ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተና  ይወስዳሉ

0
256

በኢትዮጵያ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለተማሪዎች የትምህርት ሕይወት ወሳኝ መሻገሪያ ነው። ይህ ፈተና ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚያመሩበትን መንገድ ከመወሰኑ በተጨማሪ የትምህርት ሥርዓቱን ውጤታማነትም የሚመዘንበት ነው። ስኬታማነቱ ደግሞ (ከፈተናው ዝግጅት እስከ ውጤቱ)) የተማሪዎች፣ የመምህራን፣ የወላጆች እና የትምህርት ተቋማት ቅንጅታዊ ውጤት ነው።

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ፈተና በበይነ መረብ ይሰጣል፤ ለዚህ ደግሞ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተከናወነ ነው፡፡

በኩር በሚያዚያ ወር 2018 ዓ.ም ባወጣው ዘገባ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የፈተና ዝግጅት በተመለከተ ቅኝት አድርጋ ማስነበቧ ይታወቃል፤ በዛሬው ዕትማችን ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ እያደረገ ያለውን አጠቃላይ ዝግጅት በተመለከተ እናስነብባችኋለን፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እንደገለጸው፣ በ2018 የትምህርት ዘመን 99 ሺህ 897 ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ ተዘጋጅተዋል። ይህ ቁጥር በክልሉ ያለውን የትምህርት ስፋት ከማሳየቱ በተጨማሪ ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ ለማስፈጸም የሚጠይቀውን ከፍተኛ የዝግጅት ሥራ ያመላክታል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኢየሩስ መንግሥቱ የብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎችን በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ቆይታ አድርገዋል፤ ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ እንደተናገሩት፣ የዘንድሮው የፈተና ዝግጅት በተለመደው የፈተና አስተዳደር ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም። ባለፉት ዓመታት የተማሪዎች ውጤት ዝቅ እንዲል ያደረጉ ምክንያቶችን በመለየት እና የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ትምህርት ቤቶችን ተሞክሮ በማስፋፋት የተጀመረ ሂደት ነው።

ክፍተቶችን በመለየት መፍትሔዎችን በመተግበር የተሻለ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል፤ የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸውን ትምህርት ቤቶች በማስፋፋት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የተደረገው ጥረት በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በተለይም ያልተሸፈኑ የትምህርት ይዘቶችን በማጠናከሪያ ትምህርቶች መሙላት፣ የተማሪዎችን የማንበብ ባሕልን ማሳደግ እና በቤተ መጻሕፍት አጠቃቀም ላይ ትኩረት መስጠት ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል መሆናቸውን ወ/ሮ ኢየሩስ ተናግረዋል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የትምህርት ጥራት ችግር ከመምህራን እጥረት እና ከመማሪያ ክፍል እጥረት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፤ ከዚህ በተጨማሪም የንባብ ባሕል መዳከምም ለትምህርት ጥራት መጓደል ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የጥናቱ ውጤቶች ያመላክታሉ። ተማሪዎች የማንበብ ባሕልን እንዲያዳብሩ ማድረግ ታዲያ ዘላቂ ጥቅም ያለው እርምጃ ነው።

በዚህም ቤተ መጻሕፍትን ከሰኞ እስከ ሰኞ እንዲጠቀሙ እና በቡድን በመሆን የማንበብ ባሕላቸውን እንዲያዳብሩ የማድረግ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ አስታውቀል፡፡

ከቀለም ትምህርት (አካዳሚክ) ዝግጅት በተጨማሪ ለተማሪዎች የሥነ ልቦና ድጋፍ መሰጠቱ ሌላው ወ/ሮ ኢየሩስ ያነሱት የዝግጅት ክፍል ነው። በአሁኑ ወቅት በርካታ ተማሪዎች በተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ ይገኛሉ፤ እነዚህን ተማሪዎች ለፈተና የሚያስፈልጋቸውን መረጋጋት እና ራስን የመቆጣጠር ክህሎት እንዲያገኙ መደገፍ ደግሞ የፈተና ውጤታማነትን በቀጥታ የሚያሳድግ ነው፡፡ ይህን ትኩረት በማድረግ የስነ ልቦና ዝግጁነት እንዲኖራቸው ጥረት መደረጉን ወ/ሮ ኢየሩስ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናውን የሚወስዱት በበይነ መረብ (በዲጂታል ውይም በኦንላይን) መሆኑ ይታወቃል፤ ይህም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ነው የተናገሩት። ለአብነትም  ከ539 አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች መካከል 315ቱ ተማሪዎቻቸውን በበይነ መረብ እንዲፈትኑ ለማድረግ ዝግጅት ስለመደረጉ አንስተዋል። በበይነ መረብ ተማሪዎቻቸውን ከሚያስፈትኑት መካከል ደግሞ 215 ትምህርት ቤቶች በክልሉ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚያስፈትኑ ይሆናል ነው ያሉት።

ቀሪ አንድ መቶ አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች በራሳቸው እና በአይ ሲ ቲ ማዕከላት እንደሚያስፈትኑ ተናግረዋል።

ቀሪዎቹ ትምህርት ቤቶች (224) ደግሞ በተለመደው የወረቀት ፈተና አሰጣጥ ሂደት ፈተናውን እንደሚያካሂዱ ገልጸዋል።

ተማሪዎችን በበይነ መረብ ማስፈተን ለኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ወደ ዲጂታል ሽግግር የሚወሰድ አስፈላጊ እርምጃ ነው፤ ይሁን እንጂ ከኢንተርኔት፣ ከኤሌክትሪክ እና ከቴክኒክ ዕውቀት ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችንም አብሮ ይዟል።

እንደ ምክትል ኃላፊዋ ገለጻ ቢሮው ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየሠራ ነው፡፡

የዲጂታል ፈተና ሥርዓት በተማሪዎች መካከል የዕድል ልዩነት እንዳይፈጥር ትኩረት ይፈልጋል፤ በተለይ በገጠር እና በከተማ እንዲሁም በመንግሥት እና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል ያለውን የቴክኖሎጂ ክፍተት ለመቀነስ ዘላቂ መፍትሄ ያስፈልጋል ነው ያሉ።

የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ዝግጅት ከቀደሙት ዓመታት የተለዬ መሆኑን በርካታ ማሳያዎች አሉ። ከትምህርት ይዘት ሽፋን እስከ ሥነ ልቦና ድጋፍ፣ ከመሠረተ ልማት እስከ ዲጂታል ፈተና (በይነ መረብ) ድረስ የተደረጉ ዝግጅቶች ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል። ይሁን እንጂ የፈተና ስኬት የሚወሰነው በዝግጅት ብቻ አለመሆኑንም ወ/ሮ ኢየሩስ አንስተዋል፤ በመሆኑም ተማሪዎች ያገኙትን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም፣ በትጋት እና በጥረት ለስኬት መብቃት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ለዚህ ደግሞ ተፈታኝ ተማሪዎች ቴክኖሎጂውን እንዲለማመዱት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ነው።

የበይነ መረብ ፈተና ሥርዓት ኩረጃን በማስቀረት፣ ጊዜን በመቆጠብ እና ወጭን ለመቀነስ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ወ/ሮ ኢየሩስ መንግሥቱ ተናግረዋል።

አማርኛ በአማርኛ

ሄደ — ተጓዘ

ለማ— ዳበረ፣ፋፋ

ላጠ — ቀረፋ፣ገሸለጠ

መዘነ — መጠነ

ረዳ — አገዘ

ተጋ — ጣረ

አሰበ — አሰላሰለ

አሸነፈ — ድል አደረገ

(ሰናይት በየነ)

በኲር የሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here