በአንድ ወቅት በጥንታዊቷ ግሪክ ኮሪንዝ ከተማ ግዛቶችንና ነገሥታትን ያንቀጠቀጠው ወጣት ታላቁ እስክንድር እና ምንም ዓይነት ቁሳዊ ሀብት ያልነበረው ስልጡኑ ፈላስፋ ዲዮጋን ተገናኙ።
የዕለቱ ፀሐይ በደማቅ ሁኔታ ታበራለች። እስክንድር በታላቅ ግርማ ሞገስ በወርቅ በተለበጡ ጋሻዎችና በፈረሰኞች ጦር ታጅቦ ሲመጣ የከተማው ሕዝብ በአክብሮትና በፍርሃት መንገድ ይለቅለት ነበር።
ነገር ግን ይህ ሁሉ ግርግር ፈጽሞ ያልገደደው ዲዮጋን በጎዳና ዳር በተቀመጠች ባለ አንድ በርሜል የእንጨት ጎጆው ውስጥ ጋደም ብሎ የፀሐዩን ሙቀት እየተገነዘበ ነበር።
ታላቁ ንጉሥ እስክንድር በዚህ ሰው ነፃነትና እርካታ ተገርሞ ወደ በርሜሉ ጠጋ አለ። በፈረሱ ላይ ሆኖ በትዕቢትና በደግነት በተቀላቀለ ድምፅ እንዲህ አለው “እኔ ታላቁ እስክንድር ነኝ፤ በዓለም ላይ ካሉ ነገሮች የምትመኘውን ማንኛውንም ነገር ጠይቀኝ እሰጥሃለሁ።” ዲዮጋን ግን ፈጽሞ አልደነገጠም።
በቀስታ አይኖቹን ገልጦ ንጉሡን ተመለከተውና “አንድ ነገር ብቻ እንድታደርግልኝ እፈልጋለሁ፤ ከፀሐዩ ላይ ዘወር በልልኝ ጥላ አትጋርደኝ” ሲል መለሰለት።
ታላቁ ንጉሥ በዚህ አስገራሚና ቀላል ምላሽ ደንግጦ ለጥቂት ሰከንዶች በዝምታ ፈዘዘ። ወደ ኋላ ሲመለስም ለተከታዮቹ እንዲህ አለ “እስክንድር ባልሆን ኖሮ ዲዮጋንን መሆን እመኝ ነበር።”
ይህ ታሪካዊ ውይይት በሰው ልጅ የሕይወት ጎዳና ላይ ያሉትን ሁለት ታላላቅ ምሰሶዎች በግልጽ ያሳያል። በአንድ በኩል እንደ እስክንድር ዓለምን ለመግዛት፣ ስምና ዝናን ለማከማቸት፣ ሀብትና ሥልጣን ለመቆለል ቀን ከሌሊት የሚተጉ አሉ።
እነዚህ ሰዎች ሕይወትን እንደ ውድድርና የክምችት መድረክ ያዩታል። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ዲዮጋን ባላቸው ነገር ረክተው የሕይወትን እውነተኛ ትርጉም በነፃነት፣ በጸጥታ እና በቀላል ኑሮ ውስጥ የሚፈልጉ አሉ። ለእነዚህ ሰዎች መኖር ማለት ራሱ ትልቅ ስጦታ ነው።
ዛሬ በምንኖርበት ዘመናዊ ዓለም ቁሳዊ ክምችት፣ ትልቅ ቤት፣ እና የዝና ማማ ላይ መውጣት ዘላቂ እርካታን የሚሰጠን ይመስለናል። ነገር ግን በስነልቦና እና በሳይንስ ዓለም “ሄዶኒክ አዳፕቴሽን” የሚባል ፅንሰ-ሐሳብ አለ።
በ1978 እ.አ.አ. በፒሊፕ ብሪክማን እና በባልደረቦቹ የተደረገው ታዋቂው የሥነልቦና ጥናት ይህንን እውነት በግልጽ ያሳያል። ተመራማሪዎቹ የሎተሪ አሸናፊዎችን እና በተሽከርካሪ ወንበር ላይ የሚኖሩ አካል ጉዳተኞችን የደስታ መጠን አነጻጽረዋል።
