መቸም ሰው ሲኖር ብዙ ይገጥመዋል፤ የማያየው የለም፡፡ ደግ፣ ክፉ እና ይሄ ነው ተብሎ ምድብ ሊወጣለት የማይችል ክስተት ያጋጥመዋል። ማለዳ ሲነሳ “ሰላም አውለኝ” ማለትን የሚያክል ብርቱ ጸሎት ውሎን ለመቀደስ አስፈላጊ መሆኑ የሚገባን አንዳንድ ስክነት የጎደላቸው ሰዎችን ስንመለከት ነው። “ከዕለታት ባንዱ ቀን” ብሎ ንግግርንም ሆነ ጽህፈትን መጀመር በሃገራችን የትረካ ስርዓት ይትበሃል ነው እና እኔም እንዲሁ ብዬ ልጀምር። አንድ ቀን ውሎዬን በመጠነኛ ተዝናኖት ለማሳለፍ አስቤ ያለኝ እንዳቅሜ ለባብሼ ወጣሁ።
ከየት መጣ ሳልለው ድንገት ዶፍ ዝናብ ያዘኝ። ከዝናቡ ለማምለጥ የእጥፍ እጥፍ ዋጋ ከፍዬ ባጃጅ ተኮናትሬ ወደ መዳረሻዬ ሳቀና አንድ ጎልማሳ ቁሞ ዝናብ እየተመታ ሳየው አላስችል ብሎኝ ለአሽከርካሪው እንዲጭነው ነገርኩትና ጫነው። ሰውየው እንደገባ “በደንብ ጠጋ በል” ብሎ አንባረቀብኝ። በመጠኑ ፈገግ ብዬ ያቅሜን ያህል ተጠጋሁ። ሰውዬው በዚህ አልበቃውም “የለበስከው ነጭ ጫማ እንዳይበላሽ ነው ምትሽኮረመመው?” አለኝ። አልቻልኩም ሳቅ እና ቁጣ ተከታትለው መጡብኝ። “ባጎረስኩ ተነከስኩ” ብሎ የተረተውን የሃገሬ ሰው አግኝቼ አቅፌ ብስመው ብዬ ተመኘሁ።
ነገር ግን እንደምንም ክፉ ቃል ላለማውጣት ዝምታን መርጬ አለፍኩት። ሰውዬው መች በዚህ በቃው ጭራሽ “እሁድን ጠብቆ መዘነጥ ምን ያደርጋል?” ብሎኝ እርፍ። እስኪ ፈጣሪ ያሳያችሁ ይሄን ምን ትሉታላችሁ? በስራዬ የመንግስት ተቀጣሪ በመሆኔ ያለችኝ ብቸኛ ሳምንታዊ የረፍት ቀን እሁድ ናት። በዚች የረፍት ቀኔ ያለኝን አጥቤ ለብሼ ለመዝናናት ብወጣ ቅኔው እንደጠፋበት ዘራፊ አንዴ ከዚህ አንዴ ከወዲያ የሚረግጥ ዘባራቂ ጣለብኝ፤ ብቻ ነገር በሶስት ይጸናል እና አሁንም ዝም ብዬ አሳለፍኩት። ታዲያ እሱ መቼ በዚህ በቃውና ቀጠለ “አሁን በዚህ ወቅት ነጭ ጫማ ይደረጋል?” አለኝ አተኩሮ እያየኝ።
አልቻልኩም ገነፈልኩ። “እኔ የምልህ!” አልኩት ሞቅ ባለ ድምጽ። “ኧህ” አለኝ። “በዓለም ላይ ከአምስት በመቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለምን እንደሚሞቱ ታውቃለህ አልኩት” ግራ ገብቶት “ማለት?” አለኝ። “አየህ እነዚህ ሰዎች የሚሞቱት ልክ እንዳንተ ፍጹም በማያገባቸው እየገቡ ሲዘባርቁ ነው!” አልኩት ድምጼን ፈርጠም አድርጌ። እንዴው ሲጨንቀኝ ያመጣሁት ምሳሌ እንጂ በጉዳዩ ዙሪያ ያየሁት ጥናት እንደሌለ ልብ ይሏል። ሰውየው ድንገት ወራጅ ብሎ ዱብ ብሎ ጠፋ። “ተመስገን” አልኩ። አሽከርካሪው በምልልሳችን ሲዝናና የቆዬ ይመስለኛል። ፈገግ ብሎ እያየኝ ዞር አለ። ለማንኛውም ዝም ብዬው የቆየሁ “ሃሪፍ አይቸኩልም” ብዬ እንጂ ፈርቼ እንዳይመስላችሁ።
እና አንዳንድ ሰዎች ድንበር ወይም ለከት የሚባል ነገር ሲጠራ የሰሙም አይመስሉ። ሰው ነጻ ፍጡር መሆኑን መገንዘብ እና የራስን መብት እና ግዴታ እንዲሁም የሌሎችንም መብት እና ግዴታ ጠንቅቆ ማወቅ ከማንኛውም ሰው የሚጠበቅ ተግባር ነው እላለሁ። በተለይ በጋራ መኖሪያዎች አካባቢ እና ትራንስፖርት ላይ የሌሎችን ግላዊነት ላለመጋፋት ጥረት መደረግ አለበት ባይ ነኝ። ማንኛውም አዋቂ ሰው ለሚከውነው ነገር ኀላፊነት መውሰድ ስለሚችል ነው መታወቂያ ካርድ ከመንግስት የሚያገኘው ስለዚህ ከግል ከፈቃድ ውጭ የሰዎችን ግላዊነት ለመናድ መነካካት በህግም በሞራልም የሚደገፍ ጉዳይ አይደለም።
