ኤሌክቶራል ኢንስቲትዩት ፎር ሰስተኔብል ዴሞክራሲ የተባለውና የአፍሪካ ሀገራትን የምርጫ እና መሰል ጉዳዮች በተመለከተ መረጃ የሚያጋራው ተቋም እንዳስነበበው በአፍሪካ ዘመናዊ ምርጫ የተጀመረው እ.አ.አ በ1950ዎቹ መጨረሻ በቅኝ ግዛት ዘመን ነው፤ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ደግሞ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ (እ.አ.አ በ1990ዎቹ) ወቅት ነው፡፡
የመረጃ ምንጩ እንዳስነበበው ላይቤሪያ እ.አ.አ በ1927 የመጀመሪያ ምርጫዋን አካሂዳለች፡፡ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1957 በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የመጀመሪያውን ዘመናዊ የንጉሠ ነገሥት ፓርላማ ምርጫ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ እ.አ.አ ከ1960ዎቹ እስከ 1980ዎቹ ባሉት የነጻነት ጊዜያት በኋላ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከምርጫ ጋር ተለያይተዋል፡፡ አህጉሪቱ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት፣ በራስ ወዳድ ገዥዎች ወይም የአንድ ፓርቲ ሥርዓት ምርጫዎች ብቻ ይካሄዱባት ነበር፡፡
ኢንተርናሽናል ፒስ ኢንስቲትዩት ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ደግሞ እ.አ.አ በ1990ዎቹ የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ ትልቅ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ተፈጥሯል፡፡ በዚህም ግልጽና ፉክክር የታየበት የመድበለ ፓርቲ ምርጫ ያካሄዱት የአፍሪካ ሀገራት ከሰባት በመቶ ወደ 40 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ታዲያ የምርጫ ውጤትን በሰላም መቀበል ለማንኛውም ሀገር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያስመሰከሩ ሀገራት አሉ፡፡ የዴሞክራሲ መሠረታዊ ዋነኛ ምሰሶም ነው፡፡
ይሁንና ሕዝብ የምርጫ ውጤትን በሰላም ካልተቀበለ ሀገራት ወደ ብጥብጥ፣ ግጭት እና አለመረጋጋት ሊገቡ ይችላሉ፡፡ የምርጫ ውጤትን በሰላም መቀበል ደግሞ ግጭትን እና ጦርነትን ያስቀራል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ተወዳዳሪዎች የምርጫ ውጤትን በጸጋ ሲቀበሉ ሀገራቸው ከአመፅ፣ ከዘር ግጭት፣ ከወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እና ከእርስ በርስ ጦርነት ትጠበቃለች፡፡ በዓለም ላይ ብዙ የፖለቲካ ቀውሶች ምንጫቸው የምርጫ ውጤትን ባለመቀበል መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የምርጫ ውጤትን በሰላም መቀበል ዜጎች በሰላም የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ያግዛል፡፡
ኢንተርናሽናል ፒስ ኢንስቲትዩት እንዳስገነዘበው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መንግሥታት እንዲፈጠሩ ያስችላል፡፡ ዴሞክራሲ ዕውን የሚሆነውም አሸናፊዎችም ሆኑ ተሸናፊዎች ሕግንና የሕዝብን ፍላጎት እንዲሁም ውሳኔን ሲያከብሩ ነው፡፡ ይህም ሕግ ከግለሰቦች በላይ መሆኑን፣ ሥልጣን በሰላም ሊተላለፍ እንደሚችል፣ የሕዝብ ድምፅ ክብር እንዳለው ያሳያል፡፡
የፖለቲካ መረጋጋት ለኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የምርጫን ውጤት በሰላም መቀበል የሀገር መረጋጋትን ስለሚጠብቅ እሱን ተከትሎ ንግድ ይቀጥላል፣ ትምህርት ቤቶች ክፍት ይሆናሉ፣ ባለሀብቶች እምነት ይኖራቸዋል፣ የመንግሥት ተቋማት በመደበኛነት ይሠራሉ፡፡ በተጨማሪም ሰዎች ምርጫ በሰላም ሲጠናቀቅ ሲያዩ ድምፅ ለመስጠት ይበረታታሉ፣ በፖለቲካ ይሳተፋሉ፣ በዴሞክራሲያዊ ተቋማት ላይ እምነት ይኖራቸዋል፡፡
