ለማሕበራዊ ትስስር ማጠናከሪያ

0
114

ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓቶች በማህበረሰብ እምነትና ሥነ-ልቦና ላይ የተመሰረቱ፣ ግጭቶችን በሽምግልና በመፍታት ዘላቂ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነትን የሚያሰፍኑ ማህበራዊ ተቋማት ናቸው። በደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ የፎክሎር ባሕል ጥናት መምህር እና ተመራማሪ  ተባባሪ ፕሮፌሰር መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር) እንደሚገልፁት ሀገር በቀል እውቀቶች ማህበረሰቡ ለረጅም ዘመናት በቃል ቅብብሎሽ ሲጠቀምባቸው የኖሩ እና ዛሬም ድረስ የዘለቁ  ዕሴቶቹ ናቸው::

እንደ  ተመራማሪው ማብራሪያ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ማለት በአንድ  ማሕበረሰብ ውሥጥ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ፣ሃሳቦችን ወይም ወንጀሎችን በማህበረሰብ ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ወይም ታዋቂ እና ክብር በሚሰጣቸው ሰዎች አማካኝነት በእርቅ እና በስምምነት የመፍታት ሂደት ነው:: ይህ ሂደት ታዲያ ትኩረቱ ጥፋተኛውን  መቅጣት ሳይሆን የተበላሸውን ማህበራዊ ግንኙነት መጠገን እና ተበዳይ እና በዳይን በማቀራረብ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው::

የባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት የራሱ የሆኑ መገለጫዎች አሉት ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር)፤ ከነዚህም አሳታፊነት አንዱ ነው:: አሳታፊነት ሲባል የማህበረሰቡ አባላት በዳይ እና ተበዳይ ዘመዶች በሂደቱ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲያደርጉ የሚጋብዝበት ሥርዓት ነው::

ሌላው ተደራሽነት እና ተለዋዋጭነት ነው:: ይህም እንደ ዘመናዊ ፍትሕ ሥርዓት ጥብቅ ስርዓት ስለሌለው በቦታ እና በጊዜ እንደ ማይገደብ ዶ/ር መስፍን ፈቃዴ ጠቁመዋል::

የባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በእሴቶች ላይ የተመሠረተ ነው፣ ይህም ስንል ውሳኔዎች የሚወሰኑት ከማሕበረሰቡ እምነት፣ ባህል እና ሞራል የመነጨ ነው::

ሌላው የባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት  የእርቅ ትኩረት አለው:: በዚህም አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ሳይሆን ሁለቱም አሸናፊ የሚሆኑበትን ሰላም መፍጠር፤ ሁለቱም ወደ ቀደመ ግንኙነታቸው እንዲመጡ  ማድረግ ነው:: የእርቅ ሥነ ሥርዓቱ ጠበቃ እና የፍርድ ቤት ክፍያ አይጠይቅም፤  እዛው በዛው ገንዘብንም ጊዜንም ቆጥቦ ይጠናቀቃል::

መምህር እና ተመራማሪው እንደ ግለሰብ ባደረጉት ጥናት በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሰዴ አካባቢ ባህላዊ የግጭት አፈታት አንድ ሰው ነፍስ የማጥፋት ወንጀል ከፈፀመ በአካባቢው ሽማግሌ ”አንተ ጥፋተኛ ነህ:: ብር ካሳ ትክሳለህ” ብሎ ከፈረደበት መክፈል ቢችልም እንኳን በራሱ እንዲከፍል ወይም ዘመድ እንዲከፍልለት አይደረግም:: አንድ አኮፋዳ ይሰጠውና  በየሰፈሩ እየዞረ ብሩ እስኪሞላ ይለምናል:: ይሄም የሰው ፊት ምን ያህል ከባድ እንደሆነና በሄደበት ሁሉ በደሉን እንዲናገር ሲገደድ ድጋሚ ሰው ፊት ላለመቆም ወንጀሉን እንዳይደጋግም ይረዳል::

