ምርጫ ለተረጋጋ  ሕዝብና ሀገር፤ እንዲሁም ለፀና ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ ነው

0
14

ምርጫ ለሀገር ግንባታ አንዱ ሂደት ነው፤ ምርጫ-የዲሞክራሲ ግንባታን በማፋጠን የተረጋጋ ሀገርና የጸና መንግስትን ለመፍጠር ያግዛል ምርጫ ሰው በሀገሩና በራሱ የወደፊት ህይወት ላይ እንዲሆን የሚፈልገውን ውሳኔ በቀጥታ የሚያሳልፍበትና ይህንን ተጠቅሞ ነጻነቱን የሚገልጽበት የስልጡንነት ምልክትና መንገድ ነው። ሰው ራሱ የሚያምነውን እና የሚፈልገውን በምርጫ በመግለጽ ዲሞክራሲያዊ መብቱን የሚገልጽበትና የወደፊት እጣ ፈንታውን የሚወስንበት ወሳኝ መንገድ ነው፡፡ ይህ ሂደትም የህዝብ ተሳትፎን ይጨምራል-ተሳትፎው ደግሞ የኔነትና የባለቤትነት ስሜትን ይፈጥራል፤ እንደሀገር ስኬት ብቻ ሳይሆን ውድቀትም ቢመጣ ውጤቱን አብሮ ለመካፈል ያመቻል፡፡

በዚህ የምርጫ ሂደት ሚዲያ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡

ሚዲያ በምርጫ ሂደት ተወዳዳሪዎች ፕሮግራሞቻቸውን፣ ፖሊሲዎቻቸውን እና አጀንዳዎቻቸውን ለህዝብ በግልጽ መልኩ እንዲያቀርቡ በፍትሀዊነት እኩል እድልና ጊዜ በመመደብ እንዲያስተዋውቁ ያመቻቻል፡፡ በመረጃ ላይ ተመስርቶ የሚመርጠውን ለመወሰን የሚያስችለውን ግንዛቤ በመስጠት የዲሞክራሲ ግንባታን ይጠናክራል። ምርጫ ከተካሄደ በኋላም ውጤቱን ሙያዊ በሆነ መንገድ በመግለጽና በምርጫ ሂደት የሚገነባውን የዲሞክራሲ ግንባታ ባህል በማስገንዘብ ሀገር ወደፊት እንድትሄድ የማድረግ ሙያዊ ግዴታና ኀላፊነት አለበት፡፡

በምርጫ ወቅት ብዙኃን መገናኛ ሚናዎቹን በአግባቡ መወጣት ከቻለ ለሀገር ሰላም እና መረጋጋት ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡

ያልተረጋገጠ መረጃና ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ ዘገባዎችን ከማሰራጨት በመቆጠብ ሚዛናዊና ፍትሐዊ ዘገባን በመዘገብ ሀገር ማረጋጋትና መታደግ የሚዲያና የጋዜጠኛው ሚና ነው፡፡ ሚዲያ ኃላፊነቱን ሲወጣ ለሀገር መረጋጋት፣ ለአንድነት፣ ለመተማመን በተለይ ዴሞክራሲ አድጎ ሰላም እንዲሰፍን እና ልማት እንዲወጣ ያደርጋል፡፡

በሀገራችንም 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ በዚህ ሂደትም መራጩ ባለው መረጃ ተመስርቶ ይበጀኛል የሚለውን መርጧል፡፡ ምርጫ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት ሲሆን፣ ለኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። በምርጫ ለመንግስት የህዝብ ተቀባይነትን ይፈጥራል፡፡ ለመንግስት ህጋዊ ስልጣን እንዲኖረው ያደርጋል። ህዝቡም የመረጠውን መንግስት ተቀብሎ ይተባበራል። ይህም ፖሊሲዎችን በቀላሉ ለመተግበር እና ለውጤታማነቱ እጅጉን ያግዛል። ከዚህ በተጨማሪም ተጠያቂነትን ያሳድጋል፡፡ በምርጫና በይሁንታ የመጣ መንግስት ተጠያቂነት ስላለበት ህዝቡን በማክበር ቃል የገባውን በተግባር በመግለጥና ስራን በጊዜ ከፋፍሎ በመስራት ለዳግም ምርጫ እንደእርሾ የሚሆነውን ስራ ይሰራል፡፡

በሰላማዊና በምርጫ ስልጣን የመያዝ ሂደት ግጭትን ይቀንሳል። የተረጋጋ ሀገርና መንግስትን ለመፍጠርም ያስችላል፡፡ ምርጫ አምባገነንነትን በማስወገድ የዲሞክራሲ ግንባታ ልምምድንና ምክንያታዊ አስተሳሰብን ለመፍጠር ሁነኛ መንገድ ነው፡፡ ምርጫ የስልጣንን ሽግግር ሰላማዊ ከማድረግ ባሻገር ለሰከነና ለጸና ሀገረመንግስት ግንባታና ለሰላም ያለው ዋጋ በጣም ትልቅ ነው። ትክክለኛና ሰላማዊ ምርጫ የመንግስትን መረጋጋት ያጠናክራል፤ ግጭትንም በእጅጉ ይቀንሳል።

በምርጫ ሕግ እና የፍርድ ሥርዓት ይከበራል፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በነፃነት ይሳተፋሉ፡፡ በዚህ የምርጫ ሂደት ጠንካራ ተቋማት፣ የሕግ የበላይነት፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚ፣ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በጥንቃቄ መጠቀም የምትችልና ጠንካራ ሀገረመንግስትና የተረጋጋ ህዝብ ለመፍጠር ቁልፍ ሚና አለው፡፡ ከምርጫ በኋላ ተፎካካሪዎችና ደጋፊዎች የምርጫ ውጤትን በጸጋና በምክንያታዊነት የመቀበል ልምድ መዳበር ሀገርን ከአመፅ፣ ከዘር ግጭት፣ እና ከእርስ በርስ ጦርነት ሲታደግ አይተናል፡፡ ይህንን ልማድ በማዳበር ምርጫን የስልጡንና የምክንያታዊነት መገለጫ በማድረግ ሀገርን ማሻገር የሁሉም ሚና መሆን ይገባዋል፡፡

በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here