“አማርኛ የዓለም ሀብት ነው፤ በትክክል ተናገሩት፤በትክክል ጻፉት”

0
176

ቋንቋ የአንድ ማህበረሰብ መታወቂያ፣ የታሪክ ማቆያ እና የባህል መገለጫ ነው። አማርኛ ቋንቋ በረጅም ዘመናት ጉዞው ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ዛሬ ላይ ደርሷል። በቋንቋው አጠቃቀም ላይ የሚታዩ  ጉድለቶች ምንድን ናቸው? ምን መደረግ አለበት? በሚሉና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ እና ሥነጽሑፍ ትምህርት ክፍል ኀላፊ መምህርት እና ተመራማሪ ከሆኑት ዶክተር ኂሩት አድማሱ ጋራ በኩር ጋዜጣ ቆይታ አድርጋለች።

 

ዶክተር ኂሩት በመጀመሪያ ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን። በመቀጠል የዛሬ ማንነትዎን የቀረጸውን የትምህርት ጉዞዎን እና የልጅነት ትዝታዎን ቢያካፍሉን?

ተወልጄ ያደግሁት አዲስ አበባ ከተማ ነው። የትምህርት ሕይወቴ የጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ ነው። ከአጸደ ሕጻናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ድረስ እዚያው ነው የተማርኩት። በተለይ አንደኛ ደረጃን “መሰረተ እድገት” በሚባለውና ከቤታችን በጣም ቅርብ በነበረ ትምህርት ቤት ነው የተከታተልኩት። ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በኮልፌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘጠነኛ እና አስረኛን ከጨረስኩ በኋላ በወቅቱ በነበረው የትምህርት መዋቅር መሰረት የሶስት ዓመት የሁለተኛ ደረጃ ዲፕሎማ በአካውንቲንግ በጀነራል ዊንጌት ተከታትያለሁ።

ከአካውንቲንግ ትምህርት በኋላ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን በጥሩ ውጤት በማለፌ በ1993 ዓ.ም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመደብኩ። በወቅቱ ዩኒቨርሲቲው ወደ ዩኒቨርሲቲነት የተሸጋገረበት ዓመት ማግስት ስለነበረ በደንብ የሚታወቀው የባሕር ዳር መምህራን ማሰልጠኛ “ፔዳጎጂ” በሚለው ስሙ ነበር። የመጀመሪያ ዓመት ትምህርቴን እንደጨረስኩ በ1994 ዓ.ም አማርኛ ትምህርት ክፍልን ተቀላቀልኩና እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ ተማርኩ። ከዚያም በዩኒቨርሲቲው የመቀጠር እድል አግኝቼ  ለአንድ ዓመት ካስተማርኩ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመሄድ የማስተርስ ትምህርቴን በሥነጽሑፍ (Literature) ዘርፍ ቀጠልኩ። የሥነጽሑፍ  ትምህርትን ከምንም በላይ ስለምወደውና ዝንባሌው ስላለኝ የፒኤችዲ ትምህርቴንም እዚህ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በዚሁ ዘርፍ አጠናቅቄያለሁ።

 

ዋና ዋና ጥናቶችና ምርምሮችዎ በምን ላይ ያተኮሩ ናቸው?

አብዛኞቹ ጥናቶቼ ስርዓተ-ጾታ (Gender) እና  ሥነጽሑፍ ላይ ያተኮሩ ናቸው። የመጀመሪያ ዲግሪ መመረቂያዬ ‘’ግጭት በእንቡጥ ጽጌሬዳ ልብወለድ ውስጥ’’ የሚል ነበር። ለሁለተኛ ዲግሪ የሠራሁት ጥናት ደግሞ “ያልተለመዱ ሴቶች አቀራረብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ” በሚል ነበር። የፒኤች ዲ ጥናቴ ደግሞ “በፊልሞች ውስጥ ስርዓተ-ጾታ እንዴት ቀረበ?” የሚለውን በተለይም ወንድና ሴት አዘጋጆች  ሴቶችና ወንዶችን እንዴት እንደሚያቀርቧቸው  አይቻለሁ። ብዙ ጊዜ በሥነ-ጽሑፍ እና በፊልሞች ውስጥ ሴቶች እንደ ተጠቂ፣ ደካማ እና ጥገኛ ተደርገው ይቀርባሉ። እኔ ግን በምርምሬ ጠንካራ ሴቶችን ፈልጌ ለማውጣት ጥረት አድርጌያለሁ።

