ትዳር ምንድን ነው?

0
122
Just married couple, holding hands and walking in nature

ትዳር ማለት ሁለት ሰዎች በሕግ፣ በማኅበረሰብ እና በባሕል እውቅና አግኝተው በጋራ ቃል ኪዳን አንድ ላይ የሚኖሩበት የማኅበረሰብ መሠረታዊ ምሰሶ እና ተቋም ነው። ይህንን የሕይወት ጉዞ ከማኅበራዊና ከሥነ ልቦናዊ አንፃር  በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጅ መምህር  አቶ አውግቸው ሽመላሽ  አብራርተውልናል፡፡

ከማኅበራዊ ዕይታ አኳያ

የሳይኮሎጅ መምህሩ አቶ አውግቸው ሽመልስ እንደሚሉት ማኅበረሰቡ ትዳርን የሚመለከተው የትውልድ ቀጣይነት የሚረጋገጥበት እንዲሁም   የሥነ ምግባርና የባሕል እሴቶች የሚተላለፉበት መሠረታዊ የማኅበረሰብ ክፍል አድርጎ ነው። ይህም ሲባል ቤተሰብ  ማፍራት የሚቻልበት( ሰዎች ሲጋቡ የአንድ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን የሁለት ቤተሰቦች እና የማኅበራዊ አውታሮች መቀላቀል የሚፈጠርበት) ማለት ነው። በትዳር አማካኝነት ሰፊ የማኅበራዊ ትስስር እና የድጋፍ ሥርዓት ይመሰረታል።

በሌላ በኩል  ደግሞ የማኅበረሰብ ሕግ እና ሚናዎች አሉ ፡- ማኅበረሰቡ ለትዳር የራሱ የሆኑ መመሪያዎችን (ባለትዳርን ማክበር እና የሰማንያ ሚስት ወይም ባል) ነው ብሎ መስጠቱ፣ በሁለቱም በኩል እንደ ፆታቸው የሚጠበቁ የሥርዓተ-ፆታ ሚናዎችን (የባል እና ሚስት)  ኃላፊነቶችን መሠጠት። ባልና ሚስት በትዳር ውስጥ ማኅበራዊ እውቅና ያለው የጎልማሳነት እና የኃላፊነት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይፈረጃል።

በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የማኅበራዊ ቁጥጥር ነው፡፡ ትዳር የተረጋጋ ማኅበረሰብ ለመገንባት እንደ ወንጀል እና ብልሹ አመለካከት ያሉ ነገሮችን ለመከላከል የራሱ የሆነ የሞራልና የሥነ ምግባር ማዕቀፍ በመፍጠር ሰዎችን በኃላፊነት ስሜት እንዲኖሩ ያደርጋል።

ከሥነ ልቦና ዕይታ አኳያ

በሥነ-ልቦና ጥናት ትዳር የሰውን ስሜታዊ፣ አዕምሯዊ እና አጠቃላይ የደኅንነት ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ የሚያደርግ ጥብቅ ግንኙነት ነው። ይህም   ሰብዓዊ ፍጡር ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ከሌላው ሰው ጋር የመተሳሰር ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለው። የትዳር አጋሮች የብቸኝነት ስሜትን በመቅረፍ፣ በአዕምሯዊና በአካል ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት አስተማማኝ የስሜት ማረፊያ ነው።

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ጥሩ ትዳር ውስጥ ያሉ ጥንዶች  የዕለት ተዕለት ውጥረቶችን፣ ጭንቀቶችን እና የሕይወት ፈተናዎችን በጋራ ለመወጣት የሚያስችል የሥነ-ልቦና አቅም ያዳብራሉ። አንደኛው አጋር ለሌላው የስሜት ድጋፍ በመስጠት ለግለሰቡ የአዕምሮ ጤና ትልቅ ሚና ይጫወታል።

የማንነት እድገት በትዳር ውስጥ አንድ ሰው ብቻውን የነበረውን ማንነት እና አመለካከት ከሌላው ሰው ጋር አቀናጅቶ አዲስ የጋራ ማንነት ይፈጥራል። ይህ የሥነ-ልቦና መስተጋብር ግለሰቦች የራሳቸውን ድክመትና ጥንካሬ አውቀው አዲስ የዕውቀትና የስሜት ብስለት እንዲያገኙ ይረዳል።

በአጠቃላይ ትዳር ማለት አካላዊ እና ቁሳዊ ነገሮችን ከመጋራት ባለፈ፣ የሥነ-ልቦና መረጋጋትን እና የማኅበራዊ ሕይወት ትርጉም የሚሰጥበት የሁለት አዕምሮ፣ መንፈስና አካል ውህደት ነው።

ሰዎች ብቻቸውን ኖረው ወደ ትዳር ሲገቡ ሊያደርጉት የሚገባ ቅድመ ዝግጅት

ሰዎች ከብቸኝነት ሕይወት ቆይተው  ወደ ትዳር ሲገቡ ሊያደርጉት የሚገባ ትልቅ የሕይወት ለውጥ እና ቅድመ ዝግጅት መኖሩን ባለሙያው ጠቁመዋል። ትዳር አጋርን ማግኘት ብቻ ሳይሆን አዲስ የአኗኗር ዘይቤን መለማመድ በመሆኑ ስኬታማ እንዲሆን ከማኅበራዊ፣ ከሥነ ልቦናዊ እና ከኢኮኖሚያዊ አንፃር ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል።

