በዘመናዊው ዓለም ሁለት ሰዎች ወይም ተቋማት አለመግባባት ሲፈጠርባቸው የመጀመሪያ ምርጫቸው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ማምራት እና የፍርድ ቤት ደጃፍ ላይ መገኘት ነው። በዚህም የተነሳ የዘመናችን ፍርድ ቤቶች በመዝገብ ብዛት የተጨናነቁ፣ ውሳኔ ለመስጠት ዓመታትን የሚፈጁ እና ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ የሚጠይቁ ሆነዋል፡፡
ይሁንና ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ባሻገር ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲጠቀሙበት የኖረ፤ ዛሬም ድረስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያልደበዘዘ ትልቅ የሰላም ግንባታ ጥበብ አላቸው፤ እርሱም የሽምግልና እና የዕርቅ ስነ-ስርዐት ነው።
ይህ ሥርዐት ጊዜንና ገንዘብን ከመቆጠብ ባለፈ የተበጠሰን ማህበራዊ ትስስር መልሶ በመጠገን ረገድ ከዘመናዊው የህግ ሥርዓት የላቀ ሚና እንዳለው በርካታ ጥናቶች ያመለክታሉ።
ዘመናዊው የሕግ ሥርዐት በአብዛኛው ያተኮረው “ቀጪ ፍትህ” (Retributive Justice) ላይ ነው። አንድ ሰው ጥፋት ሲያጠፋ ፍርድ ቤቱ የሚያተኩረው የሕጉን አንቀጽ በመጥቀስ ጥፋተኛውን በመቅጣት ላይ ነው። በፍርድ ቤት ቋንቋ “አሸናፊ” እና “ተሸናፊ” እንጂ ሁለቱም ወገኖች የሚያሸንፉበት አጋጣሚ ጠባብ ነው። ብዙ ጊዜ በፍርድ ቤት የተረታ ሰው እዳውን ቢከፍል ወይም ቅጣቱን ቢጨርስም በልቡ ውስጥ ያለው ቂም ግን አይጠፋም።
በአንጻሩ የሽምግልና ሥርዐት መሠረቱ “አስታራቂ ፍትሕ” (Restorative Justice) ነው። በታላላቅ ዛፎች (እንደ ዋርካ፣ ሾላ ወይም ዝግባ) ጥላ ስር የሚሰየመው የሽማግሌዎች ሸንጎ ትኩረቱ ጥፋተኛውን መቅጣት ላይ ሳይሆን የተበላሸውን ግንኙነት ማደስ ላይ ነው። አጥፊው ጥፋቱን አምኖ ካሳ እንዲከፍል እና ይቅርታ እንዲጠይቅ ተበዳይ ደግሞ ልቡ አርፎ ይቅር እንዲል ይደረጋል። በዚህም ምክንያት ከዕርቅ በኋላ ሁለቱም ወገኖች አብረው በልተው፣ ጠጥተው፣ ተቃቅፈው ወደ ቀድሞ ማህበራዊ ህይወታቸው ይመለሳሉ። በሃይማኖታቸው፣ በሚያምኑበት ልማድ፣ በባህላቸው መሠረት ቃል ይገባሉ። ይማማላሉ። ጥሉን ከብት አርደው በመብላት መስዋእት ያደርጋሉ። ጠብመንጃቸውን አጋድመው ይራመዱታል።
ዶክተር ታረቀኝ አደቦ በኢትዮጵያ ጥናቶች ማዕከል ባሳተሙት “One Hundred Years of Conflict in the Horn of Africa” የሚል ርዕስ በሰጡት መጽሐፍ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሽምግልና ሥርዐት የዳበረ እና ተቋማዊ ይዘት ያለው ነው። የተለያዩ ብሄረሰቦች የየራሳቸው የሆነ ጥልቅ የዕርቅ እና የፍትሕ ሥርዓት አላቸው።
በኢትዮጵያ ሕግ ታሪክ ውስጥ የባህላዊ የፍትሕ ስርዐት ቦታው የላቀ ነው። ሕግ በዋናነት ከህዝብ የሚመነጭ እንጂ ከመንግሥት የሚፈጠር አይደለም። ባህላዊ የፍትሕ ስርዐት በኢትዮጵያ አጠቃላይ በሆነ መልኩ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኝ ቢሆንም፣ በተግባር ግን በእያንዳንዱ ብሔረሰብ አካባቢ የተገደበ ነው። እነዚህ ስርዓቶች ግለሰቦች እርስ በርስ በሚተዋወቁባቸው ማህበረሰቦች ውስጥ መተማመንን መሰረት አድርገው ለዕለታዊ ሰላም መከበር የማይተኩ ሚና ይጫወታሉ።
