አቶ ሀሊድ ደሳለኝ መሀመድ ይባላሉ፤ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ የ38 ዓመቱ ጎልማሳ የባጃጅ ሾፌር አቶ ሀሊድ ደሳለኝ ደም በመለገስ ይታወቃሉ፤ 23 ጊዜ ደም የለገሱ በጎ አድራጊ ናቸው፡፡
ለነፍሰጡር እናቶች እና ለበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት ማበርከትም ሌላኛው መታወቂያቸው ነው፡፡ በእነዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የበኩር እንግዳ አድርገናቸዋል! መልካም ቆይታ!
በመጀመሪያ ለዚህ ቃለ-መጠይቅ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን! በቅድሚያ ስለ ሥራ አጀማመርዎ ቢያካፍሉን?
አመሰግናለሁ፤ በ2002 ዓ.ም ከወንድሜ ባጃጅ ተቀጥሬ እሠራ ነበር፡፡ የተወሰነ ከሠራሁ በኋላ ለረጅም ጊዜ ከባጃጅ ሥራ ውጭ ሆንኩ፡፡ በ2012 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ እንደገና ወደ ባጃጅ ሥራ ተመለስኩ፡፡ ከዚያ ጀምሮ ይሄው በዚሁ ሥራ ላይ እገኛለሁ፡፡
እንድንገናኝ መነሻችን የበጎ ፈቃድ ሥራ ነውና ነብሰ ጡሮችን እና ደም ለጋሾችን በነጻ ለማጓጓዝ ምን አነሳሳዎት?
ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ስለ ደም ልገሳ በተደጋጋሚ እሰማ ነበር፤ ግንዛቤውም ተፈጠረልኝ፡፡ ከዚያ በመነሳት ደም በመለገስ እና ለማህበረሰቡ ስለ ደም ልገሳ ግንዛቤ እንዲኖረው በራሪ ወረቀቶችን በመያዝ በእግሬ እየዞርኩ አዳርስ ነበር፡፡
ይህን ተግባር ባጃጅ በያዝኩ ሰዓት አጠናከርኩት፤ እንቅስቃሴየን በማሳደግም ለሰዎች ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እና ለበጎ ፈቃደኞች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት አሳደግሁት፡፡ ነብሰ ጡሮችን እና አረጋውያንን መሸኘትን ደግሞ ማስታወቂያ የማያስፈልገው የእግረ መንገድ ተግባሬ አደረግሁት፡፡
ይህንን በጎ ተግባር ለመጀመር ያነሳሳዎት የተለዬ አጋጣሚ ይኖር ይሆን?
የተለዬ ነገር የለኝም፡፡ ዋናው ምክንያት ግን ደም በመለገሴ የሰውን ህይወት ማትረፍ እንደምችል ግንዛቤውን መረዳቴ ነው፡፡
ነጻ አገልግሎቱን ለማን እና በምን ሁኔታ ይሰጣሉ?
ደም ለመለገስ ፈቃደኛ እና ብቁ ለሆነ ለማንኛውም ሰው አገልግሎቱን በነጻ እሰጣለሁ፡፡ ይህንን ተግባር በማንኛውም የሥራ ሰዓት ነው የማከናውነው፡፡ አገልግሎቱን ስሰጥም አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ነው አድርሼ የምመልሰው፡፡
በቀን ወይም በሳምንት ምን ያህል ሰዎችን ያጓጉዛሉ?
ወጥ አይደለም፣ ከሳምንት ሳምንት ይለያያል፡፡ አንዳንዴ በተከታታይ ደም ለጋሾች ይኖራሉ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ረገብ የሚልበት ጊዜ ይኖራል፡፡ ቁጥሩን በትክክል ይህን ያህል ነው ብሎ መናገር ባይቻልም ደም ለጋሾች እስካሉ ድረስ የነጻ ትራንስፖርት አገልግሎቱን እሰጣለሁ፡፡
ነብሰ ጡሮችን በሚያጓጉዙበት ወቅት የሚያስታውሱት የተለዬ አጋጣሚ ይኖር ይሆን? ቢያጫውቱን!
