ሀገራት ከደም አፋሳሽ ግጭት እንዴት ወጡ?  

0
118

ጦርነት ሲነሳ መጀመሪያ የሚሞተው ሰው ነው፤ መጨረሻ የሚወድቀው ደግሞ ሀገር ነው:: በጦርነት ምክንያት ትምህርት ይቋረጣል፣ የጤና ሥርዓቱ  ይታወካል፣ ኢኮኖሚ ይደቃል፣ ቤተሰብ ይበተናል፣ ትውልድ በፍርሃት ውስጥ ያድጋል:: በጦርነት አሸናፊ የለም፤ ትርፉ  የጋራ ሀዘን ብቻ ነው::

ጦርነት የሚያጠፋው ሕይወትን ብቻ አይደለም፤ ተስፋን ያጠፋል፣ ቤተሰብን ያፈርሳል። አንድ ቤት ሲፈርስ ግንብ ብቻ አይወድቅም፤ በውስጡ የነበረው ቤተሰብ፣ የሕጻናት ሳቅ፣ የወላጆች  ተስፋ እና  ድካም መና ይቀራል::

ጦርነት የሚበላው በጥይት የተመታውን ብቻ አይደለም፤ በረሀብ የሚሞተውን፣ በመድኃኒት እጥረት የሚጠፋውን፣ በፍርሃት የሚርደውን እና በመፈናቀል መንገድ ላይ የሚሰቃየውንም ጭምር ነው::

በዓለም አቀፍ ድጃ ሰላምን ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ድረ ገጽ እንደሚያብራራው  የሚበዛው የዓለማችን ታሪክ በአስከፊ ጦርነት ውስጥ ያለፈ ነው። ጦርነት ውስጥ የገቡ ሀገራትም የኋላ ኋላ ችግራቸውን የሚፈቱት በውይይት ነው::

በኋላ የሚከተሉት ደግሞ የተለያዩ የሰላም መሠረቶች ናቸው:: በጦርነት ወቅት የተማረኩ የጦር ሰራዊቶችን ማስፈታት፣ ተዋጊዎችን ወደ ማሕበረሰብ መመለስ፣ እውነትን ማጋለጥ፣ ተጎጂዎችን መርዳት፣ የሕግ ተቋማትን መጠናከር እና የጦርነትን  መንስኤዎች ከሥር መሠረቱ መፍታት ያስፈልጋል::

የመረጃ ምንጩ እንዳብራራው በርካታ የዓለም ሀገራትም የነበሩበትን አስከፊ የጦርነት ታሪክ ተሻግረው ጠባሳቸውን አክምው በሰላም አየር እየተነፈሱ ይገኛሉ::

ለአብነትም ሴራሊዮን ከግጭት በኋላ የተሻለ መንገድ ላይ ቆማለች፣ ላይቤሪያ እና ሞዛምቢክም በግጭት ምክንያት ከወደቁበት አፈራቸውን አራግፈው ቆመዋል::  ሩዋንዳም ከሰቆቃ ተነስታ አዲስ የሰላም እና የልማት ታሪክ እየጻፈች ነው:: ደቡብ አፍሪካም ከአፓርታይድ ግፍ ወደ ዴሞክራሲ ተሸጋግራለች::

ሴራሊዮን እ.አ.አ ከ1991 እስከ 2002 ድረስ በከባድ የእርስ በርስ ጦርነት ተናውጣ ነበር:: ይህ ጦርነት ከ50 ሺህ በላይ ሰዎችን ሕይዎት ቀጥፏል:: ሀገሪቱን እና ዜጎቿን በፍርሃትና በፍርስራሽ ውስጥ አስገብቷል::

ጦርነቱ እንዲቆም ዋና መሠረት የሆነው እ.አ.አ በ1999 የሎሜ የሰላም ስምምነት (Lomé Peace Agreement) መደረጉ ነበር፤ ይህ ስምምነት ተዋጊ ወገኖችን ወደ ድርድር አመጣ፣ የትጥቅ ማስፈታትን መሠረት አስቀመጠ፣  የሰላም ሂደቱም ከውጭ የሰላም ኃይል ድጋፍ አገኘ::