ይህ መጽሐፍ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ግጭትን በማርገብ ፍትሕ የሚያሰፍኑባቸውን ስርዐቶች በዝርዝር አቅርቧል።
በአማራ ክልል የግጭት አፈታት አራት እርስ በርስ የሚተሳሰሩ ተቋማትን የያዘ ነው። አንደኛው መደበኛ ያልሆነ የሽማግሌዎች ጉባኤ፣ ሁለተኛው ሃይማኖታዊ መሪዎች (ኦርቶዶክስ ክርስቲያን፣ ሙስሊም እና የአካባቢ መንፈሳዊ መሪዎች)፣ሦስተኛው ሌቦችን ለማግኘት የሚደረጉ የህዝብ መሰብሰቢያዎች እና ሌባ ፈላጊዎች፣ እና አራተኛው እንደ ዕድር፣ የብድር እና የቁጠባ ማህበራት ያሉ፣ በአባላት መካከል የሚፈጠር ግጭትን የሚፈቱ ማህበራትን ያካተተ ነው።
በአማራ ክልል በአካባቢ ደረጃ የሚፈጠር ግጭትን ለመፍታት በጣም የተለመደው መንገድ “ሽማግሌዎች” የሚባሉት ናቸው፤ እነዚህም በሽምግልና ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። “ሽማግሌ” የሚለው ቃል ዕድሜን ብቻ ሳይሆን “አስታራቂ” የሚል ትርጉምም አለው። የሽምግልና ሂደት በራሱ “ሽምግልና” ይባላል። ወገኖቹ በውሳኔው ካልተስማሙ ጉዳዩን ወደ መደበኛው መዋቅር፣ ቀደም ሲል ወደ “ጭቃ ሹም” አሁን ደግሞ ወደ ወረዳ ወይም ዞን ፍርድ ቤት ሊወስዱት ይችላሉ፤ ይህም የገንዘብ ወጪን ይጨምራል።
ሽማግሌዎች የሁለቱንም ወገን ክርክር ካዳመጡ በኋላ ማስረጃውን ለመመርመር እና በአንድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ይወያያሉ። አንዳንድ ግጭቶች “ካሳ” ወይም “እርቅ” ይፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ “ይቅር ለእግዚአብሔር” በሚል ይፈታሉ።
የሃይማኖታዊ መሪዎች (ኦርቶዶክስ እና ሙስሊም) ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። በአብዛኛው የኦርቶዶክስ አካባቢዎች ካህናት እና በተለይም “የንስሃ አባት” በግጭት አፈታት ውስጥ ወሳኝ ናቸው። በደቡብ ወሎ “አበጋር” ወይም “ደም አድርቅ” የሚባሉት የባህላዊ ሃይማኖት መሪዎች በደም መፋሰስ (ግድያ) ጉዳዮች ላይ ትልቅ ሚና አላቸው።
የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ግጭትን በማርገብ ረገድ ትልቅ ታሪክ እና ሚና ያለው ነው። በገዳ ሥርዓት ውስጥ “ጃርሱማ” (ሽምግልና) ትልቅ ስፍራ አለው። ግጭት ሲፈጠር የሀገር ሽማግሌዎች (አባ ገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች) በ”ኦዳ” ዛፍ ስር በመቀመጥ ሰላም ያወርዳሉ። በ2016 (እ.ኤ.አ) በዩኔስኮ (UNESCO) የዓለም የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው ይህ ሥርዐት ከግለሰብ እስከ ጎሳ ግጭቶችን የመፍታት አቅም አለው።
የጉራጌ ብሔረሰብ የ”ያጆካ ቂጫ” የሚባል ሥርዐት አለው። ይህ የጉራጌ ብሔረሰብ ለዘመናት ሲተዳደርበት የቆየው የፍትሕ ሥርዐት ሲሆን ሽማግሌዎች ተሰብስበው ሕግ የሚያወጡበትና የተጣላን የሚያስታርቁበት ጥብቅ እና የተከበረ ባህላዊ ፍርድ ቤት ነው።
