መንቆረር

0
110

እንድማጣ ማርያም ከደጇ ደርሼ፣

ወይ እድለቢሱ መጣሁ ተመልሼ፤

ተብሎ የተዘፈነላት በኢትዮጵያ የታሪክ ድርና ማግ ውስጥ የምሥራቅ ጎጃም ዋና ከተማ የሆነችው ደብረ ማርቆስ በጥንታዊ ስሟ “መንቆረር” የራሷ የሆነ ወጥ እና ጥልቅ መገለጫ ያላት ከተማ ናት። ከመዲናዋ አዲስ አበባ በሰሜን አቅጣጫ 304 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው መንቆረር ከባሕር ዳር 254 ኪሎ ሜትር ላይ ትገኛለች። መንቆረር ለዘመናት የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የጥበብ እና የንግድ ማዕከል ሆና አገልግላለች። መንቆረርን ማወቅ ማለት የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ጉዞ፣ የጀግንነት ታሪክ እና የኪነ-ጥበብ ጥልቀትን በአንድ ላይ መመልከት ማለት ነው።

በ1845 ዓ.ም አካባቢ በደጃች ጎሹ ዘመን በገጠር መንደርነት ተጀምራ በደጃዝማች ተድላ ጓሉ ወደ ከተማነት እንዳደገች ይነገራል፤ ቀደምቷ መንቆረር የአሁኗ ደብረ ማርቆስ ከተማ።

በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው የከተማዋ ስያሜ የተሰጠው አካባቢውን  በርስትነት ያሥተዳድሩ በነበሩት “ሳርን” በተባሉ ባላባት ልጆች በአንደኛው ስም “መንቆረር”  እንደሆነ ይነገራል።

መንቆረር የሚለው ስያሜ ወደ ደብረ ማርቆስ የተቀየረው ደግሞ በንጉሥ ተከለ ሃይማኖት ነው።  ይህም ዐፄ ዮሐንስ በ1873 ዓ.ም ከነበሯቸው አራት ጽላቶች የቅዱስ ሚካኤልን ለራሳቸው በማስቀረት፣ የቅዱስ ጊዮርጊስን ለንጉሥ ምኒልክ፣ የቅድስት ማርያምን ለአማራ ሳይንት እና የቅዱስ ማርቆስን ለንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከመስጠታቸው ጋር ይያያዛል፡፡

ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከንጉሠ ነገሥቱ የተሰጣቸውን የመልዕልተ አድባር ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን መንቆረር እንዲተከል አደረጉ።

ቤተ ክርስቲያኑ “መልዕልተ አድባር ደብረ ማርቆስ” ተብሎ እንዲሰየም በመወሰን  ሕዝቡ አዲሱን የከተማ ስያሜ እንዲቀበለው በአዋጅ አስነገሩ፡፡ ከአዋጁ በኋላ የከተማዋ እና አካባቢው ስያሜ ቀስ በቀስ ደብረ ማርቆስ በሚል ሥም እየተጠራ ሄደ።

ደብረ ማርቆስ ከተማ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በጥር ወር 1872 ዓ.ም ከነገሡ በኋላ በ1874 ዓ.ም በተተከለው የቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ስያሜውን አግኝቶ  እስካሁን ድረስ እየተጠራ ይገኛል፡፡

ደብረ ማርቆስ በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ጎጃም፣ ዳሞት፣ አገው ምድር እና ባሕር ዳር አካባቢ ተብለው ሲጠሩ የነበሩት ግዛቶችን በአንድ እንዲጠቃለሉ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ኢህአዴግ ሥልጣን እስከ ያዘበት ዘመን ድረስ የጎጃም አሥተዳደር ዋና ከተማ በመሆን ለረጅም ዘመን አገልግላለች፡፡ አሁን ላይ ደግሞ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ሆና  በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡

ከተማዋ ስያሜዋን ያገኘችበት የቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቤተ መንግሥት እና አደባባይን ጨምሮ በርከት ያሉ የመስህብ ሀብቶች በደብረ ማርቆስ ይገኛሉ።

