አለመታመም ጤናማነትን አያረጋግጥም!

0
145

“እኔ ካልታመምሁ የጤንነቴን ሁኔታ ቀድሜ ለማወቅ ወደ ሕክምና አልሄድም፡፡ ምክንያቴ ደግሞ አንዱን በሽታ አለብሽ ብባል ምድን ስለማይመስለኝ ጭንቀቱ ይፈጥርብኛል ብየ ስለማስብ ነው፡፡ በዚህም ቅድመ ምርመራ ማድረግ አልፈልግም” በማለት አስተያየታቸውን የሰጡን ወይዘሮ ዓለም መኮንን የተባሉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ናቸው፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ ግን ከወይዘሮ ዓለም የተለየ ሀሳብ ነው የሰጡን፡፡ ሕመም ሲሰማቸው  ፈጥነው ወደ ሆስፒታል እንደሚሄዱ ተናግረዋል፡፡ ስለግፊት፣ ስኳር፣ ልብ…ሕመም ሲወራ በመስማታቸው የጤንነታቸውን ሁኔታ ለማወቅ ምርመራ አድርገዋል፡፡ ጤነኛ መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላም ደስተኛ ናቸው፡፡ ድጋሚ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ሙያዊ ማብራሪያ ይሰጡን ዘንድ በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው በኪዳነ-ምሕረት ከፍተኛ ክሊኒክ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ኢብራሒም የሻው ጋር በኵር ቆይታ አድርጋለች፡፡ ዶ/ር ኢብራሒም እንዳስረዱት  ቅድመ ጤና ምርመራ በማድረግ የተለያዩ ጥቅሞችን ማግኘት ይቻላል፡፡ የአኗኗር ዘይቤን ለመቀየር፣ ሊከሰቱ የሚችሉ የበሽታ አይነቶችን ቀድሞ በምርመራ በመለየት  እየመጡ ያሉ በሽታዎችን ስር ነቀል በሆኑ መንገዶች ሕክምና ለማድረግ፣ ለሕክምና ሊወጡ የሚችሉ ዎጪዎችን ለመቀነስ፣ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ የአዕምሮ እርካታ እንዲኖር ለማድረግ ቅድመ ምርመራ ጠቃሚ ነው፡፡

የትኞቹን በሽታዎች አስቀድሞ ምርመራ በማድረግ መከላከል ይቻላል?

ባለሙያው እንደሚሉት በሽታዎች በአጠቃላይ በተሕዋሲያን ምክንያት የሚመጡ እና  በዘረመል ወይም በተለያዩ ምክንያት ሊከሰቱ  የሚችሉ ተብለው በሁለት ይከፈላሉ፡፡  በተለይም  ቀድመን ልንከላከላቸው ከምንችላቸው በዘረመል ሊከሰቱ ከሚችሉ በሽታዎች መካከል አንዱ ግፊት ነው፡፡ ዝምተኛው ገዳይ (ሳይለንት ኪለር) ይባላል፡፡ አድፍጦ ምንም ምልክት ሳያሳይ የሚገድል በሽታ ነው፡፡

ግፊትን በቀላሉ በመለካት መኖር አለመኖሩን ማወቅ ቀድሞ ለመከላከል ይረዳናል፡፡ ሌላው የሰውነት የቅባት መጠን መጨመር ከልብ እና ከልብ ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ችግሮች ጋር የተያያዙ በሽታዎችን ስለሚያመጣ ቅድመ ምርመራ ማደረግ እነዚህን በሽታዎች  ለመከላከል ይረዳል፡፡

