የሰው ልጅ አእምሮ ከዋክብት ከሞሉበት ሰማይ በላይ ጥልቅ፣ ውስብስብ እና ምስጢራዊ ነው። ይህንን አደገኛ የነፍስ ምስጢር እርቃኑን ያወጣ፤ አእምሮን እንደ መጽሐፍ የገለጠ እና የሰውን ልጅ የህልውና ቀውስ ወደ ማይሞት የኪነ-ጥበብ ስራ የቀየረ ጠቢብ ቢኖር የ19ኛው ክፍለ ዘመን ስመ ጥር ደራሲ ሩሲያዊው ፊዮዶር ዶስቶየቭስኪ ብቻ ነው ይላሉ፤ የዘርፉ ምሁራን። የእሱ ልቦለድ ስራዎች የሚነበቡ ብቻ አይደሉም፤ ይልቁንም የሰው ልጅ በምድር ላይ ያለውን የመኖር ትርጉም የሚፈትሹ፣ ንዑስ- አእምሮን (Subconscious) የሚፈትኑ ጥልቅ የፍልስፍና እና የስነ-ልቦና መስተዋቶች ናቸው።
ከሞት አፋፍ የተጠለፈች ዘላለም
ታላላቅ የጥበብ ስራዎች የሚፈጠሩት ከምቾት ሳይሆን ከሲኦል ማህጸን ነው። የዶስቶየቭስኪ ሊቅነትም የመነጨው ከገጠመው አሰቃቂ መከራ ነው። በሀያ ስምንት ዓመቱ በፖለቲካ ተሳትፎ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በተኳሽ ወታደሮች ፊት ቆሞ ነበር። ሊገደል ሴኮንዶች ሲቀሩት ምህረት ተደርጎለት ወደ ሳይቤሪያ የጉልበት ብዝበዛ ካምፕ ተላከ። ያች ሞትን ፊት ለፊት ያየባት ቅጽበት፣ የሳይቤሪያው አሰቃቂ እስር፣ የቁማር ሱሱ፣ የሚወዳቸውን ሰዎች ማጣቱ እና የሚጥል በሽታ (Epilepsy) ህመሙ አላጠፉትም፤ የሰውን ልጅ የነፍስ ስብራት በሚገባ እንዲረዳ አእምሮውን አጠሩት እንጂ።
በ”The Idiot” መጽሐፉ እንዳሳየው ሞትን የጠበቀ ሰው ህይወት ዳግም ዕድል ስትሰጠው እያንዳንዷ ደቂቃ ለእሱ “ዘላለም” ትሆናለች። ዶስቶየቭስኪ የራሱን መከራ እና የህይወት ውጣ ውረድ እንደ ጥሬ እቃ በመጠቀም የሰውን ልጅ ስቃይ ወደ ከፍተኛ የኪነ-ጥበብ ውበት ቀይሮታል። መከራን መሸሽ ሳይሆን፣ መከራን ትርጉም ባለው መንገድ መቀበል ታላቅ እንደሚያደርግ በተግባር አሳይቷል።
የ”ዩቶፒያ” ቅዠት እና የሰው ልጅ አመጸኛ ተፈጥሮ
ዶስቶየቭስኪ በዘመኑ የነበሩትን እንደ ኒሂሊዝም (Nihilism) እና አምላክ የለሽነት ያሉ አደገኛ አስተሳሰቦችን አጥብቆ ታግሏል። ዘመናዊው ዓለም የሰውን ልጅ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በሂሳብ ስሌት ብቻ ፍጹም ደስተኛ የሆነ ማህበረሰብ (Utopia) ውስጥ ማኖር ይቻላል ብሎ ያምን ነበር። ዶስቶየቭስኪ ግን “የስርቻው ስር መጣጥፍ” በተሰኘው ስራው ይህን ሀሳብ አፈረሰው።
እንደ እሱ እይታ የሰው ልጅ ማሽን ወይም የፒያኖ ቁልፍ አይደለም። ሁለት ሲደመር ሁለት እኩል ነው አራት የሚለው አመክንዮ ለሰው ልጅ ህልውና በቂ አይደለም። የሰው ልጅ ተፈጥሮው አመጸኛ እና አጥፊ ጭምር ነው። በምቾት እና በሀብት የተሞላ ፍጹም ገነት ውስጥ ብናስቀምጠውና “ብላ፣ ጠጣ፣ ተኛ” ብንለው እንኳ የራሱን “ነጻ ፍቃድ” (Free Will) ለማረጋገጥ ሲል ብቻ ያንን ገነት ሊያፈርሰው ይችላል። የሰው ልጅ ከግዴታ ደስታ ይልቅ ነጻነቱን፤ ከስሌት ይልቅ ደግሞ የራሱን ህልውና የሚያረጋግጥበትን ስቃይ ይመርጣል። የሰውን ልጅ አእምሮ በሂሳብ ቀመር ልንፈታው አንችልም በማለት ጽፏል።
