“የተባበረ ሃሳብ ለተሻለ ውጤት”

0
81

በተቻለ መጠን የሀገር ውሥጥ ምርቶችን እና እቃዎችን በመጠቀም ሥለሚሠሩ የንግድ ስማቸውን “ቪንቴጅ” (የድሮ) በሚል  ሥያሜ ሰጥተውታል:: የሥራ ቦታቸው በባሕርዳር ከተማ በዳግማዊ ሚኒሊክ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ልደታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው::

በ”ቪንቴጅ” የሚሠሩት የህፃናት ቦርሳ፣ የምሳ ዕቃ መያዣ፣ ሻንጣዎች፣ የሴቶች ቦርሳዎችን በመሥራት የሚሸጡበት ሲሆን “ቪንቴጅ”  ኬክ ቤት ደግሞ ኬክ እና ጣፋጭ  ነገሮች የሚሸጡበት ነው::

ወጣቶቹ ቤዛዊት አጥናፉ፣ ሄርሜላ ኃይለማርያም ፣ቃልኪዳን አለኸኝ  እና አፎሚያ ቢሆነኝ ይባላሉ:: ትውልድ እና ዕድገታቸው በባሕር ዳር ከተማ ሲሆን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሲማሩም በጓደኝነት በጋራ ነው የተማሩት:: ወደ ዩንቨርሲቲ ሲገቡ ግን ቤዛዊት ባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ ኃይድሮሊክስ፣ ሄርሜላ በፓሊ ድራፍቲንግ፣ ቃልኪዳን በአርክቴክት ፣አፎሚያ ደግሞ መቱ ዩንቨርሲቲ በአግሪካልቸር  ትምህርታቸውን በተለያየ መንገድ እና መሥክ ተከታትለው ተመርቀዋል::

በ2012 ዓ.ም ግን ከምርቃት በኋላ በጋራ በመሆን ሥራዎችን ለመሥራት ተስማምተው በቀላሉ ሃይፐር ሲኒማ ውስጥ ህፃናት ፊት ላይ የተለያየ ዲዛይን ያላቸው የፊት ቀለም በመቀባት ሥራን በጋራ ጀመሩ:: ሥራው ጥሩ እንደነበረ የሚያስታውሱት ወጣቶቹ የኮረና መከሰት ምክንያት ግን ሥራውን መቀጠል ስላልቻሉ ተቋረጠ::

ቤታቸው በተቀመጡበት ወቅት ግን በርቀት የማኔጅመንት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል:: በተጓዳኝም ከ2013ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በዓላት ሲመጡ በተለይ ለአዲስ ዓመት በቤታቸው ሆነው በጋራ የአደይ አበባ ጌጣጌጦችን ለፀጉር፣ ለጆሮ እና ለአንገት በመሥራት ሲሸጡ ቆይተዋል::

የቡድኑ አባል የሆነችው ሄርሜላ ኃይለማርያም እንደምትገልፀው በዩንቨርሲቲ ቆይታቸው የተማሩት የተለያየ የትምህርት ዘርፍ ቢሆንም ሥራ ለመሥራት ባላቸው ዝንባሌ እና ፍላጎት እንዲሁም የየራሳቸውን የግል ችሎታ በማቀናጀት ሊሠሩት የሚችሉትን ነገር በማመቻቸት ቆይተው እንደየ ዝንባሌአቸው ሁለቱ ወደ ፋሽኑ ስለሚያደሉ የልብስ ስፌት ስልጠና ለሦስት ወራት ሲሠለጥኑ፣ ሁለቱ ደግሞ የኬክ መጋገር ሥልጠናን አዲስ አበባ ከተማ ተምረው እና የተወሰነ ጊዜ እዛው ሥራ ሠርተው ችሎታቸውን አዳብረው በመመለሥ ሁለቱንም ሥራ በጋራ ለመሥራት በጋራ እና በግል ሠርተው ያጠራቀሙትን ብር 20 ሺህ በማዋጣት እና ቤተሠብ ድጋፍ አድርጎላቸው  በ100 ሺህ ብር የኬክ መጋገሪያ ገዝተው ሥራ ጀመሩ::

ሄርሜላ እንደምትለው ኬክ ቤቱ ሲከፈት  ምንም እንኳን መኖሪያ ሰፈር አካባቢ ቢሆንም ሰዎችን በመጋበዝ  አንዱ አንዱን እያመጣ በማሳየት እና በሚቀርበው አገልግሎት ተደስቶ ከኬክ ሽያጭ በተጨማሪ ለሰርግ፣ለልደት፣ እና ለከተለያዩ ዝግጅቶች የኬተሪንግ /የተለያዩ ጣፋጮችን/ የማቅረብ አገልግሎት መሥጠት ጀምረዋል::