ዶ/ር ኢብራሒም እንደሚሉት የስኳር በሽታንም  ቀድሞ ምርመራ በማድረግ  ስር እንዳይሰድ ማድረግ ይቻላል፡፡

ከመታመም በፊት ምርመራ በማድረግ  የአንጀት፣ የማሕፀን ጫፍ፣ የጡት ፣ የፕሮስቴት እና የፊኛ ካንሠሮች ከሚያደርሱት ከፍተኛ ጉዳት መጠበቅ ይቻላል፡፡ የአጥንት መሳሳትን፣ የጉበት የስብ መጠን እና በተሕዋሲያን ምክንያት የሚመጡ የጉበት ቫይረስ በሽታዎችን መከላከል ይቻላል፡፡  እንደ ኤች አይ ቪ ያሉ የአባላዘር በሽታዎችን ቅድመ ምርመራ በማድረግ መከላከል እንደሚቻል ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ኢብራሒም ማብራሪያ ከከተማነት ጋር ተያይዞ የተለያዩ የበሽታ አይነቶች አሉ፡፡ በተለይም ደግሞ የሥነ አዕምሮ መቃወስ (ድብርትን) ቅድመ ምርመራ በማድረግ መከላከል ይቻላል፡፡  እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ቀድመው የዓይን እና የጆሮ ምርመራ በማድረግ ከዕይታ እና ከመስማት ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን ከባድ ጉዳት ሳያስከትሉ አስቀድሞ በመታከም የጉዳት መጠናቸውን መቀነስ ይቻላል፡፡

በዕድሜ ደረጃ የሚመከሩ ምርመራዎች

ዶ/ር ኢብራሒም እንዳብራሩት ሁሉም ሰው አንድ አይነት ምርመራ አይደረግለትም፡፡ ዕድሜ፣ ፆታ፣ የቤተሰብ የበሽታ ታሪክ፣ የኑሮ ዘይቤ፣ ቀደም ሲል  ያለ በሽታን እና የአደጋ ሁኔታን መሠረት በማድረግ ምርመራዎች ከሰው ሰው ይለያያሉ፡፡ ቢሆንም ግን ብዙ ሰዎች በየጊዜው ሊያደርጉ የሚገባቸው መሠረታዊ ምርመራዎች እንዳሉ ነው የተናገሩት፡፡ የደም ግፊትን መለካት፣ የደም ስኳርን መመርመር፣ የኮሌስትሮል መጠንን ማወቅ፣ የደም አጠቃላይ ምርመራዎችን ማድረግ፣ እንደ ሁኔታው የኩላሊት እና የጉበት ተግባር ምርመራዎች ማድረግ ሊከሰት የሚችልን ስቃይ እና ወጪን ይታደጋል፡፡

ለሴቶች እንደ ዕድሜ እና ሐኪም ምክር የማሕፀን ጫፍ  ወይም የጡት ምርመራ እና ለሁሉም እንደ ሁኔታው የክትባት ክትትል እና የተወሰኑ ቅድመ ጥንቃቄ ምክሮች ይሰጣሉ፡፡ ይሁንና እነዚህ ምርመራዎች በሕክምና ባለሙያ ምክር የሚደረጉ ናቸው፡፡ በሐኪም የታገዘ ምርመራ አላስፈላጊ ወጪን ይቀንሳል፣ አስፈላጊው ምርመራም እንዳይቀርም ያደርጋል፡፡