ነገር ግን ስምምነቱ ብቻውን በቂ አልነበረም:: የታጠቁ ኃሎችን የጦር መሣሪያቸውን እንዲያወርዱ አስደርጋለች::  በዚህም ከ45 ሺህ በላይ መሣሪያዎች ተሰበሰቡ፤ ከ70 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ማሕበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደረገ::

በኋላም የእውነት እና የእርቅ ኮሚሽን (ትሩዝ ኤንድ ሪኮንሲሌሽን – Truth and Reconciliation Commission ወይም TRC) ተቋቋመ፤ ዓላማው የተፈጸሙ ጥፋቶችን ማስመዝገብ፣ ተጎጂዎችን ማዳመጥ፣ የተደበቀ እውነትን ማውጣት እና ድጋሚ እንዳይደገም መሠረት መጣል ነበር::

ከሴራሊዮን ዓለም ጦርነት የሚቆመው ስምምነት ሲፈረም ብቻ ሳይሆን፤ መሣሪያ ሲሰበሰብ፣ ተዋጊ ሲመለስ፣ እውነት ሲነገር እንዲሁም ተጎጂ ሲካስ መሆኑን ግንዛቤ መውሰዷን የመረጃ ምንጩ አክሏል::

በተመሳሳይ ላይቤሪያ በእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ከደቀቀች በኋላ እ.አ.አ በ2003 በጋና ዋና ከተማ አክራ የተሟላ የሰላም ስምምነት ከተደረገ በኋላ ሰላም እንደሰፈነባት ድረ ገጹ አስነብቧል:: ይህ ስምምነት የመንግሥትን፣ የአማጺ ኃይሎችን እና የፖለቲካ ቡድኖችን በአንድ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጧል፤ ከዚያም የሽግግር መንግሥት አቋቋመ፣ በመጨረሻም የትጥቅ ማስፈታት ሂደትን ጀመረ::

ከዚያ በኋላ ሀገሪቱ  እ.አ.አ ከ1979 እስከ 2003 ድረስ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር፣ ተጎጂዎችን ለማዳመጥ፣ እውነትን ለማስቀመጥ እና የሀገር ውስጥ የፍትሕ ሂደትን ለማበረታታት የሚያስችል ኮሚሽን አቋቋመች:: ኮሚሽኑ አንዳንድ ድክመቶች ቢኖሩትም ሀገሪቱ ወደ ሰላም ሽግግር እንድትገባ ትልቅ ሚና ተጫውቷል::

ሌላዋ ለአብነት ተጠቃሽ ሀገር ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ናት:: ሰላምን የተመለከቱ መረጃዎች እና ሀሳቦች የሚጋሩበት ሬዲት የተባለቅ  (Reddit) ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ደቡብ አፍሪካዊያን  ከበቀል ይልቅ እውነትን መርጠዋል:: ደቡብ አፍሪካ በሙሉ እንደ ሴራሊዮን ወይም ላይቤሪያ ዓይነት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ አልገባችም:: የአፓርታይድ ዘመን ግፍና የፖለቲካ ግጭት ግን ሀገሪቱን ወደ ከፋ ደም መፋሰስ ሊወስዳት እንደሚችል ተሰግቶ ነበር:: ያንዣበበውን ስጋት ግን በእርቅ ተሻገሩት።

የሰላም መንገዱ የተጀመረው በድርድር ነበር፤ የአፓርታይድ ሥርዓትን በመቃወማቸው ለ27 ዓመታት ወሕኒ ቤት እንዲቆዩ የተደረጉት  የኔልሰን ማንዴላ መፈታት፣ የአፓርታይድ ሕጎች መፍረስ እና  እ.አ.አ 1994 ወደ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ መሸጋገር ታላቅ የታሪክ መለወጫ ሆነ::

ከዚያ በኋላ የተከናወነው የእውነት እና የእርቅ ኮሚሽንን (Truth and Reconciliation Commission) ማቋቋም ነበር። የኮሚሽኑ ዋና ሀሳቦች የመበሩት ሀገር ወደ ሰላም ለመሄድ የተደበቀ የትናንትን ጥፋት በሕዝብ ፊት መግለጥ፣ ሁሉን በበቀል ማስተካከል አይቻልም፤ ሁሉን በመደበቅም ዘላቂ ሰላም አይመጣም የሚሉ ነበሩ::

የደቡብ አፍሪካ ታሪክ እንደሚያመላክተው ሀገርን ለመዳን እውነተኛ እርቅ ወሳኝ መሆኑን ነው::

