የውል እርሻ እንዴት ይፈፀማል?

0
180

የግብርና ውል እርሻ (Contract Farming) በአርሶ አደሮች (አምራቾች)፣ በአስመራቾች እና በገዢዎች (ብዙውን ጊዜ የግብርና ምርት አቀነባባሪ ኩባንያዎች ወይም ላኪዎች) መካከል የሚደረግ ሕጋዊ የምርት እና ግብይት ስምምነት ነው። የውል እርሻ  ምርቱ ከመመረቱ ወይም ከመዘራቱ በፊት አርሶ አደሩ የተወሰነ መጠን እና ጥራት ያለው ምርት በተስማማበት ጊዜ ለማቅረብ፤ ገዢው ደግሞ ምርቱን አስቀድሞ በተተመነ ዋጋ ለመግዛት ግዴታ የሚገቡበት ዘመናዊ የግብርና አሠራር ውል ነው።

የውል እርሻ አሠራር ለአርሶ አደሩ አስተማማኝ የገበያ ትስስር በመፍጠር የዋጋ መዋዠቅ ስጋትን ይቀንሳል፤ በተጨማሪም ከገዢው ድርጅት ሙያዊ የምክር አገልግሎትን ጨምሮ የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያ፣ የብድር እና የቴክኒክ ድጋፎችን ለማግኘት ያስችለዋል። ለገዢው ኩባንያ ደግሞ ለፋብሪካው ወይም ለውጭ ገበያ የሚፈልገውን የተለየ የጥራት ደረጃ፣ መጠን እና አይነት ያለው ጥሬ እቃ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማግኘት ይረዳዋል።

በአማራ ክልል የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ያለው የውል እርሻ ከውጭ የሚገቡ የፋብሪካ ጥሬ እቃዎችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ትልቅ ተስፋ የፈነጠቀ ስለመሆኑም ተጠቁሟል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በግብርና ውል እርሻ አሠራር ላይ ግንቦት 08 ቀን 2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።

የምክክሩ ተሳታፊ አርሶ አደሮች እና አልሚዎች  የምክክር መድረኩ መዘጋጀቱ ሥራው የበለጠ እንዲሳለጥ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። በውል እርሻው አርሶ አደሩ ይበልጥ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል።

ከምዕራብ ጎጃም ዞን ወምበርማ ወረዳ የመጡት አርሶ አደር አሸብር ጥላሁን  ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት በአርሶ አደሮች እና በአልሚዎች መካከል ጣልቃ  በሚገቡ ደላላዎች ምክንያት የገበያ ችግር በመኖሩ ተጠቃሚ እንዳልነበሩም አስታውሰዋል። አሁን የውል እርሻ አሠራር መዘርጋቱ ለአርሶ አደሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው።  “ከዚህ ቀደም አቅም በማጣት እና ምንም ሳይዘራ ጦም የሚያድረውን መሬት አርሶ አደሩ አሁን ላይ በወቅቱ ዘርቶ እንዲያመርት እና ምርቱን በልበ ሙሉነት ወደ ገበያ እንዲያቀርብ አስችሎታል” ብለዋል። ይህም አርሶ አደሩ በለፋበት የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን እድል እንደፈጠረለት አብራርተዋል።

ሌላው በውይይቱ ላይ የተገኙት ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጃዊ ወረዳ የመጡት የውጭ ንግድ ላኪ (ኤክስፖርተር) አቶ ጋሻው አምላኬ ለበኵር እንደገለጹት በወረዳው የተጀመረው  የውል እርሻ ለአርሶ አደሩም ሆነ ለላኪው ትልቅ ጠቀሜታ እያስገኘ ነው። የውጭ ንግድ ላኪዎችን (ኤክስፖርተሮችን) ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጋሻው፤ በተለይም ከችርቻሮ ንግድ ወጥቶ ወደ ውጭ (ኤክስፖርት) ንግድ መግባት የተሻለ ለውጥ እንደሚያመጣ አረጋግጠዋል።

“ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ስታስገባ እንደ ሀገር ሞራል ይኖርሀል፤ እንደ ግለሰብም ትበረታታለህ” በማለት የዘርፉን ሀገራዊ እና ግላዊ ጠቀሜታ አቶ ጋሻው አምላኬ አብራርተዋል። በሌላ በኩል በአካባቢው ያሉ የግብርና ባለሙያዎች እያደረጉት ያለውን የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ አድንቀዋል። በተለይም የግብርና ባለሙያዎቹ ለአርሶ አደሩም ሆነ ለላኪው በወቅቱ ተገቢውን ሙያዊ እገዛ እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ቅንጅታዊ አሠራር ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ጠይቀዋል።

