ከፈጠራ ባሻገር

0
123

“ፈጠራ የአእምሮ መዝናኛ ነው፤ አዲስ ነገር ለመሞከር እና ለመፍጠር ደፍሞ ስህተትን መቀበል ያስፈልጋል። ያለ ስህተት ትክክለኛው የፈጠራ መንገድ አይገኝም”። ታላቁ የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንስታይን ስለ ፈጠራ ከተናገራቸው አባባሎች አንዱ ነው።

ቶማስ ኤዲሰን እንዳለውም ፈጠራ አንድ በመቶው እንቅስቃሴ ሲሆን 99 በመቶ ደግሞ ጥረት ነው።

ዓለም በአሁኑ ወቅት በፈጣን የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትገኛለች፤ ይህም የሰዎችን ኑሮ እጅግ ቀላል እንዲሆን አስችሏል። የሚበዙት የፈጠራ ውጤቶች ደግሞ መነሻቸው ችግር ሲሆን ለችግሩ መፍትሔ በመስጠት ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ነው።

በአጠቃላይ ቴክኖሎጂ ማለት ሳይንሳዊ ዕውቀትን፣ ክህሎትን እና መሣሪያዎችን በማዋቀር የሰው ልጅ ችግሮችን ለመፍታት፣ ሥራን ለማቅለል እና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ጽንሰ-ሀሳብ ነው። የዕለት ተዕለት ኑሮን ለማሻሻልም የጎላ ድርሻ አለው።

በሀገራችን በርካቶች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በማቅረብ ለተለያዩ ችግሮች መፍትሔ እየሆኑ ነው። የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህር እና ተመራማሪው ቻላቸው እምሬ አንዱ ናቸው።

የሀገራችን ግብርና ዕድሜ ጠገብ ነው። ይሁን እንጂ ከዕድሜው ጋር መዘመን የተሳነው ሆኖ ቆይቷል። የመምህር ቻላቸው የፈጠራ ሥራዎች ደግሞ ዘርፉን ማሻሻል ላይ ያተኮሩ ናቸው።

መምህሩ የፈጠራ ሥራቸውን በተመለከተ ከበኩር ጋር ቆይታ አድርገዋል፤ በትምህርታቸው ጊዜ የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ሙከራዎችን የጀመሩት መምህሩ፣ ሙከራዎችን ወደ ተግባር በመቀየር ለአርሶ አደሮች ቀጥታ የሚጠቅሙ መሣሪያዎችን አዘጋጅተዋል። ከእነዚህም መካከል የበቆሎ መፈልፈያ፣ የመኖ መፍጫ፣ የሩዝ መፈልፈያ እና የውኃ መሳቢያዎች ይገኙበታል።

እነዚህ ማሽኖች በባሕላዊ መንገድ ለረጅም ጊዜ የሚፈጅ ስራን በአጭር ጊዜ እንዲፈጽም በማድረግ የአርሶ አደሮችን ጉልበትና ጊዜ በእጅጉ እየቆጠቡ ነው።

መምህር ቻላቸው እንዳሉት የበቆሎ መፈልፈያው ማሽን በሰዓት ከ45 እስከ 65 ኩንታል ድረስ ማሽከርከር አቅም አለው፤ ይህ ሥራ ደግሞ ቀደም ባለው አሠራር ቀናትን ሊወስድ የሚችል አድካሚ ተግባር ነው:: የመምህሩ አዲሱ የፈጠራ ሥራ ግን በሰዓታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ያስችላል።

ማሽኑ በሁለት የተለያዩ ንድፎች (ዲዛይኖች) የተሠራ ነው፤  አንደኛው በቆሎን ከነቆረቆንዳው ጨምሮ የትኛውንም የጥራጥሬ አይነት መፍጨት ይችላል። በሰዓት ሰባት ኩንታል የመፍጨት አቅም አለው።

ሁለተኛው ደግሞ የሰብል አገዳን ለከብቶች በሚመች መልኩ የሚቆራርጥ እና የሚፈጭ ማሽን ነው። ይህ የፈጠራ ውጤት በሰዓት እስከ 11 ኩንታል ምርት ይፈጫል። ማሽኖቹ በቀላሉ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፤ በመሆኑም አርሶ አደሮች በራሳቸው ማሳ ላይ መኖውን እንዲያዘጋጁ ያስችላቸዋል። ማሽኖቹ አሁን ላይ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እንደቀረቡ መምህሩ አስታውቀዋል።

የመኖ መፍጫ ሌላው የመምህር ቻላቸው የፈጠራ ሥራ ነው፤ ማሽኖቹ በሰዓት ከሰባት እስከ 11 ኩንታል ማቀናበር ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ አርሶ አደሮች እንስሳትን ለመመገብ የሚፈልጉትን መኖ በቀላሉ እንዲያዘጋጁ ያስችላቸዋል። የፈጠራ ሥራው በአርሶ አደሮች ቀዬ ዘንድ ተደራሽ እንደሆነ ልብ ይሏል::