ከሥነ ልቦና አንፃር

የሥነ ልቦና ዝግጅት በትዳር ውስጥ ለሚፈጠሩ አዳዲስ ፈተናዎች እና ለውጦች የአዕምሮ እና ስሜት ብስለት ማዳበር ነው። ይህም ሲባል ይላሉ አቶ አውግቸው፤ ከ“እኔ” ወደ “እኛ” ማሰብ፣ ብቻውን ሲኖር የለመደውን ፍፁም የግል ነፃነት እና ውሳኔዎች  ከሌላ ሰው ጋር በጋራ መወሰን እና ማማከር መለማመድ ይፈልጋል፡፡

የትዳር አጋር ሁሉም የተለያየ አስተዳደግ፣ ባሕርይ እና አመለካከት እንዳለው አውቆ ነገሮችን በውይይትና በመግባባት ለመፍታት የአዕምሮ ዝግጁነት መፍጠር ተገቢ ነው። ሌላው ደግሞ የስሜት ቁጥጥር እና ትዕግሥት ነው፡፡

በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶችን በንዴት ሳይሆን በስሜት ብስለት  ለመያዝ እና ይቅር ለማለት መዘጋጀት ይገባል። ትዳር ፍፁም ደስታ ብቻ ሳይሆን ኃላፊነትም ያለበት መሆኑን ተረድቶ ከአጋር የሚጠበቁ ነገሮችን ከእውነታው ጋር ለማገናዘብ ዝግጁ መሆን ይጠይቃል።

ከማኅበራዊ አንፃር

የማኅበራዊ ዝግጅት ማለት በግለሰቡ ዙሪያ ካሉ ሰዎች እና ከአዲሱ ማኅበራዊ ሕይወት ጋር ጤናማ ግንኙነት መፍጠር ማለት ነው። የቤተሰብ ትስስርን ማስተካከል፡- የአጋርን ቤተሰቦች እና ዘመዶች ማክበር፣ መቀበል እና ከአዲሱ የትዳር አጋር ቤተሰብ ጋር ጤናማ ግንኙነት ለመመሥረት ራስን ማዘጋጀት ይገባል።

የጓደኝነት ወሰንን ማበጀት ተገቢ መሆኑንም ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

ይህ ማለትም  ተጋቢዎች ብቻውን በሚኖሩበት ጊዜ ከጓደኞቻቻው  ጋር የሚያሳልፉትን ጊዜ እና የሚደረጉ ነገሮችን በትዳር ሕይወት ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ በመወሰን  ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች  ማስተካከል ይገባል። የቤት ውስጥ የሥራ ድርሻዎችን መጋራት፡፡ ምግብ ማብሰል፣ ማጽዳት እና ሌሎች የቤት ውስጥ ኃላፊነቶች የአንድ ሰው ብቻ ሳይሆኑ የጋራ መሆናቸውን አውቆ ለሥራ ክፍፍል መዘጋጀት እንደሚገባም ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

ከኢኮኖሚ አንፃር

የኢኮኖሚ ዝግጅት የትዳርን የረጅም ጊዜ መረጋጋት እና የቤተሰብን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚደረግ የገንዘብ/የምጣኔ ሃብት/ ዕቅድ ነው።

ይህም ሲባል በገንዘብ ዙሪያ ግልጽ የገንዘብ ውይይት ማድረግ ይገባል፡፡ ወደ ትዳር ከመግባቱ በፊት እያንዳንዱ አጋር ያለውን ገቢ፣ ዕዳ፣ እና የገንዘብ አጠቃቀም ልምድ (Money Habits) በግልጽ መነጋገርም ተገቢ ነው።

ባለትዳሮች የጋራ በጀት እና ዕቅድ ማውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ የቤት ኪራይ፣ የቤት ውስጥ ወጪዎች እና የወደፊት ቁጠባዎችን በጋራ እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል የጋራ ዕቅድ ማውጣት ይገባል።

ሌላው የአስቸኳይ ጊዜ የሚሆን ገንዘብ ማዘጋጀት ነው፡፡ ይህም ለመታከሚያ፣ ሥራ ማጣት ሲያጋጥም ወይም ለድንገተኛ ወጪዎች የሚሆን የገንዘብ ክምችት አስቀድሞ መያዝ ማለት ነው።

በመጨረሻ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ግቦችን ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ቤት መግዛት፣ ልጆችን ማሳደግና የመሰሉ ትላልቅ የሕይወት ግቦች ላይ አስቀድሞ በመስማማት የጋራ ዕቅድ ማውጣት ይጠይቃል።

ባጠቃላይ ከሁለቱ ጥንዶች በጋራ አንድ የጋራ ግብ እና ራዕይ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በኢኮኖሚ፣ በልጆች አስተዳደግ እና በወደፊት ሕይወት ላይ የጋራ ዕቅድ (በጀት) አውጥቶ እንደ አንድ ቡድን መሥራት ተገቢ እንደሆነ አቶ አውግቸው አስገንዝበዋል። ወሰን በማበጀት ደግሞ ትዳራቸውን ከውጭ (ከጓደኛ ወይም ከቤተሰብ) የሚመጡ ጣልቃ ገብነቶችን በጋራ መከላከል እና የትዳራቸውን ምስጢር በውስጥ ብቻ መፍታት ይጠበቅባቸዋል።

 (ማራኪ ሰውነት)

በኲር የግንቦት 17   ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here