የሕይወት መሠረት የሆኑት ህዋሳት ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ይሞታሉ፡፡ የሞቱ ሕዋሳት ደግሞ ከሰውነት መወገድ ይገባቸዋል። ነገር ግን ይህ ሂደት ከተዛባ ሕዋሳት በሰውነት ውስጥ በፍጥነት በመራባት እና በማደግ ከቁጥጥር ውጭ በመሆን አንድ ቦታ ተጠራቅመው እባጭን ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ያልተለመደ የሕዋሳት ዕድገት በመደበኛ የሰውነት ሥርዓት ውስጥ ጣልቃ በመግባት የደም ሕዋሳትን ወይም ሌሎች የአካል ክፍሎችን በመጉዳት ለተለያዩ የካንሰር በሽታዎች ያጋልጣሉ።
ከላይ ለመግቢያ ያነሳነውን ሙያዊ ሐሳብ ያጋሩን በፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል የኤች አይ ቪ አገልግሎት አስተባባሪ ዕጩ ዶክተር በቀለ የኔው ናቸው፡፡ እንደ ባለሙያው ማብራሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከሚሞቱ ሰዎች መካከል 71 በመቶው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 31 በመቶው በካንሰር ነው፡፡
የካንሰር በሽታ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ያነሱት ዕጩ ዶክተር በቀለ የኔው ማጨስ፣ ለከፍተኛ ጨረር እና ኬሚካል መጋለጥ፣ ዘረመል (genetic)፣ ቫይረሶች እና ባክቴሪያዎች፣ የኢስትሮጅን ሆርሞን መዛባት፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ (ከልክ ያለፈ ስኳር፣ ጨው፣ ቅባት መመገብ)፣ በቂ የእንቅልፍ መዛባት (ማነስ)፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እጥረት እና ጭንቀት ተጠቃሽ መንስኤዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋልወ።
እንደ ባለሙያው ገለጻ ካንሰር በዋናነት ጉበትን፣ አንጀትን፣ ሳንባን፣ ጡትን፣ ጭንቅላትን ማሕፀንን… ይጎዳል፡፡ የማሕፀን በር ካንሰር ደግሞ አንደኛው ነው።
የማሕፀን በር ካንሰር በማሕፀን እና በሴት ብልት መካከል ባለው የታችኛው ክፍል (የማህፀን በር) ላይ የሚፈጠር የካንሰር አይነት ነው። 97 ነጥብ 71 በመቶ ያህሉ የማሕፀን በር ካንሰር የሚፈጠረው ሂውማን ፓፒሎማ (Human Papilloma Virus) በተባለ ቫይረስ አማካኝነት ነው። ቫይረሱ ወደ ካንሰርነት ለመቀየር ከ10 እሰከ 20 ዓመት ሊቆይ ይችላል፡፡
የግብረ-ሥጋ ግንኙነት በልጅነት ቀደሞ መጀመር እና ከበርካታ ወንዶች ጋር ልቅ ግንኙነት መፍጠር፣ ማጨስ፣ የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም መቀነስ፣ የቤተሰብ ታሪክ (እናት እና እህት ካንሰር የተከሰተባቸው ከሆኑ) የችግሩ አጋላጭ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ምልክቶች፦
የማሕፀን በር ካንሰር በመጀመርያ ደረጃ ምልክት ላይኖረው ይችላል፤ ነገር ግን በሴት ብልት ፈሳሽ መጨመር ወይም ያልተለመደ ከመደበኛ የወር አበባ ውጭ ባሉ ጊዜያት ረዘም ላሉ ቀናት የደም መፍሰስ፣ መጥፎ ጠረን (ሽታ)፣ በጾታዊ ግንኙነት ወቅት ወይም በኋላ የደም መፍሰስ ወይም ሕመም፣ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ እና ከወትሮው የበለጠ የወር አበባ መፍሰስ፣ ከማረጥ በኋላ የደም መፍሰስ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በሽታው እየተባባሰ ከሄደ ደግሞ እንብርት እና የታችኛው የወገብ ክፍል ላይ ሕመም ይከሰታል፡፡
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተሠራውን ጥናት ዋቢ አድርገው ባለሙያው እንደጠቀሱት 80 በመቶ ሴቶች ወደ ሕክምና የሚሄዱት በሽታው ከተሰራጨ በኋላ ነው፡፡ ነገር ግን የማሕፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ እና ክትባቱን በመውሰድ መከላከል ይቻላል፡፡ የማሕፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ ወደ ካንሰር ደረጃ ሳያድግ መቆጣጠር እንዲሁም በሽታው ቢከሰትም እንኳ ደረጃውን ማወቅ እና ሳይሰራጭ መታከም ይቻላል፡፡