የቦርሳ ሥራውንም ሱቅ በመክፈት ጎን ለጎን ማሳለጡን ተያያዙት ይገኛሉ:: “ነገሮችን ለማስተካል ወደ አራት ወር ፈጅቶብናል”፤ የምትለው ሄርሜላ  ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ሁለቱንም ሥራዎች ቀን እና ሌሊት በጋራ ሠርተው ማቅረብ መጀመራቸውን ነው የተናገረችው::

ታዲያ ሁለቱንም ሥራ ቀንም ሆነ ለሊት ሢሠሩ አምሽተው በቅርብ ከሚገኘው የአንዷ ባልደረባው ቤተሰብ ቤት ነበር የሚያድሩት::

ብዙ ሰዎች በጋራ ሥራ ጀምረው በጋራ  ለማደግ አስበው ከገቡ በኋላ ሥምምነት ጠፍቶ የተበተኑ ማህበራት ብዙ ናቸው:: እና እናንተስ ጋ በጋራ ሥትሠሩ አለመግባባት የለም ወይ ? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄም  ሄርሜላ ስትመልስ “የተባበረ ሃሳብ የተሻለ ውጤት ይኖረዋል፤ የተለያየ ሃሳብ ይኖራል እነዛን ሀሳቦች ግን በማቀናጀት ጥሩ ውጤት ማግኘት ይቻላል እኛም ይህንኑ ነው ያደረገነው፡፤” ትላለች:: በነሱ መካከል ያለው  ያአንዱ የጨርቅ መቁረጥ ችሎታ ቢሆን፣ ሌላዋ ትሰፋለች፣ ሌላዋ ገበያውን ፈልጋ ታመጣለች:: ሁሉም የቡድኑ አባላት  የየራሳቸውን እውቀት እና ችሎታ ተጠቅመው የሚፈለገውን ጥሩ ውጤት በጋራ በመሥራት አምጥተዋል::

በኬኩም ቢሆን ገና ብዙ  ያልተሠራበት ዘርፍ በመሆኑ የተሻለ እና ተመራጭ ለመሆን ሀገር አቀፍ ሁኔታዎችን በማህበራዊ ሚዲያ ተከታትሎ አዳዲስ ሃሳቦችን ጨምሮ በመሥራት ውጤታማ ለመሆን እየጣሩ እንደሚገኙ ነው፤ ወጣቷ የገለጸችልን::

በቦርሳ ሥራውም ቢሆን ሥራቸውን በባዛሮች በማስተዋወቅ ጥሩ እይታ ማግኘቱን ገልፃ ይህም በቀጣይ  ጋርመንት በመክፈት የህፃናት ልብሶችን የማምረት ትልቅ ህልም እንዲሠንቁ ማድረጉን ነው የገለጸችው::

“አራት ሰዎች በመሆናችን አራት አይነት ዕይታ እና ሃሳብ እንዲመጣ በማድረግ ብዙ ጥቅም አግኝተናል በደንብም እንተዋወቃለን” የምትለው ሄርሜላ ሁለቱም ሥራዎቻቸው በፍላጎት እና  ፍቅር የሚሠሩ ከመሆኑ ባሻገር ዘርፎቹ እንደ ሀገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጅ ብዙ መሠራት የሚቻልባቸው በመሆኑ ቶሎ እንደሚያድጉ ነው የምትገልፀው::

ሥራቸውን ሲጨርሱ በብዛት የሚያድሩባት የቃልኪዳን እናት ወ/ሮ አበባ ፀሃይነህ ልጆቻቸው እነሱ ከመተዋወቅ አልፈው ቤተሰብም እንዲቀራረብ መንገድ ሆነዋል ያላሉ::

የተወሰነ ገንዘብ መስጠት እና የበለጠ መደገፍ የሚችሉበት አጋጣሚ ቢኖር ከመደገፍ ወደ ኋላ እንደማይሉ የሚገልጹት ወ/ሮ አበባ   በልጆቹ ሥራ እና አቅም ትልቅ እምነት እንዲያሳድሩ የሚያደርግ አሳማኝ እንቅስቃሴ እና የሥራ ትጋት እንዳላቸው ነው የሚገልፁት::

ለዛ

 

“በሕይወትህ ከዚህ በፊት ያልነበረህ አዲስ ነገር ለማግኘት ከፈለክ፣ አዲስ ሠርተኸው የማታውቀውን ሥራ ለመሥራት መፍቀድ ይኖርብሀል፡፡”

ቶማስ ጄፈርሰን

“እውቀት ብቻ አይበቃም ተግባራዊ ካልተደረገ በስተቀር፣ ፍቃደኛነት ብቻ አይበቃም ካልተሠራ በስተቀር፡፡”

ብሩስ ሊ

“በምድር ላይ ትልቁ አስደሳች ነገር ሰዎች አትችልም ያሉህን ሠርተህ ማሳየትህ ነው፡፡”

ዋልተር ባግሆት

“ወንዝ ድንጋይ ቦርቡሮ የሚገባው ሀይለኛ ስለሆነ ሳይሆን ያለማቋረጥ ስለሚፈስ ነው፡፡”

ጂም ዋትኪንስ

 

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here