በዙሪያዋ ደግሞ እንደ አባ አስራት ገዳም፣ ውርግርግ ፋፋቴ፣ የዓባይ የተፈጥሮ ፍል ውኃ፣ ብሔረ ህያዋን ቅድስት ሥላሴ አንድነት ገዳም፣ ደብረ ገነት አቦ ቤተ ክርስትያን፣ አባ ፈቂህ ያሲን ክብረ በዓል፣ የደብረ ኤሊያስ ቤተ ክርስቲያን፣ አንቀጸ ብፁዓን ቅዱስ ላሊበላ አንድነት ገዳም፣ ሙቀት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን፣  እንዶዳም ኪዳነ ምህረት፣ አጋምና ጊዮርጊስ፣ የሞላሌ ዋሻ፣ የእግዜር ድልድይ እና  ቀቢ ፏፏቴ  የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ እና ባሕላዊ የመስህብ ቦታዎች እንደሚገኙ የአማራ ድንቅ ምድር መጽሐፍ መረጃ ያሳያል፡፡

የባህልና የሥነ-ጽሑፍ መፍለቂያ

መንቆረርን ከሌሎች ከተሞች ለየት የሚያደርጋት ትልቁ እሴቷ “የቅኔና የጥበብ ከተማ” መሆኗ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የቅኔ ትምህርት በከፍተኛ ደረጃ ከሚሰጥባቸው እና የሊቃውንት መፍለቂያ ከሆኑት አድባራት መካከል ደብረ ማርቆስ ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች። የከተማዋ ነዋሪ ከሕፃንነቱ ጀምሮ በቅኔ እና በቃላት ጨዋታ ታሽቶ የሚያድግ በመሆኑ አካባቢው ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ እጅግ ግዙፍ ነው።

የነዋሪው ማህበራዊ ባህል ደግሞ በእንግዳ ተቀባይነት እና በጨዋነት የተገነባ ነው። “የጎጃም ሰው” ሲባል በታማኝነቱ፣ በጀግንነቱ እና ለባህል ባለው ቀናኢነት ይታወቃል። በአካባቢው የሚዘወተሩት ባህላዊ ጭፈራዎች (በተለይም የጎጃም እስክስታ) የራሳቸው የሆነ የትከሻ እንቅስቃሴ እና ምት አላቸው።

የአመጋገብ ባህሏም ቢሆን ሌላው ሊጠቀስ የሚገባው ሀብት ነው። በጎጃም ማር እና ጠጅ የታወቀው የመንቆረር ማህበረሰብ እንግዳን ማክበርን እንደ ትልቅ ሃይማኖታዊ እና ሞራላዊ ግዴታ ይቆጥረዋል። በየቤቱ የሚዘጋጀው የገብስ ቆሎ፣ የሽንብራ እሸት እና ሌሎች የጥራጥሬ ምግቦች የአካባቢውን የግብር እና ምርታማነት የሚያሳዩ ናቸው።

የቱሪስት መስህቦች እና የተፈጥሮ ስጦታዎች

መንቆረር ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች በርካታ አማራጮችን የምታቀርብ ከተማ ናት። የከተማዋ የቱሪዝም አቅም በሦስት ዋና ዋና ዘርፎች ሊከፈል ይችላል፡- የታሪክ ቱሪዝም፣ የሃይማኖት ቱሪዝም እና የተፈጥሮ ቱሪዝም።

የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቤተ መንግሥት አንዱ ነው፤ ይህ በከተማዋ እምብርት ላይ የሚገኘው ታሪካዊ ስፍራ የ19ኛው ክፍለ ዘመን የህንፃ ጥበብ ማሳያ ነው። ቤተ መንግሥቱ ውስጥ የሚገኙት ጥንታዊ ቁሳቁሶች፣ የጦር መሣሪያዎች እና ንጉሣዊ አልባሳት የዘመኑን የሥልጣኔ ደረጃ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ።

የደብረ ማርቆስ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ሌላኛው መጎብኘት ያለበት ቅርስ ነው። ይህ ቤተክርስቲያን የመንፈሳዊ አገልግሎት ስፍራ ብቻ ሳይሆን ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት፣ በወርቅ እና በብር የተለበጡ መስቀሎችና የጥንት ሥዕላት የሚገኙበት ሙዚየምም ጭምር ነው። የህንፃው ቅርጽ እና በውስጡ ያሉት የግድግዳ ሥዕሎች የቱሪስቶችን ቀልብ ይስባሉ።

