በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ሕፃን ማለት “ማንኛውም ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነው ሰው” ነው፡፡ ቀዳማይ ልጅነት የሚባለው ደግሞ ከእርግዝና እስከ ስድስት ዓመት ያለው ጊዜ ነው፡፡ ይህ የዕድሜ ክልል በሰው የዕድገት ደረጃዎች ውስጥ ፈጣን አካላዊ፣ አዕምሯዊና ስሜታዊ ዕድገት የሚከሰትበት ወሰን ነው፡፡
ሕፃናት ከጽንሰት ጀምሮ እስከ ሦስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ከ80 እስ 90 በመቶ አዕምሮቸው እንደሚያድግ በአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡ በቢሮው የሕጻናት ድጋፍ እና ክትትል ዳይሬክተር አቶ አሻግሬ ዘውዱ እንዳብራሩት እናት እና አባትን ጨምሮ በቤት ውስጥ በሚኖራቸው የቤተሰብ ጊዜ በተለይ ለጨቅላ ሕጻናት (ከልደት እስከ አንድ ዓመት) ልዩ ክትትል ማድረግ ይገባል፤ እንቅስቃሴዎቻቸውን (መሳቅ፣ በሆድ መሳብ፣ መቀመጥ፣ መቆም፣ ቃላትን መሞከር) በትኩረት መከታተል ተገቢ ነው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ደግሞ በቂ የጡት ወተት መስጠት፣ ክትባት ማሟላት፣ አብሮ መጫወት እና ማውራት የቤተሰብ ኃላፊነት ነው።
ሕጻናትን በመከታተል ወቅት ድምጽ ሲሰማ ደንግጦ የማይመለከት፣ ከሌላ ሰው ጋር ዐይን ለዐይን የማይገጥም ወይም አቅጣጫን የማይከተል ከሆነ ደግሞ ችግር እንዳለበት አመላካች በመሆኑ ቤተሰብ መፍትሔ መፈለግ እንደሚገባው ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡
ሕጻናት ድክድክ (ከአንድ እስከ አራት ዓመት) በሚሉበት ጊዜ መራመድ፣ መሮጥ፣ እምቢ ማለት ማብዛት፣ ዕቃዎችን መለየት መቻል አለባቸው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ቤተሰብ ንጽሕናቸውን መጠበቅ፣ ቃላትን ማስተማር እና ከአደጋ መከላከል ይጠበቅበታል።
ሕጻናት ከአራት እስከ ስድስት ዓመት (ቅድመ ትምህርት) ባሉት ጊዜያት ጥያቄ ማብዛት፣ “ለምን?” ማለት፣ ከጓደኛ ጋር መጫወት፣ ቀለም መለየት የሚጀምሩበት ነው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ቤተሰብ ተረት መንገር፣ ለጥያቄዎቻቸው በትዕግስት መመለስ፣ ሥነ ሥርዓት ማስተማር ይጠበቅባቸዋል። እስከ 18 ወር ባይራመድ፣ ጥቂት ቃላትንም መናገር ካልቻለ መፍትሔ ያስፈልገዋል። ከሌሎች ልጆች ጋር ፈጽሞ የማይቀላቀሉ ከሆነ፣ ንግግራቸውን ሌላው ሰው የማይረዳቸው ከሆነ ግን መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ከሰባት እስከ 12 ዓመት ያሉ ሕጻናት ደግሞ ማንበብና መጻፍ፣ በራስ መተማመን መጨመር፣ የጓደኝነት ትስስር መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወላጆች በዚህ ወቅት በትምህርት ማገዝ፣ ጥሩ ሥነ-ምግባርን ማበረታታት፣ የትርፍ ጊዜ ሥራዎችን ማመቻቸት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። በዚህ የዕድሜ ክልል ታዲያ በትምህርት ውጤት ድንገት መቀነስ፣ ከሰው መገለል፣ ከፍተኛ ፍርሃት ከተከሰተባቸው ወላጆች ለችግሩ መፍትሔ ማፈላለግ ይኖርባቸዋል፡፡
