ወይዘሮ ማሪቱ ዳኛው በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በዘንዘልማ ቀበሌ በእርሻ ሥራ የሚተዳደሩ ብርቱ አርሶ አደር ናቸው:: የግብርና ሥራቸውን ከበጋ እስከ ክረምት ወደው የሚያከናውኑት ተግባር ነው:: በበጋ ወራት አትክልት እና ፍራፍሬ ያመርታሉ:: በክረምቱ ወራት ደግሞ ማሳቸውን በቆሎን ጨምሮ በሌሎች ሰብሎች ይሸፍናሉ::
አርሶ አደሯ ለ2018/19 የመኸር እርሻ ማሳቸውን በሚገባ ለዘር እያዘጋጁ መሆኑን ለበኵር በስልክ ነግረውናል:: ለግብርና ሥራቸው ውጤታማነት ደግሞ ግብዓት አስፈላጊ መሆኑን ነው የገለጹልን:: በተለይም “ሊሙ” የተባለው የበቆሎ ምርጥ ዘር ውጤታማ መሆኑን ተገንዝበዋል:: ነገር ግን ለመጭው መኸር ወቅት በበቂ ሁኔታ ማግኘት ፈታኝ እንደሆነባቸው ጠቁመዋል::
የሰብል ልማት ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በተደራጀ መንገድ ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ማቅረብ፣ ማሰራጨት እና በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎችም ይመክራሉ፡፡ ከምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች መካከል ደግሞ ምርጥ ዘር ተጠቃሽ ነው:: ምርጥ ዘርን በወቅቱ፣ በብዛት፣ በጥራት፣ በተመጣጣኝ ዋጋ እና በዓይነት ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ከተቻለ ምርታማነትን መጨመር እንደሚቻል አስገንዝበዋል::
ለውጤታማነቱም ወይዘሮ ማሪቱን ጨምሮ አርሶ አደሮች በአብዛኛው የሚያነሱትን የምርጥ ዘር እጥረት ለመፍታት በክልሉ በዘር ብዜት የተለያዩ አካላት ተሠማርተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ የተሰማራው ዮናስ ተሾመ ምርጥ ዘር አምራች ድርጅት ተጠቃሽ ነው፡፡ ድርጅቱ በወረዳው በ60 ሄክታር መሬት ላይ ቢ ኤች (BH 661) የተባለ የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት እያከናወነ መሆኑን ለበኵር ጋዜጣ በስልክ ተናግሯል::
ባለፉት ስድስት ዓመታት ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት መስራች ዘር በመውሰድ የዘር ብዜት ሥራዎችን በማከናወን በአጎራባች ለሚገኙ ለደንበጫ፣ ለቡሬ ዙሪያ፣ ለጃቢ ጠህናን እና ለደብረ ኤሊያስ ወረዳዎች ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር እያሰራጨ መሆኑን አሳውቋል::
እንደ አቶ ዮናስ ማብራሪያ በዚህ ዓመትም ሦስት ሺህ 100 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ለተጠቃሚው ለማሰራጨት ታቅዷል፡፡
ሌላው በክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦት እና ስርጭት ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን እያባዛ የሚገኘው የአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ነው:: የኢንተርፕራይዙ የዘር ማምረት መምሪያ ኃላፊ አቶ እምሻው ወርቅነህ ለበኵር ጋዜጣ እንደተናገሩት ምርታማነትን ለማሳደግ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብለዋል:: ኢንተርፕራይዙ 12 የሰብል ዓይነቶችን በግል ባለሃብቶች እና በአርሶ አደሩ ማሳ እንዲሁም መሬት በኮንትራት እየተከራየ እና በኢንተርፕራይዙ ባለው መሬት ላይ መሥራች ዘር እያባዛ መሆኑን ተናግረዋል::