በተጨማሪም የሩዝ መፈልፈያው ቴክኖሎጂ ከፍተኛ የምርት ብክነትን የሚቀንስ ነው፤ የምርት ብክነትን እስከ 33 በመቶ ድረስ ማስቀረት የሚችል የፈጠራ ውጤት ስለመሆኑ ነው መምህሩ የነገሩን፤ ይህን የፈጠራ ሥራም “የብክነት ጠላት” ሲሉ ነው የጠሩት። ይህ ደግሞ ከአርሶ አደሮች ባለፈ እንደ ሀገር ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ አበርክቶ እንዳለው ጠቁመዋል። የውጭ ምንዛሪን ማስቀረቱ ደግሞ ሌላው የዚህ የፈጠራ ሥራ አበርክቶ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ ማሽኑ በሀገር ውስጥ ምርት የተሠራ በመሆኑ ነውና።

እንደ መምህር ቻላቸው ገለጻ፣ ከሞተር በስተቀር ማሽኖቹ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የተመረቱ ናቸው፤ ይህ መሆኑ ደግሞ የፈጠራ ሥራዎቹ ላይ ፈጠራ ዕሴትን ይጨምራል። እስካሁንም ከ50 በላይ አርሶ አደሮች እነዚህን መሣሪያዎች በነፃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፤ ይህ መሆኑም የማኅበረሰቡን አቅም ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

እንደዚህ ዓይነት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎች የኢትዮጵያን ግብርና ከባሕላዊ አሠራር ወደ ዘመናዊ ሥርዓት ለመቀየር መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን መምህር ቻላቸው ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በወጣቶች ዘንድ የሥራ ፈጠራ መንፈስን ያነሳሳሉ፤ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራሉ። ይህም የሃገርን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ጠቁመዋል።

“ግብርናን በቴክኖሎጂ መደገፍ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው” የሚሉት መምህር ቻላቸው፣ በቀጣይ እነዚህን ማሽኖች በብዛት እና በጥራት ማምረት ዕቅዳቸው መሆኑን ነግረውናል፤ ለአርሶ አደሮች በበቂ መጠን ተደራሽ ለማድረግም በትኩረት ይሠራሉ። “ይህ ደግሞ እንደ ሀገር የምንመኘውን ዘመናዊ ግብርና ለመገንባት ትልቅ እርምጃ ነው” ብለዋል::

መረጃ

የፈጠራ ስራ ምን ማለት ነው?

ፈጠራ የሰው ልጅ ከጥንት ጀምሮ ሕይወቱን ለማሻሻል የተጠቀመበት አስፈላጊ ችሎታ ነው። ዛሬ ዓለም በፍጥነት እየተለወጠ ያለው በፈጠራ ስራዎች ምክንያት ነው። ከቀላል የዕለት ተዕለት አጠቃቀም ዕቃዎች እስከ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ድረስ ያሉ ነገሮች ሁሉ በሰው ልጅ ፈጠራ የተፈጠሩ ናቸው። ስለዚህ ፈጠራ ለማኅበረሰብ እድገትና ለኢኮኖሚ ልማት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።

የፈጠራ ስራ ማለት አዲስ ሀሳብ፣ አዲስ ዘዴ ወይም አዲስ ምርት በመፍጠር የሰዎችን ችግር ለመፍታት የሚደረግ ተግባር ነው። ፈጠራ ሁልጊዜ ትልቅ ማሽን ወይም ውስብስብ ቴክኖሎጂ ማለት አይደለም፤ አንዳንድ ጊዜ ቀላል ነገርን በተሻለ መንገድ መጠቀምም ፈጠራ ይሆናል። ለምሳሌ የተጣሉ እቃዎችን በድጋሚ በመጠቀም ጠቃሚ ዕቃ መስራት ወይም የእርሻ ስራን የሚያቀላጥፍ መሳሪያ ማዘጋጀት የፈጠራ ስራ ምሳሌዎች ናቸው።

በአጠቃላይ ፈጠራ ስራ ማለት አዲስና ጠቃሚ ሀሳብን ወደ ተግባር መቀየር ነው። ፈጠራ የሰውን ልጅ ሕይወት ያሻሽላል፣ የሥራ እድል ይፈጥራል፣ የሀገርን ኢኮኖሚ ያጠናክራል። ስለዚህ ፈጠራን ማበረታታትና ወጣቶች በአዳዲስ ሀሳቦች እንዲሳተፉ ማድረግ ለሀገር እድገት አስፈላጊ ነው።

ምንጭ፡-Peter F.Drucker,Innovation and Entrepreneurship

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here