በአጠቃላይ በጃዊ ወረዳ እየተተገበረ ያለው የኮንትራት እርሻ አሠራር ምርታማነትን በማሳደግ እና አርሶ አደሩን ከላኪው ጋር በማስተሳሰር የሀገርን የውጭ ንግድ ለማሳደግ ተስፋ ሰጪ እርምጃ መሆኑን የአቶ ጋሻው ተሞክሮ ያሳያል። ሆኖም ይህን ጅምር ይበልጥ ለማሳደግ እና የውጭ ንግድና (ኤክስፖርቱን) ለማበረታታት የገንዘብ (የፋይናንስ) ተቋማት አሠራር ለዘርፉ ምቹ ሊሆን እንደሚገባ አቶ ጋሻው ጠይቀዋል። መንግሥት በባንክ በኩል የሚሰጠውን የብድር አሠራር እንዲያስተካክል አክለዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ውል እርሻ እና ሜካናዜሽን ቡድን መሪ አቶ አለባቸው ባዩ እንደገለጹት መንግሥት በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገው የውል እርሻ መመሪያ ከዚህ ቀደም በግብርናው የገበያ ትስስር ላይ ይታዩ የነበሩ ማነቆዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው።

ባለፉት ዓመታት በገበያ ሰንሰለቱ ውስጥ ደላሎች ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያስታወሱት ቡድን መሪዉ፤ በዚህም ምክንያት አርሶ አደሩ የልፋቱን ያህል ተመጣጣኝ ዋጋ ሳያገኝ መቆየቱን ተናግረዋል። “በተለይም ደላሎች ከባለሀብቱ (ነጋዴው) ጋር በመመሳጠር ምርት በማከማቸት እና በገበያው ላይ የዋጋ መዛባት በመፍጠር አርሶ አደሩ ምርቱን በተገቢው ሰዓት እና አዋጭ በሆነ ዋጋ እንዳይሸጥ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድሩበት ቆይተዋል” በማለት አርሶ አደሩ ይገጥመው የነበረውን የዘመናት ችግር አስታውሰዋል። ይህ ሕገ-ወጥ አሠራር አርሶ አደሩን ለኪሳራ ሲዳርግ፣ ሸማቹንም ለከፍተኛ የዋጋ ንረት አጋልጦት መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታትም  በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የውል እርሻ አሠራር ሕጋዊ ያልሆኑ አሻጥር ፈጣሪ ደላሎችን ከገበያው በማስወገድ አርሶ አደሩ ከነጋዴው ወይም ከተጠቃሚው ጋር በቀጥታ የሚገናኝበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

አቶ አለባቸው አክለውም “ይህ አሠራር አርሶ አደሩ የደከመበትን እና ያመረተውን ምርት ትክክለኛ በሆነ የገበያ ዋጋ እንዲሸጥ እድል ፈጥሯል፡፡ ሕገ-ወጥ ደላሎች እና ነጋዴዎች በሕዝብ እና በመንግሥት ላይ ሲፈጥሩት የነበረውን ጫናም ያስቀራል” ብለዋል። ይህ አሠራር በተግባር እውነተኛ ለውጥ እንዲያመጣ እና አርሶ አደሩ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ እንዲሆን በዞኑ እና በየደረጃው በሚገኙ አሥተዳደሮች በኩል ጥብቅ የቁጥጥር እና የክትትል ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው እንደገለጹት የውል እርሻ አርሶ አደሩ እና ምርት ፈላጊው (አስመራቹ) አካል በቅድሚያ በሚያደርጉት ሕጋዊ ስምምነት ላይ ተመስርቶ የሚከናወን የግብርና ሥራ ነው። ይህ አሰራር ክላስተርን (የኩታ ገጠም እርሻን) መሰረት ያደረገ በመሆኑ አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ፣ የግብዓት፣ የምክር እና የእውቀት ክፍተቶችን በቀላሉ ማስቀረት ያስችለዋል። የውል እርሻ በአምራቾች እና አስመራቾች መካከል ያለውን ግንኙነት ጤናማ በማድረግ ምርት እና ምርታማነት ላይ በጎ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም  ተናግረዋል።