ውጤቱ እንደሚያሳየው የሎተሪ አሸናፊዎቹ መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ የደስታ ስሜት ቢሰማቸውም ከአንድ ዓመት በኋላ ግን የደስታ መጠናቸው ወደ ቀድሞው መደበኛ ደረጃው ተመልሷል። በተመሳሳይ ሁኔታ አካል ጉዳተኞቹ መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ቢገቡም ከጊዜ በኋላ ግን የደስታ መጠናቸው አገግሞ ወደ መደበኛው ደረጃ መድረስ ችሏል።
ይህ ጥናት እንደሚያረጋግጠው የሰው ልጅ አእምሮ ከማንኛውም አዲስ ቁሳዊ ስኬት ወይም ፈተና ጋር በፍጥነት ይላመዳል፤ ይህም “ሄዶኒክ ትሪድሚል” በመባል ይታወቃል። በሌላ አነጋገር በስኬት ስም የምናከማቻቸው ነገሮች በሙሉ በራሳቸው ዘላቂ እርካታን ሊሰጡን አይችሉም።
አዲስ መኪና ስንገዛ የሚሰማን ደስታ ከጥቂት ወራት በኋላ ተራ ነገር ይሆናል፤ ከዚያም ሌላ አዲስ መኪና ፍለጋ መሮጥ እንጀምራለን። ይህ ማለቂያ የሌለው አዙሪት የሰው ልጅን አእምሮ ሁልጊዜ እረፍት አልባ ያደርገዋል።
ባሪ ሽዋርትዝ የምርጫ ተቃርኖ በተሰኘው መጽሐፉ ላይ እንደሚገልጸው በዘመናዊው ሕይወት ውስጥ ብዙ አማራጮችን ማከማቸት እና በሁሉም ረገድ “ከፍተኛውን” ነገር ለመድረስ መሞከር ሰዎችን ይበልጥ ለጭንቀትና ለጸጸት ይዳርጋቸዋል።
ብዙ ልብሶች፣ ብዙ መኪኖች፣ ብዙ ምርጫዎች ባሉን ቁጥር በአእምሯችን ውስጥ “የተሻለውን አጣሁ ይሆን?” የሚል ስጋት ይፈጠራል። ቁሳዊ ክምችት የሰው ልጅን ነፃነት ከመጨመር ይልቅ አዳዲስ የቤት ሥራዎችን በመፍጠር የአእምሮ ሰላምን ይነጥቃል።
በተቃራኒው ባለው ነገር የሚረካ ሰው አላስፈላጊ ውድድሮችን በማስወገድ ቀላል ግን ሰላማዊ ሕይወትን መምራት ይችላል። ይህ ሰው በዙሪያው ካሉ ቁሳቁሶች ይልቅ በውስጣዊ ማንነቱ ላይ ትኩረት ያደርጋል።
በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና ፕሮፌሰር በሆኑት ቶማስ ጊሎቪች የተመራው ሌላው ጥናት ደግሞ ለምን አንዳንዶች በቀላል ሕይወት እንደሚደሰቱ ያስረዳል። ጥናቱ እንደሚያሳየው ሰዎች በቁሳዊ ነገሮች (ዕቃዎች፣ ቤቶች፣ መኪኖች) ላይ ከሚያወጡት ገንዘብ ይልቅ በልምዶችና ተሞክሮዎች (ጉዞዎች፣ ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፍ፣ አዳዲስ ክህሎቶችን መማር ወይም ቀላል የእግር ጉዞዎች) ላይ የሚያወጡት ገንዘብ የበለጠ ዘላቂ ደስታን ይሰጣቸዋል።
ቁሳዊ ነገሮች ከጊዜ በኋላ አሮጌ እና ተራ ሲሆኑ ቀላል ተሞክሮዎች ግን በአእምሯችን ውስጥ ውድ ትውስታ ሆነው ይቀጥላሉ። በተጨማሪም ቁሳዊ ነገሮች ከሌሎች ሰዎች ጋር በቀላሉ እንድንወዳደርና እንድንቀና ያደርጉናል፤ ትውስታዎች ግን ማንም ሊነጥቀን የማይችለው የራሳችን ውድ ሀብቶች ናቸው።