ሕግ  በመጣስ ወንጀል  ከደገመ ግን ሀገር ሁሉ ያገለዋል:: ግለሰቡ ማሕበራዊ ግንኙነቱን ለመጠበቅ ከወንጀል ተጠብቆ ይኖራል:: በደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ አዲስ አለማየሁ ጥናት ተቋም ምስራቅ ጎጃም ደባይ ጥላት ግን ወረዳ ለበርካታ ዘመናት በደም ከአካባቢው ሰዎች በመራቃቸው ቤተሰብ ተበትኖ፣ ልጆች አላሳዳጊ ቀርተው ፣ከትምህርት ርቀው እና የእረርሻ ማሳዎች ሳይታረሱ በመቅረታቸው በሀገሩ ባሕል እና ወግ መሠረት ፣በፍትሕ አካላት ፣ የሃይማኖት አባቶች ጭምር የተሳተፉበት የማስታረቅ ሥራ ተሠርቶ የካሳ ሥርዓት ተከናውኖ  ዘላቂ ሰላም ሰፍኗል::

ባሕላዊ የግጭት አፈታት ለማህበረሰቡ ያለው አስተዋፅኦ

  • ማህበራዊ ትስስርን ያጠናክራል

ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ ተቀያይመው የነበሩ ወገኖች በዳይ እና ተበዳይ አብረው እንዲኖሩ እና እንዲገባበዙ ያደርጋል:: በዘመናዊ ፍትሕ ሥርዓት  ማስረጃን መሰረት ተደርጎ ሲወሰን ”ተፈረደልኝ፣ ተፈረደብኝ” ነው ሚባለው:: በባህላዊ እርቅ ግን ሁለቱም አሸናፊዎች በበመሆናቸው ወደ ነበረው ማህበራዊ፣ እምነት፣ እና ባህላዊ  ግንኙነት አብረው ለመከወን ያስችላቸዋል::

  • የፍርድ ቤቶችን ጫና ይቀንሳል

ቀላል እና መካከለኛ ግጭቶች በባህሉ ስለሚፈቱ የመንግስት የሥራ ጫና ይቀንሳል፣ የእርሻ ሥራና ሌሎችን ተግባር በፍርድ ቤት ምልልስ ከማቃጠል፣ ጉልበት እና ጊዜንም በአካቢው በማሥማማት ይቀንስበታል::

  • ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ሚናው የጎላ ነው በፍቃደኝነት እና በይቅርታ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ቂም በቀል እንዳይቀጥል ይረዳል:: በዘመናዊ ፍትሕ ቂም አርግዘው ታራሚው በአመክሮ ከእስር ሲወጣ ለመበቀል ይሄዳሉ:: በባህላዊ እርቅ ግን ሽማግሌዎች ተበዳይን “ሀገር ይጫንህ ወይስ ድንጋይ ይጫንህ” ተብሎ ሲጠየቅ ”አይ ድንጋይ ይጫነኝ ምክንያቱም ሀገር ተባብሮ ያነሳልኛል ፣ሀገር ከተጫነኝ ማን ያነሳልኛል” ብሎ እርቁን  ይቀበላል::
  • ፍትሕ ማስፈኑ

መደበኛ ፍርድ ቤት  በማይደርስባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች እንደ መደበኛ የፍትሕ ሥርዓት በመሆን/አማራጭ የፍትሕ ሥርዓት/ ያገለግላል::

ከዘመናዊ ፍትሕ ሥርዓት ጋር ያለው ትስስር

የኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ሕግ አንዳንድ ጉዳዮችን በሽምግልና እንዲያልቁ መንገድ ይከፍታል:: ውሳኔን በማፅናት በኩል በሽምግልና የተወሰኑ ውሳኔዎች፣ ስምምነት በፍርድ ቤት ተመዝግበው ሕጋዊ ተፈፃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል::

በሌላ በኩል ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት ባህላዊውን ሲያከብር በማሕበረሰቡ ዘንድ የባለቤትንት መንፈስ ስላለ ፍትሕ ሥርዓቱን እንዲቀበለው ፣እዲያከብር ያደርጋል::

ልዩነታቸው

ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት በጽሑፍ ፣በሥርዓት ላይ ሲያተኩር የባሕል ሥርዓት ግን በቃል ትውፊቶች በካሳ ላይ ትኩረት ያደርጋል::

በባሕላዊ አሸናፊና ተሸናፊ ሳይኖር ይቅር ተባብለው ማህበራዊ ግንኙነት መመለስ መቻሉ::

