ከዓለም አቀፉ የእርሻ ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው እ.አ.አ በ2050 የዓለማችን ሕዝቦች የምግብ ፍላጎት 30 በመቶ ይጨምራል፤ ለዚህ መሠረታዊው ምክንያት ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው ፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገት ነው።
በሌላ በኩል የሕዝብ ቁጥር መጨመሩ የመኖሪያ ቤት፣ የማገዶ እና መሰል ፍላጎቶች አብረው ይጨምራሉ። በመሆኑም ለእርሻ የሚውለው መሬት ለእነዚህ ፍላጎቶች ማሟያ ይውላል። ይህም የምግብ ፍላጎትን በቂ ለማድረግ ፈተና ይሆናል።
በመሆኑም የግብርና ሥራን ማዘመን እጅግ ወሳኝ መሆኑን ነው ድርጅቱ የሚያስገነዝበው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚጠቀሱት ደግሞ በዋናነት የአፍሪካ ሀገራት ሲሆኑ የኢትዮጵያ ግብርናም ከዕድሜው ጋር ካልዘመኑት መካከል አንዱ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ33 በመቶ በላይ የሀገሪቱን የግብርና ምርት አቅርቦት የሚሸፍነው የአማራ ክልል ነው። ከሰፊ የእርሻ መሬት በተጨማሪ ሁሉንም የአየር ንብረት ባለጸጋ መሆኑም ሁሉንም የግብርና ምርቶችን እንዲያመርት አስችሎታል።
ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በሄክታር የሚገኘው የምርት መጠን ጭማሪን እያሳዬ ነው፤ ለዚህ ደግሞ የባለሙያ ድጋፍ እና የግብዓት አጠቃቀም ድርሻ የጎላ ነው።
ይህን መነሻ በማድረግ የክልሉን የ2018/19 የመኸር እርሻ ዝግጅት በተመለከተ የሚመለከታቸውን አናግረናል:: ሐሳባቸውን በስልክ ያካፈሉን አርሶ አደሮች እንዳሉት የማሳ ማለስለስ ሥራቸውን እያከናወኑ ነው። የተፈጥሮ ማዳበሪያም እያዘጋጁ ነው።
የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም መጀመራቸው ትልቅ ለውጥ እንዳስገኘላቸው የነገሩን በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ግዛቸው አዲስ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ማሳቸውን እያለሰለሱ መሆኑን ያነሱት አርሶ አደሩ ሰው ከዓመት ዓመት ምርታማነታቸው እያደገ መሆኑን አክለዋል:: ለዚህም የግብዓት አጠቃቀማቸው እና የባለሙያን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ ማድረጋቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡
ቀደም ብሎ ማዳበሪያው መሰራጨቱ የዘር ሥራውን በወቅቱ ከማከናወን ባለፈ ለአርሶ አደሩ ምርታማነቱን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አክለዋል። አርሶ አደሩ አክለውም መንግሥት ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያን በነጋዴ እጅ ሳይገባ በቀጥታ ከዩኒየኖች እንዲያገኙ በማድረግ ከተጨማሪ ወጪ ማዳን እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
ሌላው ሀሳባቸውን ያጋሩት በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የግብዓት አቅርቦት ቡድን መሪ አቶ አምደ ወርቅ ልዬው የ2018/2019 የምርት ዘመን ከ478 ሺህ ኩንታል በላይ ለመኸር ሰብል የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ገቢ በማድረግ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ 50 ሺህ የበቆሎ ምርጥ ዘር በማስገባት ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ መሆኑንም ቡድን መሪው ገልፀዋል።
አቶ አምደወርቅ እንዳሉት ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች ከስምንት ሺህ በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቷል:: የአፈር ማዳበሪው በሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ሳይበዘበዝ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ ነው::
አርሶ አደር አንዱዓለም አዳሙ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የጓጉሳ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ እንደተናገሩት የግብዓት አጠቃቀማቸው እያደገ መምጣቱ እና የግብርና ባለሙያዎችን ሙያዊ ምክር መተግባራቸው ውጤት አስገኝቶላቸዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ማሳቸውን በማለስለስና ግብዓቶችን በመሰብሰብ ለመኸር እርሻ እየተዘጋጁ ነው።
በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ የግብርና ግብአቶች አቅርቦት ቡድን መሪ ወ/ሮ አበራሽ አስማረ የመኸር እርሻ ዝግጅትን በተመለከተ ሐሳብ ሰጥተውናል:: እንደ ቡድን መሪዋ ማብራሪያ በበጀት ዓመቱ ከ841 ሺህ በላይ ኩንታል ዳፕ እና ዩሪያ ለማቅረብ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፤ ከዚህ ውስጥ 341 ሺህ ያህሉ (40 ነጥብ አምስት በመቶ) መቅረቡን ነው የተናገሩት::
