“መተው ነገሬን ከተተው”

0
133

በእስያ ጫካዎች ውስጥ አዳኞች ዝንጀሮዎችን የሚይዙበት አንድ ጥንታዊ እና አስገራሚ ዘዴ አላቸው፡፡ ዛፍ ላይ ትንሽ ቀዳዳ ያለውን ጠንካራ እንስራ ያስሩና ውስጡ ጣፋጭ የለውዝ ፍሬ ያስቀምጣሉ፡፡ ዝንጀሮዋ መጥታ እጇን በጠባቡ ቀዳዳ አስገብታ ፍሬውን ትዘግናለች፡፡ ነገር ግን እጇን ጨብጣ (በእፍኝ) ስለያዘች ከጠበበው ቀዳዳ ውስጥ መልሳ ማውጣት አትችልም፡፡ አዳኙ ሲመጣ ዝንጀሮዋ በፍርሃት ትርበደበዳለች፤ ልታመልጥ የምትችልበት ብቸኛው መንገድ ፍሬውን “መልቀቅ” ብቻ ነበር፡፡ እሷ ግን የጨበጠችውን ፍሬ ላለመተው ስትታገል ሕይወቷን ታጣለች፡፡

ይህ አጭር ታሪክ የኛ የሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ሕይወት ማሳያ ነው፡፡ መቆጣጠር የማንችላቸውን ሰዎች፣ ሁኔታዎች፣ የሌሎች ሰዎችን ሐሳብ ወይም ያለፉ ስሕተቶችን አጥብቀን በመያዝ የራሳችንን ሰላምና ነጻነት እናጣለን፡፡ የሥነልቦና ሊቃውንት ይህንን ፈውስ “የመለየት ጥበብ” (The Art of Detachment) ብለው ይጠሩታል፡፡

የመለየት ጥበብ ምንድን ነው?

መለየት ወይም መልቀቅ ማለት ግድ አይስጠን፣ ኃላፊነት አንውሰድ ወይም አንውደድ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ለውጤቱ (Outcome) ያለንን ከመጠን ያለፈ ጥብቅ ስሜታዊ ቁርኝት መቁረጥ ማለት ነው፡፡ የምንችለውን ሁሉ በትጋት ከሠራን በኋላ የቀረውን ለአምላክ ወይም ለተፈጥሮ ሒደት መተው ማለት ነው፡፡

በዘመናዊው የሥነልቦና ዓለም ይህ ጽንሰ ሐሳብ (Locus of Control) ከሚባለው ዕይታ ጋር በእጅጉ ይያያዛል፡፡ የአሜሪካ ሥነልቦና ማኅበር ያወጣቸው ጥናቶች እንደሚያሳዩት “ሁሉንም ነገር መቆጣጠር አለብኝ” ብለው የሚያስቡ ሰዎች ለከፍተኛ የጭንቀት ሆርሞን (ኮርቲሶል) የተጋለጡ ናቸው፡፡ የልብ ሕመምና የድብርት ተጠቂ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በተቃራኒው ከቁጥጥራቸው ውጭ የሆኑ ሁኔታዎችን የመቀበል አቅም ያላቸው ሰዎች የተሻለ የአእምሮ ጤና፣ የፈጠራ ብቃት እና የደስታ መጠን አላቸው፡፡ በዘመናዊው የሥነ-ልቦና ሕክምና መቆጣጠር በማንችለው ነገር ላይ መጨነቅ “የዕውቀት ስሕተት” (Cognitive Distortion) ተብሎ ይፈረጃል፡፡

ታዋቂው ጸሐፊ ሮበርት ግሪን “በ48 የኃይል ሕጎች” እና “የሰው ተፈጥሮ ሕግ” በተሰኙት መጻሕፍቱ  ስለዚህ ጉዳይ በጥልቀት ጽፏል፡፡ ግሪን የመለየት ጥበብን ከስልታዊ አስተሳሰብ ጋር አያይዞ እንዲህ ያስቀምጠዋል፡፡