ከዚህ በተጨማሪ በልጆች  ሥነጽሑፍ፣ የጊዜ እይታ በተመረጡ የአማርኛ ግጥሞች፣ የታሪካዊ እውነታ አቀራረብ በተውኔቶች ውስጥ፣ የሴት ገጸባሕሪያት አቀራረብ በታሪካዊ ተውኔቶች ውስጥ እና የመሳሰሉ ጥናቶችን በግሌ ሰርቻለሁ። ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር ደግሞ የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም በአማራ ኤፍ ኤም ባሕር ዳር 96.9 ራዲዮ እንዲሁም በአማራ ክልል በሚገኙ ከተማዎች የንግድ ቤቶች ስያሜ ዙሪያ ሰፋ ያሉ ጥናቶችን አድርጌአለሁ።

 

የአማርኛ ቋንቋን አሁን ያለበትን የእድገት ደረጃ እንዴት ይገመግሙታል?

አማርኛ ቋንቋ የራሱ የጽሕፈት ስርዓት ያለው እና ከአረብኛ ቀጥሎ ሰፊ ተናጋሪ ያለው አገር በቀል ቋንቋ ነው። ኢትዮጵያን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚወክል፣ የመንግሥት ሥራ ቋንቋ፣ የትምህርት እና ምርምር እንዲሁም የሳይንስ ቋንቋ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። የመንግሥት የሥራ ቋንቋነቱ በተለይ በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን የጀመረ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አገልግሎቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየሰፋ መጥቷል። ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ደርግ ጊዜ ብሔራዊ ቋንቋ ተብሎ አገልግሎት እየሰጠ ነበር። ዛሬም በውጭ አገራት ሳይቀር በትምህርትነት እና በመግባቢያነት  አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ስለዚህ ሰፊ ተጠቃሚ ያለው ተደራሽነቱም ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገራት ድረስ  ነው ማለት ይቻላል። ሆኖም ግን እድገቱ ከጊዜው ጋር አብሮ እንዲሄድ ሳይንሳዊ ምርምሮች ሊደረጉበት ይገባል።

 

በቋንቋው አጠቃቀም ዙሪያ በስፋት የሚታዩ ዋና ዋና ጉድለቶች ምንድናቸው?

በቋንቋ አጠቃቀም ዙሪያ ዛሬ ላይ በርካታ ውስንነቶች አሉ። አንደኛው በተማረው ማህበረሰብ ዘንድ አማርኛን ከሌላ ቋንቋ (በተለይ ከእንግሊዝኛ) ጋር ቀላቅሎ የመናገር ልማድ ነው። ይሄ “ኮድ ሚክሲንግ” የሚባለው ነገር በረጅም ጊዜ ሂደት  የቋንቋውን ወጥነት እና ገጽታ ይጎዳዋል።

