ሀያ ሰባት ኪሎ ግራም የምትመዝነው የዘጠኝ ዓመቷ ታዳጊ ከክብደቷ ሦስት እጥፍ ወይም 81 ኪሎ ግራም ክብደት ማንሳቷ፤ በአካል ተገኝተውም ሆነ በሚዲያ ተከታትለው የተመለከቷትን እንዳስደነገጠች ኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ አስነብቧል::
ሉሲ ሚልግሪም የተሰኘችው የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ አብዛኛዎቹ የእደሜ ዕኩዮቿ ጊዜያቸውን ከሞባይል ስልካቸው ጋር ሲያሳልፉ እሷ ግን በሳምንት አምስት ቀናት ክብደት በማንሳት ልምምድ ታደርጋለች። በዚህም በሃገሯ አሜሪካ በተካፈለችባቸው የክብደት ማንሳት ውድድሮች ሦስት ክብረወሰን ማስመዝገብ ችላለች::
ከሁሉም በላይ ደግሞ ባለፈው ወር ኦሃዮ በተካሄደው የአርኖልድ ስፖርት ፌስቲቫል ያስመዘገበችው ውጤት በማህበራዊ ድረ ገፆች መሰራጨቱን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል:: ከነዚህ መካከል ከፊሎቹ ታዳጊዋ ከክብደቷ አንፃር ውጤቷ አስደናቂ ቢሆንም በጤናዋ ላይ ችግር ሊያስከትልባት እንደሚችል ጠቁመዋል። በተመሳሳይ ከፊሎቹ የአካል ጥንካሬዋ እና እድሜዋ ከአነሳችው ክብደት ጋር እንደማይመጣጠን በመግለፅ ጉዳት ሊያስከትልባት እንደሚችል ስጋታቸውን አካፍለዋል::
ታዳጊዋ የክብደቷን ሦስት እጥፍ ስታነሳ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በመለቀቃቸው ውዝግብ ማስነሳቱን ድረ ገጹ በማጠቃለያት አስፍሯል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሚያዚያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