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 49 ያሉ ሴቶች ከሁለት እስከ አምስት ዓመታት ባሉት ጊዜያት አንድ ጊዜ የቅድመ ካንሰር ምርመራ እና ልየታ በማድረግ በሽታውን መከላከል ይቻላል፡፡ ዕድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ 14 ዓመት የሆኑ ታዳጊ ሴቶችን ደግሞ ወላጆች በማስከተብ በሽታ አምጪውን ቫይረስ ቀደሞ መከላከል ይቻላል፡፡
አሁን ላይ በስፋት እየተሰራጨ ያለውን የካንሰር በሽታ ቀድሞ መከላከል ካልተቻለ ጉዳቱ ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆሙት ደግሞ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የበሽታዎች መከላከል እና ቁጥጥር ባለሙያ ዶክተር ቴዎድሮስ ጌታቸው ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ማብራሪያ የካንሰር በሽታ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ስምንት ሺህ ሰዎች ይያዛሉ፤ ከነዚህ ውስጥ ስድስት ሺህ ያህሉ ይሞታሉ፡፡
በአማራ ክልልም በተያዘው ዓመት በስድስት ወራት ብቻ ምርመራ ካደረጉ ከ12 ሺህ በላይ ዜጎች ውስጥ አራት ሺህ 512 ሴቶች በቅድመ ካንሰር እንዲሁም 744ቱ በካንሰር መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ቅድመ ካንሰር የማሕፀን በር ካንሰር ምርመራ በማድረግ የሚረጋገጥ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የተጎዳው አካል ወደ ካንሰር አድጎ እንዳይሰራጭ በሕክምና ስለሚወገድ መዳን ይቻላል፡፡ በማሕፀን በር የካንሰር ምርመራ ቅድመ ካንሰር የተገኘባት ሴት ቀድማ ምርመራ በማድረጓ በሽታው ሳይሰራጭ እንድትታከም በማድረግ በቀላሉ መዳን ትችላለች።
የማሕፀን ካንሰር በገዳይነቱ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ባለሙያው ወንዶችም በጡት ካንሰር አንድ በመቶው እንደሚያዙ አስገንዝበዋል፡፡ በርካቶች “ካንሰር አይድንም“ በማለት እነሱም ሆነ ልጆቻቸው ምርመራ ከማድረግ ወደ ኋላ እንደሚሉም ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጅ በየጊዜው የካንሰር ምርመራ በማድረግ ፈጽሞ መከላከል ወይም ቢከሰት እንኳ ሳይሰራጭ ታክሞ መዳን እንደሚቻል ነው ያስገነዘቡት፡፡
መረጃ
የካንሰር ሕክምና አይነቶች፦
- የቀዶ ጥገና (Surgery):
እጢውን ወይም የተጎዳውን የሰውነት ክፍል በቀዶ ጥገና በማስወገድ የሚደረግ ህክምና ነው።
- የጨረር ሕክምና(Radiotherapy): ከፍተኛ የጨረር መጠን በመጠቀም የካንሰር ህዋሳትን ለማጥፋት እና እጢዎችን ለማኮማተር የሚረዳ ህክምና ነው።
- ኬሞቴራፒ (Chemotherapy):
ካንሰርን ለመግደል መድሃኒቶችን በመጠቀም የሚሰጥ የህክምና አይነት ነው።
- የሆርሞን ሕክምና (Hormone Therapy):
የካንሰር እድገትን ለማዘግየት ወይም ለማስቆም ሰውነት የሚያመነጨውን የሆርሞን መጠን የሚቀንስ ወይም የሚያግድ ህክምና ነው።
- ኢሚውኖቴራፒ (Immunotherapy):
የሰውነት በሽታ የመከላከል ስርዓት ካንሰርን እንዲዋጋ የሚያግዝ የህክምና አይነት ነው።
- የመቅኔ ቅየራ/ስቴም ሴል ንቅለ ተከላ (Stem Cell Transplant): በከፍተኛ የኬሞቴራፒ ወይም የጨረር ህክምና የተጎዱትን የመቅኔ ህዋሳት በአዲስ ጤናማ ሴሎች የሚተካበት ዘዴ ነው።
(ሙሉ ዓብይ)
በኲር የሚያዚያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