ዶ/ር ኢብራሒም እንዳሉት ሕጻናት የስኳር ምርመራዎች ሊደረጉላቸው ይችላል፡፡ በተለይም  በቤተሰባቸው ታሪክ የስኳር በሽታ ያለበት ሰው ካለ በልጅነታቸው የመከሰት አጋጣሚው  ከፍተኛ በመሆኑ ቅድመ ምርመራ ያስፈልጋቸዋል፡፡  ከዕድሜያቸው በላይ ውፍረት ያላቸው ሕጻናት ምርመራዎች ይደረጉላቸዋል፡፡ ከዛ ውጭ እድሜያቸው  ከ18 ዓመት ጀመሮ ቅድመ ምርመራ  እንዲያደርጉ ይመከራል፤ ተመርምረው ጤነኛ ከሆኑ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት እየደጋገሙ መመርመር ይችላሉ፡፡ ከ40 ዓመት በኋላ ግን ተደጋጋሚ የግፊት መጠንን ለማወቅ ምርመራ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ይሁንና ጠንካራ የሆነ በቤተሰብ ታሪክ የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች፣ በእርግዝና ወቅት ግፊት እና ስኳር የተከሰተባቸው፣ ከልክ ያለፈ የወፈሩ ሰዎች ከሃያ ዓመት ጀምሮ ምርመራውን  በተደጋጋሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዛ በኋላ ከአራት ዓመት እስከ ስድስት ዓመት ባሉት ጊዜዎች መመርመር ይኖርባቸዋል፡፡ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ግን በየጊዜው ቢመረመሩ  ይመከራል፡፡

ሳይንቲስቶች የስኳር በሽታን በተመለከተ ብዙ ጊዜ ከ35 ዓመት  በኋላ  እንዲመረመሩ  እንደሚመክሩ የተናገሩት ባለሙያው፤ ይህ ግን ተጋላጭ ሰዎችን አያጠቃልልም፡፡ ግፊት ያለባቸው እና  በዘር የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ምርመራዎችን ቀደም ብለው ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

የአንጀት ካንሰርን ዕድሜያቸው ከ50  ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች እንዲመረመሩ ባለሙያው መክረዋል፡፡ ለጡት ካንሰር ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች፣ የማሕጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራን  ከ21 ዓመት ጀምሮ ለጤነኛ ሰዎች በየሦስት ዓመቱ እንዲሁም  ከ50 ወይም ከ65 ዓመት በኋላ ለሚገኙ ሴቶች ደግሞ በየአምስት ዓመቱ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡

በተሕዋሲያን ምክንያት እንደ ኤች አይቪ ያሉ በሽታዎችን ሰዎች በሕይዎት ዘመናቸው አንድ ጊዜ መመርመር አለባቸው፤ ይሁንና ከአኗኗር ዘይቤያቸው ጋር ተያይዞና ሥራቸው  ለበሽታው ተጋላጭ የሚያደርጋቸው ከሆነ ግን በየጊዜው መመርመር ሊጠበቅባቸው ይችላል፡፡ እንደ ሄፐታይተስ ሲ ያሉ የጉበት በሽታዎችን ደግሞ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ መመርመር ግድ ይላል፡፡ ሄፐታይተስ ቢ የሚባለው ሌላኛው የጉበት ቫይረስ ምርመራን  ደግሞ እንደ ኤች አይቪ ተላላፊ በሽታ በመሆኑ (ልቅ የሆነ ግንኙነት ከተፈጸመ፣ ስለታማ ቁሶችን በጋራ ተጠቅመው ከሆነ …)በሽታው መኖር እና አለመኖሩን ለማረጋገጥ በየጊዜው ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

የአባላዘርን በሽታ በሕይዎት ዘመን አንድ ጊዜ መመርመር እንዳለ ሆኖ አጋላጭ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ግን በዓመት እንደ አስፈላጊነቱ ምርመራዎች መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡

ሰዎች መመርመርን ለምን ይፈራሉ?

ባለሙያው የጤና ምርመራዎችን ለማድረግ ለሚፈሩ አንዳንድ ሰዎች በለገሱት ምክር አንድ ሰው ከሚፈራው በሽታ ለመጠበቅ በመጀመሪያ መመርመር አለበት፡፡ ተመርምሮ ነጻ ከሆነ በበሽታው እንዳይያዝ  አሰፈላጊ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይችላል፡፡ የሚፈራው በሽታ  በምርመራ መኖሩ ከተረጋገጠ  ደግሞ በሽታው   ስር ሳይሰድ መታከም ይኖርበታል፡፡ ፍርሃት ተፈጥሯዊ  በመሆኑ  እሱን በመጋፈጥ እየመጣ ያለውን ችግር መቋቋም ያስፈልጋል፡፡

