ጓዴ አወቀ ደግሞ “አደራ ሩቅ ነው፣ ሰማይ ቅርብ ነው” በሚል እምነት የልጁን ውሎና ትምህርት እየተከታተሉ በአግባቡ ኮትኩተውታል።

ከአሳዳጊ ወላጆቹ በተጨማሪ፣ የአካባቢው ነዋሪ ወጣት ብዙዓለም ታየ እና የቀድሞ መምህሩ መምህር ጥላሁን አንተነህ፣ ብሩክ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ንቁ፣ ፈጣን፣ አስተዋይ እና በትምህርቱ ላይ ትጉህ እንደነበር ይመሰክራሉ።

ሆኖም ብሩክ ላስመዘገበው ውጤት አሳዳጊዎቹ ደስተኛ ቢሆኑም፣ በቀጣይ ለትምህርቱ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ወጪ ማሟላት እንደሚከብዳቸው ገልጸዋል። በመሆኑም ይህ ጎበዝ ተማሪ ሐኪም የመሆን ሕልሙን አሳክቶ ለሀገር የሚጠቅም ባለሙያ እንዲሆን የመልካም ልብ ባለቤቶች፣ በጎ አድራጊዎች እና የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ሊያደርጉለት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

 

ምሳሌያዊ አነጋገር

     ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ፤ውሀ ቢያንቅ በምን ይውጡ

     ሹመት በተርታ ስጋ በገበታ

     ሀኪም የያዘው መፍስ ባያድር ይውላል

     ሂድ አትበለው እንዲሄድ አድርገው

     ራስ ሳይጠና ጉተና

(ሰናይት በየነ)

በኲር የጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here