“ስሜታዊ መሆን የስትራቴጂ እና የኃይል ትልቁ ጠላት ነው፡፡ ማሸነፍ ከፈለግህ ከሁኔታዎች ራስህን አግልለህ ከሩቅ መመልከት አለብህ፡፡ ሰዎች ሊያናድዱህ ወይም ከቁጥጥርህ ውጭ የሆኑ ክስተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፤ አንተ ግን ምላሽ ከመስጠትህ በፊት ስሜትህን በማስወገድ በምክንያታዊነት መገምገም አለብህ” ይላል፡፡

ግሪን እንደሚለው ከሰዎች ድርጊት እና ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር ስሜታችንን ካልነዳነው ማንም ሰው ሊቆጣጠረን አይችልም፡፡ እውነተኛው ኃይል ያለው “ምላሽን በማዘግየት እና ራስን በማራቅ” ውስጥ ነው ይላል፡፡

እንደ ሰው በዙሪያችን ባለው ነገር ላይ ሀሳብ መስጠት እና መቆጣጠር እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ብዙው ጉዳይ ልንቆጣጠረው የምንችለው አይደለም፡፡ ዓለምን ለመቆጣጠር ጥረት ስናደርግ ትኩረታችን በማንለውጠው ነገር ላይ ይባክናል፡፡  ይህን ተከትሎ ስሜታችን መፍሰስ ይጀምራል፡፡ በባዶ ሜዳ የተበተነ ዘር ይሆናል፡፡ ቀጥሎ የማንለውጣቸውን ነገሮች እንዴት እንተው የሚለውን የሚመልሱልን ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡

የመጀመሪያው ድንበር ማበጀት ነው፡፡ በእኛ ኀላፊነት ሥር ያለውን (የራሳችንን ጥረት፣ አመለካከት፣ ቃላት) እና ከእኛ አቅም በላይ የሆነውን (የሌሎች ሰዎችን ድርጊት፣ የአየር ንብረት፣ ያለፈውን ጊዜ፣ ጦርነቱን፣ የኑሮ ውድነቱን ) አጥርተን መለየት አለብን፡፡

ሁለተኛው አስተውሎትን መለማመድ ነው፡፡ አንድ የሚያናድድ ነገር ሲፈጠር ወዲያውኑ ስሜታዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በጥልቀት መተንፈስ፡፡ ሁኔታውን እንደ ሦስተኛ ወገን ታዛቢ ሆኖ መመልከት፡፡

ሦስተኛው ራስን ከውጤቱ ማላቀቅ ነው፤ ሥራውን በትጋት መሥራት፡፡ ነገር ግን “እንዲህ ካልሆነ እሞታለሁ” የሚል ግትርነት አለመያዝ፡፡ ምርጡን ተግባር ማቀድ፤ መጥፎውን ለመቀበል ዝግጁ መሆን፡፡

ዘ አንቴዘርድ ሶል (The Untethered Soul) መጽሐፍ ደራሲ ሚካኤል ሲንገር ስለ “መለየት ጥበብ” ሲተርክ ነፍስ ከእስራት እንዴት ነጻ እንደምትወጣ ያሳያል፡፡ ራሥን ከውስጣዊ ጩኸት እና ከስሜት እስረኝነት ስለማላቀቅ በጥልቀት ጽፏል፡፡

