ሃንታ ቫይረስ

0
128

ሃንታ ቫይረስ   በዋነኝነት የሚተላለፈው በአይጦች ሽንት፣ እዳሪ ወይም ምራቅ የተበከለን አየር ሰዎች ወደ ውስጥ በሚተነፍሱበት ወቅት ነው። በፈረንጆች አቆጣጠር ባለፈው በሚያዝያ ወር በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ በሚጓዝ የጎብኝዎች (ቱሪስት) መርከብ ላይ ቫይረሱ መገኘቱን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ አመላክቷል፡፡ ይሁን እንጂ ባለሙያዎች ደጋግመው እንደሚያሳስቡት ይህ ቫይረስ እንደ ኮቪድ-19 በአየር ላይ በቀላሉ አይተላለፍም። ይልቁንም ስርጭቱ ጥብቅና የቅርብ ንክኪን ይጠይቃል። ይህንን ልዩነት በሚገባ መገንዘብ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግ ይረዳል፡፡

ቫይረሱ እንደ ኢንፍሉዌንዛ ወይም ኮቪድ-19 በቀላሉ በሰዎች መካከል አይተላለፍም፡፡

ቤትን ንፁህ ማድረግ፣ አይጦችን መቆጣጠር እና ደህንነቱ የተጠበቀ ንፅህናን መከተል ያሉ መሰረታዊ የዕለት ተዕለት ጥንቃቄዎች አደጋውን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

ቫይረሱ ስሙን ያገኘው በደቡብ ኮሪያ ከሚገኘው ሃንታን ወንዝ ሲሆን በ1970ዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው እዚያ ነው። ሳይንቲስቶች በኮሪያ ጦርነት ወቅት ወታደሮችን ሲያጠቃ የነበረ ሚስጥራዊ ትኩሳትን ሲመረምሩ ያገኙት በሽታ ነው።

በዓለም ዙሪያ ብዙ የተለያዩ የሃንታ ቫይረስ ዝርያዎች አሉ። ይህም የሆነው  በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ  አይጦች  የተለያየ የቫይረስ ዝርያዎች ስላሏቸው ነው፡፡ ሃንታ ቫይረስ   አይጦች  በሚኖሩባቸው  አህጉራት ሁሉ ይገኛል፡፡

 

የሃንታ ቫይረስ ስርጭት

ቫይረሱ የሚተላለፈው አንድ ሰው በተበከሉ አይጦች ለተበከሉ ቁሳቁሶች ሲጋለጥ ነው። ይህ በብዙ መንገዶች ሊከሰት ይችላል፤   የአይጥ ሽንት፣ እድፍ ወይም የጎጆ ቁሳቁሶች ሲደርቁ ትናንሽ የቫይረስ ቅንጣቶች አየር ላይ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ በተለይም አይጦች ያሉበትን አቧራማ ክፍል መጥረግ፣ የቆዩ የእቃ ማከማቻ ክፍልን ማጽዳት ወይም ለወራት በማከማቻ ውስጥ የተቀመጡ ሳጥኖችን ማንቀሳቀስ እነዚህን ቅንጣቶች ሊያነቃቃ ይችላል።

አንድ ሰው ይህንን የተበከለ አቧራ ሲተነፍስ ቫይረሱ ወደ ሳንባው ውስጥ ሊገባ ይችላል።  አንድ ሰው የአይጥ እድፍ፣ ሽንት ወይም የጎጆ ቁሳቁስ ከነካና ዐይኖቹን፣ አፍንጫውን ወይም አፉን ከነካ ቫይረሱ ወደ ሰውነቱ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ የአይጥ ንክሻዎች ወይም ጭረቶችም   አልፎ አልፎ ቫይረሱን ሊያስተላልፍ ይችላል። በአይጦች ፈሳሽ የተበከለ ምግብ መመገብ ወይም ውሃ መጠጣት ሌላው መተላለፊያ  መንገድ ነው። አይጦቹ እራሳቸው አይታመሙም፤ ቫይረሱን በጸጥታ ተሸክመው በሽንታቸው፣ በቆሻሻቸው  እና በምራቅ ያፈሳሉ። ይህ ቫይረስ ከሌሎች ቫይረሶች የሚለየውም ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ “ዙኖቲክ”  በሽታ በመሆኑ ነው።

የሃንታቫይረስ ምልክቶች አንድ ሰው ለቫይረሱ ከተጋለጠ ከአንድ እስከ ስምንት ሳምንታት በኋላ ይታያሉ። ዶክተሮች ይህንን ክፍተት የመታቀፊያ ጊዜ ብለው ይጠሩታል። አፖሎ ሆስፒል ዶት ኮም (apollohospitals.com) መረጃ እንደ ሚያመላክተው የሃንታ ቫይረስ የመጀመሪያ ምልክቶች ትኩሳትና ብርድ ብርድ ማለት፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ ህመም፣ በተለይም በጭኖች፣ በዳሌዎች፣ በጀርባ እና በትከሻ ላይ ድካም፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ ወይም የሆድ ህመም ፣ማዞር ናቸው፡፡ ኢንፌክሽኑ እየገፋ ከሄደ ዋናው ምልክት ድንገተኛ የመተንፈስ ችግር ነው። ታካሚዎች በሳንባዎች ውስጥ ፈሳሽ ሲከማች ሳል፣ የትንፋሽ ማጠር እና በደረት ውስጥ የመወጠር ስሜት ሊሰማቸው ይችላል።

