”ካርድ የሚወጣው ለጨዋታው ውበት ሲባል እንጂ ብዙ ካርድ ማውጣት የዳኛ ጉብዝናን አይለካም።“
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ሦስት ጊዜ የዓመቱ ኮከብ ዳኛ በመባል የተሸለመ ብቸኛው የክብረወሰን ባለቤት ነው። በ16 ዓመቱ በ1993 ዓ.ም ዳኝነትን ጀምሯል፡፡ በ2004 ዓ.ም ደግሞ የፊፋ ባጅ አግኝቷል፡፡
በስፖርት ሳይንስ ሦስተኛ ዲግሪ (PhD) ያለው ዳኛ በ25 ዓመታት የዳኝነት ዘመኑ ከ34 በላይ ሀገራትን በመጓዝ ከ16 በላይ የካፍ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን፤ የተለያዩ የሴካፋ ውድድሮችን መርቷል፡፡
በቅርቡ እግር ኳሱን ከሚመሩ አካላት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በ41 ዓመቱ ፊሽካውን ሰቅሏል፡፡ አሚኮ በኩር ጋዜጣ ከዓለም አቀፉ ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው (ዶክተር) ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡ መልካም ንባብ!
ወደ ዳኝነት ዓለም እንዴት ገባህ? የልጅነት ህልምህ ምን ነበር?
በልጅነቴ የእግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ትልቅ ህልም ቢኖረኝም የቤተሰቤ ትኩረት ትምህርት ላይ በመሆኑ ህልሜ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ሆኖም በ1993 ዓ.ም ከ17 ዓመት በታች ለሆኑ ወጣቶች በተዘጋጀው የዳኝነት ፕሮጀክት ስልጠና በመሳተፍ አቅጣጫዬን ቀየርኩ፡፡ እናም ገና በ16 ዓመቴ የዳኝነት ህይወቴን በይፋ ለመጀመር በቅቻለሁ፡፡
ወደ ዳኝነት ስትገባ የገጠመህ ችግር ምን ነበር?
ከቤተሰብ ተቃውሞ ባለፈ ሕግ አክባሪ በመሆኔ ከስፖርት ኮሚቴዎች ጋር ተጣልቼ ነበር፡፡ በሀሰት ክስ ታግጄ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ የነበሩት የከተማው ከንቲባ ግን አስነስተውልኛል፡፡ ጫናውን ለማምለጥም ዶክመንቴን ወደ ምዕራብ ጎጃም አዙሬ ሠርቻለሁ፡፡
የመጀመሪያ የፕሮፌሽናል ዳኝነትን ከየትኛው የሊግ እርከን ነው የጀመርከው?
በ1994 ዓ.ም በባህር ዳር የ “ቢ” ቡድኖችን በማጫወት ብጀምርም ወዲያው ወደ “ኤ” ቡድን እና የክልል ውድድሮች አደግኩ፡፡ በ1998 ዓ.ም የፌደራል ዳኝነት ኮርስን አዲስ አበባ ላይ ወስጄ፣ በድሬዳዋው የፕሮጀክት ውድድር የዋና ዳኝነት እድል አገኘሁ፡፡ በ1999 ዓ.ም ደግሞ በብሄራዊ ሊግ ኦሜድላ ከመቻሬ ያደረጉትን ጨዋታ በማጫወት የፕሮፌሽናል ጉዞዬን ጀመርኩ፡፡
መቼ ነው ዓለም አቀፍ ዳኛ የሆንከው? እንዴት ነበር አጀማመሩ?
የ2003ቱን የኢትዮጵያ ቡና የዋንጫ ጨዋታ እጅግ በሞላ ስታዲየም በብቃት መምራቴ ለዓለም አቀፍ ዳኝነት ትልቅ በር ከፍቶልኛል፡፡ ፊፋ የሚጠይቀውን የአካል ብቃት፣ የሕግ፣ የቋንቋ እና የኮምፒውተር እውቀት ፈተናዎችን በሚገባ አልፌ በ2004 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ዳኛ ሆንኩ፡፡ በዚሁ ዓመትም ወደ ሩዋንዳ ተጉዤ በአራተኛ ዳኝነት በማገልገል የመጀመሪያዬ የሆነውን ዓለም አቀፍ ውድድር መራሁ፡፡
በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም አጠቃላይ ምን ያህል ጨዋታዎችን መርተሃል?