አንዳንድ ሰዎች የቤታቸውን አመል ይዘውት ገበያ ወጥተው ከአላፊ አግዳሚው ጋር እንካሰላንትያ ሲገጥሙ ይስተዋላል። መልካሙን ነገር ከሰው አይቶ መማር ቀናተኛ ሳይሆን ልበ ቀና የሚያስብል ጉዳይ በመሆኑ አንዳንዴ ከበጎ ሰዎች መልካሙን እንውሰድ። ብዙ ጊዜ ነጮች ኤርፎን/ማዳመጫ/ አድርገው በተለያዩ ቦታዎች ሲንቀሳቀሱ ይታያል። ታዲያ ይሄን የሚያደርጉት ማስታወቂያ ለመስራት ሳይሆን የሌሎችን ሰዎች ግላዊነት ላለመጋፋት ነው። ብዙ ጊዜ ትኩረት የማንሰጣቸውን ስህተቶች እንፈጽማለን። ለምሳሌ ስልክ እንኳ ስናወራ በምን ያክል የድምጽ መጠን እንደምንጮህ፣ ታክሲ ውስጥ የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ ስንጠቀም የምንገለገልበት የድምጽ ከፍታ ምን መሆን እንዳለበት ትኩረት ሰጥተን ስንመጥን አይስተዋልም። አንዳንድ ጊዜ ታክሲ ውስጥ እኛ የተመቸንን ሙዚቃ ከፍተን በግድ ተጋበዙልን የምንል ሰዎችም አንጠፋም። ሰው እንደ መልኩ ስብዕናው እና ያለፈበት የህይወት መንገድ ልዩ ልዩ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። አንዳንዱ ደስታ፣ አንዱ ሀዘን፣ ሌላው ደግሞ በሌላ ዓይነት ሁኔታ እና የስሜት ደረጃ ላይ ሊገኝ ይችላል። ስለዚህ የሚወደው ወይም የሚጠላው ነገር ልዩ ልዩ በመሆኑ ሰውን ለምርጫው መተው ብልህነት ነው።
በርግጥ የሰውን የግላዊነት ወሰን ማክበር እና ለምርጫው መተው ሲባል በተሳሳተ አተረጓጎም መታየት የለበትም። ሰውን ለምርጫው መተው ማለት ማህበራዊ ህይወትን ገሸሽ ማድረግ እና ግላዊነትን ማበረታታት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ማህበራዊ ህይወት ማለት ሰዎች የራሳቸውን ግላዊ መስመር ጠብቀው ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚመሰርቱት የጋራ የህይዎት ዑደት ነው። ስለሆነም ይብዛም ይነስም ሁሉም ሰው የራሱ የግላዊነት ማዕቀፍ አለው። ይሄን የግላዊነት ማዕቀፍ ሌሎች እንዲንዱበት የሚፈልግ ሰው እስካሁን አላጋጠመኝም። የሰዎችን የግላዊነት ማዕቀፍ መናድ “እኔ አውቅልሃለሁ” የሚል የሰዎችን ሞራል በዕንጨት እንደመንካት የሚቆጠር ውስጠ ወይራ መልዕክት አለው።
ያነሳነውን ሃሳብ ለማጠናከር የሚረዳ አንድ በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ያየሁትን ሃሳብ ላንሳ። ሃሳቡ “ብስለት ማለት ሁሉም ሰው የራሱ ህመም እንዳለው መረዳት ነው” ይላል። ሁሉም ሰው እንደሚኖረው የህወት ዘይቤ የሚያልፍበት ከፍታ እና ዝቅታ አለው። ስለዚህ እኛ ስንደሰት ሁሉም ይደሰት፣ እኛ ስንከፋ ደግሞ ሁሉም ይከፋ ከሚል በጣም የገነነ የራስ ወዳድነት ስሜት መውጣት ይገባል። ማህበረሰባዊ የዲሞክራሲ ልምምድም ከዚህ ሃሳብ የሚመነጭ ይመስለኛል።
አንዳንዴ ስልጣኔን የምንረዳባት መንገድ መስተካከል አለበት ብዬ አምናለሁ። ብዙ ማውራት እና ሰዎችን መንቀፍ አዋቂ ወይም ስልጡን የሚያስብል ጉዳይ አይደለም። ብልህ ሰው መቼ ማውራት እና መቼ ዝም ማለት እንዳለበት ያውቃል። የሰው ልጅ ብስለት መለኪያ ከሆነው አንዱ የሚናገረውን ንግግር ቀድሞ መመዘን መቻል እና አለመቻል አንዱ ነው። ንግግር ሰዎችን ስላሳቀ ወይም ስላዝናና ብቻ በዘፈቀደ እንደ ወረደ መነገር የለበትም። በቅድሚያ ተናጋሪው የሚያደምጠውን ሰው ማንነት፣ በሱ ላይ የሚኖረውን ጫና እና አጠቃላይ የንግግር አውዱን መረዳት እና የሚኖረውን ግብረ መልስ መገምገም አለበት። ይሄን ሂደት መከወን ጥቅሙ የአንድ ወገን ሳይሆን የጋራ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል።
ማረፊያ
“የእናት ምክር”
ልጄ ሆይ!
ሰው ማመን ቀብድ የለውም ይሉሃል አትመናቸው፣
የሚጠረጥሩህን ሁሉ ጠርጥራቸው፣
ይህንን ምክሬን ግን አትጠራጠረው፡፡
በበውቀቱ ስዩም
(ደረጀ ደርበው)
በኲር የግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


