ህዋሳት በውስጣቸው የሚገኝ ፈሳሽን እንደ ሞገድ ግፊቱን ለኃይል ምንጭነት በመገልገል መንቀሳቀስ መቻላቸው በሰውነት ውስጥ ካንሰር እንዴት በፍጥነት እንደሚሰራጭ ማመላከቱን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል::
በአሜሪካ የኦሪገን ጤና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በመረጃ ምንጭነት ለንባብ እንዳበቃው ህዋሳት ከዚህ ቀደም እንደሚታመነው በአንድ ቦታ የተወሰኑ አይደሉም፤ ምክንያቱ ደግሞ በውስጣቸው የሚገኝ ፈሳሽን እንደሞገድ የኃይል ምንጭ አድርገው መንቀሳቀስ ይችላሉና ነው:: ተመራማሪዎቹ በተገነዘቡት አዲስ እውነት ህዋሳት ከአንድ ጥግ ወደ ሌላው በአካል ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመጠገን እና ገንቢ ንጥረ ነገር ለማድረስም ያጓጉዛሉ::
ህዋሳት በማጓጓዝ ሂደት በ”ዲፊውዠን” ወይም ስርገት እንደሚገለገሉ ነበር የሚታመነው- በጠበብቱ:: አሁን ላይ ተመራማሪዎቹ ባደረጉት ጥልቅ ምርምር ግን የተጐዳ አካልን ለመጠገን እና የገንቢ ምግብ እንሽርሽሪትም/ዝውውርም/ ሆነ በካንሰር ከተጠቃ ህዋስ ወዳልተጠቃው የመዛመት ሂደቱ ተመሳሳይነት ሊኖረው እንደሚችል ደርሰውበታል::
የካንሰር ስርጭት በካንሰር የተጠቃ ህዋስ በውስጡ ያለ ፈሳሽን እንደ “ስፖንጅ” በሽታው ካለበት ወደ ሌለበት በመጫን ወይም በመጭመቅ መሰራጨት እንደሚችልም ነው የደረሱበት – ተመራማሪዎቹ:: በዚህም የካንሰር ስርጭት ፈጣን መሆኑን ተገንዝበዋል::
በመጨረሻም በካንሰር የተጠቃ ህዋስ ካልተጠቃው ያለውን ልዩነት በመገንዘብ የበሽታውን ስርጭት ገቶ መድሃኒት ለመሻት ስንቅ ማግኘታቸውን ተመራማሪዎቹ አስገንዝበዋል።
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሚያዚያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