በሀገር ውስጥ ከ300 በላይ (ፕሪሚየር ሊጉ በዲኤስቲቪ ከገባ ወዲህ ከ75 በላይ) መርቻለሁ። ከሀገር ውጪ ከ34 በላይ ሀገራትን በማዳረስ ከ16 በላይ የካፍ ጨዋታዎችንና 16 የሴካፋ ግጥሚያዎችን አጫውቻለሁ፡፡
የካርድ ሰው ነኝ ብለህ ታስባለህ?
(ሳቅ…..) መጀመሪያ ስጀምር በጣም የካርድ ሰው ነበርኩ፤ ቤተሰቦቼም ይቀልዱብኝ ነበር፡፡ በኋላ ግን ልምድ ሳዳብር ከተጫዋቾች ጋር በማውራት ያለ ካርድ ማስተዳደር ጀመርኩ። ካርድ የሚወጣው ለጨዋታው ውበት ሲባል እንጂ ብዙ ካርድ ማውጣት የዳኛ ጉብዝናን አይለካም፡፡
ዳኛ ለመሆን በጣም አስፈላጊ ናቸው የምትላቸው ሦስት ነገሮች ምንድን ናቸው?
አንደኛ የአካል ብቃት (በአካሉ ብቁ መሆን)፣ ሁለተኛ የሕግ እውቀትን በተግባር መተርጎም መቻል (ሕግን ማወቅ ብቻ ሳይሆን መተግበር) ሦስተኛ የስነ ልቦና ዝግጅት ናቸው፡፡
በዳኝነት ሙያ ፈታኝ የሆኑ ነገሮችስ ምንድን ናቸው?
አንደኛ ውጫዊ ጫናዎችን (ከአወዳዳሪ አካላት፣ ደጋፊዎች ወዘተ የሚመጣን) መቋቋም፣ ሁለተኛ የቡድን ውጤት የሚያመጣው ጫና፣ ሦስተኛ ተጫዋቾች ዳኞችን ለመረበሽ የሚያደርጉትን የስነ ልቦና ጫና ማስተናገድ፡፡
በብቃት ተወጥቼዋለሁ ብለህ ምታስበው ጨዋታ የቱ ነው?
መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዋንጫ ሲጫወቱ አበባው ቡጣቆን እና ደጉ ደበበን በቀይ ካርድ ያስወጣሁበት ጨዋታ እጅግ ፈታኝ ነበር፡፡ የመከላከያ ደጋፊ የነበሩ አንድ ኮሎኔል ሽጉጥ አውጥተው እንደዛቱብኝ አስታውሳለሁ፡፡
ለመዳኘት ያስቸገረህን ጨዋታ ታስታውሳለህ? ዳኝነቱንስ በቃኝ ልተው ብለህ ያሰብክበት አጋጣሚ ነበር?
ለመዳኘት ያስቸገረኝን ጨዋታ የለም፤ ምክንያቱም ጫና ያለባቸውን እና ከባድ ጨዋታዎችን መምራት ያዝናናኝ ነበር፡፡
ስፖርት ሳይንስ ማጥናትህ፣ የስፖርት ሳይንስ መምህር መሆንህ ለዳኝነት ሙያህ አግዞኛል ብለህ ታስባለህ?
አዎ! እስከ ሶስተኛ ዲግሪ መማሬ የተጫዋቾችን ስነ ልቦና እና ታክቲክ ቀድሞ ለማንበብ አግዞኛል፡፡ በዚህም በ25 ዓመታት ውስጥ አላስፈላጊ ግጭቶችን አስወግጄ እንድመራ ረድቶኛል፡፡
እንኳንም ይሄን ጨዋታ መራሁት የምትለው ጨዋታ አለ?