ሌላው ታዳጊነት (Adolescence) የሚባለው የዕድሜ ክልል ሲሆን ከ13 እስከ 18 ዓመት ያለውን ያጠቃልላል፤ የሰውነት ለውጥ (ጉርምስና)፣ የራሳቸውን ማንነት መፈለግ፣ ከጓደኛ ጋር በግልጽ መወያየት፣ የግል ምስጢራቸውን መጠበቅ፣ አርዓያ መሆን የሚፈልጉበት ነው፡፡
ነገር ግን በዚህ የዕድሜ ደረጃ ሱስ ውስጥ መግባት፣ ከፍተኛ የባህርይ ለውጥ መታየት፣ ራስን የመጉዳት ሀሳብ የሚጠነሰስበት በመሆኑ የቤተሰብን ጥብቅ ክትትል ይፈልጋል።
በእነዚህ የዕድሜ ክልሎች ቤተሰብ የሕጻናትን የዕድገት ሁኔታና ስሜት አለመረዳት በርካታ ችግሮችን እንደሚያስከትሉ አቶ አሻግሬ ጠቁመዋል፡፡ ለምሳሌ የአካልና የአዕምሮ የዕድገት ደረጃዎችን የማያውቅ ወላጅ ልጁ ላይ የሚታዩ የክህሎት ጉድለቶችን (ለምሳሌ በወቅቱ አለመናገር ወይም አለመራመድ) እንደ ተራ ነገር ሊመለከተው ይችላል። ይህም ልጁ በጊዜ ማግኘት የሚገባውን የህክምና ወይም የትምህርት ድጋፍ እንዲያጣ ያደርጋል፡፡
ሌላው ቤተሰብ የልጆችን የተፈጥሮ ዕድገት መገለጫዎች እንደ ሥርዓት አልበኝነት ወይም እልኸኝነት በመቁጠር የተሳሳተ የቅጣት እና የዲሲፕሊን እርምጃ ይወስዳል፡፡ ለምሳሌ የሦስት ዓመት ሕጻን “ለምን?” ብሎ ቢጠይቅ ዓለምን የመረዳት ፍላጎቱ እንጂ ወላጆቹን ለማድከም አይደለም። ይህን ያልተረዳ ወላጅ ልጁን ሊቆጣ ወይም ሊቀጣ ይችላል፡፡ ይህም የልጁን የፈጠራ እና የማወቅ ጉጉት በእጅጉ ይጎዳል።
ደካማ የወላጅና የልጅ ትስስር መኖርም ሌላው ችግር ነው፡፡ የሕጻኑን ፍላጎት በዕድሜው ደረጃ መረዳት አለመቻል በመካከላቸው ያለውን ቅርርብ ያላላዋል። ልጁ “ቤተሰቦቼ አይረዱኝም!” የሚል ስሜት ስለሚያድርበት ምስጢሩን መደበቅ እና መሸሽ ይጀምራል። ይህ ለአደጋ ሊያጋልጥ ችላል፡፡
በመሆኑም እንደ ዕድሜ ክልሉ ወላጅ ለልጆች አስፈላጊውን እገዛ የማድረግ ግድ እንዳለበት አስገንዝበዋል፤ ከልደት እስከ 18 ዓመት ላሉ ሕጻናት በቤተሰብ ልዩ ትኩረት መስጠት አዎንታዊ ሥርዓትን ለማበረታታት፤ የጋራ ኃላፊነት ለመፍጠር፤ ተሳትፏቸውን እና ችግሮችን የመቋቋም ክህሎታቸውን ለማሳደግ ያስችላል፡፡ ለአብነት ስህተት እንዲሠሩ በመፍቀድ ከስህተት እንዲማሩ፤ ትችት በቀላሉ የማይሰብራቸው እንዲሆኑ ማድረግ፤ ከመውደቅ መነሳት፣ ከሙከራ ስኬት እንደሚገኝ ማሳየት እና ጤናማ ዓርአያ መፍጠር ከወላጆች ይጠበቃል፡፡
ሕጻናት በዚህ የዕድሜ ክልላቸው የሕይወት ዘመን ማንነታቸው ላይ መሠረት የሚጣልበት ወሳኝ የዕድገት ደረጃ መሆኑንም አቶ አሻግሬ አንስተዋል፡፡ አንድ ልጅ በቅድመ ልጅነት ሁለንተናዊ እንክብካቤ ውስጥ የተመጣጠነ አመጋገብና ጤናው የተጠበቀ እንዲሁም መልካም የወላጅ-ልጆች መስተጋብር አግኝቶ ካደገ የተሻለ ዜጋ ይሆናል።
ለሕጻናት መልካም አስተዳደግ ወላጆች፣ ቤተሰብ /አሳዳጊዎች/ የልጆቻቸውን ሁለንተናዊ ዕድገት ከሕጻንነት እስከ አዋቂነት ባለው ሂደት በተሻለ እንክብካቤ፣ ፍቅር፣ ክብር እና በግልጽ ግንኙነት ላይ ተመስርቶ የማሳደግ ጥበብ ነው፡፡ በልጅች አስተዳደግ ትልቁን ድርሻ የሚወጡት ወላጆች “የልጆች የሕይወት መስታዎት” ናቸው፡፡
በሕጻናት መልካም አስተዳደግና አያያዝ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በተመለከተ አቶ አሻግሬ አብራርተዋል፡፡ በቤተሰብና ማሕበረሰብ መካከል የሚፈጠሩ መስተጋብሮች፣ የገቢ ሁኔታና የምጣኔ ሀብት ልዩነት፣ ማህበራዊ ሥርዓቶች፣
