ዐፄ ቴዎድሮስ ዳግማዊ (የቀድሞ ስማቸው ካሳ ኃይሉ)ጀግና፣ እውነተኛ፣ ታማኝ፣ የማያወላውሉ፣ ቆራጥ፣ ደፋር፣ የራሳቸውን እና የሀገራቸውን ክብር የማያስደፍሩ፣ ማንንም የማይለማመጡ፣ ይቅርታን ለሚጠይቁ ይቅርታ የሚያደርጉ…በማለት ፍስሃ ያዜ ኢትዮጵያ ታሪክ ከኖህ እስከ ኢሕአዴግ በሚለው መጽሐፉ ገልጿቸዋል። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የከፈቱ ሀገራዊ ፍቅር እና የለውጥ ናፍቆት በእጅጉ የሚታይባቸው መሪ ነበሩ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ወደ ስልጣን የመጡት እኚህ ታላቅ ሰው ኢትዮጵያን ከነበረችበት የመከፋፈል እና የድህነት አዘቅት ውስጥ አውጥተው ወደ ዘመናዊ ስልጣኔ ለማሸጋገር የነበራቸው ራእይ ዛሬም ድረስ በአድናቆት ይነሳል።
ዐፄ ቴዎድሮስ ስልጣን በያዙበት ወቅት ኢትዮጵያ በ”ዘመነ መሳፍንት” ቀንበር ስር ወድቃ እርስ በእርስ በሚሻኮቱ መሳፍንት ተከፋፍላ ነበር። ንጉሡ ይህንን ውጥንቅጥ ለማስቆም “የኢትዮጵያ አንድነት” የሚለውን ታላቅ መርህ ይዘው ተነሱ። የአስተዳደር ስርዓቱን በማዕከላዊ መንግሥት ስር ለመጠቅለል የወታደራዊ አደረጃጀቱን በደመወዝ በሚተዳደር ቋሚ ሰራዊት ለመለወጥ እንዲሁም የባሪያ ንግድን ለመከልከል የጀመሯቸው ስራዎች ለዘመኑ አብዮታዊ እርምጃዎች ነበሩ። ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ እንድትበለጽግ የነበራቸው ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ ነበር። በአውሮፓውያን ድጋፍና በሀገር ውስጥ ሙያተኞች አማካኝነት “ሴባስቶፖል” የተባለውን ግዙፍ መድፍ መቅደላ ላይ ማምረታቸው ኢትዮጵያን ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር ለማስገባት የነበራቸው ጉጉት ማሳያ ነው።
የዐፄ ቴዎድሮስ ራእይ በሀገር ውስጥ ተቃውሞ እና በውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ሳቢያ ፈተና ገጠመው። በተለይም ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር የነበረው ግንኙነት በደብዳቤዎች ልውውጥ እና በዲፕሎማሲያዊ አለመግባባቶች ምክንያት እየሻከረ መጣ። ንጉሡ የእንግሊዝን መንግሥት ትኩረት ለመሳብ እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያግዟቸውን ባለሙያዎች ለማግኘት ሲሉ በሀገሪቱ የነበሩ አውሮፓውያንን አስረው በመቅደላ አቆዩ።
ይህ ድርጊት በእንግሊዝ መንግሥት በኩል “የክብር ጥሰት” ተደርጎ በመወሰዱ በጄነራል ሮበርት ናፒየር የሚመራ እና ከ30 ሺህ በላይ ወታደሮችን እና በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳትን ያሳተፈ ግዙፍ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ዘመተ። ቴዎድሮስ ይህን ግዙፍ ጦር ለመጋፈጥ በመቅደላ ምሽግ ላይ ተገኙ።
ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም የእንግሊዝ ጦር የመቅደላን ምሽግ ሰብሮ ለመግባት ተቃረበ። የንጉሡ ሰራዊት በዘመናዊ መሣሪያ በታጠቀው የጠላት ጦር ቢዳከምም ቴዎድሮስ ግን ፍጻሜያቸው ምን መሆን እንዳለበት ቀድመው ወስነው ነበር።
