የፕላስቲክ እገዳ

0
96

የመሬት ደህንነት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው ኧርዝ ዶት ኦርግ እንዳስነበበው በየዓመቱ 430 ሚሊዮን ቶን (ፊስታል) የፕላስቲክ ተረፈ ምርቶች ወደ መሬት ይለቀቃሉ፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 3/4ኛ ያህሉ ድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል የማይችሉ የፕላስቲክ ውጤቶች ናቸው::

መረጃው እንደሚለው አሁን ላይ ፕላስቲክ የሌለበትን ሥፍራ ማግኘት አይቻልም:: ከምግባችን እስከ ሰውነታችን፣ ከውኃ መሥመሮቻችን እስከ አፈር እና መንገዶቻችን ድረስ በፕላስቲክእና ተረፈ ምርቶቹ ተውጧል::

ኢትዮጵያም ለፕላስቲክ ማሸጊያ ዕቃዎች በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ከሚያደርጉ ሀገራት መካል አንዷ ናት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከምርቶቹ ብዛት ባለፈ ድጋሚ ጥቅም ላይ አለመዋላቸው ልዩ የአወጋገድ ሥርዓትን ይፈልጋል፤ ይሁን እንጂ በአወጋገድ ሥርዓት ጉድለቶች ምክንያት ለጤና ጠንቅ ከመሆን ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን ያስከትላል:: ለአብነትም ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ  የፍሳሽ ቆሻሻ የሚከማችበት አካባቢ (የሚበዛው የፕላስቲክ ተረፈ ምርት መሆኑን ልብ ይሏል) ተደርምሶ የበርካችን ሕይወት መንጠቁ ማሳያ ነው::

በተመሳሳይ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚስተዋለው በተለይ የፕላስቲክ ምርቶች ከአገልግሎት በኋላ የትም ነው የሚጣሉት፤ ይህ ደግሞ  የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓቱን ይደፍናል፣ አረንጓዴ ቦታዎቻችንም ይበክላል፤ አለፍ ሲልም የማሕበረሰብን ጤና ይጎዳል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ታዲያ ሀገራችን የተለያዩ መመሪያዎችን በማውጣት ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ ነው፤ ለአብነትም በቅርቡ አዲስ አበባ፣ ከሰሞኑ ደግሞ ባሕርዳር ከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ እያደረጉ የሚገኙት መመሪያ ይጠቀሳል::

ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ ተግባራዊ መደረግ የጀመረውን የፕላስቲክ ምርቶች እገዳ በተመለለከተ የተለያዩ ሐሳቦች እየተነሱ ነው፤ ምርቱን ሊተካ የሚችል ምን አማራጭ ቀረበ? የሚለው ደግሞ በተለይ ተጠቃሚዎች የሚያነሱት ጥያቄ ነው::

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር እንዳስታወቀው ከመጋቢት 21 ቀን 2018 ጀምሮ የፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀም አይቻልም:: የከተማ አስተዳደሩ አካባቢ  ጥበቃ ጽዳትና ውበት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ጽጌረዳ አበበ እንደገለጹት የፕላስቲክ ምርት ለረጅም ጊዜ የማይበሰብስ በመሆኑ በብዝኀ ሕይወት፣ በሰው እና በእንስሳት ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያመጣል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የፕላስቲክ ውጤቶች ከፍተኛውን መጠን ይይዛሉ።

በባሕዳር ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ቁጥር 1383/2017 እንደተደነገገው ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ማምረት፣ ወደ ገበያ ማቅረብ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ መሸጥ እና ማከማቸት እንዲሁም መጠቀም በሙሉ የተከለከለ ነው።