ሚካኤል ሲንገር ቀዳሚው ያደረገው  ያለ ቅድመ ሁኔታ ደስተኛ መሆን መቻልን ነው፡፡ አብዛኛው ሰው “ይህቺን መኪና ስገዛ፣ እገሌ ሲወደኝ፣ ይህ ሥራ ሲሳካልኝ ደስተኛ እሆናለሁ” ብሎ ደስታውን ከውጫዊ ነገሮች ጋር ያስተሳስራል፡፡ መጽሐፉ ግን “ደስታ ውሳኔ እንጂ የሁኔታዎች ውጤት አይደለም” ይላል፡፡ ዛሬውኑ አሁን ባለንበት ሁኔታ “ምንም ቢፈጠር ደስተኛ ሆኜ እቀጥላለሁ” ብለን ከወሰንን ዓለም ምንም ዓይነት መጥፎ ክስተት ብታመጣብን እንኳ ውስጣዊ ሠላማችንን ልትነጥቀን አትችልም፡፡ ይህ ፍጹማዊ የመለየት ጥበብ ነው፡፡ ደስታን ከውጤት ጥገኝነት ነጻ ማውጣት!

ሁለተኛው ዘዴ ሞትን እንደ ምርጥ አማካሪ መጠቀም ነው፡፡ ሲንገር የሕይወትን እውነተኛ ጣዕም ለማወቅ ሞትን ማሰብ አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ማናችንም ብንሆን በዚህች ምድር ላይ ለዘላለም አንኖርም፡፡ ይህንን እውነት ዘወትር ማስታወስ ለማይረቡ ትናንሽ ነገሮች፣ ለሰዎች ሐሜት እና ለንዴት የምናባክነውን ጊዜ እንድንገታ ያደርገናል፡፡ “ይህች ቀን የመጨረሻዬ ብትሆን በዚህ ትንሽ ጉዳይ እበሳጭ ነበር?” ብሎ ራስን መጠየቅ ከማይረቡ ቁርኝቶች ነጻ ያወጣናል፡፡

የመጨረሻው የሲንገር ዘዴ የልብን በር አለመዝጋት ነው፡፡ ሰዎች አንድ የሚያሳምም ወይም የሚያስፈራ ክስተት ሲያጋጥማቸው ወዲያውኑ ራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ የልባቸውን እና የስሜታቸውን በር ይዘጋሉ፡፡ ሲንገር ይህንን የታመቀ ስሜት በዮጋ ፍልስፍና “ሳምስካራ” (Samskara) ይለዋል፡፡ አንድ ጊዜ የተዘጋ ስሜት የውስጥ ኃይል እንዳይዘዋወር ያግዳል፤ ለድብርት እና ለጭንቀትም ይዳርጋል፡፡ ጥበቡ ያለው ሕመም ሲመጣ ከመሸሽ ወይም ለማፈን ከመሞከር ይልቅ ዘና ብሎ ስሜቱ በውስጣችን አልፎ እንዲሄድ መፍቀድ ነው፡፡ በሩን ዘግቶ ከመታገል ከፍቶ ማሳለፍ የተሻለ የነጻነት ጥበብ ነው፡፡

ሕይወት ልክ እንደ ወንዝ ናት፡፡ ወንዙን ወደ ኋላ እንዲፈስ መታገል አቅምን ያባክናል፡፡ የመለየት ጥበብ ማለት በወንዙ ፍሰት ላይ ጀልባችንን በአግባቡ መቅዘፍ እንጂ ወንዙን ለማስቆም መሞከር አይደለም፡፡ ሠላማችን በሌሎች ሰዎች ድርጊት ወይም የውጤት ጥገኛ ሲሆን ነጻነታችንን አሳልፈን ሰጥተናል ማለት ነው፡፡ ልክ እንደዚያች ዝንጀሮ ያጠመደንና የሙጥኝ ያልነውን የተስፋ መቁረጥ ፍሬ ዛሬውኑ እንልቀቀውና ነጻነታችንን እናውጅ! አዎ እውነተኛ ኃይል ያለው በመያዝ ውስጥ ሳይሆን በመተው (በመልቀቅ) ውስጥ ነው! አበው “መተው ነገሬን ከተተው” የሚሉት ለዚህ እኮ ነው፡፡

(አቢብ አለሜ)

በኲር በኲር የሚዚያ 5  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here