“የመራጭነት ካርድ የሰላም መታወቂያ ነው”   – የምርጫ ተመዝጋቢዎች

0
83

በኢፌዴሪ ሕገ – መንግሥት አንቀፅ 38 ላይ ዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብት ተደንግጓል፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር፣ በፆታ፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ወይም አቋም ላይ የተመሠረተ ልዩነት ሳይደረግበት የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳለው ደግሞ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ያረጋግጣል፡፡ ይህ ደግሞ የምርጫ ሂደት ግልጽነት፣ ታማኝነትና የሕዝብ እምነት በዴሞክራሲ ልማት ውስጥ ዋና ሚና እንደሚጫዎት አመላካች ነው።

ዓለም አቀፉ የምርጫ ሥርዓት እና ዲሞክራሲ ሪፖርት እንደሚያሳየው ግልጽነት፣ የሕግ ታማኝነት፣ ነፃነት እና የሕዝብ ንቁ ተሳትፎ የስኬታማ ምርጫ አመላካቾች ናቸው። እንደ ኖርዌይና ስዊድን ያሉ ሀገራት ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ያላቸው ሲሆን፣ ይህም በመንግሥታቸው ላይ የተገነባ እምነትን ያመለክታል።

በሌላ በኩል እንደ ካናዳና ጀርመን ያሉ ሀገራት የተደራጀ እና በሕግ የተጠበቀ የምርጫ ሂደት ያላቸው ናቸው። ነፃና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ መኖሩ በምርጫ ውጤት ላይ ከፍተኛ እምነት እንዲፈጠር ያግዛል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም እኩል ዕድል በማግኘታቸው ፍትሃዊ ውድድር ይኖራል።

የሀገራቱ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ምርጫ በአንድ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሥርዓት ውስጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ነው። ከሥልጣን ሽግግር ባለፈ፣ የአንድን ሀገር የወደፊት አቅጣጫ የሚወሰንበት መሠረታዊ መሣሪያም ነው።

ምርጫ ዜጎች በማን መተዳደር እንዳለባቸው የሚወስኑበት ቀጥተኛ መንገድ ነው። “ሥልጣን የሕዝብ ነው” የሚለው የዲሞክራሲ መርህ በተግባር የሚተረጎመው በምርጫ አማካኝነት ነው። ዜጎች በነፃነት ድምፅ በመስጠት የመንግሥትን ሕጋዊነት (Legitimacy) ያረጋግጣሉ።

መራጮች ከላይ የተነሱትን ጥቅሞች ለማግኜት ታዲያ ምርጫ ካርድን ማውጣት እና የሚፈልጉትን ለመምረጥ መዘጋጀት ዋናው ጉዳይ ነው፡፡

ሀገራችንም ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ለግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ቀነ ቀጠሮ ይዛለች፤ ለዚህም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ መራጮች የምርጫየ መተግበሪያን ጨምሮ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የመራጮች ምዝገባ ጣቢያ በመሄድ የምርጫ ካርድ እያወጡ እና ለመራጭነት እየተመዘገቡ ይገኛል፡፡

ምልከታ ካደረግንባቸው ቦታዎች አንዱ በባሕር ዳር ከተማ ግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ አብነት ቀበሌ ነው፤ የቀበሌው ነዋሪዎች ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ እየወሰዱ ተመልክተናል።

“የሕዝብን የልማት ጥያቄ የሚመልሰ፣ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች የሚፈታ፣ ሰላምን የሚያርጋግጥ፣ ሀገርን የሚያሻግር እና ለዜጎች ተጠቃሚነት የሚሠራ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ማውጣት ቀደሚው ጉዳይ ነው፤ ለዚህም የምርጫ ካርድ አውጥተናል” ብለዋል።

“የመራጭነት ካርድ የሰላም መታወቂያ ነው” ያሉት ደግሞ የምርጫ ካርድ ሲያወጡ አግኝተን ያነጋገርናቸው የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። የከተማዋ ነዋሪዎች ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ እየወሰዱ ነው። የመራጭነት ካርድ መያዝ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መብትን ከመጠቀም ባለፈ፣ የሚፈልጉትን ለመምረጥ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

በመራጮች ምዝገባ ጣቢያ በመገኘት የምርጫ ካርድ ሲያወጡ ሐሳባቸውን የሰጡ በሰሜን ወሎ ዞን የመርሳ ከተማ ነዋሪዎችም “መሪን በንቃት መምረጥ ሥልጡንነት ነው፤ የምርጫ ካርድ ማውጣት እና በቀጣይ የሚወክለንን መምረጥም ዴሞክራሲያዊ መብታችን ነው” ብለዋል።

ይህን መብታቸውን ለመጠቀምም የምርጫ ካርድ በወቅቱ በግንባር ቀደምነት እንዳወጡ ነው የተናገሩት። ቀኑ ሲደርስም ይመራኛል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ምርጫ ለተመራጮች ትልቅ ኃላፊነት ሲሆን ይህንንም ቃል በመግባት ነው የሚጀምሩት፤ ሥልጣን ላይ ያለው አካል ለሕዝብ የገባውን ቃል ካልጠበቀና በአግባቡ ካላገለገለ፣ ሕዝቡ በቀጣይ ምርጫ ድምፅ ሊነፍገው ይችላል። ይህ አሠራር ደግሞ ተመራጮች ቃል ለገቡት ታማኝ እንዲሆኑና ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡ ያስገድዳቸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የየራሳቸውን የልማት፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፖሊሲዎች ለሕዝብ በማቅረብ እየተከራከሩ ነው። ይህም ዜጎች የተሻለ ነው ያሉትን የሐሳብ አማራጭ እንዲመርጡ ዕድል ይሰጣል። ምርጫ የሐሳቦች የገበያ ቦታ በመሆኑ ሀገርን ወደተሻለ ዕድገት የሚመሩ አዳዲስ ፈጠራዎችና ዕቅዶች እንዲወጡ ያደርጋል።