ጠላት ምሽጉን ጥሶ ሲገባ ዐፄ ቴዎድሮስን በህይወት አላገኛቸውም። ንጉሡ “እጄን ለባዕድ አልሰጥም፤ የሀገሬንና የዙፋኔን ክብር አላስደፍርም” በማለት ከንግሥት ቪክቶሪያ የተላከላቸውን ሽጉጥ በአፋቸው ውስጥ አድርገው በመተኮስ ሕይወታቸውን ሰዉ። ይህ ውሳኔ በሽንፈት የሚመጣን ውርደት ከመቀበል ይልቅ በክብር እና በነፃነት ማለፍን የመረጡበት ታሪካዊ ድርጊት ነው።
የዐፄ ቴዎድሮስ መስዋዕትነት በኢትዮጵያውያን ዘንድ የጀግንነት ጥግ ተደርጎ ይወሰዳል። ንጉሡ በመቅደላ አናት ላይ ያፈሰሱት ደማቸው ቀጣዩን ትውልድ ያስተማረባቸው ቁምነገሮች አሉ፡፡
የመጀመሪያው ሀገራዊ ሉዓላዊነት ሲሆን የሀገሪቱ ክብር እና ነፃነት ከግል ሕይወት በላይ መሆኑን በተግባር አሳይተዋል። ሁለተኛው የአንድነት መንፈስ ነው፤ አሁን ላለችው ኢትዮጵያ የመሠረት ድንጋይ ያኖሩ፤ ኢትዮጵያዊነትን ከአካባቢያዊነት በላይ ያስቀደሙ መሪ ናቸው። የመጨረሻው ደግሞ የኩራት ምንጭ ነው፡፡ በቅኝ ግዛት ዘመን መጀመሪያ አካባቢ አንድ አፍሪካዊ ንጉሥ ለታላቋ ብሪታንያ አልንበረከክም ማለታቸው ለመላው ጥቁር ሕዝብ የኩራትና የጥንካሬ ምልክት ሆኗል።
ዐፄ ቴዎድሮስ በዘመናቸው ያልተረዱላቸው፤ በራዕያቸው ግን ከዘመኑ የቀደሙ ታላቅ መሪ ነበሩ። በመቅደላ ምሽግ የከፈሉት መስዋዕትነት ኢትዮጵያ ፈጽሞ ለባዕድ እንደማትገዛ ለዓለም የተላለፈ ታላቅ መልእክት ሆኖ ለዘላለም ይኖራል፡፡
የመቅደላው ፍጻሜ የታየበት ወቅት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስገራሚ፣ በረቂቅ ስሜቶች የተሞላ እና ለዐይን የሚዘገንን የጦርነት ድራማ የታየበት ነበር። በወቅቱ በመቅደላ ምሽግ ላይ የነበረው አጠቃላይ ድባብ የጭንቀት፣ የቁርጠኝነት እና የታላቅ ተስፋ መቁረጥ ድብልቅ ሆኖ ይታይ ነበር። የቴዎድሮስ ሠራዊት በረሃብ፣ በጥም እና በጠላት ዘመናዊ መሣሪያ ተዳክሞ የነበረ ሲሆን በተለይ ከፋሲካ በፊት በነበረው ዓርብ በበሽሎ ጦርነት ላይ የደረሰው ጉዳት በምሽጉ ውስጥ የነበረውን ሰራዊት ሞራል በእጅጉ ሰብሮት ነበር።
ንጉሡ በዚያን ወቅት ጥልቅ ብቸኝነት ይሰማቸው ነበር። ለረጅም ዘመን አብረዋቸው የቆዩ ወዳጆቻቸው አልቀዋል፤ የቅርብ ሰዎችም ከድተዋቸዋል። ሆኖም ግን በንጉሡ ላይ ፍርሃት አይታይም ነበር። ይልቁንም “የኢትዮጵያ ትንሣኤ ሳይታይ ማለፌ ነው?” የሚል ጥልቅ ሐዘንና ቁጭት ውስጥ ሆነው ለተቀሩት ወታደሮቻቸው “ሕይወታችሁን አድኑ” በማለት እንዲበተኑ ሲፈቅዱላቸው ትዕይንቱ እጅግ የሚሰቀጥጥ እና የታማኝ ወታደሮች ለቅሶ የሞላበት ሆኖ አልፏል።
ከታችኛው ሜዳ ላይ ደግሞ በጄኔራል ናፒየር የሚመራው የእንግሊዝ ጦር በመቅደላ አናት ላይ የከባድ መሣሪያ ድብደባ ያካሂድ ነበር። የዝሆን ድምፅ፣ የከበሮ ጩኸት እና በዲሲፕሊን የሚጓዘው የጠላት ጦር እንቅስቃሴ መላውን አካባቢ ያናውጠው ነበር። ለኢትዮጵያ እንግዳ የሆነው የሮኬት እና የመድፍ ድብደባ አካባቢውን በጢስ እና በባሩድ አፍኖት ስለነበር የጦርነቱ ድባብ እጅግ አስፈሪና አስጨናቂ ሆኖ ይታይ ነበር።