የጮቄ ተራራ ከከተማዋ ጥቂት ራቅ ብሎ የሚገኝ ድንቅ የተፈጥሮ ሀብት ነው፤ የጮቄ ተራራ የኢትዮጵያ “የውኃ ማማ” ተብሎ ይጠራል። ይህ ተራራ ከ4 ሺህ ሜትር በላይ ከፍታ ያለው እና ከ50 በላይ ወንዞች መነሻ ነው። ከ200 በላይ ምንጮችም የሚገኝበት አስገራሚ ስፍራ ነው። አካባቢው ለተራራ መውጣት (Trekking)፣ ለወፍ ዝርያዎች ምልከታ እና ለሥነ-ምህዳር ጥናት እጅግ ተስማሚ ነው። የተራራው ቅዝቃዜ እና አረንጓዴ ገጽታ ለጎብኚው ልዩ ሰላም ይሰጣል።

የአባይ ሸለቆ (Blue Nile Gorge) ከደብረ ማርቆስ ወደ አዲስ አበባ በሚደረግ ጉዞ ላይ የሚገኝ አስደናቂ ሸለቆ ሲሆን በዓለም ላይ ካሉ ታላላቅ ሸለቆዎች አንዱ ነው። ጥልቀቱ እና የተፈጥሮ ውበቱ እንዲሁም በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ታላቁ ድልድይ ለፎቶግራፍ አንሺዎች እና ለተፈጥሮ አድናቂዎች የማይታለፍ ስፍራ ነው።

ዛሬ ደብረ ማርቆስ (መንቆረር) ከመቼውም ጊዜ በላይ በፈጣን የዕድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች። በከተማዋ የሚገኘው የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢውን የምርምር እና የትምህርት ዘርፍ እያሳደገው ይገኛል። የግብርና ምርቶች ንግድ፣ በተለይም የቅባት እህሎች እና የጥራጥሬ ምርቶች ለከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ዋነኛ ሞተሮች ናቸው።

ይሁን እንጂ ይህች ታሪካዊ ከተማ ካላት አቅም አንጻር በቱሪዝም ዘርፍ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል። የታሪክ ቅርሶችን በአግባቡ መጠገን፣ የቱሪስት መረጃ ማዕከላትን ማስፋፋት እና የጮቄ ተራራን የመሰሉ ተፈጥሯዊ ሀብቶችን ለዓለም ማስተዋወቅ የከተማዋን ገቢና ዝና ከፍ እንደሚያደርገው ይታመናል።

መንቆረር የታሪክ ማስታወሻ ብቻ ሳትሆን በሕይወት ያለች እና የምትንቀሳቀስ የታሪክ፣ የባህል እና የጥበብ ሙዚየም ናት። የሊቃውንቱ ቅኔ የሚሰማባት፣ የጀግኖች ታሪክ የሚዘከርባት እና የተፈጥሮ ውበት የሞላባት ከተማ ናት። ማንኛውም ኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ ሀገር ዜጋ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ሲጓዝ በመንቆረር ጎራ ብሎ የጎጃምን እንግዳ ተቀባይነት ሳይቀምስ፣ ታሪካዊ ቤተ መንግሥቷን ሳይጎበኝ እና የጮቄን ንጹህ አየር ሳይተነፍስ ማለፍ ግማሽ ጉዞ እንደማድረግ ይቆጠራል። መንቆረር ትላንትን በዛሬ መስኮት የምናይባት ነገን ደግሞ በጥበብ የምናልምባት የኢትዮጵያ ዕንቁ ናት። አበቃን።

ምንጭ፤ አሚኮ ቱሪዝም፤ ደብረማርቆስ ኮሙኒኬሽን እና ሌሎችም

አጫጭር እውነታዎች

ስለ ጮቄ ተራራ አጫጭር መረጃዎች:-

  • በአማራ ክልል ውስጥ፣ በኢትዮጵያ ሰሜን-ምዕራብ ክፍል ይገኛል።
  • ከ4,000 ሜትር በላይ የሚደርስ ከፍታማ ክልል ነው።
  • የአባይ ወንዝ (Blue Nile) ዋነማ ምንጮች ከዚህ ተራራ ክልል ይጀምራሉ።
  • ተራራው የተለያዩ የእፅዋትና የእንስሳት ልዩነቶች (biodiversity) ያሉበት ነው።
  • በብዙ ጊዜ ቀዝቃዛና እርጥብ ነው፣ ዝናብም በቂ ይወርዳል።
  • በዙሪያው የሚኖሩ ሰዎች በግብርና ይኖራሉ፣ ተራራውም ለመሬት ርግብነት ጠቃሚ ነው።
  • አስፈላጊ የዱር ሕይወት መጠበቂያ ቦታ ነው፣ በተለይም ለወፎች።

(መሰረት ቸኮል)

 

በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here