ሩዋንዳ እ.አ.አ  1994 የተፈጸመው  ዘር ማጥፋት በዓለም ታሪክ ከአስከፊዎቹ መካከል ነው:: ጦርነቱ በፍጥነት ቢቆምም ሀገሪቱን የከፋ የማሕበራዊ መፈራረስ ውስጥ አስገብቷት ነበር:: ሩዋንዳ ከገጠማት አደጋ ለመውጣት የወሰደችው መንገድ ከሌሎች በተለዬ ሁኔታ የማሕበረሰብ የፍትሕ ሂደትን ነበር፤ በጋቻቻ (Gacaca) ፍርድ ሂደቶች በአካባቢ ደረጃ እውነት እንዲወጣ፣ ብዙ ጉዳዮች እንዲዳኙ እና ማሕበረሰቡ ቀስ በቀስ ወደ ነበረበት ሕይዎት እንዲመለስ ማስቻሉን  የአፍሪካ የሰላም ፋውንዴሽን አስገንዘቧል:: ይህም ሕዝቡን ያሳተፈ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ያላቸውን ከፍተኛ ዋጋ ያሳያል።

ከ15 ዓመት በላይ የቆየ የእርስ በእርስ ጦርነት ተካሂዶባት የነበረችው ሌላዋ አፍሪካዊት ሀገር ሞዛምቢክም በ1992 (እ.አ.አ) በሮም በተካሄደ የሰላም ስምምነት (Rome General Peace Accords) ጦርነቱ ሊያከትም ችሏል:: የአፍሪካ ሰላም ፋውንዴሽን እንዳብራራው ስምምነቱ ተዋጊ ኃይሎችን ወደ ፖለቲካ መድረክ አመጣ፣ የዲሞክራሲያዊ ምርጫ መንገድን ከፈተ፣ ተቋማዊ ሽግግር እንዲፈጠርም መሠረት ጥሏል።

የመረጃ ምንጩ እንዳስነበበው ሀገራቱ ጦርነቱን ለማቆም በመጀመሪያ ጉዳዩን  ወደ ፖለቲካ ገበታ አምጥተውታል::  ይህም ተቡስ አቁም በማድረግ በድርድር ሰላም እንዲሰፍን በር ከፍቷል። የፍትሕ ተቋማትን በመገንባትም የግጭቱን ሥር ለመንቀል ሠርተዋል:: ይህ ታሪክ ለማንኛውም ግጭት ውስጥ ላለ ሀገር የሚሰጠው ግልጽ መልዕክት አለ፤ ሰላም የሚመጣው ጦርነት ሲያሸንፍ አይደለም፤ ፖለቲካ ጦርነትን ሲተካ ነው::

ከብዙ የአፍሪካ ግጭቶች ጀርባ ያሉት ምክንያቶች በአብዛኛው ተመሳሳይ ናቸው፤ ኢ-ፍትሐዊ የሀብት ስርጭት፣ የፖለቲካ መገለል፣ የተቋማት ድክመት፣ የሕግ አለመተግበር፣ ሙስና፣ የማንነት ፖለቲካ እና የውጭ ጣልቃ ገብነት ይጠቀሳሉ:: በመሆኑም በአህጉሪቱ የሚታዩ ግጭቶችን ከመሠረቱ ለመፍታት ለእነዚህ ምክንያቶች ምላሽ መስጠት ይገባል::

በጦርነት ውስጥ “አሸናፊ” የሚባል ቢኖር እንኳን ሁሉም ይጎዳሉ:: አንዱ ልጆቹን ያጣል፣ ሌላው ከተማውን፣ ኢኮኖሚውን ሲከፋም ሁሉም ሰብዓዊነታቸውን ያጣሉ:: ጥላቻ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል፤ ይህም አዲስ ግጭት የሚያበቅል ዘር ይሆናል:: ስለዚህ ጦርነት ድል አይደለም፤ የዘገዬ ሽንፈት ነው:: ዛሬ በመሣሪያ የተገኘ ጸጥታ ነገ በበቀል ሊፈርስ ይችላል:: እውነተኛ ድል የሚገኘው በውይይት፣ በፍትሕ፣ በመግባባት እና በሰላም ነው::

 

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሚያዚያ 5  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here