ምርጥ ዘር በሽታን እና ድርቅን የመቋቋም፣ ምርትን የመጨመር፣ ፈጥኖ የሚደርስ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ግብዓት መሆኑንም መምሪያ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
የዘር ብዜት ከፍተኛ ጥንቃቄን ይጠይቃል ያሉት አቶ እምሻው ለዚህም የጥራት ማስጠበቂያ መስፈርቶችን ተከትሎ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል:: ለ2018/19 የምርት ዘመን የባለፈውን ዓመት (የከረመውን) ጨምሮ 80 ሺህ ኩንታል የተለያዩ የዘር ዓይነቶችን
ለማቅረብ መታቀዱንም ጠቁመዋል፡፡ ከተሰበሰበው ዘር 40 ሺህ ኩንታል ተበጥሮ ለተጠቃሚው ለማሰራጨት ዝግጅቶች ተጠናቀዋል::
በአማራ ክልል የግብርና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን የዕፅዋት ዘር ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጉርሜሣ እጀታ ለበኵር እንደተናገሩት “ምርጥ ዘር ማለት ከተለያዩ የዘር ዝርያዎች መቀላቀል ነፃ የሆነ፣ የራሱ የሆነ ዘረ-መል ያለው፣ በባሕሪው እና ከፍተኛ ምርት መስጠቱ የተረጋገጠለት ዘር ነው:: ጥራት የሚረጋገጠው ደግሞ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ላብራቶሪ እና ስርጭት ድረስ ጥብቅ የጥራት ቁጥጥር መደረጉ ነው፡፡”
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት የመንግሥትም ሆኑ የግል የዘር አምራች ድርጅቶች ማሳቸው ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበታል:: በቆሎን እንደ አብነት ብንወስድ ማሳው የተፈቀደውን የግለላ ርቀት (Isolation distance) የጠበቀ መሆን አለበት:: ይህ ማለት አምራቹ ከሚዘራው የዘር አይነት ውጪ ሌላ የበቆሎ ዝርያ በአቅራቢያው መገኘት የለበትም፤ ይህም የዘር መቀላቀልን ለመከላከል ነው:: ከዚህም በተጨማሪ በማሳው ላይ በሽታ እና አደገኛ አረም አለመኖሩ ይረጋገጣል::
ዘሩ ታጭዶ እና ተሸልቅቆ ወደ ማበጠሪያ ማዕከል ከገባ በኋላ ተጠርጎ እና በኬሚካል ታሽጎ በሎት (Lot) ይደራጃል:: ለምሳሌ አንድ የበቆሎ ሎት 400 ኩንታል ሲሆን ከዚህ ውስጥ በዘፈቀደ (Randomly) ናሙና ተወስዶ ወደ ላብራቶሪ ይላካል:: በላብራቶሪ ውስጥ የንጽሕና፣ የእርጥበት መጠን እና የብቅለት ፈተና ይካሄዳል:: የብቅለት መጠኑ ከ85 በመቶ በላይ ከሆነ “ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር” ተብሎ የምስክር ወረቀት ይሰጠዋል:: ከ85 በመቶ በታች ከሆነ ግን ለዘርነት ስለማያገለግል ለምግብነት እንዲውል ይደረጋል::
በዚህ የጥራት መስፈርት በተያዘው ዓመት በተደረገው ቁጥጥር 593 ሄክታር ላይ የነበረ ዘር መስፈርቱን ባለማሟላቱ ውድቅ ተደርጓል:: እስካሁን ባለው ሂደት 65 ሺህ 226 ኩንታል ዘር ላብራቶሪ ገብቶ የተመረመረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 55 ሺህ 812 ኩንታሉ መስፈርቱን አሟልቶ አልፏል:: ሆኖም 9 ሺህ 413 ኩንታል የሚሆነው ዘር (በተለይም አኩሪ አተር እና ስንዴ) በወቅቱ በነበረው ዝናብ ምክንያት እርጥበት ስለነካው መስፈርቱን ማሟላት ባለመቻሉ ውድቅ ተደርጓል::