የመጨረሻው የፍጻሜ ሰዓት ደግሞ በታላቅ ዝምታና ዋይታ የታጀበ ነበር። ሚያዝያ 6 ቀን የትንሣኤ ዕለት መቅደላ በደም ታጥባ በነበረበት ሰዓት እንግሊዞች የምሽጉን በር ሰብረው ሲገቡ ያገኙት የንጉሡን አስከሬን ብቻ ነበር። ንጉሡ እጃቸውን ለጠላት ከመስጠት ይልቅ የክብር ሞትን መርጠው ሽጉጣቸውን ጠጥተው መውደቃቸው ሲታወቅ በዚያ ስፍራ የነበረው ጩኸት በድንገት ቆሞ ታላቅ ዝምታ ሰፈነ። ጠላቶቻቸው እንኳ ሳይቀሩ በንጉሡ ጀግንነት ተደንቀው በክብር ይመለከቱ ነበር። ከዚያም ብዙ ሳይቆይ የንጉሡን ማለፍ የሰሙ ሴቶች እና ወታደሮች ዋይታ እና “አንበሳው ወደቀ” የሚል የሐዘን እንጉርጉሮ መላውን መቅደላን አናወጠው።
እንደ ታሪክ ዘጋቢዎች ገለጻ በወቅቱ የነበረው የተፈጥሮ ሁኔታም ቢሆን በጭጋግ የተሸፈነ እና የጦርነቱን አስፈሪነት የሚያጎላ ነበር። የመቅደላ ተራራ ግርማ እና ቁልቁለቱ በባሩድ ጭስ ተሸፍኖ የሚታይበት ያ ድባብ የአንድ ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ማብቂያ እና የአንድ ኩሩ መንፈስ መስዋዕትነት የታየበት እጅግ ልብ የሚነካ ትዕይንት ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።
የዐፄ ቴዎድሮስ መስዋዕትነት በወቅቱ ሽንፈት ቢመስልም በረጅም ጊዜ ሂደት ግን ለኢትዮጵያ የህልውና እና የማንነት መሰረት የጣሉ በርካታ ውጤቶችን አስገኝቷል። ከሁሉ አስቀድሞ ይህ መስዋዕትነት ለኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ኩራት እና ለነፃነት የማይደራደር ስነ-ልቦናን ገንብቷል። ንጉሡ ለጠላት እጃቸውን ከመስጠት ይልቅ ሞትን መምረጣቸው ተከታዮቹ የኢትዮጵያ መሪዎችና ሕዝቦች ለማንኛውም ባዕድ ወራሪ እንዳይንበረከኩ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኗቸዋል። ይህ የ”መሞት እንጂ አለመሸነፍ” መንፈስ ነው ከዓመታት በኋላ ለአድዋ ድል እና ለሌሎች የነፃነት ተጋድሎዎች እንደ ዋና መነሳሻ ሆኖ ያገለገለው።
በሌላ በኩል መስዋዕትነቱ የኢትዮጵያን አንድነት በደም ያጸና ክስተት ነበር። ቴዎድሮስ ከመነሳታቸው በፊት ኢትዮጵያ በጎሳ እና በክልል መሳፍንት ተከፋፍላ የምትታመስ ሀገር ነበረች። እሳቸው ለሀገሪቱ አንድነት የከፈሉት ዋጋ እና በመጨረሻም ህይወታቸውን መስጠታቸው ኢትዮጵያዊነትን ከአካባቢያዊ ማንነት በላይ ከፍ አድርጎታል። ይህም ተከታዮቻቸው ዐፄ ዮሐንስ እና ዐፄ ምኒልክ የተጀመረውን የአንድነት ጉዞ ዳር ለማድረስ እንዲችሉ መንገድ ጠርጓል።
በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን የመቅደላው መስዋዕትነት ለኢትዮጵያ ትልቅ ክብርን አትርፏል። የአውሮፓ መንግሥታት ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ጥልቅ ስልጣኔ፣ የዳበረ ታሪክ እና ለነፃነቱ የሚሞት ሕዝብ እና መሪ ያላት ሀገር መሆኗን እንዲረዱ አድርጓል። ምንም እንኳ በወቅቱ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች እና መጻሕፍት በብሪታንያ ጦር ቢዘረፉም የንጉሡ ጀግንነት ግን በታሪክ መዝገብ ውስጥ በማይደመሰስ ቀለም ተጽፎ እንዲቀር አድርጓል።