በአዋጁ እንደተመላከተው አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅምላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ውጤቶችን በሙሉ መጠቀም አይቻልም፤ ይሁን እንጂ ከአማራጭ አኳያ እና በቀላሉ የሚበላሹ (በፕላስቲክ ብቻ የሚቀመጡ) ፍጆታዎችን በተመለከተ ቅሬታ ተነስቷል፤ በመሆኑም እንደ ከተማ መጠቀም የተከለከለው ለዕለት ከዕለት ግብይት የሚውሉ የኩርቱ እና ጥቁር የገበያ ፌስታሎችን ነው፤ የአፕል ማሸጊያ ላስቲክ  (በዚያ ፕላስቲክ ካልታሸገ ስለሚበላሽ)፣ የባልትና እና ስኳር ማሸጊዎያች አማራጭ  ማሸጊያ እስኪተካ ለጊዜው የተፈቀዱ መሆናቸውን ነው ወ/ሮ ጽጌረዳ የተናጉሩት::

ከዚህ ባለፈ የተከለከሉ የፕላስቲክ ከረቶችን መጠቀም ወይም ይዞ መገኘት ከሁለት ሺህ እስከ አምስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትን ያስከትላል::

ለንግድ ዓላማ ያመረቱ፣ ያስገቡ፣ የሸጡ ወይም ያከማቹ ግለሰቦች ደግሞ ከ50,000 እስከ 200,000 ብር ወይም እስከ አምስት ዓመት እስራት ያስቀጣቸዋል::

የቅጣት አፈፃፀሙም ከመጋቢት 21 ቀነ 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ ሆኗል። አማራጮችን በተመለከተም ፋብሪካዎች እንዲያቀርቡ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል::

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት  ለ19 ዓመታት ያህል ስትጠቀምበት የነበረውን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ የሚያትተውን አዋጅ አሻሽላ በአዲስ አዋጅ ተክታለች። አዋጅ ቁጥር 513/1999 ተብሎ ሲጠራ የነበረው አዋጅ በአዲሱ 1383/2017 ተተክቷል። ይህ አዋጅ በ2017 ዓ.ም ፀድቆ ከጥር 23/2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል። በሀገር አቀፍ ደረጃ  የፕላስቲክ ከረጢት ማምረት፣ ወደ ሀገር ማስገባት፣ መሸጥ እና መጠቀምን በተመለከተ የሚደነግግ አዋጅ ነው።

ይህ አዋጅ ሲወጣ በርካታ ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን በዋናነት ከፕላስቲክ ምርቶች ጋር በተያያዘ ትልቅ ትኩረት ስለመስጠቱ የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን አየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አወቀ ይታይህ ተናግረዋል::

ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት በሰጠችው ከፍተኛ ትኩረት ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶችን ከልክላለች። ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶችን ማምረት፣ ማከፋፈል እና አለፍ ሲልም ሲጠቀሙ መገኘት የሕግ ተጠያቂነትን ያስከትላሉ።

አዋጁ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። በክልሉ በሚገኙ ከፍተኛ ከተሞች የግንዛቤ ፈጠራን ጨምሮ ሌሎች ተግባራት ተከናውነዋል። ለአዋጁ ተፈፃሚነትም የጋራ ጥረትን ይጠይቃል ነው ያሉት።

የፕላስቲክ ብክለት በየቦታው በመበራከቱ፣ ቀድሞ የነበረንን የቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አቅም አጥፍቶታል። የፕላስቲክ ቆሻሻ መስፋፋት፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ዘዴዎችን በመዝጋት እና የውኃ ምንጮቻችንን በክሎ የበሽታ መራቢያ ቦታን በመፍጠር በነዋሪዎች ጤና እና ደህንነት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል። ይህ የሕዝብ ጤናን፣ የምግብ ሥርዓታችንን እና ሥነ-ምኅዳራችንን አደጋ ላይ ይጥላል።

የፕላስቲክ ምርት በዓለም አካባቢ በካይ ከሆኑት ምርቶች መካከል ዋነኛው በመኾኑ በኅብረተሰብ ጤና ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። ፕላስቲክ በአካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ከባድ ብክለት ለመቀነስ እና ለጤና ደህንነት ሲባል ማስወገድ አስፈላጊ ነው። በተለይም የፕላስቲክ ምርቶች በቀላሉ የማይበሰብሱ፣ የውኃ አካላትን የሚበክሉ እና ለእንስሳት ህይወት አደገኛ በመሆናቸው በዘላቂ እና ታዳሽ አማራጮች መተካት ግድ ነው ተብሏል።