በሌላ በኩል ካለፈው ዓመት የተረፈ (የከረመ) 92 ሺህ 215 ኩንታል ዘር ድጋሚ ተመርምሮ 91 ሺህ 929 ኩንታሉ የብቅለቱን ዝቅተኛ መስፈርት በማሟላቱ ለዚህ ዓመት ዘር እንዲውል ተፈቅዷል::
ምንም እንኳን የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይህንን ሁሉ ጥረት ቢያደርግም ለአርሶ አደሩ ጥራቱን የጠበቀ ዘር እንዳይደርስ እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮች መኖራቸውንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ጉርሜሣ እንደገለጹት ዋነኛው ችግር ሕገ-ወጥ የዘር ንግድ ነው:: ዘር ያልሆነውን እህል “ዘር ነው” ብለው በማታለል ለአርሶ አደሩ የሚሸጡ አካላት መኖራቸው ትልቅ ፈተና ሆኗል:: ሕገ-ወጥነትን በጋራ በመከላከል አርሶ አደሩ የልፋቱን ዋጋ እንዲያገኝ መሥራት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት ነው:: በተጨማሪም አምራቾች ዘሩን መጋዘን ካስገቡ በኋላ ቶሎ ወደ ላብራቶሪ ወስደው አለማስመርመር እና የመጋዘን አያያዝ ችግሮች የዘሩን ጥራት ይቀንሱታል::
ለአርሶ አደሩ የሚቀርብ ማንኛውም የግብርና ምርት “እውነተኛ ዘር” ተብሎ ሊጠራ የሚችለው ሕጋዊ የዘር መለያ ምልክት (ታግ) ሲኖረው ብቻ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል:: ከዚህም ባሻገር አንድን ምርት ትክክለኛ ዘር የሚያሰኘው እና ወሳኙ መለያ ናሙናው በላብራቶሪ ተፈትሾ እና በሚመለከተው ባለሥልጣን የጥራት ቁጥጥር ማለፉን የሚያረጋግጠው በመጨረሻ የሚለጠፈው ምልክት (ታግ) ነው:: ይህንን የጥራት ቁጥጥር ሥርዓት ይበልጥ ተፈጻሚ ለማድረግም አከፋፋዮች ሕጋዊ መለያ የሌለውን ዘር እንዳይረከቡ ጥብቅ መመሪያ የተላለፈ ሲሆን እስካሁንም ለ500 ያህል አከፋፋዮች ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል::
በመሆኑም የጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣኑ ኃላፊነት ዘሩን መርምሮ ማስረጃ (ሰርተፍኬት) እስከመስጠት ቢሆንም ከዚያ በኋላ ባለው የስርጭት ሂደት ላይ የሁሉም አካላት ርብርብ ያስፈልጋል::
ዩኒየኖች፣ ህብረት ሥራ ማህበራት እና ነጋዴዎች ዘሩን በትክክል ለአርሶ አደሩ ማድረስ አለባቸው:: በተለይም ሕገ-ወጥ ዘር አዘዋዋሪዎችን ለመቆጣጠር የፖሊስ፣ የንግድ ቢሮ እና የሌሎችም ሕግ አስከባሪ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር እጅግ ወሳኝ መሆኑን ዳይሬክተሩ በአጽንኦት አሳስበዋል::
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የዘር ብዜት ባለሙያ አቶ ጥላዬ ሞገስ በበኩላቸው በ2017/18 የምርት ዘመን በክልሉ 15 ሺህ 787 ሄክታር መሬት በዘር ብዜት ለመሸፈን ታቅዶ 10 ሺህ 606 ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል:: በጥራትና ቁጥጥር ፍተሻ (ኢንስፔክሽን) ያለፈ 232 ሺህ 589 ኩንታል ምርጥ ዘር ተገኝቷል:: እስካሁንም መሰብሰብ የተቻለው 170 ሺህ 536 ኩንታል መሆኑን አብራርተዋል::