ይህንን በቀላል የመኖር ጥበብ በተግባር ያሳየን ሌላው ታዋቂ ሰው ሄንሪ ዴቪድ ቶሮው ነው። ቶሮው በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ከከተማው ግርግርና ከኢንዱስትሪ ልማት ጫጫታ ወጣ ብሎ በዎልደን ሐይቅ ዳርቻ የራሱን ትንሽ የእንጨት ጎጆ በመሥራት ለሁለት ዓመታት ብቻውን ኖሯል።
ይህንንም ተሞክሮውን Walden በተሰኘው ታዋቂ መጽሐፉ ላይ አስፍሮታል። ቶሮው እንዲህ ሲል ጽፏል “በራሴ ምርጫ ሕይወትን ፊት ለፊት ለመጋፈጥ እና እውነተኛውን ፍሬዋን ለመቅመስ ወደ ጫካ ሄድኩ።”
እሱ እንደሚያምነው የሰው ልጅ ነፃነቱን የሚቀዳጀው የሚያስፈልጉትን ነገሮች መጠን እጅግ ሲቀንስ ነው። “አብዛኞቹ ሰዎች በጸጥታ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይኖራሉ” ይላል ቶሮው። ሰዎች ለቅንጦት ዕቃዎች ሲሉ ዕድሜያቸውን በሙሉ በሥራ ጠፍረው ሲይዙ ትክክለኛውን የመኖር ነፃነት ያጡታል። ብዙ ባከማቸን ቁጥር የእነዚያ ዕቃዎች ጠባቂና ባሪያ እንሆናለን።
ኦሊቨር ቡርክማን አራት ሺህ ሳምንታት (Four Thousand Weeks) በተሰኘው መጽሐፉ አንድ ሰው በአማካይ እስከ 80 ዓመት ቢኖር የሚኖረው ዕድሜ 4,000 ሳምንታት ብቻ እንደሆነ ያስታውሰናል።
ይህ አኃዝ የሰውን ልጅ ዕድሜ ምን ያህል አጭር እንደሆነ ያሳያል። ቡርክማን እንደሚለው በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ነገር ለማሳካት፣ ሁሉንም ሀብት እና ዝና ለመሰብሰብ መሞከር ከንቱ ልፋት ነው። እውነተኛው ሰላም የሚገኘው የእኛን ውስንነት አምነን በመቀበል ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር በቀላል ሁኔታ የምናሳልፈውን እያንዳንዱን ሳምንት በጥልቀት መኖር ስንችል ብቻ ነው። ሕይወት ረጅም መንገድ ነው። በእያንዳንዱ እርምጃ መደሰት እና ሰላም መሆን ነው። ጉዞ እንጂ መድረሻ አይደለም።
እርግጥ ነው አንዳንዱ ታላቅ ታሪክ ለመጻፍ ትልቅ ግዛት ለመገንባትና ስሙን በድንጋይ ላይ ለመቅረጽ ይጥራል፤ ይህ የእሱ ምርጫ ነው። ሌላው ደግሞ ልጆቹን በጥሩ ስነ-ምግባር አሳድጎ፣ ወዳጆቹን አክብሮ፣ የዕለት ጉርሱን አግኝቶ በሰላም መኖርን የሕይወት ትርጉም ያደርገዋል።
ሁለቱም የሰው ልጅ የመኖር ፍላጎት መገለጫዎች ናቸው። ዋናው ጥያቄ “የትኛው የተሻለ ነው?” የሚለው ሳይሆን “ለእኔ የሚስማማኝ እና እውነተኛ ሰላም የሚሰጠኝ የትኛው ነው?” የሚለው ነው። የሕይወት ትርጉሙ የሚገኘው በውጭው ዓለም ክምችት ላይ ሳይሆን በውስጣችን ባለው እርካታ ላይ ነው። እያንዳንዱ ሰው የሕይወቱን ትርጉም የሚሰጠው ራሱ በምርጫዎቹ ነው።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


