ቾቤ ብሔራዊ ፓርክ

0
21

ቾቤ ብሔራዊ ፓርክ በ1967 እ.አ.አ የተመሰረተ ለቦትሱዋና የመጀመሪያው ፓርክ ነው:: የፓርኩ ስፋት 11 ሺህ 700 ስኩዌር ኪሎ ሜተር ተለክቷል:: ቾቤ የሚለው መጠሪያው የፓርኩን ሰሜናዊ ድንበር የሚያካልለውን የቾቤ ወንዝን ስም መነሻ ያደረገ ነው::

የቾቤ ብሔራዊ ፓርክ መገኛ በመልካ ምድራዊ አቀማመጡ የተለያዩ ስነ ምህዳሮችን ያካተተ ነው:: ለአብነትም ደን ለበስ፣ የቁጥቋጦ እና ሳር ምድር፣ የቾቤ ወንዝ ዳርቻ እና ደለል የተኛባቸው ሜዳዎች ይጠቀሳሉ::

በፓርኩ ከሚገኙ የዱር እንስሳት የአህጉሪቱን አንድ ሦስተኛ የሚገመቱትን ከ120 ሺህ በላይ ዝሆኖችን መያዙ በቀዳሚነት የፓርኩ መለያ መሆኑን ድረ ገፆች አስነብበዋል:: በተጨማሪም በአካል ግዝፈት አንበሳ፣ አቦሸማኔ፣ ጐሽ፣ አውራሪስ መገኘታቸው ተረጋግጧል::

ከአእዋፍ 560 ዝርያዎች የሚገኙበት ሲሆን ሽመላ፣ ዝይ፣  “ኪንግፊሽር” የመሳሰሉትን ጨምሮ እንደየወቅቶቹ ወደ ሰሜን አፍሪካ እና አውሮፓ የሚፈልሱ ዝርያዎች መኖራቸውም ነው በድረ ገፆች የተጠቆመው::

ቾቤ በደቡብ አፍሪካ ቀጣና በዚምባቡዌ፣ ዛምቢያ እና ናሚቢያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን  ለፓርኩ በቅርበት የምትገኝ ከተማ ካሳኔ (kasane) ትሰኛለች:: በከተማዋ የእንግዶች ማረፊያ “ሎጂ” እና የድንኳን መጠለያዎች ይገኛሉ፤ ምግብ እና መጠጥም እንዲሁ::

የቾቤ ብሔራዊ ፓርክ መገኛ ቀጣና ለወባ መራቢያ የተመቸ በመሆኑ ጐብኚዎችን ከትንኝ ንክሻ መከላከያ መያዝ በውሎ አዳራቸው ምቹ አልባሳት እና አጐበር መገልገል ግድ ይላቸዋል::

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት- ቦትስዋና ቱሪዝም፣ ቾቤ ናሽናል ፓርክ፣ ቾቤ ዶት ኮም እና ቱር ራዳር ድረገፆችን ተጠቅመናል::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here