የምርጫ ካርድ ከመያዝ ባለፈ…

0
101

ምርጫ ዜጎች በቀጥታ ወይም በተወካዮቻቸው በመምረጥ መሪዎቹን እና ተወካዮችን ለመምረጥ የሚደረግ ሕጋዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሂደት ነው::

ይህ ደግሞ የሕዝብን ፍላጎት ለማሳካት፣ መንግሥትን ህጋዊ ለማድረግ እና የዲሚክራሲ ሥርዓትን ለማጠናከር ያስችላል::

ሀገራችንም ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ይዛለች፤ ለዚህ ደግሞ የመራጮች የመራጭነት ካርድ ማውጣትን ጨምሮ በርካታ የቅድመ ምርጫ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው::

ከአንድ ወር በላይ በቆየው የመራጮች የምዝገባ ጊዜ ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ ማውጣታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል::

ይሁን እንጂ የምርጫ ካርድ መያዝ ብቻ በቂ አይደለም፤ የሚበጃቸውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ በቂ መረጃ ሊኖራቸው ይገባል:: ከዚህ ጋር በተገናኘ ታዲያ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ እያካሄዱ ነው፤ በተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎችም ፖሊሲዎቻቸውን እያስተዋወቁ ነው::

ይህ መሆኑ ደግሞ መራጮች ዕጩዎችን፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና የሚያቀርቧቸውን ፕሮግራሞች ለመመርመር አቅም ይሆናቸዋል።

በመጪው ግንቦት የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎችን በስልክ አነጋግረናል::

የኮምቦልቻ ከተማ በርበሬ ወንዝ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ መሠረት ሰይድ ሀሰን ለበኩር ሀሳባቸውን በስልክ እንዳጋሩት የምርጫ ካርድ በወቅቱ አውጥተዋል፤ “የምርጫ ካርድ መያዝ ብቻ በቂ አይደለም” የሚሉት ነዋሪዋ በቀጣይ  ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊሰሩባቸው የሚችሉትን ፖሲዎች እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል::

“በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች የሚቀርቡትን ፖሊሲዎች በመከታተል እና በመመርመር ይሆነኛል የምለውን ለመምረጥ እራሴን እያዘጋጀሁ ነው” ብለዋል:: የሴቶች የምርጫ ተሳትፎም ከፍ እንዲል ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል::

ሌላኛዋ ያነጋገርናቸው በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ይታይ በላይ ናቸው፤ ከዚህ በፊት በሀገራችን በተካሄዱት ምርጫዎች በመሳተፍ ልምድ እንዳላቸው ጠቁመዉ በቀጣይ በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመራጭነት ለመሳተፍ የምርጫ ካርድ ማውጣታቸውንም ገልጸውልናል::

ወይዘሮ ይታይ እንዳሉ የመራጭነት ካርድ ያወጡት ፍላጎታቸውን ሊያሳካ የሚችል የፖለቲካ ፓርቲን ለመምረጥ ነው፤ ለዚህ ደግሞ የምርጫ ካርድ ከማውጣት በተጨማሪ ስለ ፓርቲዎቹ አማራጭ ሥራዎች መረጃ ሊኖር ይገባል:: “ምርጫ ካርድ በማውጣት ብቻ አልተገደብኩም” ያሉት ወይዘሮዋ መምረጥ ያለብኝን ፓርቲ ለመለየት ዕጩዎች በሚዲያ እያቀረቡ ያሉትን የመወደደሪያ ሀሳብ  እየተከታተልኩ ነው” ሲሉ ሀሳባቸውን አጋርተውናል::

ሌላው ሐሳባቸውን ያካፈሉን በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የግሽ ዓባይ ቀበሌ ነዋሪው ቦሴ አሕመድ ናቸው፤ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ በተደረጉ ምርጫዎች በመምረጥ ተሳትፎ እንደነበራቸው ነግረውናል። በመጪው ለሚከናወነዉ 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫም የተሻለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ማውጣታቸውን ነው የገለጹት።

ወይዘሮዋ አክለውም የምርጫ ቀን ሲደርስ ያለማንም ግፊት እና አስገዳጅነት በራሳቸው ግምገማ እና ውሳኔ መሠረት ይበጀኛል የሚሉትን እንደሚመርጡ ነው የተናገሩት:: ለዚህም የዕጩ ተወዳደሪዎችን እና የፓርቲዎችን መወዳደሪያ የክርክር ሀሳብ እየተከታተሉ መሆኑን ነው የነገሩን::

ወይዘሮ ቦሴ አክለውም ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል ብለዋል። ያልመረጥኩት ግለሰብ እና መንግሥት ነው እያስተዳደረኝ ያለ ላለማለት በምርጫ ሂደት መሳተፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

“ሴቶች በምርጫ ሂደት በመምረጥ እና በመመረጥ ካልተሳተፋ ሴቶችን የተመለከቱ ጉዳዮች ይዘነጋሉ” ያሉት ወይዘሮ ቦሴ በመሆኑም “በምርጫው በንቃት መሳተፍ ይገባቸዋል” ነው ያሉት።

የሰባተኛው ጠቅላላ የመራጮች ምዝገባ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም መጠናቀቁ ይታወሳል። በዚህም ከ50 ሚሊየን 514 ሺህ በላይ መራጮች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ አስታውቀዋል።

ሰብሳቢዋ እንዳሉት ዜጎች በምርጫዬ የሞባይል መተግበሪያ የዲጂታል አማራጭና በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት የመራጮች ምዝገባ አከናውነዋል።

ከአምስት ሚሊዮን 503 ሺህ በላይ የሚሆኑት መራጮች የተመዘገቡት በዲጂታል አማራጭ ሲሆን ቀሪዎቹ በማንዋል የተመዘገቡ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለምርጫው ሰላማዊነት አስፈላጊው ሥራ መከናወኑን የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ  አስታውቋል፤ የቢሮው ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም “የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል” ብለዋል።

የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን የክልሉን ሰላም ለማጽናት እና የምርጫ ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

“በጸጥታ ችግር ምክንያት የሚስተጓጎል የምርጫ ክልልም ሆነ ጣቢያ የለም” ያሉት ዶክተር እሸቱ ለዚህም “አስተማማኝ ዝግጅት ተደርጓል” ነው ያሉት።

በክልሉ በምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ሰላማዊ የምርጫ ምዝገባ ሂደት እንደተከናወነም አንስተዋል። ምርጫውም በስኬት እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

ማኅበረሰቡ ያሥተዳድረኛል የሚለውን መሪ በምርጫ ሂደት ለመመሥረት የምርጫ ደኅንነቱን በመጠበቅ እና በመምረጥ ኀላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል።

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here