አዎ! ከምኖርበት አካባቢ ያለች ጎረቤቴ ከሌሊቱ 10፡00 አካባቢ ምጧ መጥቶ እኔን ቀስቅሰው ወደ አዲናስ ሆስፒታል እየሄድን እያለን በጣም ትጮሀለች፡፡ እኔ ቶሎ ለመድረስ ፍጥነት ጨምሬ እየነዳሁ ነበር፡፡ ድንገት ጩኸቷን አቁማ ወለድኩት አለችን፡፡ በዚያ ወቅት ሁላችንም በጣም ነበር የደነገጥነው፡፡
ዞር ብየ ሳያት የልጇን ጭንቅላት በእጇ ይዛዋለች፡፡ ከነበረኝ ፍጥነት በላይ እየነዳሁ ከሆስፒታሉ ደረስን እና ነርሶችን ጠርተን ከባጃጅ እንዳለች እትብቱን ቆርጠው በሰላም አገላገሏት፡፡ ወዲያውኑም ልጇን ወደ ማሞቂያ እሷን ደግሞ ወደ ማረፊያ ክፍሏ ወሰዷት፡፡ አሁን ልጁ አድጎ ሦስት ዓመት አልፎታል፡፡
የሰሞኑን ሌላ ገጠመኝም ላንሳ፤ አንዲት ነብሰ ጡር እናት ጸሐይ ላይ ለረጅም ሰዓት ቆማ ትራንስፖርት ትጠባበቃለች፡፡ በደነዳጅ መጥፋት ምክንያት ባጃጆች ያለኮንትራት አይሠሩም፡፡ በአጋጣሚ እኔ ደረስኩ፤ ወዲያውኑም ከሕክምና ቦታዋ አደረስኳት፡፡ በጣም ነው የተደሰተችው፤ በጣም ነው የመረቀችኝ፡፡ እኔን የሚያረካኝም ይኸው ነው፡፡
ደም ለጋሾችን በነጻ ማጓጓዝ ለማሕበረሰቡ ምን ጥቅም አለው ብለው ያስባሉ?
ለራስ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ለሌሎች ተነሳሽነት እንዲኖር ያደርጋል ብየ አስባለሁ፡፡
በዚህ ስራዎት ምክንያት ከማህረሰቡ ምን አይነት አስተያት ወይም ድጋፍ ያገኛሉ?
በእድሜ ገፋ ካደረጉ ሰዎች ምርቃት አገኛለሁ፡፡
በሚሰሩበት ወቅት በገንዘብ፣ በነዳጅ ወይም በሌሎች ችግሮች ተፈትነው ያውቃሉ?
በጣም! የነዳጅ እጥረት ትልቁ መሰናክል ነው፤ አሁንም ቢሆን በዋናነት የሚቸግረኝ እና የሚፈትነኝ ይህ ችግር ነው፡፡
ቤተሰብ ወይም ጓደኛ ለዚህ ተግባርዎት ምን ይላሉ?
ያበረታቱኛል፤ በመገረም ሀሳቡ እንዴት መጣልህ ይሉኛል፤ የተወሰኑት በየ ሶስት ወሩ ቋሚ ደም ለጋሾች ናቸው፡፡ ሶስት ወር ሲሞላቸው ባጃጅ በኔ ይጠቀማሉ፡፡ ሲረሱ እኔ አስታውሳቸዋለሁ፡፡
በሥራዎ ላይ አደገኛ ወይም አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞዎት ያውቃል? ቢያጫውቱን!
እስካሁን አልሀምዱሊላህ ከቤኒዚን እጥረት በስተቀር የከፋ ነገር ብዙም አላጋጠመኝም፡፡
አንዴ ብቻ አንድ ተሳፋሪ እያሽከረከርኩ የደም ልገሳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ወረቀት ስሰጠው ሳያነበው የሀይማኖት ማስተማሪያ /መስበኪያ/ መስሎት ባጃጁ ሳይቆም በብስጭት ዘሎ ሲወርድ ወደቀና በጣም ተጎዳ፤ ከዛ ውጭ የከፋ ነገር ገጥሞኝ አያውቅም፡፡
በዚህ በጎ ተግባር የተለየ እውቅና ወይም ሽልማት አግኝተዋል?