ከምንም በላይ የውል እርሻ ለአርሶ አደሩ የሚሰጠው ትልቁ ጥቅም የገበያ ስጋትን ማስቀረቱ ነው። የአርሶ አደሩ  ምርት ገና መሬት ላይ እያለ የመሸጫ ዋጋው እና ገዢው አስቀድሞ ስለሚታወቅ፣ ያለምንም የገበያ እጦት ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ያደርገዋል።

በሌላ በኩል ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች፣ ለቢራ እና  ለዱቄት ፋብሪካዎች እንዲሁም ለውጭ ላኪዎች (ኤክስፖርተሮች) ወሳኝ ጠቀሜታ አለው። ፋብሪካዎቹ በውጭ ምንዛሬ ከውጭ ሀገር ያስገቡ የነበረውን ጥሬ እቃ በውል እርሻ አማካኝነት በሀገር ውስጥ ማግኘት ይችላሉ። ይህም ጥራቱን የጠበቀ፣ በበቂ መጠን እና በተፈለገው ጊዜ ምርት ለማግኘት ከማስቻሉም ባሻገር የሀገርን የውጭ ምንዛሬ ያድናል፤ ለበርካታ ወጣቶችም ሰፊ የሥራ እድል ይፈጥራል።

አምራቹ እና አስመራቹ ስለ ውል እርሻ በቂ ግንዛቤ ሊኖረው እንደሚገባም ምክትል ቢሮ ኃላፊው አብራርተዋል። በአሰራሩ እና በገቡት ውል መሠረት ሊሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል። የንግድ፣ የፍትሕ እና የግብርና ተቋማት በዚህ ሥራ ላይ የጋራ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት በተከናወነው የውል እርሻ ሥራ ከ750 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የለማ ሲሆን ከዚህም ዘጠኝ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ ተችሏል። በዘንድሮው የምርት ዘመን ደግሞ ይህንን አሃዝ ይበልጥ ለማሳደግ ታቅዷል። ስለሆነም ከ850 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 10 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት በውል እርሻ ለማምረት ግብ ተጥሏል።

እቅዱን ለማሳካትም እስከ ግንቦት 30 ድረስ አስመራቾቹ እና አምራች አርሶ አደሮች ውል የማሰር እና የቅድመ ዝግጅት ሥራቸውን መጨረስ እንዳለባቸው ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስገንዝበዋል፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ባሉት ወራት ደግሞ ወደ ዋናው የማምረት ሥራ የግብዓት አቅርቦት እና የክትትል ሥራዎች ትኩረት ይደረጋል።

ምንም እንኳ የውል እርሻ ፋይዳው የጎላ ቢሆንም በሂደቱ ውስጥ የሚታዩ ተግዳሮቶች እንዳሉም  ገልጸዋል። ከእነዚህ ችግሮች መካከል አስመራቾች ለአርሶ አደሩ ምርትን ሊጨምሩ የሚችሉ አሠራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በበቂ ሁኔታ አለማቅረብ፣ ውል ከያዙ በኋላ ውሉን አስገዳጅ አለማድረግ፣ ቴክኒካል የሙያ ድጋፍ አለመስጠት፣ በመንግሥት አካላት፣ በላኪዎች እና በባለድርሻ አካላት መካከል ያለው ቅንጅት ማነስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ችግሮችም በግብርና ምርቶች ንግድ ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ ነው። ይህም ምርቶች በወቅቱ እና በጥራት ወደ ውጭ ገበያ እንዳይደርሱ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ስለሆነም በመንግሥት አካላት፣ በላኪዎች እና በባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን ቅንጅት ማጠናከር እና የውል ስምምነቶች በአግባቡ እንዲፈጸሙ ማድረግ ያስፈልጋል። የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ችግሮችን በመፍታት ምርቶች በወቅቱ እና በጥራት ወደ ውጭ ገበያ እንዲደርሱ ማድረግ ይገባል። በአምራች፣ በአስመራች እና በደጋፊ አካላት (በመንግሥት) በኩል ያለው ግንኙነት ሊጠናከር እንደሚገባም ምክትል ቢሮ ኃላፊው  አመላክተዋል።

መረጃ

የግብርና ምርት ውል ጠቀሜታ:-

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ለማስተዋወቅ እድል ይፈጥራል፡፡

የግብርና ግብዓት አቅርቦት እና የቴክኒክ ድጋፍ ያስገኛል፡፡

አስመራቹ ለአርሶ አደሮች የእውቀት ሽግግር እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፤ እንዲሁም የግብይት ወጪን እና የገበያ ስጋት ይቀንሳል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here