ምርጫ ካርድ በመረጡት ሕጋዊ ወኪል ለመመራት!

0
16

ምርጫ በአንድ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ዕድገት ይመዘገብ ዘንድ  የማይተካ ሚና ይጫወታል። ምርጫ ዜጎች በማን መተዳደር እንዳለባቸው የሚወስኑበት ቀጥተኛ መንገድ በመኾኑ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር  እንዲኖር ያደርጋል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማስፈን ዕድገትንና ብልጽግናን ማፋጠንን ዓልመው የሚንቀሳቀሱ ሀገራት  በሕግ የተጠበቀ የምርጫ ሂደት አላቸው። የምርጫ ሂደታቸው በሕግ የተጠበቀ ለመኾኑ አንዱ አብነት ሀገራቱ ነፃና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ ያላቸው መኾኑ ነው፡፡ ሀገራቱ ነፃና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ ባለቤት መኾናቸው በምርጫ ውጤት ላይ ከፍተኛ እምነት እንዲፈጠር ስለማገዙ የየሀገራቱ የምርጫ ተሞክሮ ይጠቁማል። ሀገራቱ ነፃና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ አቋቁመው መኾኑ ምርጫ ማካሄዳቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ለመወዳደር እኩል ዕድል እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማሕበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተውም በሀገራችን ከዚህ በፊት ስድስት ምርጫዎች ተደርገዋል፡፡ በእነዚህ ምርጫዎች እንደተስተዋለው  የመራጮች ቁጥር ዕድገት አሳይቷል፡፡ የመራጮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣት ደግሞ የሕዝቡ ሕገ መንግሥታዊ ግንዛቤ ለመዳበሩና በምርጫ የሚያደርገው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ እየጎለበተ ለመምጣቱ ማሳያ ነው፡፡

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚደረገው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ሕዝቡን በንቃት ባሳተፈ መልኩ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡  መራጮች የምርጫዬ መተግበሪያን በመጠቀም እንዲሁም በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የመራጮች ምዝገባ ጣቢያ በመሄድ እየተመዘገቡ የምርጫ ካርድ በማውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢመረጡ ሊያከናውኑ ያሰቧቸውን  ተግባራት በፖሊሲዎቻቸው በማካተት ለመራጮች በማቅረብ እየተከራከሩ ነው።

የብዙኃን መገናኛ አውታሮችም ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የአየር ሰዓት በመመደብ  ፕሮግራሞቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ምቹ ሁነታን ፈጥረዋል፡፡

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም መራጩ ሕዝብ የሚበጀውን ፓርቲ ለመምረጥ ይችል ዘንድ በሰላም እና በምርጫ  ጉዳይ ወጥ አቋም ወስዶ እየሠራ ነው፡፡

መንግሥትም የምርጫ ሂደቱ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየሠራ ነው፡፡ በተለያዩ የብዙኃን መገናኛ አውታሮች ስለምርጫዉ ፋይዳና ሂደት የሚያስገነዝቡ መግለጫዎችን መስጠቱ፣ በያካባቢው የመራጮች የምዝገባ ጣቢያዎችን መክፈቱ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ፕሮግራሞቻቸውን ለሚመርጣቸው ሕዝብ ያስተዋውቁ ዘንድ በብዙኃን መገናኛ አውታሮች የአየር ሰዓት መመደቡ መንግሥት ለምርጫዉ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት   የሚያሳዩ መልካም ርምጃዎች ናቸው፡፡

የምርጫ ካርድን መውሰድና መሪን በንቃት መምረጥ የሥልጡንነት ምልክት ነው፡፡  የምርጫ ካርድ ማውጣትና ይጠቅመኛል የሚሉትን ፓርቲ መምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብትን መጠቀም፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት የዜግነት ግዴታን መወጣትም ነው።

ይመራኛል ያሉትን ፓርቲ በምርጫ ካርድ  መምረጥ ለተመራጩ ፓርቲ  ትልቅ ኃላፊነት  እንዲሁም አደራ መስጠት ነው፡፡ የሕዝብ አደራ ደግሞ የትም የሚጣል አይደለም፡፡ ተመራጩ ሥልጣኑን የሚረከበው ሕዝብ የመረጠው ይሠራልኛል፤ ጥያቄዎቼን ይመልስልኛል፤ ችግሬን ይፈታልኛል፤ ኑሮየን ይለውጥልኛል ብሎ እንደሆነ በማሰብ በሕዝብ ለተጣለበት አደራ ተግባራዊነት ቃል ገብቶ ነው፡፡ ተመራጩ ሥልጣኑን ያገኘው በሕዝብ ይሁንታ መሆኑን በማጤንም ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ይህን ቃሉን ጠብቆ አደራውን ለመወጣት ይጥራል፤ ሥልጣኑም በሕዝብ ይሁንታ የተሰጠ እንደ መሆኑ መጠን ተመራጩ  ፓርቲ ለሕዝብ የገባውን ቃል ካልጠበቀና በአግባቡ ካላገለገለ፣ ሕዝቡ በቀጣይ ምርጫ ድምፅ ሊነፍገው እንደሚችል በማሰብ። ይህም የምርጫን ጠቀሜታ ከፍተኛነት የሚጠቁም ነው፡፡ ስለሆነም  የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት አሳታፊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ ይጠናቀቅ ዘንድ በመራጩ፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ በምርጫ ቦርድ፣  በመንግሥት የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ መራጮች የሚፈልጉትን ፓርቲ መምረጥ፣ በጸና እና ቅቡልነት ባለው ሕጋዊ መንግሥት መመራት የሚችሉት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው መምረጥ ሲችሉ ነውና ለዚህ የሚያበቃቸውን የምርጫ ካርዳቸውን ከወዲሁ ማውጣት አለባቸው፡፡

በኲር የሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here