(ሳቅ…..) ብዙ ጨዋታ አለ! በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ታንዛኒያ ላይ 60 ሺህ ደጋፊ በተገኘበት ያንግ አፍሪካንስና አልሃሊን ያጫወትኩበት ፈጽሞ አይረሳኝም፡፡ የጨዋታው ኮሚሽነር ውጤት እንድንቀይር ለዋና ዳኛ ዐስር ሺህ እና ለረዳቶች ሰባት ሺህ 500 ዶላር ጉቦ ቢያቀርቡልንም አልተቀበልንም፡፡ እኔ እና ኢትዮጵያውያን አጋሮቼ ገንዘቡን ንቀን ጨዋታውን በፍትሀዊነት በመምራት ሀገራችንን በማስጠራታችን ሁሌም እኮራለሁ፡፡ ከሀገር ውስጥ ደግሞ በ2003 ዓ.ም ኢትዮጵያ ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ ያነሳበትን ትልቁን የፍጻሜ ጨዋታ ያጫወትኩበትን አልረሳውም፡፡ ሌላው ከስድስት በላይ የሸገር ደርቢዎችን (ቡና እና ጊዮርጊስን) ምንም አይነት የዳኝነት ክስ ሳይነሳብኝ በማጫወቴ እኮራለሁ፡፡
አላሳካሁትም ብለህ የምትቆጭበት ነገር አለ?
አዎ! ያላሳካሁት ህልም አለ፡፡ በ2029 ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለማጫወት ትልቅ ራዕይ ነበረኝ፣ ያ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አንድን ዓለም አቀፍ ዳኛ አሳድጌ ተተኪዬ ይህ ነው ብዬ በይፋ ሳላወጣ ማቆሜ ይቆጨኛል፡፡
ሜዳ ውስጥ የገጠመህ እንግዳ ነገር?
ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሲጫወቱ ኤልያስ ማሞ ሜዳ ላይ ወደቀ። ወጌሻ ገብቶ ውሀ አጠጣው፣ ስጠጋው “ኧረ ቁጭ ብዬ ልረፍ ብዬ ነው” አለኝ፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኤልያስ አታሮ የሚባል የጅማ ተጫዋች ወልቂጤ ላይ በቀይ ካርድ ሲወጣ ካርዱ ቢጫ መስሎት ዝም ብሎ ሜዳ ውስጥ ይሮጥ ነበር፡፡ ተከላካዮቹ “ቀይ እኮ ነው አውጥቶብሃል” ብለው እስኪነግሩት አላወቀም ነበር፡፡
አሁን ላይ በድንገት ከዳኝነት ዓለም ራሴን አግልያለሁ የሚል ውሳኔህን አሰማህ ምክንያቱ ምንድነው?
ዳኝነትን በዚህ ጊዜ አቆማለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ እቅዴ በ2029 ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ማጫወት ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር በፈቀደው ጊዜ አሁን ለማቆም ተገደድኩ፡፡
ገና በ41 ዓመቴ ዳኝነትን ያቆምኩት እግር ኳሱን ከሚመሩት ኮሚቴዎች ጋር በተፈጠረ እና መግባባት ባልተቻለበት አሰራር ምክንያት ነው፡፡ በሰላማዊ ውይይት መፍታት የሚቻሉ ጉዳዮች ከሕግ አግባብ ውጪ በመሆናቸው እና የሕግ ጥያቄዬም ምላሽ በማጣቱ ራሴን ለማግለል ተገድጃለሁ፡፡
ወደፊትስ ወደ ዳኝነቱ የምትመለስበት እድል አለ?
ፊሽካ ይዤ ወደ ሜዳ ባልመለስም በካፍ እና በፊፋ የኢንስትራክተርነት ኮርሶችን ወስጄ ሕግን የሚያከብሩ አዳዲስ ብቁ ዳኞችን በማፍራትና ልምዴን በማካፈል ድርሻዬን መወጣት እቀጥላለሁ፡፡
እንግዳችን ዓለም አቀፉ ዳኝ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው እናመሰግናለን!
እኔም አመሰግናለሁ!::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