በክልሉ አሁን ላይ በዋናነት እየተባዙ ያሉት የጤፍ፣ የስንዴ፣ የበቆሎ እና የማሽላ ዝርያዎች ናቸው:: ይሁንና አርሶ አደሩ ለጥራጥሬ ሰብሎች (እንደ ባቄላ እና አተር)፣ ለቢራ ገብስ እንዲሁም ለምግብ ገብስ ያለው የዘር ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም በበቂ ሁኔታ ማቅረብ አልተቻለም:: በተጨማሪም እንደ ሊሙ ያሉ የበቆሎ ዝርያዎችን አርሶ አደሩ አጥብቆ የሚፈልግ ቢሆንም ከዘር መነሻ (Primary Seed) እጥረት ጋር በተያያዘ ፍላጎቱን ማሟላት ፈተና እንደሆነ ጠቁመዋል:: አርሶ አደሩ የሚፈልገውን ዘር በበቂ ሁኔታ ማባዛት ባለመቻሉ የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም መኖሩን ጠቅሰዋል::
በሌላ በኩል ከውጭ የሚገቡ የድቅል (Hybrid) በቆሎ ዘር ዝርያዎች (እንደ ሊሙ፣ ፓዮነር፣ ዳሞት፣ ሾኔ ያሉት) ምርታማነታቸው ከፍተኛ ቢሆንም የዋጋቸው መወደዱ ለአርሶ አደሩ ሌላኛው ፈተና ሆኗል:: ይህን ችግር ለመፍታት የባኮ ድቅል ዘሮችን (እንደ 661፣ 546፣ 49) በስፋት በማባዛት አማራጭ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑ ተጠቁሟል::
በዘርፉ ከፀጥታ ችግር በተጨማሪ ዋነኛው ማነቆ ሆኖ የተገኘው የሕገ-ወጥ ዘር ዝውውር ነው:: የጥራትና ቁጥጥር ፍተሻ ያላለፉ እና ምንጫቸው ያልታወቁ ዘሮች በሕገ-ወጥ መንገድ እየተሸጡ በመሆኑ በአርሶ አደሩ ምርታማነት ላይ ትልቅ ስጋት ደቅኗል:: በተለይም አሁን ላይ ያለውን የመሬት አቅርቦት ችግር ለመፍታት በኮንትራት እርሻዎችን (Contrat Farming) በስፋት ለመጠቀም ታቅዷል:: ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመርም በዘር ብዜት ላይ ማሕበራት፣ ጥራትና ቁጥጥር፣ የዘር አባዥ ኢንተርፕራይዞች በቅንጅት ጠንካራ ሥራ ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል::
ባለሙያው ለአርሶ አደሮች እና ለሚመለከታቸው አካላት ጥብቅ መልእክት አስተላልፈዋል:: “ዘር ሕይወት ነው:: ዘሩ ጥራቱን የጠበቀ ካልሆነ የመሬት ዝግጅቱና ድካሙ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ሊቀር ይችላል:: ስለዚህ አርሶ አደሩ የጥራት ማረጋገጫ ምልክት ያላቸውን እና በትክክል የተመረመሩ ዘሮችን ብቻ በመጠቀም ከኪሳራ ሊድን ይገባል::” አርሶ አደሩ ለሚያወጣው ወጪ እና ለሚያፈሰው ጉልበት ተመጣጣኝ ምርት ማግኘት የሚችለው ትክክለኛ እና ጥራቱ የተረጋገጠ ዘር ሲቀርብለት ብቻ መሆኑን ነው ባለሙያው የተናገሩት::
መረጃ
የኢትዮጵያ የ2018/19 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት
@ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈፅሟል።
@ ዓመታዊ የማዳበሪያ ፍላጎት ከ15 እስከ 16 ሚሊዮን ኩንታል ነው።
@ በአሁኑ ወቅት ከ21 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ክምችት አለ።
@ በፍጥነት ለተጠቃሚው ለማሠራጨት ከመኪና በተጨማሪ ባቡር በማጓጓዣነት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።
ምንጭ፦ ግብርና ሚኒስቴር
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