አምላክ የመሆን አባዜ እና የስነ- ልቦናው ሲኦል
የጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ “አምላክ ሞቷል” በሚለው ብሂሉ የፈጠረውን ቀውስ ዶስቶየቭስኪ ቀድሞ አይቶት ነበር። ፈጣሪ (ወሰን የለሹ ሀይል) ከሌለ የሰው ልጅ ያን ክፍተት ለመሙላት ራሱ “አምላክ” መሆን ይፈልጋል።
በታላቁ “ወንጀልና ቅጣት” መጽሐፉ ውስጥ ራስኮልኒኮቭ የተባለው ገጸ-ባህሪ የዚህ ማሳያ ነው። “እንደ ናፖሊዮን ያሉ ታላላቅ ሰዎች ለብዙኀኑ ጥቅም ሲሉ የሞራል ህጎችን ጥሰው ሰውን የመግደል መብት አላቸው” በሚል እብሪት (ራሱን አምላክ አድርጎ በመሾም) አንዲት አሮጊትን ይገድላል። ሆኖም ወንጀሉን ከፈጸመ በኋላ እውነተኛው ቅጣት የህግ እስር ቤት ሳይሆን የገዛ ‘ህሊናው’ መሆኑን ይረዳል። ራስኮልኒኮቭ በራሱ አእምሮ ውስጥ ይታሰራል፤ ፍርሃትና የጥፋተኝነት ስሜት ነፍሱን ይከፍለዋል። የሰው ልጅ ከሞራል ህግ በላይ ነኝ ብሎ ሲያስብ መጨረሻው የስነ-ልቦና እብደት (Schizophrenia) መሆኑን ይህ መጽሐፍ በሚገርም ጥበባዊ ውበት ያሳያል።
ፖሊፎኒ እና “ሬሊጋሬ” (Religare) የነፍስ ስብራት ጥገና
ዶስቶየቭስኪ “ካራማዞቭ ወንድማማቾች” (The Brothers Karamazov) በተሰኘው የህይወቱ የመጨረሻ ድንቅ ስራው የእምነትን፣ የጥርጣሬን እና የስጋዊ ስሜትን ፍልሚያ አሳይቷል። እሱ የ”ፖሊፎኒ” (የብዙ ድምጾች ውህደት) አባት ነው። ይህ ማለት የራሱን ሀሳብ በገጸ-ባህሪያቱ ላይ አይጭንም፤ እያንዳንዱ ገጸ-ባህሪ የራሱ የሆነ ነጻ ፍልስፍና እና ጠንካራ ድምጽ አለው።
የሰው ልጅ ህልውና መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ ‘ወሰን ለሌለው ታላቅ ነገር’ (ለፈጣሪ) መገዛት ነው። ሰዎች ከዚህ ታላቅ ነገር ከተነጠሉ በተስፋ መቁረጥ ይሞታሉ። “ሀይማኖት” (Religion) የሚለው ቃል የመጣው “Religare” ከሚለው የላቲን ቃል ሲሆን ትርጉሙም “የተሰበረውን መልሶ ማዋሃድ ወይም መጠገን” ማለት ነው። ዶስቶየቭስኪ የሰው ልጅ የተበታተነ ውስጣዊ ማንነቱን መልሶ መጠገን እና ስቃዩን ማሸነፍ የሚችለው ከፈጣሪው ጋር መንፈሳዊ ትስስር ሲፈጥር፣ በእምነት እና በፍቅር ሲመራ ብቻ እንደሆነ ያምናል።
ዘመን የማይሽረው መስተዋት
የፊዮዶር ዶስቶየቭስኪ የኪነ-ጥበብ ሥራ ዛሬም ድረስ የገነነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እሱ የጻፈው ስለ 19ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካ ሳይሆን ጊዜና ቦታ ስለማይገድበው ሁልጊዜም ውስብስብ ስለሆነው የሰው ልጅ ነፍስ በመሆኑ ነው። እያንዳንዱ መጽሐፉ የሰው ልጅ የራሱን አጋንንት እና መላእክት ፊት ለፊት እንዲያይ የሚያስገድድ የስነ-ልቦና መስተዋት ነው።
ፍቅር እና ትዳር
የዶስቶየቭስኪ የፍቅር እና የትዳር ህይወት ውስብስብ እና ፈታኝ ነበር።
