“ተንቀሳቃሿ የአፍሪካ ጉዳዮች ኢንሳይክሎፒዲያ”

0
97

የሙያ አጋሮቻቸው ሁሉ “ተንቀሳቃሿ የአፍሪካ ጉዳዮች ኢንሳይክሎፒዲያ (The Walking Encyclopedia of African Affairs)” ብለው ይጠሯቸዋል። ለ52 ዓመት ከ10 ወራት  የኖሩበት የዲፕሎማሲው ዓለም ደግሞ “ባለረጅም ዘመን አገልግሎቷ አፍሪካዊት ዲፕሎማት” አሰኝቷቸዋል – አምባሳር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስን::

የኒውስ ኔት መረጃ እንደሚያሳየው አምባሳር ቆንጂት በ1932 ዓ.ም ሐረር ከተማ  ተወለዱ። አስተዳደጋቸው በራስ የመተማመን እና የነፃነት ስሜት እንዲኖራቸው ዕድል ሰጥቷቸዋል። ለዚህም የቤተሰቦቻቸው ድርሻ የጎላ ነበር። በተለይ ታላቅ ወንድማቸው እንደ ታላቅነታቸው በእንቅስቃሴዎቻቸው  ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረግ ይልቅ ነፃነትን ከኃላፊነት ጋር ይሰጧቸው ነበር:: ይህም ወንድማቸው የጣሉባቸውን እምነት እንዲያከብሩ፣ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እንዲያስቡ፣ ውሳኔዎችን ራሳቸው እንዲወስኑ ፣ በሌሎች ላይ ጥገኛ እንዳይሆኑና በኃላፊነት ስሜት እንዲንቀሳቀሱ አስቻላቸው።  የአስተዳደጋቸው አጋጣሚም ከሕይወት ቁም ነገሮች መካከል አንዱ ለራስ ክብር መስጠት መሆኑንና ይህንንም ለማሳካት ታማኝና ሐቀኛ መሆን እንደሚያስፈልግ አስተምሯቸዋል።

አምባሳር ቆንጂት የአንደኛ እና  የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐረር ከተማ ካጠናቀቁ በኋላ ከእህታቸው  ጋር ወደ  እንግሊዝ አቀኑ:: በዛም የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ለማጥናት ለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገቡ። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንም በዚሁ የትምህርት መስክ አጠናቀቁ። ዓለም አቀፍ ግንኙነት እያጠኑ በነበሩበት ጊዜ ስለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (United Nations) የተጻፉ መጻሕፍትን ያነቡ ነበር። ይህም ስለድርጅቱ አደረጃጀት፣ አሠራርና ተግባራት በጥልቀት የማወቅ ጉጉት አሳደረባቸው። በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያን ወክሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑክ ውስጥ የማገልገል ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችል በተሰጣቸው ምክር መሠረት ለውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር ማመልከቻ አስገቡ።

በወቅቱ የሥራ ምደባ ወደ ሚካሄድበት ቢሮ በማቅናት የተማሩት ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስለሆነ መሥራት የሚፈልጉት በውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር ውስጥ እንደሆነ ተናገሩ። ማመልከቻዋን ያቀረቡላቸው የሥራ ኃላፊ ግን “እሱ ለሴት የሚሆን ቦታ አይደለም” የሚል ምላሽ ሰጧቸው። አምባሳደሯ በተሰጣቸው ምላሽ ቢደነግጡም የግድ የውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር መግባት እንዳለባቸው ወስነዋል። ምላሹ እንደተለመደው ቢሆንም እርሳቸው ግን በየቀኑ ወደ ሚኒሥቴሩ እየሄዱ ይቀመጡ ነበር። ከዚያም “ይቺ ልጅ አልለቀቀችንም፤ ደብዳቤ ተጽፎላት ትግባ” ተብሎ ተፈቀደላቸው:: በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት ከመመሥረቱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በ1954 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴርን ለመቀላቀል በቅተዋል።

