“ቀጣዩ ዓመት የኛ ነው” የሚለው የተለመደ የተስፋ ቃል ዘንድሮ እውን ሆነ፤ የ22 ዓመታት የናፍቆት፣ የትዕግስት እና የፈተና ጉዞ በመጨረሻም ተቋጨ፡፡ በቪታሊቲ ስቴዲየም የበርንማውዝ እና የማንቸስተር ሲቲን ጨዋታ የመሩት ዳኛ አንቶኒ ቴለር የጨዋታውን መጠናቀቅ ያበሰረውን የመጨረሻውን የፊሽካ ድምጽ ሲያሰሙ የሁለት ዐስርት ዓመታት መከራ፣ ስላቅ፣ ትዕግስት እና ተስፋ በደስታ እንባ ተደመደመ፡፡
አርሴናል የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት የጠበቀው ጊዜ አንድ ህፃን ተወልዶ፣ አድጎ ትምህርቱን አጠናቆ እና ለወግ ለማዕረግ የሚበቃበት ሙሉ የህይወት ምዕራፍ ነው፡፡ አርሴናል በ2003/04 የውድድር ዘመን አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ለመጨረሻ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ ማክስ ዶውማን እና ሊዊስ ስኬሊ ገና አልተወለዱም ነበር፡፡ ቡካዮ ሳካ እና ጋብርኤል ማርቲኔሊ ገና ዳዴ የሚሉ የሁለት ዓመት ጨቅላ ህፃናት ነበሩ፤ ዊሊያም ሳሊባም የሦስት ዓመት ህጻን ነበር፡፡ የቡድኑ ሞተር ዴክላይን ራይስ የአምስት ዓመት፣ ካይ ሀቫርትዝ የአራት ዓመት፣ ጦረኛው ጋብርኤል ማጋሌሽ ደግሞ የስድስት ዓመት ታዳጊ እንደነበር የአርሴናል ይፋዊ ድረገጽ መረጃ ያመለክታል፡፡
አየሩ ቢከፋም፣ ዘመኑ ቢረዝምም፣ ክለቡ ከውጤት ቢርቅም ደጋፊው ያሳየው የማይናወጥ ጽናት የዛሬዋን ቀን እንዲያይ አስችሎታል፡፡
ይህ የደስታ ማዕበል ታዲያ በለንደን ብቻ አልተወሰነም፤ ድምፁ የሜዲትራንያንን ባህር አቋርጦ፣ ስምንት ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ተሻግሮ በኢትዮጵያም ተሰምቷል፡፡ አርሴናል የ2025/26 የውድድር ዘመን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን መሆኑን ሲያረጋግጥ “North London forever, whatever the weather, Arsenal forever” የሚለው ዝማሬ በአራቱም የዓለም ማዕዘን ባሉ የአርሴናል ደጋፊዎች እኩል ተዘምሯል፡፡ ይህ ታሪካዊ ድል ቦትለርስ፣ አጃቢ፣ ሚዜዎች እና መሰል ቅጽል ስሞችን እየሰጡ ለዓመታት ለሚሳለቁባቸው ተቀናቃኞች የተሰጠ ምላሽ እና የደጋፊው የማይበገር ጽናት ተምሳሌት ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡
አርሴናልን መውደድ ማለት ውበትን መውደድ ማለት ነው ይላሉ-የአርሴናል ደጋፊዎች፡፡ የተማረኩትም የቬንገር ኳስ (Wengerball) ተብሎ በሚታወቀው እጅግ ማራኪ፣ ፈጣን እና አጭር ቅብብሎችን ባዋሀደው ስነ ጥበባዊ የእግር ኳስ ፍልስፍና ነው፡፡
በዘመናዊ እግር ኳስ ውስጥ አንዳንድ ክለቦች በገንዘብ ኃይል እና በጉልበት ማሸነፍን ሲመርጡ አርሴናል ግን ማሸነፍ ያለበት በሚያምር መንገድ (The Arsenal Way) መሆን አለበት ብሎ ክለቡ ያምናል፡፡ ለዚህም ነው የኤምሬትስ ስታዲየምን ለመገንባት ክለቡ ከባድ የገንዘብ መናጋት ሲገጥመው፣ ምርጥ ተጫዋቾቹን በየዓመቱ ሲያጣ እና የዋንጫ ድርቅ ሲመታው ደጋፊው ክለቡን ጥሎ ያልሸሸው፡፡ ይልቁንም በክፉም በደጉም “አብረን ነን” በሚል መንፈስ ትስስሩ ይበልጥ ጠነከረ እንጂ፡፡ አርሴናልን መውደድ ማለት ውጣ ውረድን አብሮ ማሳለፍ፣ በሽንፈት ማዘን፣ በስላቅ መሃል ፀንቶ መቆም እና “አንድ ቀን የኛ ጊዜ ይመጣል” ብሎ በተስፋ መጠበቅ ማለት ነው ይላሉ ደጋፊዎች፡፡