ብዙኃን መገናኛ በኩል ወጥ የሆነ እና የቋንቋውን ባህሪ የጠበቀ አጠቃቀም ላይ ትልልቅ ክፍተቶች አሉ። ከፊደላት አጠቃቀም ጀምሮ እስከ ሙሉ ጽሑፍ ድረስ ያለጥንቃቄ እንደፈለጉ የመጻፍ ችግር ይታያል። ሌላው ትልቁ ችግር ከማስተማር ጋራ የተያያዘ ነው። በተለይ አንደኛ ደረጃ ላይ የአማርኛን ትምህርት “ቋንቋውን ስለተናገረ ብቻ ያስተምር” ተብሎ መምህር የሚመደብበት ሁኔታ አለ። ይህ መስተካከል አለበት። ቋንቋ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተጠንቶ ካልተሰጠ ለልጆቻችን የምናስተላልፈው ቋንቋ መደበኛነቱን የጠበቀ አይሆንም። ይሄ ደግሞ በወደፊት የቋንቋው ህልውና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። መምህራን በቂ የቋንቋው ሳይንስ እውቀት እና ዝግጅት ኖሯቸው ሊያስተምሩ ይገባል።

 

ለእነዚህ የቋንቋ አጠቃቀም ክፍተቶች እና ጉድለቶች ዋና መንስኤው ምንድነው ይላሉ?

ዋነኛው ምክንያት ለቋንቋው ተገቢ ትኩረት አለመስጠት እና ግዴለሽነት ነው። ብዙ ሰዎች “አማርኛ ቀድሞውንም አድጓል፤ ጥናት አያስፈልገውም” ብለው ያስባሉ። ነገር ግን ቋንቋ ህያው እንደመሆኑ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ቃላት እና ማኅበራዊ ለውጦች በመጡ ቁጥር ቋንቋው እንዲያድግ ሆን ተብሎ የሚሠራ ክፍል ሊኖር ይገባል። ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ካልተደረገበት ቋንቋው እየተዳከመ ይሄዳል። ሌላው ችግር ደግሞ የሚደረጉ ጥናቶች ለማህበረሰቡ ተደራሽ አለመሆናቸው ነው። ምርምር ተደርጎ በቤተ-መጽሐፍት ብቻ ከተቀመጠ ለተጠቃሚው ማህበረሰብ የሚፈይደው ነገር አይኖርም።

 

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው የቋንቋ አጠቃቀምስ ምን መምሰል አለበት? በዚህ ዙሪያ ምን እየተሰራ ነው?

ማህበራዊ ሚዲያ ዛሬ ላይ የሰዎች ዋነኛ መገናኛ ሆኗል። ነገር ግን በዚያ ላይ የሚታየው የቋንቋ አጠቃቀም ጥንቃቄ የጎደለው ነው። ሰዋሰዋዊ ሕጎችን አለመከተል፣ ቃላትን አሳጥሮ መጻፍ እና የሌላ ቋንቋ ተጽእኖ በከፍተኛ ሁኔታ ይታያል። እኛም በዚህ ዙሪያ በተለይ ለጋዜጠኞች እና ለማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ስልጠናዎችን ስንሰጥ ቆይተናል።

ቃላትን አሳጥሮ መፃፍ የፊደላትን ቅርጽ እና ድምጽ ከማጥፋቱም በላይ ትክክለኛውን የቋንቋ ስርዓት ያዘበራርቃል። ማህበራዊ ሚዲያ ፈጣን መሆኑ እውነት ቢሆንም የቋንቋውን ሕግ ግን መጠበቅ ይኖርብናል። ምክንያቱም ቋንቋችን የባህላችን እና የማንነታችን መሸከሚያ ነው። አንድን ቃል በትክክል አለመጻፍ ትርጉሙን ሊያዛባው ይችላል።

የማህበራዊ ሚዲያ ቋንቋ አጠቃቀም ምን መምሰል አለበት? የሚለው ላይ ከጋዜጠኝነት  ትምህርት ክፍል ጋር ተባብረን ሰርተናል። ቋንቋው መደበኛ ይዘቱን ሳይለቅ መልእክትን በግልጽ ማስተላለፍ እንዲችል መስራት ይገባል። በተጨማሪም በቅርቡ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች አጠቃቀም ላይም ስልጠናዎችን ሰጥተናል። ቋንቋን በዘመናዊ መንገድ መጠቀም ማለት ሕጉን ማፍረስ ማለት አለመሆኑን ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።

የአማርኛ ቋንቋ በሥነጽሑፍ ውስጥ ያለውን ሚና እንዴት ያዩታል?