ስኬታማ ምርጫን በማካሄድ (የምርጫን ውጤት በመቀበል በጋራ ለሀገር ልማት መሥራት) በአፍሪካ ሀገራት መካካል እንደ አብነት የሚጠቀሱት ጋና፣ ቦትስዋና እና ናምቢያ ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት በአብዛኛው ሰላማዊ ምርጫን አካሂደዋል፤ ሥልጣንን በሰላም ለተፎካካሪያቸው አስተላልፈዋል፤ የሕግ ሥርዓትን ለማክበር ሞክረዋል፤ ፍጹም ዴሞክራሲ ባይሆኑም ከብዙ ሀገራት ጋር ሲነጻጸሩ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት እንዳላቸው አሳይተዋል፡፡
በዚህም ሀገራቱ በአፍሪካ ውስጥ በአንፃራዊነት የተረጋጋ የምርጫ እና የዴሞክራሲ ሥርዓቶች ባለቤት መሆናቸውን ለዓለም አሳውቀዋል፡፡ እነዚህ ሀገራት ምርጫን በሰላም ስለሚያካሂዱ፣ የምርጫ ውጤቱንም “አሜን!” ብለው በአብዛኛው ስለሚቀበሉ፣ ሥልጣን በሕግ መሠረት ስለሚያስተላልፉ እና ተቋማቸው ከግለሰቦች በላይ ለመሆን ስለሚሞክሩ በምርጫ ሂደት ጥሩ ታሪክ አላቸው ሲል ያስነበበው ፍሪደም ሃውስ ኦርጋናይዜሽን ነው፡፡
በመረጃው እንደተብራራው አ.አ.አ ከ1992 ጀምሮ በጋና በርካታ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡ እንዲሁም በሁለቱ ዋና የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም በናሽናል ዴሞክራቲክ ኮንግረስ (NDC) እና በኒው ፓትሪዮቲክ ፓርቲ (NPP) መካከል ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተካሂዷል፡፡
በአፍሪካ ውስጥ በጣም የተረጋጋ የዴሞክራሲ ሥርዓት ካላቸው ሀገራት አንዷ ተብላ የምትጠቀሰው ጋና እ.አ.አ በ1957 ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች በኋላ በተደጋጋሚ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች ተካሂደውባታል፡፡ ነገር ግን እ.አ.አ ከ1992 ጀምሮ ወደ መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተመልሳለች፡፡
በሀገሪቱ ምርጫዎች በአብዛኛው በሰላማዊ መንገድ መካሄዳቸውን ያስነበበው የመረጃ ምንጩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ማሸነፍ ችለዋል፡፡ የምርጫ ውጤቱም በርካታ ጊዜ ያለምንም ኮሽታ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡
እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2000 እና 2016 የተካሄዱ ምርጫዎች በተለይ ታሪካዊ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ገዢ ፓርቲዎች ሽንፈትን ተቀብለው ሥልጣንን በሰላም ያስረከቡበት ጊዜ ስለነበር ነው፡፡ በጋና ጠንካራ የምርጫ ኮሚሽን፣ ነፃ ሚዲያ፣ ንቁ የሲቪል ማሕበረሰብ እና የፍርድ ቤት ነፃነት በመኖሩ በአፍሪካ በዴሞክራሲ ከሚጠቀሱ ሀገራት ውስጥ አንዷ አድርጓታል፡፡
የድርጅቱ መረጃ እንደሚያመላክተው እ.አ.አ በ2024 ታኅሳስ ላይ የተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ነበረው፤ ተቃዋሚው ኤን ዲ ሲ (NDC) ፓርቲ ፕሬዝዳንትነቱንም ሆነ በፓርላማ አብዛኛውን መቀመጫ አሸንፏል፡፡
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆን ማሃማ (John Mahama) ከ56 በመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል፡፡ የወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ማሃሙዱ ባውሚያ ደግሞ ከ42 በመቶ በታች ድምፅ አግኝተዋል፡፡ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ የሁለት ዘመን ገደብ ስልጣናቸውን ስላጠናቀቁ እንደገና መወዳደር አልቻሉም ነበር፡፡ እንዲሁም የሀገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት ምክትል ፕሬዝደንት ጃን ናና ኦፖኩ አግይማንግ በኤን ዲ ሲ አማካኝነት ተመርጠዋል፡፡
በፓርላማ ምርጫው ኤን ዲ ሲ 183 መቀመጫዎችን ሲያሸንፍ ኤን ፒ ፒ ( NPP) ደግሞ 88 መቀመጫዎችን አግኝቷል፡፡ የግል ተወዳዳሪዎች ደግሞ አራት መቀመጫዎችን ወስደዋል፡፡ አንድ ቀሪ መቀመጫ ግን እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ውጤቱ አልታወጀም ነበር፡፡