ዛሬ ላይ በአውሮፓ፣ እስያ እና ሰሜን አሜሪካ ብቻ ሳይሆን በአፈሪካም የአርሴናል ደጋፊ መሆን በቤተሰብ የሚተላለፍ ውርስ ሆኗል፡፡
በ1990ዎቹ እና 2000ዎቹ ክለቡን መደገፍ የጀመሩ አባቶች፣ ዛሬ ለልጆቻቸው የአርሴናልን ማልያ በማልበስ እና የታሪኩ ተካፋይ በማድረግ ያሳድጋሉ፤ እያሳደጉም ይገኛሉ፡፡ መድፈኞቹ ቤተሰባዊ ትስስርን የሚፈጥሩ፣ ትውልድን ከትውልድ የሚያገናኙ ድልድዮች ሆነዋል፡፡
በተለይ አርሰን ቬንገር የሰሜን ለንደኑን ክለብ ከተረከቡ በኋላ አፍሪካውያን ተጫዋቾችን በማመን እና ትልቅ ደረጃ በማድረስ የነበራቸው ሚና የአፍሪካውያን እና የአርሴናል የፍቅር የመጀመሪያ መሆኑን የክለቡ ይፋዊ ድረገጽ አስነብቧል፡፡ ጥቁር አፍሪካውያን በአውሮፓ እግር ኳስ ውስጥ በጥርጣሬ በሚታዩበት በዚያ ዘመን ፈረንሳያዊው የእግር ኳስ ሊቅ አርሰን ቬንገር በሩን ወለል አድርገው ለአፍሪካውያን ኮከቦች መክፈታችው ትስስራቸው እንዲጠነክር አድርጎታል፡፡ ንዋንኮ ካኑ፣ ላውረን፣ ኮሎ ቱሬ፣ ኢማኑኤል አዴባዮር እና የመሳሰሉትን የያዘውን ስብስብ አፍሪካውያን እንደ ራሳቸው ቡድን እንዲቆጥሩት አድርጓቸዋል፡፡
በኢትዮጵያም አርሴናል ማለት የጥበብ እግር ኳስ ተምሳሌት ተደርጎ ከተወሰደ ውሎ አድሯል፡፡ የቲየሪ ኦንሪ ፈጣን ሩጫ፣ የዴኒስ ቤርካምፕ ቄንጠኛ አጨዋዎት እና የፓትሪክ ቪዬራ ጦረኝነት በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደ ቲያትር ድርሰት ይታይ ነበር፡፡ በፈረንጆቹ ሚሊኒየም መጀመሪያ የዲኤስ ቲቪ ስርጭት በኢትዮጵያ ሲስፋፋ፣ አርሴናል የሚጫወተው ውብ እግር ኳስ ወጣቱን ትውልድ የማረከው በዚሁ ፍልስፍናው ምክንያት መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ፡፡ ይህ ፍቅር ደግሞ ውጤት በራቀባቸው ዓመታት እንኳ አልቀነሰም፤ ይልቁንም ደጋፊው በታማኝነት ከክለቡ ጋር ተጣብቆ ቀረ እንጂ፡፡ አርሴናል ቢሸነፍ እንኳን ጨዋታው አይሰለችም፤ “በውበት ተሸንፎ መውጣት በጭንቀት ከማሸነፍ ይሻላል” የሚለው ያልተጻፈ መርህ በደጋፊው ዘንድ ለክለቡ ትልቅ ክብር እንዲሰጠው አድርጎታል፡፡
ይህ የትውልድ ቅብብሎሽ እና የእግር ኳስ ፍቅር ግን ሁልጊዜም አልጋ በአልጋ አልነበረም፤ እጅግ ፈታኝ የሆኑ የጨለማ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ ክለቡ ከ1996 እስከ 2005 እ.አ.አ የነበረው ወርቃማ ዘመን ካበቃ በኋላ ወደ አዲሱ ኤምሬትስ ስታዲየም መዘዋወሩ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ እንደከተተው የጎል ዶት ኮም መረጃ ያስነብባል፡፡ ብድር ለመክፈል ሲባል እንደ ሴስክ ፋብሪጋዝ፣ ሮቢን ቫን ፐርሲ፣ ሳሚር ናስሪ እና አሌክሲስ ሳንቼዝ ያሉ ድንቅ ባለተሰጥኦ ኮከቦችን ለተቀናቃኞች ለመሸጥም ተገዷል፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ክለቡ የስላቅ ዘመን ውስጥ የገባው፡፡ በእርግጥ በየዓመቱ በአራተኝነት ማጠናቀቅ እንደ ትልቅ ስኬት የታየበት፣ በባየር ሙኒክ ዐስር ለሁለት ዘግናኝ ሽንፈቶች የደረሰበት እና ደጋፊው በሄደበት ሁሉ አንገቱን የደፋበት ወቅት ነበር፡፡ በተለይም በማንቸስተር ዩናይትድ የደረሰው የስምንት ለሁለት ሽንፈት በደጋፊው ልብ ትልቅ ጠባሳ ጥሎ ማለፉ አይዘነጋም፡፡