የሲዳማው ብሔረሰብ “ሉዋ” እና የሶማሌ ደግሞ “ኦዳየል” የሚባሉ ሥርዐቶች አሏቸው። እነዚህም በተመሳሳይ በዕድሜ፣ በልምድ እና በስነ-ምግባር በታነፁ የሀገር ሽማግሌዎች የሚመሩ የደም ካሳን ሳይቀር በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ጥበብ ያላቸው ሥርዓቶች ናቸው።
በእነዚህ ሁሉ ሥርዓቶች ውስጥ ሽማግሌዎቹ የሚመረጡት በሀብታቸው ሳይሆን በዕውቀታቸው፣ በታማኝነታቸው፣ አንደበተ ርቱዕነታቸው እና ሚስጥር ጠባቂነታቸው ነው።
የሃገር በቀል የዕርቅ ሥርዐቶችን ጠቀሜታ ዘመናዊው ሕግም አልካደውም። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዲ.ሪ) ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ 34 (5) እና በአንቀጽ 78 (5) ላይ የሃይማኖት እና የባህል ፍርድ ቤቶች በግለሰቦች ፈቃድ ላይ ተመስርተው የቤተሰብ እና የግል ጉዳዮችን ዳኝነት ሊሰጡ እንደሚችሉ እውቅና ሰጥቷል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕግ እና በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ውስጥ “የግልግል ዳኝነት” እና “ዕርቅ” ህጋዊ ተቀባይነት ያላቸው አማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶች ሆነው ተደንግገዋል፡፡
በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በመንግሥት ፍርድ ቤቶች የሚታዩ በርካታ ከባድ የወንጀል (የግድያ ጭምር) ጉዳዮች በሕግ አግባብ ቅጣት ከተሰጠባቸው በኋላም ቢሆን ማህበራዊ ሰላሙን በዘላቂነት ለማምጣት የባህል ሽማግሌዎች ጣልቃ ገብነት ወሳኝ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ሕጉ ገዳይን ቢቀጣም የሟች ቤተሰብ በቀልን እንዲተው የሚያደርገው ግን የሽማግሌው የዕርቅ ዛፍ ስር መማፀን ነው ይላሉ የሶሺዮሎጂ ምሁራን።
ባለንበት ዘመን የከተሞች መስፋፋት፣ የዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት እና የምዕራባውያን ባህል ተጽዕኖ የሽምግልናን ሥርዐት እየተፈታተነው ይገኛል። ይሁንና ዘመናዊው የፍርድ ቤት ሥርዐት ብቻውን የአንድን ሀገር ሰላም እና ማህበራዊ ደህንነት ሊያረጋግጥ እንደማይችል በግልፅ እየታየ ነው።
ሃገር በቀል ዕውቀቶቻችንን ወደ ኋላ እንደቀረ አስተሳሰብ መቁጠራችንን አቁመን ከዘመናዊው የህግ ሥርዐት ጋር አናቦና አጠናክሮ ማስቀጠል የዘመኑ ትውልድ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል። ግጭቶች ሲፈጠሩ ፖሊስና ፍርድ ቤት ከመሮጥ በፊት “እስኪ በሽማግሌ እንየው” የሚለው ኢትዮጵያዊ ብሂል ዛሬም ቢሆን የህብረተሰባችንን ጤናማነት የሚጠብቅ ትልቅ መድኀኒት ነው።
እውነተኛ ሰላም የሚገነባው በወረቀት ላይ በሚሰጥ የፍርድ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን በዛፍ ጥላ ስር፣ በእንባ፣ በይቅርታ፣ በምርቃት እና በልብ መታደስ ውስጥ ነው!
ማረፊያ
የወንዝን ጥልቀት በሁለቱም እግሮችህ አትለካው፡፡ (የጋናዊያን አባባል)
- ብልህ ሰው አንዲት ቃል ሰምቶ ሁለት ነገር ይረዳል፡፡ (የናይጄሪያ አባባል)
- ትኩስ ሾርባን በችኮላ አይጠጡም፤ እያቀዘቀዙ እንጂ፡፡ (የማሊ / የሴኔጋል አባባል)
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