የእኔ ፍላጎት መልካም ሰርቶ ጀነት መግባት ቢሆንም የባሕር ዳር ደም ባንክ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አራት አመታት የሰርተፍኬት እና የሜዲያሊያ ሽልማት አበርክቶልኛል፡፡ በዚህም አራት የሰረተፍኬት ሶስት የሜዳሊያ ሽልማት አለኝ፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ አገልግሎቱን በመስጠቴና ለ23ኛ ጊዜ ደም በመለገሴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሌሎች ወጣቶች ከእርስዎ ምን እንዲማሩ ይፈልጋሉ?
ባሕር ዳር መሰናዶ ትምህርት ቤትን ጨምሮ ባገኘሁት አጋጣሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጠሁ ነው፡፡ እውቀቱ ለሌለው ደም ማለት ከሰው ልጅ ብቻ እና ብቻ የሚገኝ ስለሆነ እሱን የሚተካ ስለሌለ የምንለግሰው ደም ለሰዎች ህይወት ድህነት የሚሰጥ እኛን ደግሞ የማይጎዳ ስለሆነ በቀናነት እና በቋሚነት በየ ሶስት ወሩ በመለገስ ህይወትን እናታደግ እላለሁ፡፡ እውቀቱ እያላቸው ለማይለግሱ ደግሞ ችግሩ በራሳችሁ እስኪደርስ አትጠብቁ ደግነት ለራስ ነው እላለሁ፡፡
መንግስት ወይም ማህበረሰቡ እንደርሶ ያሉ በጎ አድራጊዎችን እንዴት ሊደግፍ ይገባል?
መንግስት እውቅና ሰጥቶን ነዳጅ እንድናገኝ ቢያመቻችልን፡፡ በተጨማሪም ብሔራዊ ደምባንክ እና የባሕርዳር ደም ባንክ እና ሌሎች አጋር አካላት ለደም ለጋሹ ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በማዘጋጀት አገልግሎቱን በስፋት ቢሰጡ እላለሁ፡፡ምክንያቱም ህብረተሰቡ መለገስ እየፈለገ የትራንስፖርት ወጭን በማሰብ ከመለገስ ይደናቀፋል፡፡
ወደፊት ይህንን አገልግሎት ለማስፋት ያሰቡት እቅድ ካለ?
አዎ! ሌሎች የባጃጅ ሾፌሮች እንደኔ አይነት አገልግሎት እንዲሰጡ ጥረት እያደረግሁ ነው፡፡ እንዲሁም ራሳቸው ቋሚ ለጋሾች እንዲሆኑም ግንዛቤ እያስጨበጥኩ ነው፡፡
ለነፍሰ ጡሮች፣ ለደም ለጋሾች እና ለህብረተሰቡ ምን መልዕክት ማስተላለፍ ይፈልጋሉ?
ለህብረተሰቡ ኑ! ደም በመለገስ የሰው ህይዎትን ከሞት እንታደግ፤ መልካም ስራ መልሶ ይከፍላል፤ ለደም ለጋሾች ደግሞ በቋሚነት/በየ3ወሩ/ ደም በመለገስ ለሰው ልጆች፣ ለእናቶች እና ህጻናት ጤናማ ህይወት እንዲኖራቸው የበኩላችን አስተዋጽኦ እናበርክት! ነፍሰጡሮችን በሰላም ያገላግላችሁ እላለሁ!
በመጨረሻም ሰዎች ሰብአዊነት ሲሉ ምን ማለት ነው ብለው ያስባሉ?
የሰው ልጅ ፈጣሪ አልቆ የፈጠረው ክቡር ፍጡር ነው፡፡ ከሌሎች ፍጡራን በተለየ ያስባል፤ እናም ያለማንም አስገዳጅነት ሰው ለሰው ሲያስብ እና መልካም ነገሮችን ሲተገብር ነው ሰብአዊነት ብየ የማስበው!፡፡
ለነበረን ቆይታ በበኩር ክፍል ስም አመሰግናለሁ፡፡
እኔም አመሰግናለሁ!!
(ሰናይት በየነ)
በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