በመጨረሻም የዐፄ ቴዎድሮስ መስዋዕትነት በኢትዮጵያ ስነ-ጽሑፍ፣ ስነ-ጥበብ እና ባሕል ውስጥ የማይጠፋ አሻራ ጥሏል። በሺዎች የሚቆጠሩ ግጥሞች፣ ዘፈኖች እና ድራማዎች በእሳቸው ጀግንነት ላይ ተመስርተው የተፈጠሩ ሲሆን ይህም ትውልዱ ሀገራዊ ፍቅርን እና መስዋዕትነትን እንዲማርበት ትልቅ የትምህርት ምንጭ ሆኗል። በአጠቃላይ የመቅደላው ፍጻሜ የአንድ ንጉሥ ሞት ብቻ ሳይሆን የዘመናዊት ኢትዮጵያ ትንሳኤ መሰረት ሆኖ ያገለገለ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን አለቃ ወልደ ማርያም “የዐፄ ቴዎድሮስ ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው ጠቅሰዋል።
ሳምንቱ በታሪክ
ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ተወለዱ
ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ወይም በፈረስ ስማቸው አባ ኮስትር በኢትዮጵያ የአርበኝነት ታሪክ ውስጥ ስማቸው በደመቀ ቀለም ከሚፃፉ ጀግኖች ቀዳሚው ናቸው። ሚያዝያ 7 ቀን 1904 ዓ.ም በጎጃም ክፍለ ሀገር ቢቸና ወረዳ የተወለዱት እኚህ ጀግና ገና በወጣትነታቸው ነበር የጦርነትንና የመከራን ሕይወት መቅመስ የጀመሩት። አባታቸው አቶ ዘለቀ ላቀው በወቅቱ በነበረ የፖለቲካ ግጭት ምክንያት መገደላቸው በላይን ቀድሞ ወደ በረሃ እንዲገቡ እና ራሳቸውን እንዲከላከሉ አድርጎታል። ይህ አጋጣሚ ለወደፊቱ የሽምቅ ውጊያ ስልት ትልቅ ልምድ እና ዝግጅት እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል።
ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት በላይ ዘለቀ በጎጃም በረሃዎች ሆነው የጠላትን ጦር መግቢያ መውጫ በማሳጣት የሚታወቁ ጀግና ነበሩ። በተለይም በአባይ ድልድይ እና በጮቄ ተራሮች አካባቢ ያካሄዷቸው ውጊያዎች በጠላት ጦር ላይ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥረው ነበር።
ጣሊያኖች በላይን በጉቦ፣ በሹመት እና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ለማታለልና ወደ ሰላም ለማምጣት ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። ሆኖም ግን በላይ ዘለቀ “ሀገሬንና ነፃነቴን በወርቅ እና በብር አልሸጥም” በማለት በጽናት በመታገል ለኢትዮጵያ ነፃነት የመጨረሻውን ዋጋ የከፈሉ አርበኛ ናቸው።
የበላይ ዘለቀ የጀግንነት ወሬ እስከ አዲስ አበባ እና እስከ ጣሊያን ቤተ መንግሥት ድረስ ይደርስ ነበር። የሽምቅ ውጊያ ስልታቸው እና አባባሎቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ በጎጃም ህዝብ ዘንድ በቅኔ እና በዘፈን ይወሳሉ።
ከአርበኝነት ዘመናቸው በኋላም ቢሆን በላይ ዘለቀ ለሀገራቸው እና ለክብራቸው የነበራቸው አቋም የማይናወጥ ነበር። ታሪካቸው ሲነገር የሀገር ፍቅር፣ ለፍትህ መቆም እና ለማንነት ዋጋ መስጠት ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ ያስተምራል።
ምንጭ፡- ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት”።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የሚያዚያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