አምባሳደር ታደለች ኃ/ሚካኤል ለቢቢሲ  እንዳሉት  አምባሳደር ቆንጂት አምባሳደር ለመሆን ረዥም ዓመታት መጠበቅ  ግድ ነበር:: ከተቀጠሩም በኋላ ቢሆን ሴት በመሆናቸው ብቻ በሥራው ለማስቀጠልም ሆነ አምባሳደር አድርጎ ለመሾም “ወጣት ናት፤ ልጅ ናት፤ ሴት ናት ደግሞ አግብታ አርግዛ” በሚሉ ሰበቦች” ምናልባት ውጭ ጉዳይ ከተቀጠሩ ሰዎች ወደ አምባሳደር ደረጃ ለመድረስ እጅግ ብዙ ጊዜ የወሰደባቸው እርሳቸው ሊሆኑ ይችላሉ” ሲሉ ነው የገለፁት።

አምባሳደር ቆንጂት ግን በመጀመሪያ ቅጥራቸው የተመደቡት በሚኒሥቴሩ የተባበሩት መንግሥታት ክፍል ውስጥ ነበር። ከሦስት ዓመታት በኋላ ዕድገት አግኝተው በሁለተኛ ፀሐፊ ማዕረግ ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ልዑክ ጽሕፈት ቤት ውስጥ እንዲሠሩ ተመደቡ። አምባሳደሯ ግን መሥራት የሚፈልጉት ዋና የዲፕሎማሲ ሥራ እንጂ በአስተዳደር ሥራዎች ላይ ባለመሆኑ ሕልማቸውን ለማሳካት ጥረታቸውን ቀጠሉ። በዚህም በመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ ቡድን ውስጥ የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ጉዳዮች ኦፊሰር ሆነው መሥራት ጀመሩ።

ከአምስት ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ለ10 ዓመታት ያህል በውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ገለልተኛ ሀገራት መምሪያ ውስጥ ሠርተዋል። በመቀጠልም በ1970ዎቹ ስዊዘርላንድ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ ልዑክ ምክትል ተወካይ በመሆን ለአስር ዓመታት አገልግለዋል። ከ28 ዓመታት አጠቃላይ የዲፕሎማሲ አገልግሎት በኋላ እዚያው ጀኔቫ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ እና በኦስትሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ።

በመቀጠልም ከመጋቢት 1984 ዓ.ም ጀምሮ በካናዳ፣ በሜክሲኮና በእሥራኤል የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እስከ ነሐሴ 1987 ዓ.ም ድረስ ሠርተዋል። ወዲያውኑ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እንዲሠሩ ተሾሙ።

ከአንድ ዓመት በኋላ በግብጽ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ተሹመው ከአራት ዓመታት በላይ አገልግለዋል። ከዚህ በኋላ ወደ አዲስ አባባ ተመልሰው ለሁለተኛ ጊዜ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና በውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር ውስጥ የአፍሪካ ጉዳዮች ጄነራል ዳይሬክተር ሆነው በመሾም አገልግለዋል::

በ1998 ዓ.ም በኦስትሪያ ፌዴራል ሪፐብሊክና በቪየና በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እንዲሠሩ በድጋሚ ተሾሙ። ከመስከረም ወር 2002 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በክብር በጡረታ እስከተሰናበቱበት ድረስ በአፍሪካ ሕብረት (African Union) እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሀገራቸውን በትጋት አገልግለዋል። በኋላ ደግሞ  ከሰኔ 2009 እስከ መስከረም 2011 ዓ.ም ደግሞ ኢጋድ በመራው  የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ላይ ልዩ አማካሪ እንደነበሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል::

አምባሳደር ቆንጂት በአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በነበሩበት ወቅት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተቋማዊ ለውጥ እንዲያመጣና አወቃቀሩም የተቋሙን ዓላማዎች በሚያሳካ መልኩ ወደ የአፍሪካ ሕብረት እንዲለወጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

አምባሳደር ቆንጂት በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥለው የሀገሪቱ ሁለተኛዋ ሴት አምባሳደር በመሆን ሀገራቸውን ያገለገሉ እንደሆኑ ለቢቢሲ የገልፁት ደግሞ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ናቸው::