ፍርሃቱ የሚመነጨው ለረዥም ጊዜ አብረውን ሊቆዩ የሚችሉ በሽታዎች ሊገኙብን ይችላሉ በሚል እንደሆነ የጠቆሙት ባለሙያው፤  ነገር ግን እነዚህን በሽታዎች መከላከል የሚቻለው መጀመሪያ ላይ ምርመራ በማድረግ ጤናችን ያለበትን ሁኔታ በማወቅ ነው፡፡ የጤና ምርመራ ማድረግ የአኗኗር ዘይቤን ለመቀየር እና  ለማስተካከል ይረዳል፡፡ ከፍተኛ  ወጪንም ይቀንሳል፡፡ ለአብነትም በስኳር በሽታ የሚመጣን ሕመም ተከትሎ በሽታውን በጅምር በማስወገድ፣ ከፍተኛ  የአዕምሮ ጫናን መቀነስ   እና በራስ መተማመንን ይፈጥራል፡፡

ጤናማ ሕብረተሰብ እንዲኖር ምን መደረግ አለበት?

ዶ/ር ኢብራሒም እንዳሉት በሽታዎች በአጠቃላይ በሁለት ይከፈላሉ፤ በተሕዋሲያን የሚመጡ እና በዘረመል( በአኗኗር ዘይቤ ) የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በተሕዋሲያን ከሚመጡ በሽታዎች ለመጠበቅ የግል ንጽሕናን መጠበቅ፣ እጅን መታጠብ፣ ሳል ከሚያስሉ ሰዎች ጋር ርቀትን መጠበቅ፣ የግል መጠቀሚያዎችን አለመጋራት፣ በሐኪም የታዘዙ መድኃኒቶችን በአግባቡ መውሰድ፣  የአኗኗር ዘይቤን በመቀየር (ጤናማ አመጋገብ መከተል፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ) ከተላላፊ በሽታዎች መጠበቅ ይቻላል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የተመጣጠነ ምግብ  ማለትም ፍራፍሬዎችን እና ጥራጥሬዎችን  አብዝቶ መመገብ፣ የስኳር እና ጨው አጠቃቀማችንን መቀነስ፣ በሳምንት 150 ደቂቃ  ወይም በሳምንት ለአምስት ቀናት ለ30 ደቂቃ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን (ሩጫ ፣ሳይክል መጋለብ  እና ዋና መዋኘት..) ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ አንድ ሰው በቀን ውስጥ ከሰባት እስከ ዘጠኝ ሰዓት የሚሆን ሰላማዊ እንቅልፍ መተኛት አለበት፡፡ ዓመታዊ ምርመራዎችንም ማድረግ አለበት፡፡

ጤና አዳም

አስቀድሞ ምርመራ ማድረግ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች፦

*ምርመራ ማድረግ በሽታን መጥራት  አይደለም፤ በሽታን ቀድሞ ለመለየት የሚያግዝ ብልህ እርምጃ ነው፡፡

* በሽታ ቀድሞ ሲገኝ ሕክምናው ውጤታማ ይሆናል፣ ወጪው እና የአካል ጉዳቱ ይቀንሳል፤ እንዲሁም በሕይወት የመቆየት ዕድልን ይጨምራል፡፡

*በጊዜው የታወቀ የደም ግፊት ልብን እና ኩላሊትን ከከባድ ጉዳት ሊጠብቅ ይችላል፡፡

*ቀድሞ የተገኘ የስኳር ችግር ዐይንን፣ ነርቭን እና ኩላሊትን ከቀጣይ አደጋ ሊከላከል ይችላል፡፡

*በመጀመሪያ ደረጃ የተገኜ ካንሰር  የመዳን እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

ምንጭ ፡- የዓለም ጤና ድርጅት

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሚያዚያ   12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here