የኢትዮጵያ ጥንታዊ የንግድ ታሪክ በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባሕር አካባቢ ለነበሩ ስልጣኔዎች ዋነኛ የጀርባ አጥንት ነበር። ከሁሉ አስቀድሞ የአክሱም ስልጣኔን ስንመለከት ሀገራችን በወቅቱ የነበሩትን ታላላቅ የዓለም ኃይላትን ማለትም ሮምን፣ ፋርስን እና ህንድን በንግድ የምታገናኝ ድልድይ ነበረች። በአሁኗ ኤርትራ ግዛት ውስጥ ይገኝ የነበረው የአዱሊስ ወደብም ለዚህ ዓለም አቀፍ ግንኙነት እንደ ዋና በር ያገለግል ነበር። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በዋነኝነት ወርቅን፣ የዝሆን ጥርስን እንዲሁም ለመንፈሳዊ እና ለህክምና አገልግሎት የሚውሉትን እጣን እና ከርቤን ለዓለም ገበያ ታቀርብ ነበር። በምላሹም ከባይዛንታይን እና ከህንድ የሚመጡ የሐር ልብሶች፣ ብርጭቆዎች፣ ብረት እና የወይን ጠጅ ወደ ሀገር ውስጥ ይገቡ ነበር ሲሉ ሪቻርድ ፓንክረስት “ኢትየጵያዊያዊያን በታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው አብራርተዋል።
የአክሱም መንግሥት እየደከመ ሲመጣ እና የቀይ ባሕር ጠረፍ በሌሎች ኃይሎች ቁጥጥር ስር ሲውል የንግድ መስመሮቹ አቅጣጫቸውን ወደ ውስጥኛው የሀገሪቱ ክፍል እና ወደ ደቡብ ምስራቅ ቀየሩ። በዚህም መሠረት የሐረር ከተማ በምስራቅ ኢትዮጵያ እንደ ትልቅ የንግድ መገናኛ ማዕከል ሆና ብቅ አለች። ነጋዴዎች በበረሃ እና በቆላማ አካባቢዎች በግመል ተሳቢዎች በመታገዝ ከላይኛው የኢትዮጵያ ክፍል የሚመጡ ምርቶችን ወደ ዘይላ እና በርበራ ወደቦች ያጓጉዙ ነበር። ይህ መስመር ከንግድ ባለፈ የእስልምና ሃይማኖት እና የአረብ ባሕል ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ሲሉ በተክለጻድቅ መኩሪያ “የኢትዮጵያ ታሪክ፦ ከአክሱም እስከ ዳግማዊ ምኒልክ” በሚለው መጽሐፋቸው አስፍረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በሀገር ውስጥ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ በአብዛኛው በአሞሌ ጨው ላይ የተመሰረተ ነበር። ከአፋር ዝቅተኛ ቦታዎች የሚመረተው ጨው በሺዎች በሚቆጠሩ ግመሎች ተጭኖ ወደ ደጋማው የሀገሪቱ ክፍል ይጓጓዝ ነበር። ይህ የአሞሌ ጨው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ እንደ ገንዘብ ያገለግል ስለነበር የጨው መስመሩ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ አንድ አድርጎ የሚያስተሳስር ዋና የደም ስር ሆኖ ቆይቷል። በተለይም በጎንደር እና በሸዋ ዘመነ መንግሥት ወቅት እነዚህ መስመሮች እንደ ቡና፣ ቆዳ እና ሌጦ ያሉ ምርቶችን ከደቡብ እና ከምዕራብ ኢትዮጵያ ወደ ሰሜን እና ወደ ምስራቅ በማመላለስ የሀገሪቱን የንግድ መዋቅር አጠናክረውታል። እነዚህ ጥንታዊ የንግድ መስመሮች ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ እና ከሩቅ ሀገራት ጋር የባህል፣ የቋንቋ እና የቴክኖሎጂ ልውውጥ እንድታደርግ መንገድ የከፈቱ የታሪክ አሻራዎች ናቸው።