ወ/ሮ አበራሽ እንድገለጹት የግብዓት አቅርቦቱም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ነው:: ይህንን ግብዓት ወደ አርሶ አደሩ ቀዬ ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ ነው:: ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች የተሻለ ስርጭት መኖሩንም ጠቁመዋል:: ለአብነትም ከ75 ሺህ በላይ ኩንታል ዳፕ እና ከ40 ሺህ በላይ ኩንታል ዩሪያ መሰራጨቱን አንስተዋል::
ቀሪውን በወቅቱ ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ያነሱት ቡድን መሪዋ ከአፈር ማዳበሪያ በተጨማሪም ከ28 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ ምርጥ ዘሮችን በማቅረብ ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጭ ነው የተናገሩት::
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ ለአሚኮ በሰጡት መረጃ የ2017/18 የምርት ዘመን ስኬታማ እንደነበር አስታውሰዋል። ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል። ምርታማነት በሄክታር ከነበረበት ከ32 ነጥብ ሁለት ኩንታል ወደ 34 ነጥብ ዘጠኝ ኩንታል ማድረስ መቻሉንም ነው ያብራሩት።
ለክልሉ ዕድገት የግብርናው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ቢሮ ኃላፊው ለክልሉ የኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ የሚወስደው ግብርና መሆኑን አንስተዋል። በቀጣይም ማርታማነትን ከዚህ በላይ ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2018/19 የመኸር ምርት ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱን አስታውቀዋል፤ ከዚህ ውስጥ 46 በመቶ ያህሉ ወደ ክልሉ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ግብዓትን በወቅቱ እና በፍትሐዊነት ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱንም የተናገሩት አቶ ደረጀ ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱንም አንስተዋል። ግብዓት ያለምንም ችግር ወደ አርሶ አደሮች እንዲደርስ የጸጥታ አካላት በትኩረት እየሠሩ ስለመሆኑም ተናግረዋል። ግብዓትን በወቅቱ ለማቅረብ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ መሆኑንም ነው ያብራሩት። የሚመለከታቸው አካላት ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ብቻ ጥገኛ መኾን እንደማይገባ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የነዳጅ ዋጋ መናር እና እጥረት የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ ተደራሽ እንዳይሆኑ እንቅፋት ሆኗል፤ ችግሩን ለመቀስ ደግሞ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በአግባቡ መጠቀም ይገባል፤ ከዚህ በተጨማሪም ግብዓት ለሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ቅድሚያ እንዲሠጣቸው መደረጉን ቢሮ ኃላፊው አቶ ደረጀ ማንደፍሮ ተናግረዋል።
የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ከተረጅነት መውጣት እንደሚገባም የገለጹት ኀላፊው ከተረጅነት ለመውጣት ደግሞ ምርታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል” ነው ያሉት። መሬት ጦም ማደር እንደሌለበትም ተናግረዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) “በቆራጥነት በመሥራት ተረጅነትን ታሪክ ማድረግ ይገባል” ነው ያሉት። ለዚህ መሠረቱ ደግሞ ምርታማትን ማሳድግ ነው፤ “ምርጥ ዘርን ለማዳረስ እተሠራ ነው” ብለዋል።
“ከንግግር ባሻገር መሬት ላይ የሚታዩ፣ የአርሶ አደሮችን ሕይወት የሚቀይሩ ሥራዎችን መሥራት ይገባል” ያሉት ዶክተር ድረስ አርሶ አደሮችን ለምርታማነት ማቀናጀት እና ማስተሳሰር እንደሚገባ ተናግረዋል። የማሳ ዝግጅትን ከወዲሁ ማጠናቀቅ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል። አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እንዲያለሙ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
“ባለፈው ዓመት ካስቀመጥነው ግብ በላይ ማሳካት ችለናል” ያሉት ዶክተር ድረስ 187 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ 188 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።
በ2018/19 የመኸር ምርት አምስት ነጥብ 58 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 205 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱን ገልጸዋል። ምርታማነትን በሄክታር ለማሳደግ እና ዕቅዱን ለማሳካት ብርቱ ጥረት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
(ሰናይት በየነ)
በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


