የአማራ ክልል የጠበቆች ማሕበር መመሥረቱ ይታወቃል። ማሕበሩ የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባዔ በክልሉ የፍትሕ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጉዞ የሚያጠናክር ታሪካዊ ኩነት እንደሆነ ተነግሯል።
ጉባዔው መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ነበር የተካሄደው። በዚህም በክልሉ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሕግ ባለሙያዎችን የፍትሕ ተቋም መሪዎችን እና ጥሪ የተደረገላቸውን እንግዶች በአንድ መድረክ ያሳተፈ ነበር።
የማሕበሩ ምሥረታ በክልሉ የወጣውን የአማራ ክልል የጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 293/2017 ዓ.ም ተከትሎ የመጣ ነው። ይህም ለጠበቆች ሙያዊ ነፃነት እና ለፍትሕ ሥርዓቱ መጠናከር እንደ ትልቅ ድል የሚቆጠር እርምጃ ነው።
ጉባዔው ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የጠበቆችን መብት እና ጥቅም ማስከበር አንዱ ነው። ለረጅም ጊዜ በክልሉ የሚገኙ ጠበቆች በራሳቸው የሚመራና ድምጻቸውን የሚያሰማ ጠንካራ ተቋም ባለመኖሩ ምክንያት ለተለያዩ ሙያዊ ጫናዎችና ተግዳሮቶች ተጋልጠው ቆይተዋል። ይህ ደግሞ የፍትሕ ሥርዓቱ እንዳይሻሻል መሰናክል ሆኖ መቆየቱ ተመላክቷል።
የማሕበሩ መመሥረት ታዲያ ጠበቆች በነፃነት ሙያቸውን እንዲያከናውኑ፣ ጥቅማቸው እንዲከበር እና በማናቸውም የሕግ እና የአስተዳደር ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም እንዲኖራቸው ያስችላል። ጠበቆችም ለደንበኞቻቸው የሚሰጡት አገልግሎት ጥራት እንዲጨምር እና የዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብት ይበልጥ እንዲከበር መንገድ ይከፍታል ነው የተባለው።
በምሥረታው እንደተነሳው የማሕበሩ መመሥረት ለሙያ ስነ-ምግባር መከበር የጎላ ፋይዳ አለው። የጥብቅና ሙያ ከግል ጥቅም ይልቅ ለፍትሕ መቆምን ያስቀድማል።
የጉባዔው ተፋታፊዎች እንሉት የማሕበሩ መመሥረት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል የጎላ ድርሻ ይኖረዋል፤ ማሕበሩ ደግሞ አባላቱ የሙያ ስነ-ምግባር ደንቦችን እንዲያከብሩ፣ በታማኝነት እና በቅንነት እንዲሠሩ እንዲሁም ሕዝባዊ ወገንተኝነት እንዲኖራቸው የማድረግ ኃላፊነት ይኖርበታል።
ይህ ካልሆነ ግን የፍትሕ ሥርዓቱ በሕዝብ ዘንድ ያለውን አመኔታ ሊያጣ እንደሚችል ነው ተሳታዎቹ የጠናሩት። ማሕበሩ የዲሲፕሊን ኮሚቴና የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ጥፋት የሚፈጽሙ አባላትን በማረም ሙያውን ከብክለት የመጠበቅ ስልጣን ይኖረዋል። ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታዲያ ለፍትሕ ሥርዓቱ መሻሻል ሚናው የጎላ እንደሚሆን ነው ዕምነት የተጣለበት፡፡
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም መንግሥት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን እና ግልጽነት የተሞላበት ለማድረግ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰዋል። በተለይ አዋጅ ቁጥር 293/2017 ዓ.ም መውጣቱ ጠበቆች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ እና ከመንግሥት ተጽዕኖ ነፃ የሆነ ማሕበር እንዲመሠርቱ ሕጋዊ መሠረት እንደጣለ አክለዋል።
ማሕበሩ ጠንካራ ሆኖ እንዲወጣ ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ እና በፍትሕ ማሻሻያ ሥራዎች ላይም ማሕበሩን እንደ ዋና አጋር እንደሚመለከተው አረጋግጠዋል። ይህም በመንግሥት እና በጠበቆች መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ አዲስ የትብብር ደረጃ ያሸጋግረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ጉባዔው ከስሪ አር (3R) ከተሰኘ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ነው የተዘጋጀው፤ ይህም ማሕበሩ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ከልማት አጋሮች ጋር በቅንጅት ለመሥራት መልካም አጋጣሚ ነው። ፕሮጀክቱ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እና