በተለይም በታሪካችን ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የቡና እና የዝሆን ጥርስ ንግድ ከደቡብ ወደ ሰሜን እና ወደ ምስራቅ ይደረግ የነበረው ጉዞ እጅግ አስደናቂ ነበር። ከከፋ፣ ከጂማ እና ከወለጋ የሚነሱ ነጋዴዎች በረጅም የእግር ጉዞ በጫካ እና በሸለቆዎች ውስጥ አልፈው ምርታቸውን ወደ ማዕከላዊ የንግድ ስፍራዎች ያመጡ ነበር። እነዚህ ነጋዴዎች “ጃባርቲ” በመባል የሚታወቁ ሲሆን በጉዟቸው ላይ የሚያጋጥሟቸውን የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ አደጋዎች ተቋቁመው ንግዱን ለዘመናት አቅንተዋል።
ሌላው ትኩረት የሚስበው ደግሞ በምስራቅ በኩል ያለው የሐረር የንግድ መስመር ነው። ሐረር ለዘመናት የንግድ መገናኛ ብቻ ሳይሆን የትምህርት እና የሃይማኖት ማዕከልም ነበረች። ከሸዋ (ከአሊዩ አምባ) የሚነሱ ነጋዴዎች በሐረር በኩል አልፈው ወደ ዘይላ ወደብ ሲጓዙ በግመል ጀርባ ላይ የሚጭኑት ቡና፣ ቅመማ ቅመም እና ዝባድ በዓለም ገበያ እጅግ ተፈላጊ ነበሩ። ይህ መስመር በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ የምድር ባቡር መስመር እስኪዘረጋ ድረስ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋነኛ መተላለፊያ ነበር።
በተጨማሪም የጨው ንግድ መስመርን ብንመለከት ከአፋር በረሃ (ዳሎል) የሚነሳው የአሞሌ ጨው ወደ ሰሜን እና ደቡብ ሲሰራጭ መንገዱ በሙሉ የገበያ ስፍራ ነበር። ጨው በወቅቱ ልክ እንደ ዛሬው ብር ወይም ዶላር ሆኖ ያገለግል ስለነበር ጨው የያዘ ነጋዴ በሄደበት ቦታ ሁሉ ማንኛውንም እቃ መለወጥ ይችል ነበር። ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ የተማከለ የንግድ ስርዓት ባልነበረበት ጊዜ እንኳ ህዝቡ እርስ በእርሱ እንዲገበያይ እና እንዲተሳሰር አድርጎታል።
የነጋዴዎቹ የጉዞ ሂደት እጅግ አድካሚ፣ ረጅም እና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ተግባር ነበር። በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ አንድ የንግድ ጉዞ ከጥቂት ወራት እስከ አንድ ዓመት ሊፈጅ ይችላል። ይህ ጉዞ የሚጀምረው “ካራቫን” ወይም የነጋዴዎች ስብስብ በመመሥረት ነበር። ነጋዴዎች ለደህንነታቸው ሲሉ ብቻቸውን አይጓዙም፤ ይልቁንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ግመሎች፣ በቅሎዎች እና አህዮችን በማሰለፍ በቡድን ይጓዛሉ በማለት በአፈወርቅ በቀለ “የኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ፦ ከጥንት እስከ ዛሬ” በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸዋል ።