በሀገራችን ከዚህ በፊት ስድስት ምርጫዎች የተስተናገዱ ሲሆን በምርጫው ሂደት ሕገ መንግሥታዊ ግንዛቤና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ እየጎለበተ መምጣቱ ሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን የመጠቀም ልምድና በሂደቱም ያለውን እምነት በዚያው ልክ እያሳደገ መምጣቱን ከኢትዮጵያ ብሔረራዊ ምርጫ ቦርድ የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

እነዚህ የምርጫ ዘመናትም የመራጭ ዕድገት የታየባቸው ናቸው፡፡

በዘንድሮው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም የተሻለ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ነው የተመላከተው፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መራጩ ሕዝብ የሚበጀውን ለመምረጥ ሕዝቡ የምርጫ ካርዱን በእጁ እንዲያስገባ ነው ያሳሰቡት፤ ካርድን መያዝ ነገ መንግሥት ሆኖ ሀገር ሊመራ የሚገባን አካል ለመወሰን ቁልፍ ሂደት ነው ብለዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወ/ሮ እመቤት ከበደ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝብን ያስቀደመ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ እንዲሆን መሥራት ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሕዝብን ለግጭት ከሚያነሳሱ ነገሮች መቆጠብ እና ከግል ፍላጎት ይልቅ የሕዝብን ፍላጎት የሚያስቀድም ተግባራትን መተግበር አለብን” ብለዋል።

ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን ማስተላለፍ እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።

“የፓርቲ አባል መሆን እና ዝም ብሎ መደገፍ ትርጉም የለውም” ያሉት ወይዘሮ እመቤት “የምርጫ ካርድ ማውጣት እና መምረጥ ያስፈልጋል” ነው ያሉት።

ፓርቲው የምርጫ ሂደቱ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ሰላማዊ እንዲሆን ከአባላት ጋር ውይይት በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማከናወኑንም ገልጸዋል።

በምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች የምርጫው ሂደት ሰላማዊ፤ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ እንዲሆን የፓርቲው አባላት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ጠቅሰዋል።

“ሰላማዊ ምርጫ ይከናወን ዘንድ የመንግሥት ተግባር ብቻ አይደለም” ያሉት ወይዘሮ እመቤት “የሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና የጎላ በመሆኑ በትኩረት እንሠራለን” ብለዋል።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ምርጫ ዜጎች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጡበት መሣሪያ ነው።

የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ እንደሆነ በማንሳት ይህም የሚረጋገጠው በምርጫ ነው ብለዋል። ሕዝብ የፈለገውን ወደ ሥልጣን የሚያወጣበት እና ከሥልጣን የሚያወርድበት መንገድ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በሰላም እና በምርጫ  ጉዳይ የጋራ ምክር ቤቱ ወጥ አቋም ወስዶ እየሠራ ስለመሆኑም አንስተዋል። ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ እየሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል። “ችግሮች ሲፈጠሩ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ እየሠራ ይገኛል” ነው ያሉት።

አቶ ተስፋሁን የፖለቲካ ልዩነቶችን በሠለጠነ እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ምክር ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም አመላክተዋል።

“እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሩን የወደፊት ዕጣ ፋንታ ለመወሰን የምርጫ ካርዱን በእጁ ሊያደርግ ይገባል” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ናቸው፡፡ ዋና አፈ ጉባኤዋ እንዳሉት ሕጋዊ እና ቅቡልነት ያለው መንግሥት የሚመሠረተው በምርጫ ብቻ ነው።

“በኃይል የሚያዝ ሥልጣን የጸና አይሆንም፣ ተቀባይነትም የለውም” ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ ሥልጣን በኃይል የመያዝ ልምምድ ሀገርን እንዳልጠቀመ አስገንዝበዋል። “ለኢትዮጵያውያን የሚያስፈልገው የጸና እና ቅቡልነት ያለው ሕጋዊ መንግሥት ነው” ብለዋል።

ማንኛውም ሥልጣን መያዝ ያለበት መንግሥት በሕጋዊ መንገድ በምርጫ ብቻ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

የምርጫ ካርድ ማውጣት በዋናነት በዴሚክራሲያዊ ምርጫ መሳተፍ፣ መሪን የመምረጥ እና የመጠየቅ ሕጋዊ የዜግነት መብትን ለመጠቀም ያስችላል፡፡ ካርዱ ድምጽ ለመስጠት፣ በመራጮች መዝገብ ለመካተት እና በምርጫ ጣቢያዎች መብትን ለማስከበር እንደ መታወቂያ ያገለግላል፡፡ በመሆኑም በወቅቱ የምርጫ ካርድን ማውጣት ይገባል፡፡

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የሚያዚያ   12  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here