ሜክሲኮ

0
5

በሰሜን አሜሪካ አህጉር ደቡባዊ ጫፍ የምትገኘው ሜክሲኮ በታሪክ፣ በባህል፣ በተፈጥሮ ሀብት እና በኢኮኖሚ አስፈላጊነት ረገድ በዓለም ላይ ልዩ ቦታ የያዘች ሀገር ናት። ከጥንታዊ የማያና የአዝቴክ ሥልጣኔዎች ጀምሮ እስከ ዘመናዊ ኢንዱስትሪያዊ እድገቷ ድረስ የሚዘልቀው ታሪኳ ለብዙ ተመራማሪዎች እና ታሪክ ወዳጆች የማያልቅ የጥናት ርዕስ ሆኖ ቆይቷል። በሌላ በኩል ነጭ አሸዋ የተሸፈኑ የባህር ዳርቻዎች፣ ከፍተኛ ተራሮች፣ ጥንታዊ ፒራሚዶች፣ የተፈጥሮ ሸለቆዎች እና የደማቅ ባህል ባለቤት መሆኗ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን ወደ ሀገሪቱ ይስባል።

ሜክሲኮ በዛሬው ዘመን ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት፣ በላቲን አሜሪካ ከሚገኙ ትልልቅ ሀገራት አንዷ ናት። የሀገሪቱ ዋና ከተማ ሜክሲኮ ሲቲ ሲሆን በዓለም ላይ ከሚገኙ ትልልቅ የከተማ ማዕከላት መካከል ትመደባለች። ሜክሲኮ በሰሜን ከአሜሪካ ጋር ድንበር ስትጋራ፣ በደቡብ ደግሞ ከጓቴማላ እና ቤሊዝ ጋር ትዋሰናለች። በምሥራቅ የሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ እና የካሪቢያን ባሕር፣ በምዕራብ ደግሞ ሰፊው የፓስፊክ ውቅያኖስ ያዋስኗታል።

የሜክሲኮ ታሪክ ከዓለም በጣም አስደናቂ ከሚባሉት  መካከል አንዱ ነው። ከሺዎች ዓመታት በፊት የኦልሜክ፣ የማያ እና የአዝቴክ ሥልጣኔዎች በዚህ አካባቢ አብበው ነበር። በተለይ የማያ ሥልጣኔ በሂሳብ፣ በኮከብ ጥናት እና በሥነ ሕንፃ ያሳየው እድገት እስከ ዛሬ ድረስ ምሁራንን ያስደንቃል። የአዝቴክ መንግሥትም በ15ኛው እና 16ኛው ክፍለ ዘመን ከአሜሪካ አህጉር ታላላቅ ኃያላን መንግሥታት አንዱ ነበር።

በ1519 ዓ.ም. የስፔን አሳሽ ሄርናን ኮርቴዝ ወደ ሜክሲኮ ከገባ በኋላ የአዝቴክ መንግሥት ወደቀ። ከዚያ በኋላ ሜክሲኮ ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል የስፔን ቅኝ ግዛት ሆና ቆየች። በ1821 ዓ.ም. ግን ከረጅም የነፃነት ትግል በኋላ ነፃነቷን አገኘች፤ ከዚያም ዘመናዊ መንግሥት ለመገንባት ጉዞዋን ጀመረች።

የሀገሪቱ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሳቢ እና ማራኪ ነው። በሜክሲኮ ውስጥ ሞቃታማ የባህር ዳርቻዎች፣ ደረቅ በረሃዎች፣ የበረዶ ሽፋን ያላቸው ተራሮች፣ እሳተ ገሞራዎች እና ሰፋፊ ደኖች ይገኛሉ። ይህም ለሀገሪቱ ከፍተኛ የተፈጥሮ ውበት ሰጥቷታል። ሜክሲኮ በባዮሎጂያዊ ልዩነት ከዓለም ቀዳሚ ሀገራት መካከል ትመደባለች፤ በውስጧም በሺዎች የሚቆጠሩ የእንስሳትና የእፅዋት ዝርያዎች ይገኛሉ።

የሜክሲኮ የቱሪዝም ሀብት

ሜክሲኮ በቱሪዝም ዘርፍ ከዓለም ታዋቂ ሀገራት መካከል አንዷ ናት። በየዓመቱ ከአርባ ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች ሀገሪቱን ይጎበኛሉ። ከታዋቂ መስህቦቿ መካከል ቺቸን ኢትዛ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ይህ የጥንታዊ የማያ ከተማ ከዓለም አዲስ ሰባቱ ድንቅ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። በዚያ የሚገኘው የኩኩልካን ፒራሚድ የማያውያን የሥነ ሕንፃ እና የሳይንስ እውቀት ማሳያ ነው።