የጉዞው መሪ “ነጋድራስ” በመባል ይታወቃል። ነጋድራስ የንግድ ስብስቡን የሚመራ፣ የጉዞ መስመሩን የሚያውቅ እና በመንገድ ላይ ከሚያጋጥሙ የአካባቢ መሪዎች ጋር የሚደራደር ትልቅ ስልጣን ያለው ሰው ነው። ጉዞው ከመጀመሩ በፊት ነጋዴዎች ለእንስሳቶቻቸው ቀለብ፣ ለራሳቸው የሚሆን ስንቅ (እንደ በሶ፣ ዳቦ ቆሎ እና ድርቆሽ ያሉ የማይበላሹ ምግቦች) እና ለመከላከያ የሚሆኑ መሣሪያዎችን ያዘጋጃሉ።
በጉዞው ወቅት ትልቁ ፈተና የመንገድ መቆጫ ወይም “በረንዳ” የሚባለው ክፍያ ነበር። ነጋዴዎቹ በአንድ የአካባቢ መሪ ግዛት አልፈው ወደ ሌላው ሲሸጋገሩ ለደህንነታቸው እና በመሬቱ ላይ ለማለፋቸው የተወሰነ ክፍያ (በአሞሌ ጨው ወይም በሸቀጥ) ይከፍላሉ። ይህ ካልሆነ ግን ግጭቶች ሊነሱ ይችላሉ። በመሆኑም ነጋድራሱ ከጎሳ መሪዎች ጋር ቀድሞ በመነጋገር የሰላም ስምምነት ያደርጋል።
ሌላው አስቸጋሪው ነገር የተፈጥሮ እንቅፋቶች ነበሩ። ታላላቅ ወንዞችን (እንደ አባይ እና ተከዜ ያሉ) መሻገር በተለይ በክረምት ወቅት እጅግ አደገኛ ነበር። ድልድዮች ባልነበሩበት በዚያ ዘመን ነጋዴዎች ወንዙ እስኪጎድል ለሳምንታት ሊጠብቁ ወይም በቆዳ በተሰሩ ታንኳዎች ራሳቸውን እና ዋና እንስሳቶቻቸውን እያሻገሩ ጉዟቸውን ይቀጥላሉ። በረሃማ ቦታዎችን ሲያቋርጡ ደግሞ የውኃ ጥም እንዳይገድላቸው የውኃ ጉዞአቸውን በቆዳ ከረጢት (አቅማዳ) ይዘው በለሊት ይጓዛሉ።
ማረፊያ ቦታዎችም የራሳቸው ታሪክ አላቸው። “መንደር” ወይም “በረንዳ” ተብለው በሚጠሩ የማረፊያ ስፍራዎች ነጋዴዎች ድንኳን ጥለው ያርፋሉ። እዚያም እርስ በእርሳቸው መረጃ ይለዋወጣሉ። የእንስሳቶቻቸውን ቁስል ያክማሉ። አዳዲስ የንግድ አጋሮችንም ያገኛሉ። እነዚህ ማረፊያዎች ቆይተው ወደ ትላልቅ ከተሞችነት የተቀየሩባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። የጥንት ነጋዴዎች ጉዞ የንግድ ልውውጥ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ባሕሎች እና ቋንቋዎች የሚገናኙበት፣ ዜና የሚሰራጭበት እና ሀገሪቱ ከውጭው ዓለም ጋር የምትተሳሰርበት የቀጥታ መስመር ነበር።
በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ከነበሩት የንግድ ዕቃዎች ሁሉ እጅግ ልዩ እና በዓለም ገበያ በክብር ይታይ የነበረው “ዝባድ” (Civet Musk) ነው። ዝባድ የሚገኘው ዝባድ ተብላ ከምትጠራ አነስተኛ የዱር እንስሳ ሲሆን ለሽቶ መሥሪያነት እና ለባህላዊ መድኃኒትነት እጅግ ተፈላጊ ነበር። ይህ ምርት በተለይ በደቡብ እና በምዕራብ ኢትዮጵያ በስፋት ይመረት እና በሐረር በኩል ወደ አረብ ሀገራት እና ወደ አውሮፓ ይላክ ነበር። በወቅቱ ዝባድ እንደ ወርቅ ውድ ተደርጎ ስለሚቆጠር ነጋዴዎቹ በልዩ ጥንቃቄ በትንንሽ ቀንዳቸው (ቀንድ ውስጥ) አሽገው ነበር የሚያጓጉዙት።
ሌላው እጅግ አስደናቂው እና “ነጭ ወርቅ” እየተባለ የሚጠራው የንግድ ዕቃ “እጣን እና ከርቤ” ነው። ኢትዮጵያ በተለይም ሰሜኑ እና ምስራቁ ክፍል ለእነዚህ ዕፅዋት ተስማሚ በመሆኑ በጥንታዊቷ ግብፅ ዘመን ጀምሮ ለቤተመቅደስ አገልግሎት እና ለቀብር ሥነ-ሥርዓት ወደ ውጭ ይላክ ነበር። የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ጥንታዊ ግብፅያውያን ወደ “ፑንት ምድር” (የአሁኗ ኢትዮጵያ እና አካባቢዋ) መርከቦቻቸውን እየላኩ የሚወስዱት ዋነኛው ውድ ምርት ይህንኑ እጣን ነበር።