በኦቶዋ ካናዳ ኢትዮጵያ ኢምባሲ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር ዋናው መሥሪያ ቤት በአፍሪካ እና በሌሎች ክፍሎች ውስጥ በጋራ መሥራታቸውን ያስታወሱት አምባሳደር ዲና፤ “የማስታውሳቸው ለሀገራቸው ባላቸው ከፍተኛ ፍቅር ነው” ይላሉ።  “የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት ጀምሮ የነበረውን የዲፕሎማሲ ሂደት ያውቃሉ” ያሉት አምባሳደር ታደለች፤ “እንደ ወጣት ዲፕሎማት ምን ይደረግ እንደ ነበር፤ ውሳኔዎች ለምሳሌ ከሀገራት ዕይታ ውጪ እንዴት ገብተው ሊያልፉ እንደሚችሉ በጣም ማየት ይችላሉ” ሲሉ መስክረውላቸዋል::

በአፍሪካ አንድነት ውስጥ ሲሠሩ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች የድርጅቱ መቀመጫ ከአዲስ አበባ መውጣት አለበት በሚሉበት ወቅት “ሀገር በደከመበት ሰዓት እንዴት ነገሮች ሊያልፉ እንደሚችሉ ስለሚያውቁ ነቅተው የሚጠብቁ ʽቆቅ’ ነበሩ ማለት ይቻላል” በማለትም የነበራቸውን አስተዋጽኦ ገልጸዋል።

“አምባሳደር ቆንጂት በጣም ጥንቁቅ ናቸው። ከመጠን በላይ ጥንቁቅ ናቸው” ያሉት አምባሳደር ታደለች፤ ይህ ከእርሳቸው የሚያስታውሱላቸው ነገር መሆኑን ተናግረዋል:: የእሳቸው አርዓያነት ለቀጣዩ የአፍሪካ ዲፕሎማቶች በተለይም ለሴቶች በድፍረት፣ በልዩነት እና በዓላማ እንዲያገለግሉ መነሳሳትን እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል::

“ወጣት ዲፕሎማቶች ከአምባሳደር ቆንጂት በቅድሚያ መማር ያለባቸው መንግሥትን እና ሀገርን መለየት መቻል  ነው:: የሀገርን ጥቅም ማዕከል አድርጎ መሥራት ከእርሳቸው መማር የሚገባ መሆኑን የሚናገሩት አምባሳደር ታደለች፤ ምንጊዜም ከመንግሥት ጥቅም ይልቅ የሀገር ጥቅም መቅደም እንዳለበት ከእርሳቸው መማር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

አምባሳደር ቆንጂት ለዘመናት ማኅበረሰቡ ውስጥ የኖረውን የሴቶች ዕድል መነፈግ በመስበር ወደ ፊት በመውጣት ለሴቶች ዓርዓያ መሆናቸውን ደግሞ  አምባሳደር ዲና መስክረዋል::  “አሁን እየተተገበረ ላለው የፆታ እኩልነት የእርሳቸው ሚና ከፍተኛ ነው።

አምባሳደር ቆንጂት ስለ ዲፕሎማሲ ሥነምግባር፣ ስለ ፕሮቶኮል . . . ከአለባበስ፣ ከአነጋገር፣ ከአካሄድ ጀምሮ ምን መደረግ እንዳለበት ጠንቅቀው የሚያውቁትን ለእያንዳንዱ ዲፕሎማት ለማስገንዘብ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር። “ትልቅ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት. . . ትልቅ የክፍለ ዘመኑ ዲፕሎማት” በማለትም  አምባሳደር ታደለች አወድሰዋቸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሕሙድ ዓሊ ዩሱፍ ባስተላለፉት የሐዘን መግለጫ መልዕክት ላይ “አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ በታማኝነት፣ በልዩ ብቃት እና ለጋራ የወደፊት ዕጣ ፈንታችን ባላቸው የማይናወጥ ቁርጠኝነት የታወቁ፣ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ዕሴቶች መገለጫ ነበሩ” ብለዋቸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

አምባሳደሯ  ለዚህ ሁሉ  ስኬት የበቁት ግን በቀላሉ አልነበረም። “ለሴት የሚሆን ሥራ አይደለም” ከሚለው አስደንጋጭ እሳቤ ጀምሮ ሙሉ የሕይወት ጊዜን ለሙያ  በመስጠት የደረሱ ፈተናዎችንም  ተቋቁመው በማለፍ እንደሆነ መረጃዎች ጠቁመዋል::።

አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ ለሀገራቸው በሰጡት አገልግሎትም ከጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አህመድ  የዕውቅና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። በተመሳሳይ በዲፕሎማሲው መስክ ለሀገራቸው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተበርክቶላቸዋል::

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሚያዚያ 12  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here