ቫይረሱ የተገኘበት ሰው  ወዲያውኑ ካልታከመ ለሕይወት አስጊ ሊሆን ይችላል። የውስጥ ደም መፍሰስ እና የኩላሊት ችግር ሊከሰት ይችላል።  ብዙ ጊዜ የሃንታ ቫይረስ ኢንፌክሽኖች ቀላል ወይም ሙሉ በሙሉ ሳይስተዋል የሚቀሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ልብ ሊባል ይገባል። ሁሉም በበሽታው የተያዘ ሰው ከባድ ሕመም አያጋጥመውም።

የሃንታ ቫይረስ ፈታኝነቱ መጀመሪያ ላይ እንደ ተራ ጉንፋን መምሰሉ ነው። ምልክቶቹ ከቫይረሱ ጋር ከተገናኙ ከ1 እስከ 8 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊታዩ ይችላሉ። በሽታው እየጸና ሲሄድ፦ ቫይረሱ እየገፋ ሲሄድ ታካሚዎች ድንገተኛ የትንፋሽ እጥረት እና የማያቋርጥ ሳል ያጋጥማቸዋል። ይህም የአዲሱ ዓለም የሃንታ ቫይረስ የሳምባ ሕመም (Pulmonary Syndrome) ዋና መለያ ምልክት ነው። እንደ ሲ.ዲ.ሲ (CDC) መረጃ፤ ለዚህ የሳምባ ችግር ከሚጋለጡ 10 ሰዎች መካከል እስከ 4 የሚሆኑት ፈጣን የሕክምና እርዳታ ካላገኙ ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችላል እና ምልክቶቹን ተከታትሎ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቃል።

 

የሃንታ ቫይረስ ሕክምና

በአሁኑ ጊዜ ለሃንታ ቫይረስ የተለየ የፀረ-ቫይረስ መድሃኒት ወይም በስፋት የተፈቀደ ክትባት የለውም። ሕክምናው የሚወሰነው ዶክተሮች “ድጋፍ ሰጪ እንክብካቤ” ብለው በሚጠሩት ላይ ነው፣ ይህም ማለት በሰውነት ላይ የሚወጡ ያልተለመዱ  ምልክቶችን በመቆጣጠር እና አስፈላጊ ተግባራትን በማከናወን ኢንፌክሽኑን እንዲዋጋ መርዳት ማለት ነው። ይህም

በፈሳሽ አማካኝነት በቂ እርጥበትን መጠበቅ፣ መተንፈስ ከተጎዳ ተጨማሪ ኦክስጅን መስጠት፣ በከባድ የኤችፒኤስ ጉዳዮች ላይ ሜካኒካል አየር ማናፈሻ (የመተንፈስ ድጋፍ)መስጠት እና በጽኑ እንክብካቤ ክፍል ውስጥ ክትትል ማድረግ፣ በጣም ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ቢያንስ 12 አገራት በሃንታ ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን በይፋ አሳውቋል። እንደ ካናዳ፣ ጀርመን፣ ሲንጋፖር፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ሀገራት በቫይረሱ የተጠቁ ተጓዦች በማስተናገዳቸው ወይም ዜጎቻቸው በበሽታው በተያዙ አካባቢዎች በማለፋቸው ሳቢያ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተነግሯቸዋል።

ጤና አዳም

የሃንታ ቫይረስን ለመከላከል ማድረግ የሚገባን ነገሮች

  • አይጦች ካሉባቸው አካባቢዎች ራስዎን ያርቁ።
  • አይጦች ወደ ቤትዎ ወይም መጋዘንዎ የሚገቡባቸውን ቀዳዳዎች በሽቦ ወይም በሲሚንቶ ይዝጉ።
  • አቧራማ መጋዘኖችን ወይም የተተዉ ክፍሎችን ሲያጸዱ፤ መስኮት ይክፈቱ። አየር እንዲገባ ያድርጉ። ብናኝ እንዳይተነፍሱ የመከላከያ ማስኮችን(ቁሶችን) መጠቀም አስፈላጊ ነው።
  • ደረቅ የአይጥ እዳሪን በፍጹም አይጥረጉ። ይልቁንም አካባቢውን በበረኪና ለ5 ደቂቃ ያርጥቡትና ከዚያ በእርጥብ ጨርቅ ያጽዱት።
  • ለረጅም ጊዜ ተዘግቶ የቆየ ክፍል ውስጥ ከመግባትዎ በፊት ለ30 ደቂቃ ያህል መስኮትና በሮችን ከፍቶ አየር እንዲገባ ያድርጉ!
  • ከአይጦች ጋር ንክኪ ኖሮዎት ድንገተኛ ትኩሳት ወይም የመተንፈስ ችግር ካጋጠመዎት፤ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ይሂዱ።

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here