ፈተና እና የስነ – ልቦና ዝግጅት

0
152

የትምህርት ስነ – ልቦና ባለሙያዎች (Educational Psychologist) እንደሚያስረዱት፣ የፈተና ውጤት ከትምሕርት በሚገኝ ዕውቀት ብቻ አይወሰንም፤ የተማሪዎች የአዕምሮ ዝግጁነት፣ የራስ መተማመን እና የጭንቀት ቁጥጥር የላቀ ድርሻ አላቸው።

ታዋቂው የስነ-ልቦና ምሁር ጂን ፒያጄ /Jean Piaget/ የሕፃናት ዕድገት ከአዕምሮ ዝግጁነታቸው ጋር በተያያዘ መሆኑን በመግለጽ፣ ተማሪዎች ተረጋግተው፣ በስነ ልቦና ዝግጁ ሲሆኑ የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ነው ያስገነዘቡት።

ምሁሩ እንደሚሉት በፈተና ወቅት ብዙ ተማሪዎችን የሚያስጨንቁ ጉዳዮች የፈተና ፍርሃት፣ የራስ መተማመን ማነስ፣ የጊዜ አጠቃቀም ችግር እና ከቤተሰብና ከማሕበረሰብ የሚመጡ ግፊቶች ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል የዘንድሮ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል በቅርቡ እንደሚሰጥ ይታወቃል፤ ይህን መነሻ በማድረግ ተፈታኝ ተማሪዎች ዝግጅትን በተመለከተ ተማሪዎችን እና ሌሎች ባለድርሻዎችን አነጋግረናል፡፡

ተማሪ ቃልኪዳን ገበያው በሰሜን ጎጃም ዞን፣ ይልማና ዴንሳ ወረዳ ቀለሞ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ናት፤ ት/ቤቱ ባወጣላት መርሃ ግብር መሠረት ወርክሽቶችን በመሥራትና አጋዥ መጻሕፍትን በመጠቀም ራሷን ለፈተና ማዘጋጀቷን ነግራናለች።

ተማሪዋ እንዳለችው ከማንበብ በተጨማሪ በስነ-ልቦና ምክር በመታገዝም የራስ መተማመኗን አሳድጋለች፤ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብም “ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ለመግባት እራሴን አዘጋጅቻለሁ” ነው ያለችው፡፡

በተመሳሳይ በዚሁ ት/ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪው ይታያል አማረ፣ የ5ኛና 6ኛ ክፍል ወርክ ሽቶችን በመሥራት እና ከጓደኞቹ ጋር በመረዳዳት ለክልላዊ ፈተናው መዘጋጀቱን ነው የተናገረው። በመምህራን የተሰጠው የስነ-ልቦና ስልጠና በራሱ እንዲተማመን እንዳገዘውም ያስረዳል።

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የጎርደማ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ቤዛዊት መንግሥቱም ከላይ የተነሱትን ሐሳብ ነው ያጠናከረችው፤

ተማሪዋ ለ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና የተለያዩ ወርክ ሽቶችን በመሥራት፣ የከበዷትን ጥያቄዎች መምህራንን እና ጓደኞቿን በመጠየቅ እንዲሁም ጊዜዋን በአግባቡ ለጥናት በመጠቀም ለፈተና ራሷን ማዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡

ለዚህም የቤተሰቦቿ እና የመምህራን እገዛ ከፍተኛ ነው፡፡

በባለሙያ የተደረገላት የስነ – ልቦና ስልጠናም በራስ መተማመኗን ከፍ አድርጎላታል፤ ይህም “ፈተናውን ያለ ምንም ጭንቀት በመፈተን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እችለለሁ የሚል መንፈስ እንዲያድርብኝ አግዞኛል” ብላለች፡፡

ሌላው ስለ ፈተና ቅድመ ዝግጅቱ ሐሳቡን ያጋራን በዚሁ ት/ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪው  ወርቁ ካሣው ነው፤

እሱም ወርክ ሽቶችን ከመሥራት በተጨማሪ ቤተ መጻሕፍት በመሄድ አጋዥ መጻሕፍትን ይጠቀማል፣ ያልገባውን ደግሞ መምህራንን ጠይቆ በመረዳት ለፈተና መዘጋጀቱን ነው የተናገረው፡፡ “ለፈተናው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጌያለሁ፤ ጥሩ ውጤት እንደማመጣም ጽኑ እምነት አለኝ” ብሎናል፡፡

ለዚህ በራስ መተማመኑ ደግሞ በመምህራን እና በስነ ልቦና ባለሙያ የተሰጠው የስነ ልቦና ስልጠና የጎላ ድርሻ እንዳበረከተለት ነው የተናገረው፡፡

ሌሎች ሐሳባቸውን ያካፈሉን ተማሪዎችም ከላይ የተነሱትን ነጥቦች ነው ያጠናከሩልን።

በሌላ በኩል ተማሪዎች በዕውቀት እና በስነ ልቦና ተገንብተው ለፈተና ዝግጁ እንዲሆኑ የመምህራን እገዛ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፤ ሰሜን ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ ቀለሞ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል የጄኔራል ሳይንስ መምህር እና የቤተ ሙከራ ተጠሪ መምህር ጠብቀው አገኝ የሰጡን ሓሳብም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፤ መምህሩ እንደተናገሩት ተማሪዎችን እንደየአቅማቸው በመለየት የተጠናከረ ድጋፍ እየተሰጣቸው ነው፤ ቤተ መጻሕፍትም ሙሉ ቀን ክፍት ሆነው አገልግሎት እየሰጡ ነው።

በተመሳሳይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከትምህርቱ ባሻገር ጠንካራ ስነ ልቦና አስፈላጊ መሆኑን የሚያነሱት መምህሩ፣ ለዚህም አስፈላጊውን እገዛ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ተማሪዎችም ያለምንም ፍርሃት ለፈተና ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያም በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈታኝ ተማሪዎችን ብቁና ተወዳዳሪ ለማድረግ የማጠናከሪያ ትምህርቶች፣ የስነ-ልቦና ስልጠናዎች እና የቀለም ትምህርት ውድድሮችን በስፋት ማካሄዱን ገልጿል።

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ የሺወርቅ ድረስ ለበኩር በስልክ እንደተናገሩት

ተማሪዎችን ብቁ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ የማብቂያ ስልቶችን በመንደፍ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በተለይ ለብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች (የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍሎች) በተመረጡ መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት እና ሙሉ ቀን ቤተ መጻሕፍትን ክፍት በማድረግ እንዲሁም የቀለም ትምህርት ውድድር በማካሄድ ሰፊ የማብቃት ሥራ ተሠርቷል፡፡

“ይህ ብቻ ተማሪዎችን ውጤታማ አያደርግም” ያሉት ምክትል ኃላፊዋ ተማሪዎች በስነ ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ እና በራስ መተማመናቸውን እንዲያጎለብቱ በተመረጡ መምህራን ስልጠና እንደተሰጣቸው ነው የተናገሩት፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ትበይን ባንቲሁን በበኩላቸው የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን ብቁ ለማድረግ ከክረምት ጀምሮ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል፤ ለዚህም በበጎ ፈቃደኛ መምህራን እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሰጣቸው በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

ብቁ መምህራንን በመመደብ መደበኛው የመማር ማስተማር ሥራ በአግባቡ እንዲከናወን ከማድረግ በተጨማሪ ከወላጆች ጋር በመስማማት ተማሪዎች ቅዳሜንና እሁድን ጨምሮ የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲማሩ ተደርጓል፡፡

በተመሳሳይ በየትምህርት ቤቱ ባሉ የስነ ልቦና አማካሪ ባለሙያዎች ለተማሪዎች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ምክትል ኃላፊዋ አክለውም የተማሪዎች ስኬት የመምህራን ብቻ ኃላፊነት አለመሆኑን በማንሳት ወላጆች ልጆቻቸውን ከጫና እና ከተጨማሪ ሥራዎች በመጠበቅ ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

አቶ እሱባለው ይርጋ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የስነ-ልቦና አሰልጣኝ ናቸው፤ እርሳቸው እንደሚያስገነዝቡት ብዙ ተማሪዎች ጠንክረው ቢያነቡም ለራሳቸው ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ ከሆነ የሚፈልጉትን ውጤት ማምጣት አይችሉም። ይህም የፈተና ስኬት በቀለም ዕውቀት ብቻ ሳይሆን በአዕምሮ ጥንካሬም እንደሚወሰን ያሳያል።

በመሆኑም ተማሪዎች ራሳቸውን ከሌሎች ጋር ከማነፃፀር ይልቅ በራሳቸው ዕድገት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ይመክራሉ። “እችላለሁ የሚል አዎንታዊ አስተሳሰብ በተማሪዎች ውስጥ የራስ መተማመንን ያጠናክራል። አነስተኛ ስኬቶችን ማክበር እና ቀስ በቀስ የራስን አቅም መገንዘብ ተማሪዎችን ለትልቅ ውጤት ያዘጋጃል” ነው ያሉት።

አቶ እሱባለው  እንዳሉት ተማሪዎች በማሕበራዊ ሚዲያዎች የሚያጠፉትን ጊዜ በመቀነስ ለጥናት እና ለእረፍት መጠቀም እንዲሁም በቂ የስነ-ልቦና ዝግጅት ማድረግ በፈተና ወቅት ተማሪዎችን ከፍርሃት ወደ መተማመን፣ ከጭንቀት ወደ መረጋጋት የሚያሸጋግር ዋና መንገድ ነው። ይህም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ያስችላል።

ፈተና የህይወት መጨረሻ ሳይሆን አንድ የትምህርት መለኪያ ብቻ መሆኑን ተማሪዎች ሊገነዘቡ ይገባል። ከዕውቀት ጋር የተጣመረ ጠንካራ የስነ-ልቦና ዝግጅት ሲኖር ደግሞ ፈተናዎች ፍርሃት ሳይሆኑ የስኬት መድረኮች መሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው።

ግእዝ በአማርኛ

ሰላም   –   ሰላም

ሰው  –    ብእሲ

ሴት   –   ብእሲት

ልጅ  –  ውሉድ

ቤት  –  መንበር

ውሃ  –  ማይ

እሳት –   እሳት

ፀሐይ  –   ፀሓይ

ጨረቃ –  ወርኅ

ንጉሥ –  ንጉሥ

መጽሐፍ –  መጽሐፍ

ልብ –  ልብ

መንገድ –  ፍኖት

እናት  –  እም

አባት –  አብ

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here