የመጀመሪያ ትዳሩ፡ ማሪያ ኢሳዬቫ
ዶስቶየቭስኪ የመጀመሪያ ሚስቱን ማሪያ ኢሳዬቫን ያገኘው በሳይቤሪያ በግዞት ሳለ ነው። በዚያን ጊዜ እሷ ያገባች እና አንድ ልጅ ነበራት። ባሏ ከሞተ በኋላ ዶስቶየቭስኪ በ1857 አገባት።
ይህ ትዳር በጣም አስቸጋሪ ነበር። ማሪያ በሳንባ ነቀርሳ ትሰቃይ የነበረ ሲሆን ዶስቶየቭስኪ ደግሞ በሚጥል በሽታ እና በቁማር ሱስ ይጠቃ ነበር። ግንኙነታቸው በውጥረት፣ በጭንቀት እና በገንዘብ ችግር የተሞላ ነበር። ማሪያ በ1864 ሞተች።
ከማሪያ ሞት በፊትም ሆነ በኋላ ዶስቶየቭስኪ የተለያዩ የፍቅር ግንኙነቶች ነበሩት። ከነዚህም መካከል በጣም ታዋቂዋ አፖሊናሪያ ሱዝሎቫ ነበረች። ዶስቶየቭስኪ ከእሷ ጋር በአውሮፓ ተጉዟል። ነገር ግን ግንኙነታቸው በጣም አውዳሚ እና አውሎ ነፋስ የበዛበት ነበር። የእሷ ባህሪ በ”The Gambler” ልብ ወለድ ውስጥ ለፖሊና ገጸ ባህሪ መነሻ እንደሆነ ይታመናል።
ሁለተኛ ትዳሩ፡ አና ስኒትኪና
የዶስቶየቭስኪ የፍቅር ህይወት የተረጋጋው አና ስኒትኪናን ሲያገኝ ነው። አና የ”The Gambler” ልብ ወለድን በፍጥነት ጽፎ እንዲያጠናቅቅ (በአሳታሚው የተሰጠውን የጊዜ ገደብ ለማሟላት) የተቀጠረች ወጣት ጸሃፊ ነበረች።
በስራ ሂደት ውስጥ ተዋደዱ እናም እ.አ.አ በ1867 ተጋቡ። በወቅቱ ዶስቶየቭስኪ 45፣ አና ደግሞ 20 ዓመቷ ነበር። ይህ ትዳር ለዶስቶየቭስኪ ህይወት ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። አና በጣም ታጋሽ፣ አስተዋይ እና የተግባር ሴት ነበረች።
የዶስቶየቭስኪን የገንዘብ ጉዳዮች አስተካክላለች፤ የቁማር ሱሱን እንዲያቆም ረድታዋለች፤ እናም ታላላቅ ስራዎቹን (እንደ የካራማዞቭ ወንድማማቾች እና ወንጀል እና ቅጣት) እንዲጽፍ ምቹ ሁኔታ ፈጥራለታለች። አራት ልጆችን አፍርተዋል (ምንም እንኳን ሁለቱ በልጅነታቸው ቢሞቱም)
አና ዶስቶየቭስኪ እስኪሞት ድረስ (በ1881) አብራው ነበረች። ከሞተም በኋላ ስራዎቹን በማሳተም እና በማስተዋወቅ ትልቅ ሚና ተጫውታለች። በአጠቃላይ በዚህ ጊዜ የዶስቶየቭስኪ የፍቅር ህይወት ከመከራ እና ከውጥረት ወደ መረጋጋት እና ድጋፍ የተሸጋገረ ነበር። ይህም በሁለተኛ ትዳሩ አማካኝነት የተገኘ ነው።
ሙሉ ህይወቱን በመከራ አሳልፎ የመጨረሻ መጽሐፉን ጽፎ ሲያበቃ፣ “ነገ ብሞት እንኳ ማለት የፈለኩትን ሁሉ ተናግሬያለሁ” ብሎ ነበር። እናም በ59 ዓመቱ በሰላም አረፈ።
ማረፊያ
የዲዮስቶቭስኪ አባባሎች
ገሃነም ምንድን ነው? እኔ የምለው ገሃነም ማለት መውደድ አለመቻል የሚያስከትለው ስቃይ ነው፡፡
ታላቅ አእምሮ እና ጥሩ ልብ ላላቸው ሰዎች ህመም እና ስቃይ የማይቀሩ ናቸው፡፡ እጅግ ታላቅ የሆኑ ሰዎች በምድር ላይ ትልቅ ኀዘን ሊኖራቸው እንደሚገባ አምናለሁ፡፡
በራስ መንገድ ተሳስቶ መሄድ የሌላውን ሰው መንገድ ተከትሎ በትክክል ከመሄድ ይሻላል፡፡
(አቢብ በዓለሜ)
በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