የሀገራት ተሞክሮ

ቢቢሲ በፕላስቲክ መገልገያዎችን በተለይም ፔስታልን የከለከሉ ሀገራትን ተሞክሮ ምን እንደሚስል አስነብቧል።

ኬንያ

ኬንያ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን የከለከለችው ከስምንት ዓመታት በፊት ነበር። በሕጉ መሠረትም የፕላስቲክ ከረጢቶችን ከውጭ ሲያስገባ፣ ሲሸጥ ወይም ሲያመርት የተገኘ እስከ 40 ሺህ ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት አሊያም እስከ አራት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ይጣልበታል።

የፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀም ደግሞ 500 ዶላር ወይም እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ እስር ያስቀጣል።

በፓርኮች እና ጫካዎች ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶችን መጠቀም ከልክላለች።

እገዳው ከተጣለ ጀምሮ 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀም እንዳቆመ ተመላክቷል።

ኡጋንዳ

ኡጋንዳ የፕላስቲክ ከረጢቶችን የከለከለችው እ.አ.አ በ2007 ሲሆን ሕጉን ጥሶ የተገኘ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ እስር ወይም እስከ 20 ሺህ ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል።

ታንዛኒያ

ታንዛኒያም እንደ እ.አ.አ በ2019 የፕላስቲክ ከረጢቶችን አግዳለች። በዚህም የፕላስቲክ ከረጢቶችን ይዘው የተገኙ እስከ 87 ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንዲሁም የሰባት ቀን እስር ይጠብቃቸዋል።

እነዚህን የፕላስቲክ ምርቶች ማምረት ወይም ከውጪ ማስገባት ደግሞ እስከ 430 ሺህ ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እና የሁለት ዓመት እስርን ያስከትላል።

በታንዛኒያ የፕላስቲክ ከረጢት መጠቀም በተከለከለበት ወቅት ሟቹ ፕሬዚደንት ማጉፉሊ ተግባራዊነቱን ለማበረታት ዘንቢል ይዘው ታይተዋል::

ኢትዮጵያም ቀደም ብለው የፕላስቲክ ከረጢቶችን ያገዱትን ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ቤኒን፣ ሴኔጋል፣ ኮትዲቯር እና ማዳጋስካርን ጨምሮ ከ34 በላይ የአፍሪካ ሀገራትን ተቀላቅላለች።

 

የህግ አንቀጽ

 

የመራጮች ምዝገባ ቅድመ ሁኔታ

በማንኛውም ምርጫ ለመሳተፍ አስቀድሞ በመራጭነት መመዝገብ ይኖርበታል፡፡ በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 18 አዋጅ ቁ. 1162/2011 መሠረት አንድ ሰው በመራጭነት መመዝገብ የሚችለው፡-

ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሆነ፣

በምዝገባው እለት እድሜው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆነ እና ለምዝገባ በቀረበበት የምርጫ ክልል ቢያንስ ለ6 ወራት የኖረ ከሆነ ብቻ ነው፡፡

ተመዝጋቢው በሚኖርበት የምርጫ ጣቢያ ማንነቱን የሚገልፅ የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ወይም ፓስፖርት (ያልታደሰም ቢሆን)፣

የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ማቅረብ ካልተቻለ በቅርቡ ፎቶግራፍ ተደርጎበት የተሰጠ እንደ የመንጃ ፈቃድ፣ የመኖሪያ የምስክር ወረቀት፣ ከውትድርና የተገለለበት ሰነድ፣ የትምህርት ቤት መታወቂያ የመሳሰሉ የመለያ ማስረጃዎች፣

በተለያየ ምክንያት ራሳቸውን ችለው መመዝገብ የማይችሉ ሰዎች በረዳቶቻቸው አማካኝነት በአካል ተገኝተው መመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማሕበራዊ ትስስር ገጽ፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሚያዚያ 5  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here