በተመሳሳይ ሁኔታ ቴዎቲዋካን የሚባለው ጥንታዊ ከተማ የፀሐይ እና የጨረቃ ፒራሚዶች መኖሪያ ስለሆነ በብዙ ቱሪስቶች ይጎበኛል። እንዲሁም ቱለም በካሪቢያን ባሕር ዳርቻ ላይ የተገነባ ውብ የማያ ቅርስ ሲሆን ታሪክንና የባህር ውበትን በአንድ ላይ ያጣምራል።

የሜክሲኮ የባህር ዳርቻዎችም በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ናቸው። ካነሹን በነጭ አሸዋዋ፣ በንጹህ ሰማያዊ ውሃዋ እና በቅንጡ ሆቴሎቿ ታዋቂ ናት። እንዲሁም ፖርቶ ቫላርታ እና አካፕሉኮ ለዕረፍት፣ ለውሃ ስፖርቶች እና ለባህር ጉዞ ተመራጭ ስፍራዎች ናቸው።

በተፈጥሮ መስህቦች ውስጥ ኮፐር ካንየን በተለይ ይጠቀሳል። ይህ የሸለቆዎች ስብስብ በግዝፈቱና በውበቱ በዓለም የታወቀ ነው። እንዲሁም ፖፖካቴፔቴል የተባለው ንቁ እሳተ ገሞራ የሀገሪቱ ተፈጥሯዊ ምልክት ሆኗል።

የሜክሲኮ ሕዝብ በባህል እጅግ የበለጸገ ነው። የአገር በቀል ባህሎችና የስፔን ባህል ተዋህደው ልዩ የሜክሲኮ ማንነት ፈጥረዋል። በተለይ “ማሪያቺ” ተብሎ የሚጠራው ባህላዊ ሙዚቃ የሀገሪቱ መለያ ሆኗል። በልዩ ልብስ የተጌጡ ሙዚቀኞች በጊታርና በቫዮሊን የሚያቀርቡት ሙዚቃ በዓለም ዙሪያ ይታወቃል።

የሜክሲኮ ምግብ ደግሞ ከዓለም በጣም ታዋቂ ምግቦች መካከል ይገኛል። ታኮስ፣ ጉዋቻሞል እና ኢንቺላዳ በብዙ ሀገራት የሚወደዱ ምግቦች ናቸው። በበቆሎ፣ ባቄላ፣ ቲማቲም እና በርበሬ የተመሠረተ የምግብ ባህል አላቸው።

ሜክሲኮ በበዓላትም ትታወቃለች። በተለይ ዴይ ኦፍ ዘ ዴድ የተባለው በዓል የሀገሪቱን ልዩ ባህላዊ ማንነት ያሳያል። በዚህ ቀን ሰዎች የሞቱ ቤተሰቦቻቸውን በማስታወስ ልዩ ዝግጅቶችን ያካሂዳሉ።

በኢኮኖሚ ረገድ ሜክሲኮ በላቲን አሜሪካ ካሉ ትልልቅ ኢኮኖሚዎች መካከል አንዷ ናት። የመኪና ማምረቻ፣ የኤሌክትሮኒክስ ኢንዱስትሪ፣ ግብርና፣ ነዳጅ ምርት እና ቱሪዝም የኢኮኖሚዋ ዋና ዋና ምሰሶዎች ናቸው። በተለይ የቱሪዝም ዘርፉ በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ለሀገሪቱ ያስገኛል።

በመጨረሻም ሜክሲኮ የጥንታዊ ሥልጣኔዎችን ውርስ፣ የተፈጥሮ ውበትን፣ የባህል ብልጽግናን እና ዘመናዊ ሕይወትን በአንድ ላይ ያጣመረች ሀገር ናት። ከጥንታዊ ፒራሚዶቿ እስከ ውብ የባህር ዳርቻዎቿ፣ ከተፈጥሯዊ ሸለቆዎቿ እስከ ደማቅ ባህላዊ በዓላቷ ድረስ ሜክሲኮ የዓለም ሕዝቦችን የምትማርክ ሀገር ሆና ቀጥላለች። በታሪክ፣ በባህል፣ በተፈጥሮ እና በቱሪዝም ዘርፍ ያላት ብልጽግናም ሜክሲኮን ከዓለም እጅግ አስደናቂ እና ልዩ ሀገራት መካከል አንዷ አድርጓታል።

 

አጫጭር እውነታዎች

አስገራሚ እውነታዎች

o   ቸኮሌት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙት ጥንታዊ የሜክሲኮ ሕዝቦች ነበሩ።

o   በዓለም ላይ ከፍተኛ የስፓኒሽ ተናጋሪዎች ቁጥር ካላቸው ሀገራት ውስጥ ሜክሲኮ ቀዳሚ ናት።

o   በሀገሪቱ ከ60 በላይ የአገር በቀል ቋንቋዎች ይነገራሉ።

o   ከዓለም ታላላቅ ፒራሚዶች አንዱ የሚገኘው በሜክሲኮ ነው።

o   ሜክሲኮ ከዓለም በጣም ብዙ የዩኔስኮ የቅርስ ስፍራዎች ካላቸው ሀገራት መካከል ትገኛለች።።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የሰኔ 8  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here