በሽምግልና ሂደት ላይ ያለው የማህበረሰቡ ባህላዊ ጉዳዮች የራሳቸው መገለጫ /ትዕምርታዊ ፋይዳ/ ምልክት ያላቸው ናቸው:: ማህበረሰቡ ለዘመናት በቃል ሲቀባበላቸው የኖሩ ናቸው፣ ለምሳሌ እርጥብ ሳር በአብዛኛው ብሔረሰብ  በአማራ በኦሮሞ ብሔረሰብ፣ በኦሮምያ ክልል…  የሰላም፣የለምለምነት እና የሕይወት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፤ ግጭቱ ድርቅ እንዳያስከትል  ሲታሰብ እርጥብ ሳሩ ሰላም ይውረድ ይለምልም የሚል መልክት አለው:: አንዳንዴ ደግሞ ወይራ ጥንካሬ እና ፅናትን ስለሚወክል የወይራ ዝንጣፊን ይይዛሉ::

ሌላው ነጭ ልብስ ሲለበስ የልብ ንጽህና ፣ቂም መታጠብን እና ግልፅነትን ይወክላል:: የእንስሳት መስዋትነት እና ደም ማፍሰስ ደግሞ በትልልቅ ነፍስ ማጥፋት ወንጀሎች ላይ እንሰት ታርዶ ደም ሲፈስ የሰው ደም መፍሰስ ማብቃቱን እና የበቀል ሂደት መቆምን ያሳያል:: በመጨረሻ በጋራ ሲበላ ደግሞ ሁለቱ ወገኖች በመካከላችን ክፋት የለም ብሎ ቃል መግባት ነው::

የተምሳሌታዊ ድርጊቶችም አሉ፤ ማጎንበስ ወይም እግር መሳም የተበዳይን ክብር መልሶ የመገንባ ሂደት እና የበዳይን ትሕትና የማሳየት፣እራስን ዝቅ አድርጎ ይቅርታ የመጠየቅ ሂደት ተደርጎ ይወሰዳል:: እጅ ሲጨባበጡ እና ሲተቃቀፉ ደግሞ በሰዎች መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ ማፍረስ ነው:: የነበረውን መርገም እና መመረቅ ደግሞ እንደ ሃይማኖት እና ባህላዊ ሂደት የማጽናት አንደምታ  እንዳለው መምህር እና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር) ገልፀዋል::

ዘመናዊ ሥርዓት ከባሕላዊ ስለሚነሳ ሥርዓቶቹን በሚገባ እውቅና ሰጥቶ ፣ቦታ አመቻችቶ ፣በካሪክለም አስገብቶ ለልጆች ማስተማር ማሳደግ እና ማጠንከር ይገባል:: የሕግ ድጋ ይፈልጋል ፤ ለምሳሌ የገዳ ሥርዓት በኦሮሚያ አካባቢ እንደ አንድ አማራጭ የፍትሕ ሥርዓት ገብቷል::

ባሕላዊ እርቅ ሥርዓቶች ጊዜን ፣ገንዘብን ቆጥበው ዘላቂ ሰላምን ያሰፍናሉ ችግርን ወደ ነበረው ሁኔታ የመመለስ ሥርዓት ስለሆነ መጠበቅ ግድ ይላል::፡፡

መረጃ

ዋና ዋና ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓቶች መገለጫዎች:

  • ማኅበራዊ እሴት እና የፍትሕ ሚና: ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ከመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ጎን ለጎን ፍትሕን በማስፈን፣ ሴቶችን፣ ሕፃናትንና አቅመ ደካሞችን በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው።
  • የዳኝነቱ ሥርዓት: በአካባቢው ሽማግሌዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እና የሃይማኖት አባቶች አማካኝነት የግጭት መንስኤን በመመርመር፣ ጥፋተኛውን በማረም እና የተበደለውን በማካካስ እርቅ ይፈጸማል።
  • የማስታረቅ ሂደቱ: እንደየባሕሉ ይለያያል፣ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ የይቅርታ በግ መታረድ፣ የሽማግሌዎች መማለድ፣ እና የቤተሰብ /ማኅበረሰብ መታረቅን ያካትታል። እነዚህ ሥርዓቶች በአሁኑ ወቅት የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ አካል በመሆን፣ ጎጂ ልማዶችን በመቀነስ እና የአካባቢ ሰላም ደኅንነትን በማረጋገጥ ረገድ በሕግ እውቅና ተሰጥቷቸው እየሠሩ ይገኛሉ።

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሚያዚያ  12  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here