የፍትሕ ተቋማትን አቅም ለመገንባት የሚሠራ መሆኑ ተጠቁሟል፤ ወደፊትም ማሕበሩ የአባላቱን አቅም ለመገንባት የሚያስችሉ የተለያዩ ስልጠናዎችን፣ የልምድ ልውውጦችን እና የምርምር ሥራዎችን ከነዚህ አጋሮች ጋር በመሆን እንደሚያከናውን አቶ ብርሃኑ ጎሽም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ሙሉዓለም ቢያዝን በበኩላቸው “ጥብቅና ለፍትሕ ሥርዓቱ ወሳኝ በመሆኑ በላቀ የሙያ ስነምግባር መመራት አለበት” ብለዋል። ሕብረተሰቡን በተገቢው መንገድ የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ ጠበቆች የድርሻቸውን ለመወጣት ሲደክሙ መቆየታቸውን አቶ ሙሉዓለም አንስተዋል።
አንዳንድ ሰዎች የፍትሕ ሥርዓቱ በተዛባ ሁኔታ እንዲታይ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው የገለጹት አቶ ሙሉዓለም “በተፈጠረ የጋራ መድረክ ከነዚህ ችግሮች ወጥቶ በመልካም ስነ ምግባር ሥራውን በመሥራት የሕብረተሰቡን የዳኝነትና የፍትሕ አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ እንዲገኝ መግባባት ላይ ተደርሶ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል” ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ጠበቆች ማሕበር ከተመሠረተባቸው ዋና ዋና ዓላማዎች አንዱ ለሕብረተሰቡ ነፃ የሕግ እርዳታ (Pro Bono Service) መስጠት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንዳቸው ሥራው ናቸው። ይህ አገልግሎት በተለይ አቅም ለሌላቸው ዜጎች፣ ሴቶች፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ፍትሕ እንዳይጓደልባቸው ለማድረግ ታስቦ የተዘረጋ ሥርዓት እንደሆነ ገልጸዋል።
ሌላው የማሕበሩ ዋና ተግባር የሕግ ግንዛቤ ማስጨበጥ ስለመሆኑ አንስተዋል። ዜጎች ስለ መብቶቻቸውና ግዴታዎቻቸው በቂ ዕውቀት እንዲኖራቸው በማድረግ ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት ሳይሄዱ በድርድርና በእርቅ እንዲያልቁ ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣል። ይህ ተግባር በፍርድ ቤቶች ላይ የሚፈጠረውን የሥራ ጫና ከመቀነሱም በላይ ማሕበራዊ ሰላምን ለማስፈን ትልቅ ሚና ይጫወታል። ማሕበሩ ደግሞ “ይህን አገልግሎት በበጎ ፈቃደኝነት ለሚሰጡ ጠበቆች የዕውቅና እና የማበረታቻ ሥርዓት ይኖረዋል” ብለዋል።
በጉባዔው ማጠቃለያ ላይ የማሕበሩ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የቦርድ አባላት ምርጫ ተካሂዷል። ተመራጮቹም ማሕበሩን በታማኝነት ለመምራትና የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ቃል ገብተዋል።
በጉባዔው ሰባት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ ፕሬዝደንትና ምክትል ፕሬዜደንት ተመርጧል።
መረጃ
“ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብታችን የሚረጋገጥበት ነው” ነዋሪዎች
የተሸለ ሊሰራላቸው ዪችለውን ወኪል ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን በደቡብ ጎንደር ዞን የፋርጣ ወረዳ ነዋሪዎች ተናግረዋል፤ ምርጫ የዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብት የሚረጋገጥበት መሆኑን ያነሱት ነዋሪዎቹ ለሀገራችን ይበጃል የሚሉትን ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ማውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሐሳባቸውን ለአሚኮ የሰጡ የፋርጣ ወረዳ ነዋሪዎች ሊያስተዳድራቸውና የልማት ጥያቄዎችን የሚመልስላቸውን ፓርቲ ለመምረጥ ድምፅ በመስጠት ዲሞክራሲዊ መብታቸው እንደደሚጠቀሙ ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ መረጃን በመከተታል የምርጫ ቀኑ እስኪደርስ እርስ በእርሳቸው እየተወያዩ እንደማቆዩ ነው የገለፁት።
በተለይ ሴቶች የምርጫ ካርድ በመውሰድ የምርጫና የልማት ተሳትፏቸውን ከፍ የሚያደርጉበት መሆኑንም ነዋሪዎቹ አክለዋል።
የምርጫ ካርዱንም ድምፅ እሰከሚሰጡበት ዕለት በጥንቃቄ መያዝ እንዳለባቸውም መክረዋል።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


