ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? ልጆች የአፍሪካ የሰላም ተምሳሌት ስለሚባሉት ኔልሰን ማንዴላ እንንገራችሁ፡፡
በደቡብ አፍሪካ በምትገኝ ኩኑ በምትባል ትንሽ መንደር ሮሊህላህላ የሚባል አንድ ብልህ ልጅ ተወለደ። ኔልሰን በልጅነቱ እንደማንኛውም ህፃን ከጓደኞቹ ጋር በሜዳ ላይ መጫወት፣ ከብቶችን መጠበቅ እና መዋኘት ይወድ ነበር።
ኔልሰን እያደገ ሲመጣ ግን በሀገሩ ውስጥ አንድ ትልቅ ችግር እንዳለ ተረዳ። በዚያን ጊዜ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ “አፓርታይድ” የሚባል መጥፎ ሕግ ነበር። ይህ ሕግ ሰዎችን በቀለማቸው ይለያይ ነበር። ነጮች ምርጥ ትምህርት ቤቶች፣ ትላልቅ ሆስፒታሎች እና ቆንጆ መጫወቻ ቦታዎች ሲኖሯቸው፣ ጥቁሮች ግን በደካማ ትምህርት ቤት እንዲማሩ እና መብት እንዳይኖራቸው ይደረግ ነበር። ኔልሰን ይህን ሲያይ “ለምን ሁሉም ሰው እኩል አይሆንም?” ብሎ አሰበ።
ይህንን ፍትሕ የጎደለው አሠራር ለመቀየር ኔልሰን ትልቅ ሰው ሲሆኑ ጠበቃ ሆኑ። ለሰዎች መብት መጮህ እና በሰላማዊ መንገድ መታገል ጀመሩ። ሆኖም በወቅቱ የነበሩት የሀገሪቱ መሪዎች ኔልሰን የሚያደርጉትን ነገር ስላልወደዱት ለ27 ዓመታት እስር ቤት ውስጥ እንዲቆዩ አደረጓቸው። ኔልሰን በእስር ቤት ውስጥ በነበሩባቸው በእነዚያ ሁሉ ዓመታት አላዘኑም ወይም ተስፋ አልቆረጡም። ይልቁንም መጻሕፍትን በማንበብና ራሳቸውን በማስተማር ለሀገራቸው ሰላምን ለማምጣት መዘጋጀት ጀመሩ።
በመጨረሻም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሕዝቦች ጫና አሳድረው ማንዴላ ከእስር ቤት ተፈቱ። ከእስር ሲወጡ ሁሉም ሰው የጠበቃቸው “ያሰሩኝን ሰዎች እበቀላለሁ” ይላሉ ብሎ ነበር። ኔልሰን ማዴላ ግን ያደረጉት ነገር ዓለምን አስገረመ። “ሁላችንም ሰላም መፍጠር አለብን፤ ይቅር መባባል አለብን” በማለት ነጮችን እና ጥቁሮችን በአንድነት አቀፏቸው። ሀገራቸው ደቡብ አፍሪካም ሁሉም በእኩልነት የሚኖርባት እንድትሆን አደረጉ።
እ.አ.አ በ1994 የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዝዳንት ሆኑ። ኔልሰን ማንዴላ ልጆችን በጣም ይወዱ ነበር። ሁሌም ሲናገሩ “ልጆች የሀገር ተስፋዎች ናቸው፤ እነርሱን በትምህርት ማነጽ ደግሞ ዓለምን ይለውጣል” ይሉ ነበር።
ምንጭ፡ ብሪታኒካ።
ተረት
አይጧና ዝሆኑ
ከረጅም ጊዜ በፊት በአንድ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ውስጥ አንድ በጣም ኩሩ ዝሆን ይኖር ነበር። ይህ ዝሆን “እኔ በጣም ትልቅና ጠንካራ ስለሆንኩ ማንንም አልፈራም፤ የማንንም እርዳታ አልፈልግም” እያለ ይፎክር ነበር። ትንንሾቹን እንስሳት ደግሞ “እናንተ ደካሞች ናችሁ” እያለ ያሾፍባቸው ነበር።
አንድ ቀን ይህ ዝሆን በጫካው ውስጥ ሲጓዝ አዳኞች የዘረጉት ጠንካራ መረብ ውስጥ ሳይታሰብ ገባ። ዝሆኑ ለመውጣት ቢታገልም መረቡ በጣም ጥብቅ ስለነበር ሊበጥሰው አልቻለም። በከፍተኛ ድምፅ “እባካችሁ እርዱኝ!” እያለ መጮህ ጀመረ።
ትልልቅ እንስሳት መጥተው ሊረዱት ቢሞክሩም መረቡን ግን ሊበጥሱት አልቻሉም። በዚህ ጊዜ አንዲት ትንሽ አይጥ ወደ ዝሆኑ ቀረበችና “አይዞህ እኔ እረዳሃለሁ” አለችው። ዝሆኑም እየሳቀ “አንቺ ትንሽ ፍጡ እንዴት ልትረጂኝ ትችያለሽ?” አላት።
አይጧ ግን ምንም ሳትናገር በሾሉ ጥርሶቿ መረቡን አንድ በአንድ መቁረጥ ጀመረች። ብዙም ሳይቆይ መረቡ ተበጣጠሰና ዝሆኑ ነፃ ወጣ። ዝሆኑ በጣም ተገረመ፤ በራሱም አፈረ።
“ይቅርታ አድርጊልኝ” አላት ዝሆኑ፤ አይጧን። “ትልቅ መሆን ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ዛሬ ተማርኩ። አንቺ ትንሽ ብትሆኚም እኔ ልሠራው ያልቻልኩትን ትልቅ ነገር አድርገሻል።” ከዚያ ቀን ጀምሮ ዝሆኑ እና አይጧ የቅርብ ጓደኛሞች ሆኑ።
ማንንም ሰው ትንሽ ነው ብለን መናቅ የለብንም። እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ችሎታ አለው፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ትልልቆች ሊያደርጉት የማይችሉትን ነገር ትንንሾች ሊያደርጉት ይችላሉ።
ምንጭ፡-ኢትዮጵያዊ ተረቶች።
ሞክሩ
- እግር የለውም ግን ይሮጣል፤ አፍ የለውም ግን ይጮሃል። ምንድነው?
- ሲቆርጡት የማይደማ፣ ሲመቱት የማይጮህ ምንድነው?
- የአንተ አባት ልጅ የሆነ ግን ያንተ ወንድም ያልሆነ ማን ነው?
መልስ
- ነፋስ
- ውኃ
- ራስህ
ነገር በምሳሌ
‘‘ሳይቸግር ጤፍ ብድር”፦ አላስፈላጊ ነገር ማድረግ ችግር ውስጥ ይከታል።
‘‘የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል”፡-
አንድ ሰው ችግር ላይ ሲወድቅ ወይም ሲዳከም ብዙ ሰዎች ሊተቹት ወይም ሊጎዱት ይሞክራሉ፡፡
‘‘የቆየ ይቆያል እንጂ አይቀርም”፡-
ጥሩ ነገር ለማግኘት ጊዜ ቢወስድም፣ በትዕግሥት ከጠበቅንና ከሠራን መጨረሻው መሳካቱ አይቀርም ማለት ነው።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