ከእንስሳት ተዋጽኦ ደግሞ “የዝሆን ጥርስ” ዋነኛው የንግድ ዕቃ ነበር። አክሱማውያን ለሮም ስልጣኔ እና ለህንድ የዝሆን ጥርስን በስፋት ያቀርቡ ነበር። ይህ ምርት ለጌጣጌጥ፣ ለቤት ዕቃዎች ማስጌጫና ለተለያዩ የጥበብ ሥራዎች ይውል ስለነበር ነጋዴዎች ዝሆኖችን እያደኑ ጥርሳቸውን ለሽያጭ ያቀርቡ ነበር። ይህም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የቅንጦት ዕቃዎች ገበያ ውስጥ ትልቅ ስም እንዲኖራት አድርጓታል።
ሳምንቱ በታሪክ
ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ሀገር ተመለሱ
ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከአምስት ዓመት ስደት በኋላ ግንቦት 5 ቀን 1933 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ የገቡት በታላቅ ድል እና የሕዝብ ደስታ ነበር። ንጉሡ ጉዟቸውን በጎጃም በኩል አድርገው በታዋቂው አርበኛ በላይ ዘለቀ እና በሌሎችም የጦር መሪዎች ታጅበው ወደ መሃል ሀገር መጡ። አዲስ አበባ ከመግባታቸው በፊት ለጥቂት ቀናት በደብረ ማርቆስ በኩል ካረፉ በኋላ ጉዟቸውን ወደ ዋና ከተማዋ ቀጠሉ።
የመግቢያቸው ዕለት ግንቦት 5 ቀን እንዲሆን የተመረጠው ጣሊያን አዲስ አበባን የያዘበትን አምስተኛ ዓመት መሙያ ለማድረግ እና የድሉን ታሪክ ተምሳሌታዊ ለማድረግ ታስቦ ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ በእንጦጦ በኩል ወደ ከተማዋ ሲገቡ ለዓመታት በዱር በገደሉ ሲዋጉ የነበሩት እንደ ራስ አበበ አረጋይ ያሉ ታላላቅ አርበኞች እና የከተማው ሕዝብ በእልልታ እና በደስታ ተቀበሏቸው።
ወደ ታላቁ ቤተ መንግሥት እንደደረሱም ለአምስት ዓመታት ተለይቶአቸው የነበረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በድጋሚ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ተደረገ። ንጉሡ በዚያ ታሪካዊ ዕለት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ነፃነቷን ማግኘቷን አበሰሩ። የሚገርመው ግን በንግግራቸው ውስጥ ሕዝቡ በጠላት ላይ በቀል እንዳይፈጽም ይልቁንም የተሸነፉትን ጣሊያኖች በምሕረት እንዲመለከቷቸው ማሳሰባቸው ነበር። ይህ ድርጊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢትዮጵያ ትልቅ ክብርን ያስገኘ እና የሕዝቡን የጨዋነት ባሕል ያስመሰከረ ክስተት ሆኖ እስከ ዛሬ ድረስ ይታወሳል ሲሉ ተክለጻዲቅ መኩሪያ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ” በተሰኘው መፅሐፋቸው ገልጸዋል።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