ሥነጽሑፍ የታሪክ ማቆያ ትልቅ መሳሪያ ነው። የአማርኛ  ሥነጽሑፍ ከአገራችን ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ለውጦች ጋር አብሮ ነው የሄደው። በግጥሞች ውስጥ እና በልቦለዶች ውስጥ የጊዜ አጠቃቀምን እና የቋንቋ ውበትን መመልከት ይቻላል።  ሥነጽሑፍ ቋንቋን ያበለጽጋል፤ ቋንቋ ደግሞ  ሥነ ጽሑፍን ህያው ያደርገዋል። ስለዚህ ለሥነጽሑፍ ሥራዎች ተገቢው ድጋፍ እና ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። ዛሬ ላይ የምንጽፋቸው ስራዎች የዛሬውን እውነታ ለነገው ትውልድ ያሸጋግራሉ።

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ እያከናወናችሁት ያለው የቋንቋ ማእከል ሥራ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ዩኒቨርሲቲው ለቋንቋ ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል። የቋንቋ ማእከል በማቋቋም በተለይ የአማርኛ እና ሌሎች አገር በቀል ቋንቋዎች እንዲጠኑ እያደረግን ነው። ስልጠናዎችን እንሰጣለን፤ ጥናቶችን እናሳትማለን። ዓላማችን ቋንቋው በሳይንሳዊ መንገድ እንዲያድግ እና የዘመኑን እውቀት መሸከም እንዲችል ማድረግ ነው። ይሄ ሥራ ግን የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ምሁራን ትብብር ይጠይቃል። የአማራ ክልል መንግሥትም ለዚህ ሥራ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እና ቋንቋውን ለማሳደግ ምን መደረግ አለበት ብለው ያስባሉ? ተቋማዊ አደረጃጀቱስ ምን መምሰል አለበት?

ቋንቋውን በሚገባ የሚጠብቅ፣ የሚንከባከብ እና ስርዓት የሚያስይዝ ራሱን የቻለ ተቋም ወይም ማእከል ያስፈልጋል። ዩኒቨርሲቲዎች ጥናት ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ያ ጥናት ተደራሽ የሚሆንበት መንገድ መፈለግ አለበት። ቋንቋውን በሚገባ የሚያጠኑ ሰዎች የምርምር ውጤታቸው ለማህበረሰቡ ሊደርስ ይገባል።

ሚዲያዎች እና የመንግሥት አካላትም ለቋንቋው እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው። ማንኛውም ቋንቋውን የሚያስተምር መምህር በመደበኛ ሁኔታ የቋንቋውን ሳይንስ የተማረ ሊሆን ይገባል። ቋንቋውን ከሚመጣበት የውጭ ተጽእኖ ለመከላከል እና ለቀጣዩ ትውልድ በትክክል ለማስተላለፍ ሆን ተብሎ በትጋት መሥራት ብቸኛው መፍትሄ ነው። የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንም ወደ አማርኛ በማምጣት ቋንቋው የዘመኑን እውቀት እንዲሸከም ማድረግ ይኖርብናል። ቋንቋችንን ማሳደግ አገራችንን ማሳደግ ነው።

ለወጣቱ ትውልድ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?

ቋንቋችሁን ውደዱ! ቋንቋን መውደድ ማለት ማንነትን መውደድ ነው። አማርኛ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሀብት ነው። በኩራት ተጠቀሙበት፣ በትክክል ተናገሩት፤  በትክክል ጻፉት። እኛ ካልጠበቅነው ማንም አይጠብቅልንም። በቋንቋችን እንመርምር፣ በቋንቋችን እንፍጠር። ያኔ ነው ቋንቋው ህያው ሆኖ የሚቀጥለው። ወጣት ጸሐፊዎችም ቋንቋውን በጥልቀት በማጥናት ሥራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ አበረታታለሁ።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here