ወላጆች ልጆቻቸው መጥፎ ባህርይ ሲያሳዩ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ነገር ሲያደርጉም ማሞገስ ተገቢ መሆኑን አቶ አሻግሬ ጠቁመዋል፡፡ ልጆች እንዲደረግላቸው የፈለጉትን ነገር ቀድሞ ማድረግ፣ ለምን ይህን አደረግህ? ብሎ ከመቆጣት ይልቅ “ይህ እንዳይደገም ምን ማድረግ እንችላለን?” ብሎ መጠየቅም የመልካም ወላጆች መገለጫ ነው፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የተለያዩ የልጅ አያያዝና አስተዳደጎች አሉ፡፡ ከእነዚህም በንግግር የሚያምን አስተዳደግ (Authoritative) አንዱ ነው፡፡ ይሕ የአስተዳደግ መንገድ የተወሰነ ደረጃ ኃላፊነት የሚሰጥ፣ በዲሞክራሲያዊ ንግግር የሚያምን፣ ግልጽ የቤተሰብ መመሪያዎችን ያስቀመጠ እና ለሕጻናት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት የሚያድጉ ልጆች የተረጋጋ ስሜት ያላቸው፣ ችግሮችን መቋቋም እና ስኬታማ መሆን የሚችሉ፣ በትምህርት አቀባበላቸው ውጤታማ፣ ሀሳባቸውን መግለጽ የሚችሉ፣ በራስ መተማመን እና መልካም ተግባቦት ያላቸው እንዲሁም ጠያቂና ሰው የሚያምኑ ናቸው፡፡
አምባ ገነናዊ የአስተዳደግ ዘይቤ /Authoritaria ሌላው ነው፡፡ ይህ ዘዴ ወላጆች ለልጆቻቸው ግትር፣ ጥብቅና ምላሽ የማይሰጡ፣ ድብደባ የሚያዘወትሩ፣ ወቃሾች እንዲሁም ለስህተት ትዕግስት የሌላቸው ናቸውን፡፡
በአምባገነናዊ የአስተዳደግ ዘይቤ ያደጉ ልጆች በትምህርታቸው ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘግባሉ፤ ብዙውን ጊዜ የድብርት ስሜት ይታይባቸዋል፤ ደካማ ማኅበራዊ ግንኙነት ይኖራቸዋል፤ ለራሳቸው በጣም ዝቅተኛ ግምት ይሰጣሉ፤ ከሌሎች የመገለልና የመነጠል ባህርይም ይኖራቸዋል፤ ተጠራጣሪዎችም ናቸው፡፡
ቸልተኛ የሕጻናት የአስተዳደግ ዘይቤ /Neglectfull/ ደግሞ ብዙ ጊዜ የሚስተዋለው ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸው ትኩረት በሚያንስበት ጊዜና በስሜት ወይም በአካል በሌሉበት ጊዜ፤ ከልጆቻቸው ብዙ የማይጠብቁ፤ መደበኛ ግንኙነት የሌላቸው፣ ለልጆቻቸው ፍላጎቶችና ስሜቶች ምላሽ የማይሰጡ ናቸው፡፡
በዚህ ሥርዓት የሚያድጉ ሕጻናት ዝቅተኛ ተግባቦት ያላቸው፣ በማኅበራዊ መስተጋብራቸው እና በትምህርታቸው ዝቅተኛ አፈፃፀም ያላቸው፣ በአብዛኛው በእኮዮቻቸው የመጠቃትና የመገፋት ትኩረትና ትዕግስት የሌላቸው ይሆናሉ፡፡
በአጠቃላይ ልጆች እንደ ዕድሜያቸው እና የዕድገት ደረጃቸው የተለያዩ ለውጦችን እና ዕድገትን የሚያመጡበት ነው፤ ደረጃዎቹን ታሳቢ በማድረግ ታዲያ አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ፣ ችግርም ካለ መፍትሔ ማፈላለግ ከወላጆች የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡
የሀገሪቱ ሕገ- መንግሥትም በአንቀጽ 36 ሕጻናት ወላጆቻቸውን ወይም በሕግ የማሳደግ መብት ያላቸውን ሰዎች የማወቅና የእነሱንም እንክብካቤ የማግኘት መብትና ነፃነት ያላቸው ዜጎች መሆናቸውን አስፍሯል፡፡
(ሙሉ ዓብይ)
በኲር በኲር የግንቦት 10ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