የደጋፊው ተስፋ የሽንፈት ማስታገሻ ሳይሆን ነገ የተሻለ ቀን እንደሚመጣ የሚያሳይ የፅናት ምልክት ነበር፡፡ እናም ደጋፊው ሂደቱን በማመን የዛሬውን ብርሃን ለማየት በቅቷል፡፡
የመድፈኞቹ የንጋት ብርሃን መታየት የጀመረው እ.አ.አ በ2019 የቀድሞው የቀድሞ ተጫዋቹ ሚኬል አርቴታ ቡድኑን ሲረከብ ነው፡፡
ሰፔናዊው አሰልጣኝ በወጣት ተጫዋቾች ላይ የተመሰረተ አዲስ መንፈስ በመፍጠር የክለቡን ታሪክ መቀየር ጀመረ፡፡ መድፈኞቹ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ከማንቸስተር ሲቲ ጋር እስከመጨረሻው ደቂቃ ተፋልመው በጠባብ ልዩነት ዋንጫ ማጣታችው የቅርብ ጊዜ የልብ ስብራት ትዝታቸው ነው፡፡ በመጨረሻ ግን የክለቡ፣ የተጫዋቾቹ እና የደጋፊው ትዕግስት ፍሬ አፍርቶ ህልማቸው እውን ሆኗል፤ አርሴናል የፕሪሚየር ሊጉን ሻምፒዮንነት ዘውድ ደፍቷል፡፡
በተለያዩ ጥናቶች መሠረት 35 በመቶ የሚሆነው የአርሴናል ደጋፊ በእስያ ይገኛል፡፡
30 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በአፍሪካ ነው የሚገኘው፡፡ በተለይም ናይጄሪያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሩዋንዳ የአርሴናል ደጋፊዎች በብዛት የሚገኙባቸው የክለቡ ምሽጎች መሆናቸውን የሱፐር ስፖርት መረጃ አመልክቷል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተከታታዮች መካከል አርሴናል ከ35 በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በከተማ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የገጠር ቀበሌ የመድፈኞችን መለያ የለበሰ ሰው ማግኘት የተለመደ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአርሴናል ደጋፊዎች በማህበራዊ የትስስር ገጽ ባላቸው ንቁ ተሳትፎ እና ውጤት በሌለበት ጊዜ እንኳ “እኛ ምርጥ ነን” ብለው ማሰባቸው ለተቀናቃኞች እንደ እብሪት ሲታይባቸው ቆይቷል፡፡ አሁን ግን አርሴናል ዋንጫ ማንሳቱ ሁሉንም ዝም አሰኝቷል፡፡
ዛሬ አርሴናል ለሁሉም ደጋፊዎቹ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ለአፍሪካውያን የጥበብ፣ የታማኝነት፣ እና የወድቆ መነሳት ምልክት ሆኗል፡፡ ይህም ለደጋፊዎቹ ትልቅ የኩራት ምንጭ መሆን ችሏል፡፡ አርሴናልን መውደድ ማለት ውበትን ማድነቅ፣ መውደቅን መታገስ እና መነሳትን በጽኑ ማመን ማለት እንደሆነ ዛሬ ለዓለም አሳይቷል ይላል የክለቡ ይፋዊ ድረገጽ፡፡ ‘‘Trust the process’’ ቃሉ በተግባር ተፈፅሟል! አርሴናልም ሻምፒዮን ሆኗል!
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