በ12 የምርጫ ክልሎች ውጤቶች ላይ ክርክር ቢነሳም የምርጫ ኮሚሽኑ የድምፅ ቆጠራን እንደገና መርምሯል፡፡ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ታዛቢ ቡድኖች ግን ምርጫውን በአጠቃላይ ነፃና ፍትሃዊ ነበር ብለው ገልጸውታል፡፡
የቦትስዋናን የምርጫ ታሪክ እና ሁኔታ በምንቃኝበት ጊዜም ሀገሪቱ በአፍሪካ በጣም የተረጋጋ እና ዝቅተኛ ሙስና ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት፡፡ ቦትስዋና እ.አ.አ በ1966 ከቅኝ ግዛት ባርነት ከተላቀቀች በኋላ የጎላ የፖለቲካ ግጭት ወይም ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አላጋጠማትም፡፡
በሀገሪቱ ምርጫዎች በሰላም ይካሄዳሉ፣ ሕግ እና የፍርድ ሥርዓት ይከበራሉ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በነፃነት ይሳተፋሉ፡፡ ለበርካታ ዓመታት አንድ ፓርቲ ቢገዛም የምርጫ ሂደቱ በአብዛኛው በሰላማዊ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡ ጠንካራ ተቋማት፣ የሕግ የበላይነት፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚ መኖር፣ ያላትን የተፈጥሮ ሀብትን በጥንቃቄ መጠቀም እንደ ጠንካራ የሀገሪቱ ጎን ይጠቀሳሉ፡፡
ሌላዋ በአፍሪካ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ የምትጠቀሰው ሀገር ናምቢያ ናት፡፡ ናምቢያ እ.አ.አ በ1990 ከደቡብ አፍሪካ ነፃ ከወጣች በኋላ በአብዛኛው የተረጋጋ የምርጫ ሂደት እንዳላት ኢንተርናሽናል ፒስ ኢንስቲትዩት አስነብቧል፡፡
እንደ መረጃው በሀገሪቱ ስዋፖ (SWAPO) የተባለው የነፃነት እንቅስቃሴ ከነፃነት በኋላ ዋና ገዢ ፓርቲ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ታዲያ በሀገሪቱ ምርጫዎች በሚካሄዱበት ጊዜ ሰላማዊ ናቸው፡፡ ምክንያቱም የሕገ መንግሥት ሥርዓት ይከበራል፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሳተፋሉ፣ የፕሬስ ነፃነትም አለ፡፡
በጋና፣ ቦትስዋና እና ናምቢያ ከምርጫ በኋላ ሚዲያዎች ሕዝቡ የምርጫ ውጤቱን በሰላም እንዲቀበል ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ይህ በተለይ በአፍሪካ ውስጥ ምርጫዎች ከፍተኛ የፖለቲካ ግጭት ሊፈጥሩ በሚችሉበት ሁኔታ አስፈላጊ ነበር፡፡
በእነዚህ ሀገራት ሚዲያዎቹ ያልተረጋገጡ ወሬዎችን ከማሰራጨት ተቆጥበው ከምርጫ ኮሚሽን የሚወጡ የመጨረሻ ውጤቶችን ብቻ አቅርበዋል፡፡ ይህ ሀሰተኛ መረጃ እንዳይበዛ እና ሕዝቡ እንዳይደናገጥ አግዟል፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ በተደጋጋሚ “ሰላምን እናስቀድም”፣ “የሕዝብ ውሳኔን እናክብር” እና “ግጭት ሀገርን ያጎዳል” የሚሉ መልዕክቶችን ነው የሚያስተጋቡት፡፡
በጋና የተሸነፉ ዕጩዎች ውጤቱን እንዲቀበሉ እና ደጋፊዎቻቸውን እንዲያረጋጉ መገናኛ ብዙኃን በቀጥታ ቃለ መጠይቅ በማድረግ ጫና ፈጥረዋል፡፡ በተለይ በሬዲዮ ጣቢያዎች እና በማሕበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ አነቃቂ ንግግሮችን በመከላከል፣ ሰዎች በብሔር ወይም በፓርቲ እንዳይከፋፈሉ አድርገዋል፡፡
በቦትስዋና እና ጋና ከምርጫ በኋላ የሀገር አንድነት፣ የዴሞክራሲ ክብር እና የሕዝብ ትብብር ላይ ውይይቶችን አዘጋጅተዋል፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ሙቀት እንዲቀንስ አግዟል፡፡ ሚዲያዎች የምርጫ ኮሚሽን ሂደትን በግልጽ በመከታተል ውጤቱ እንዴት ተቆጠረ? የሚለውን ጥያቄ ለሕዝብ መልሰዋል፡፡ ይህ ጥርጣሬን እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ በጋና እና ቦትስዋና ሚዲያዎች ከምርጫ በኋላ የውጤት አሳዋቂ ብቻ ሳይሆኑ የ“ሰላም ዘብ ሚናን በተግባር ማሳየታቸውን የመረጃ ምንጩ አስነብቧል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


